ደቂቀ ናቡቴ

Tuesday, October 25, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተጀመረ


 የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳ ረቂቅ ላይ ሲወያይ ዋለ 

  • በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እና በዕርቀ ሰላም ጉዳይ አጀንዳ ላይ ልዩነቶች አሉ 
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና ማኅበረ ቅዱሳን ከማ/መምሪያው ጋራ ስላለው ግንኙነት የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት በአጀንዳው ረቂቅ ውስጥ ተካተዋል 
  • “ያረፉ ብፁዓን አበው ሀብት እና ንብረት ወራሾች ነን” በሚሉ ሐሰተኞች ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየተቸገረ መሆኑ ተገለጸ
  • “በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ይጨመርበት፤ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ ጉዳይ የቀድሞው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይመለስ” (የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ)፤
  • “ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም” (ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ)፤
 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 11/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 22/2011)፦ ስምንት አባላት ያሉትን የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በመምረጥ ዛሬ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2004 ጠዋት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንዲያዙላቸው ካቀረቧቸው የአጀንዳ ረቂቆች መካከል በተጨማሪ ኤጶስ ቆጶሳት ሹመት እና የኮሚቴው አባላት ካቀረቧቸው አጀንዳዎች አንዱ በሆነው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዕርቀ ሰላም ጉዳይ ላይ ሲወያይ ውሏል፤ በፓትርያርኩ እና በተቀሩት የጉባኤው አባላት መካከል በታየው የአቋም ልዩነት ምክንያት ውሳኔ ሳይደረግበትም ለነገ አድሯል፡፡

የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ሆነው የተመረጡት ስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በ2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 30 ያህል ኤጲስ ቆጶሳትን መሾምን አስመልክቶ የነበራቸውን አቋም አጠናክረው ቀርበዋል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ከሹመቱ አስቀድሞ የኤጲስ ቆጶሳቱሿሿም በተመለከተ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የታዘዘውን ከማስጠበቅ እና በዚህም መንፈስ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ከማጠናከር እንዲሁም ከተሚ ዕጩዎቹ አኳያ የተገቢነት እና ወቅታዊነት ጥያቄ በማንሣት ከስምምነት ሊደረስ ባለመቻሉ አጀንዳው ለነገ አድሯል፡፡

ከትናንት በስቲያ ለኅትመት የዋለው የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ በበኩሉ፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እና ዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ጋዜጣው በመስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም እትሙ ባሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፣ ከቀድሞዎቹ አባቶቻችን ሲደረግ በቆየውና ዛሬም ድረስ በቀጠለው ጥረት “ቤተ ክርስቲያን ከድህነት መሥመር ወጥታ ካህናት አገልጋዮቿ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን” ያውጃል፡፡ በዚህም መሠረት አበው ጳጳሳት በወርሐዊ ደመወዝ፣ በትራንስፖርት፣ በሕክምና፣ በመኖሪያ (ማረፊያ) ቤት፣ በማዕድ አገልግሎት ሳይቀር የትናንቱ ሰቀቀን እንደቀረላቸው በመዘርዝር በሞተ ዕረፍት በሚለዩበት ወቅት ያስታመመቻቸው፣ የተንከባከበቻቸው ቤተ ክርስቲያን ሳለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡ ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ መሆናቸውን አትቷል፤ ውርሱ ይገባናል ባዮቹ ይህን የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

ርእሰ አንቀጹ የችግሩ መንሥኤ በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ መሆኑን ገልጧል፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ጠይቋል፡፡

ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥ እና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም እንደሚገባቸው ያስታወሰው ርእሰ አንቀጹ፣ ይህን በማድረግ  ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡
/ሙሉውን የርእሰ አንቀጹን ይዘት ከዚህ በታች ይመልከቱ/
+ + +
የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ
አስታማሚ ቤተ ክርስቲያን ወራሽ ቤተሰብ
/ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ 57ኛ ዓመት ቁጥር 122፤ መስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም/
ከዛሬ ዐርባ ዓመት በፊት በነበረው የዘውድ መንግሥት ሥርዐት ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የጠበቀ ግንኙነትና ትስስር ነበራቸው፡፡በየዘመናቱ የሚነግሡትን ነገሥታት ሁሉ ቀብታ የምታነግሥ እሷ ነበረች፡፡ ከዚህም የተነሣ ነገሥታቱም ሆኑ መሳፍንቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ይሰጡት የነበረው አክብሮት፣ ያደርጉት የነበረው ድጋፍ፣ ጥበቃና ክብካቤ እጅግ በጣም የተለየ ነበር፡፡ ከግብጻውያን የባርነት ቀንበር ተላቅቃ መንፈሳዊ ነጻነቷን ሙሉ በሙሉ እንድትጎናጸፍ የከፈሉትም መሥዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አልነበረም፡፡ የምትጠቀምበት ርስት ጉልት ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ በሕገ መንግሥታቸውም ከፍተኛ ሥፍራ ነበራት፡፡

ከዚህም ሌላ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በሞያቸው፣ በቅድስናቸው እና በአገልግሎታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን ከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበት ጊዜ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን የሚፈጽሙባቸው መኪናዎች፣ የእጅ መስቀሎችና አርዌ ብርቶች፣ ልብሰ ተክህኖም ጭምር ይሰጧቸው ነበር፤ ወርሐዊ ደመወዛቸውንም የሚያገኙት ከመንግሥት ነበር፤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትም መንግሥት መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ ያደርግ ነበር፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት አላት”እየተባለ ይነገር የነበረውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡

ይህም በመሆኑ ጳጳሳቱም ሆኑ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናት በሙሉ በጸሎተ ቅዳሴያቸው ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው በሚያቀርቡት ጸሎት “ዕቀብ ንግሦ ወሠራዊቶ ለንጉሥነ እገሌ፤ አግርር ፀሮ ታህተ እገሪሁ” ማለት “ንጉሥን ከነሠራዊቱ ጠብቀው፤ ጠላቶቹንም ከእግሩ ሥር አስገዛለት” እያሉ በመጸለይ አያሌ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ ደብተሮቹ ወይም ያሬዳውያን መዘምራኑም በበኩላቸው በያሬዳዊ ዝማሬያቸውና በቅኔያቸው ጣልቃ እያስገቡ ነገሥታቱን ሲያወድሷቸው፣ ሲያሞግሷቸውና ንጉሣዊ ተግባራቸውን በማጋነን ሲገልጡላቸው ይስተዋሉ ነበር፡፡

ከዚህም በላይ እንደተገለጸው ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የመንግሥት ጥገኛ ሆና ራሷን ሳትችል መኖሯ በሁሉም ዘንድ የተሰወረ ምሥጢር አይደለም፤ በዘመነ ደርግ የደረሰባትን ከፍተኛ ተጽዕኖም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ተረኛ ሆኖ አገሪቱን መምራትና ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ግን የተወረሱት ቦታዎች፣ ቤቶችና ንብረቶች ሁሉ ተመልሰውላት ራሷን በራሷ እንድትመራና እንድታስተዳድር መደረጉ ትጋትንና ጥንካሬን እንድታገኝ በእጅጉ ረድቷል፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጻ የወጣች እንጅ እንደ ትላንቱ ጥገኛ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ አሁን በሚመሯት ዓለም አቀፍ አባት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የበላይ መሪነት፣ በልጆቿ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስተዳዳሪነት የምትመራ ቤተ ክርስቲያን እንጅ እንደ ትላንቱ ቋንቋዋን የማያውቅ ምእመን ከቤተ መንግሥት ተልኮ የሚያስተዳድራት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡

በኢኮኖሚውም አኳያ ያለፉት ብፁዓን አባቶቿና አገልጋዮቿ ካህናት ጦም ውለው ጦም አድረው ለዝንተ ዓለም በአክፍሎት እየኖሩ ያገለግሏት የነበረችው የትላንቷ ደሃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በድህነት መስመር አትገኝም፡፡ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንዲሉ እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የመሳሰሉት አርቆ አስተዋዮች አባቶቿ በሰበካ ጉባኤ አደራጅተዋት ስለ አለፉ ዛሬ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ሆኑ አገልጋዮቿ ካህናት ሁሉ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትላንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም፡፡ የትላንቱን አስተንትኖና ከፍተኛ ለውጡን በውል ተገንዝቦ ተመስገን ለማለት እንዲችል የዛሬው አገልጋይ እና ተጠቃሚ ሁሉ ትላንት ቢኖር ኖሮ ምንኛ መልካም ነበር፡፡

በቀድሞው ጊዜ የነበሩት የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ተጠርተው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉት ቤት ተከራይተው ነበር፤ ወይም እንደሀገራችን ባህልና ሥርዐት ለብፁዓን አበው በማይስማማና በማይገባ በሆቴል ቤት ነበር፤ ለቁመተ ሥጋ ያህል ወይም ጥቂት ጥቂት የሚመገቡትም ለብፁዓን አበው የማይስማማና የማይገባ የግዥ እንጀራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ያለፉት ብፁዓን አበው እንደተመኙት በሞተ ሥጋ የተለዩት ዓለምአቀፍ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ አሁን ባሉት የቤተ ክርስቲያን ርእስ ከፍተኛ ጥረት በመላው አህጉረ ስብከት አስተዋፅኦ ተገንብቶ ዓለም አቀፍ እንግዶችን በማስተናገድ ቤተ ክርስቲያኒቱን እጅግ አኩርቷታል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ መኖሪያና ቢሮ በመሆንም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ልዩ ገስት ሐውስም ተገንብቶ ቅዱስነታቸው አቻዎቻቸውን የውጭ ፓትርያርኮችን እያስተናግዱበት ነው፤ እንደ ትላንቱ ከፍተኛ ወጭ በሚጠይቁና ለአባቶች ክብር በማይስማሙ ታላላቅ ሆቴሎች ማስተናገዱ ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከዚህም ጋራ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ከየአህጉረ ስብከቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉበት ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት የሚበቃ ቤተ አበው በተሟላ ሁኔታ በዘመናዊ መልክ ተሠርቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ እንደ ትላንቱ ለአባቶች ክብር በማይመጥን መንደር ውስጥ ገብቶ ቤት መከራየትና ሆቴል ቤት ማደር የለም፤ እንደ ትላንቱ የግዥ እንጀራ ቢያምርም አይገኝም፤ አሁንም ዛሬ ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእስ የተለየ ጥረትና ፍላጎት በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ለሚኖሩትም ሆነ ከየአህጉረ ስብከቱ ለሚመጡት ብፁዓን አበውና በግቢ ለሚኖሩት አገልጋዮች መነኮሳትም ጭምር በገዳም ሥርዐት የአንድነት ማዕድ ገበታ በነጻ ተዘርግቶላቸዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የአባቶችን የአንድነት ገበታ በቅጡ ሲመለከቱት ሢመተ ጵጵስናው ብቻ ሳይሆን ሥርዐተ ማዕዱም ከግብጽ የመጣ ይመስላል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበትም ጊዜ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው መኪናዎችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶችን ገዝታ የምትሸልማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ መኪናዎችን መግዛት ብቻም አይደለም፤ አደጋ ሲያጋጥማቸውና በአገልግሎት ብዛት ሲዳከሙም ጋራዥ በማስገባት አሳድሳ የምትሰጣቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ብፁዓን አበው ሲታመሙም እስከ ውጭ አገር ድረስ በመላክ የምታሳክማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበትም ጊዜ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ በክብር የምትሸኛቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለብፁዓን አባቶች የሚሰጠው ወርሐዊ ደመወዝ ከአባትነታቸው፣ ከአገልግሎታቸው ስፋትና ከኑሮው ወድነት ጋራ የማይመጣጠን ስለሆነ የተዘረዘረው በጎ አድራጎትና ክብካቤ ሁሉ ቢደረግላቸው የሚደሰት እንጂ የሚከፋው የለም፤ በረከትን እንጅ መርገምን ያመጣል ብሎ የሚያስብም ወገን አይገኝም፡፡

ይሁን እንጅ ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደርም ሆነ በምጣኔ ሀብት ራሷን ችላ ይህ ሁሉ እየተደረገ እያለ ብፁዓን አበው በዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በሚለዩበት ጊዜ ቀብታ የሾመቻቸውና ሲታመሙ ያስታመማቻቸው ቤተ ክርስቲያን እያለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡት ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ሆኑ አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ ናቸው፤ ውርሱ ይገባናል ባዮቹ አልፈው ተርፈውም ያንኑ የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህን ሁሉ ችግር የፈጠረውና መልኩን ለውጦ የመጣው በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ ነው፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ያስፈልጋል፡፡

ስለ ብፁዓን አበው ሀብትና ንብረት አወራረስ ጉዳይ የቀደሙት አበው የወሰኑት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ምናልባት በብፁዓን አባቶች ይረዱ የነበሩ እጓለማውታዎች ካሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በቤተሰብና በሕፃናት አስተዳደግ ድርጅት ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡ የእናትና የአባት ወይም የቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ግን “ዘኢኃደግ አባሁ ወእሞ፤ ወብእሲቶ ወውሉዶ፣ ኢይክል ይጸመደኒ” የሚለውን አምላካዊ ቃል መዘንጋት አያሻም፡፡

በጳጳሳት ምርጫ ጉዳይም እንደቀድሞው የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ከተጨመረበት ከሞት በኋላ የሚመጣውን ጣጣ ለማስወገድ ያስችላል፡፡ ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ከሆነ ዘንድ ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም ይቻላል፡፡ ከሹመት በኋላ የሚመጣውን ወቀሳና ከሰሳ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሊሸከም አይችልም፡፡

የቀድሞዎቹ አባቶች በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ አይኖራቸውም እንጅ ገንዘብና ሀብት ካላቸው የእግዚአብሔር ገንዘብ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስለአለበት ገንዘባቸውንም ሆነ ሀብታቸውን ሁሉ የሚያወርሱት ለቤተ ክርስቲያን ነበር፤ ወይም በትውልድ መንደራቸውም ሆነ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን በማሠራት፣ ገዳም በማስገደም፣ ት/ቤት በመክፈትና የምግባረ ሠናይ ድርጅት በማቋቋም ከአባትነት የሚጠበቅ መልካም አርኣያነት ያለው ሥራ ሠርተውበትና ዝክረ ስማቸውን ተክለውበት ያልፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ይህን ዓለም በመናቅ ሹመት በቃኝ ብለው በምናኔ ሕይወታቸውን በኢየሩሳሌም በርሓ የፈጸሙትን የቀድሞውን የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡

እኒያ እውነተኛ ብፁዕ አባት ቅድመ ሢመተ ጵጵስናም ሆነ ድኅረ ሢመተ ጵጵስና ከዕለት ምግባቸው እየቀነሱ ዕድሜ ልክ ባጠራቀሙት ገንዘብ በትውልድ ቀያቸው ዝክረ ስማቸው ለዘለዓለም ሲታወስ የሚኖርበት ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ በሚሞቱበትም ጊዜ በቁጠባ ገንዘብ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን እንዲገለገልበት በኑዛዜ አውርሰው በማለፋቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ “የታዴዎስን ነፍስ ይማር” እያለ በመገልገል ላይ የሚገኘው ብፁዕነታቸው በኑዛዜ ባወረሱት ገንዘብ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን የእኒህን ብፁዕ አባት አሠረ ጽድቅ ተከትለው የሚሠሩ አባቶች የሉም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ሆኖም ብፁዓን አበው እንደ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ያሉ አባቶች በተጓዙበት መንገድ እየተጓዙ ቢያልፉ የራሳቸውንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናቸውን ክብር ሊያስጠብቁና ዝክረ ስማቸውን ተክለው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ማለትም በውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እናዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባዋል፡፡

(መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ) by Deje Selam

Wednesday, October 19, 2011

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 2ኛ ቀን ሪፖርታዥ


ጉባኤው ቤተ ክህነቱ ቃለ ዐዋዲውን ማስከበር እንዳልቻለ አመለከተ
· የቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ/ሕግ፣ ደንብ/ እና የኦዲት ሪፖርት ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ዕውቅና መነፈጉ በመንግሥት አካላት ፊት የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፤
· “የመንበረ ፓትርያርኩ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዘንድ ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል” (የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተሳታፊ)
· “. . . ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ  በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት ቃለ ዐዋዲው በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አለው፤ [ነገር ግን] የሕግ አገልግሎቱ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁልጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” (ብፁዕ አቡነ ናትናኤል)
· “. . . አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ/ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም እያሉ በተደጋጋሚ ይነግሩናል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፡፡. . . ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም መተኛት በዝቷል፡፡ ይህ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ አቋሙን ማሳወቅ ይኖርበታል፤ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳ ተነጋግሮ መወሰን አለበት፡፡” (ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ)
· “ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን፡፡” (ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ)
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 20/2011)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምእመናን አንድነት በሰበካ ጉባኤ ተደራጅታ በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በአገልግሎት እና በምጣኔ ሀብት በኩል በራሷ ሕግና ሥርዓት በመመራት እንድትሠራ ለማድረግ ታስቦ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ያወጣው ቃለ ዐዋዲ ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ሀብቷን እና ንብረቷን ለማስጠበቅ ያለው ኀይል፣ በፍትሕ ተቋማት ዘንድ የሚሰጠው ዕውቅና እና ተቀባይነት እያጸጸ/ እያነሰ በመምጣቱ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ፡፡ ለቃለ ዐዋዲው ሕግ እና ደንብ ዕውቅና እና ተቀባይነት ማጣት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት ክፍል ሞያዊ አቅም ማጣት ቀዳሚ ሓላፊነቱን እንደሚወስድ የተመለከተ ቢሆንም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት “የድሮው ይበቃችኋል” በሚል መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ስለ መሆናቸው የሚደነግገውን አንቀጽ እንዳሻቸው እየተረጎሙ ለቃለ ዐዋዲው ተፈጻሚነት ዕንቅፋት በመፍጠር ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያጠቁ ተነግሯል፡፡


ረቡዕ ጥቅምት ስምንት፣ 2004 ዓ.ም ሁለተኛ ቀኑን በያዘው 30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ላይ እየቀረቡ በሚገኙት የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት ከደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ተወክለው የመጡ ተሳታፊ፣ “የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ የመዘበሩ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በኦዲት ምርመራ የተረጋገጠውን ማስረጃ ለፍርድ ቤት እናቀርባለን፤ ነገር ግን አይቀበሉንም፤ እንዲያውም የሙያ ማረጋገጫ እና የሥራ ፈቃድ ባላቸው የተሠራ ኦዲት ካልሆነ በቀር የመንበረ ፓትርያርክ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው ይነግሩናል፡፡ በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮ ቢወስንበት” በማለት ጠይቀዋል፡፡


ለተወካዩ ጥያቄ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ “ኦዲት ተደርጎ ጥፋት ከተገኘ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ በሕጋችን መሠረት ኦዲተር የሚላከው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች በመንግሥት ፍ/ቤቶች ዕውቅና አላቸው” ቢሉም የሰጡት ምላሽ በጥያቄው በተጨባጭ ከተጠቀሰው ችግር አኳያ በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡


ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተወካዩ ጥያቄያቸውን እንዲያብራሩ ዳግመኛ በሰጧቸው ዕድል፣ ቤተ ክርስቲያን “ኦዲተር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው የሚመደበው” የሚል ሕግ የላትም፤ ሕጉ ቢኖርም ሁሉንም አህጉረ ስብከት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ኦዲተር ብቻ ለማዳረስ አይቻልም፤ የቤተ ክርስቲያናችን ኦዲተሮች በሕግ ዕውቅና እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል፤ እዚህ አዳራሽ ተቀምጠን ዕውቅና አለን በማለት ብቻ የሚሆን አይደለም፤ በየቦታው ስንሄድ የኦዲት ሰነዳችን ውድቅ እየሆነ ነው ያለው፤ ሊታሰብበት ይገባል” በማለት ጥያቄያቸውን አጠናክረዋል፡፡


የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት የቁጥጥር /ኦዲት/ አገልግሎቱ የተመሠረተበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ /ቃለ ዐዋዲው/ በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው አስረድተዋል፤ እንደ አብነትም በአንድ ወቅት የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንደ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይመዝገብ ተብሎ በነበረበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጠየቁት ማብራሪያ መሠረት ኮሚሽኑ በተቋማዊ ሕጋችን፣ ደንባችንና መመሪያችን እንደሚመራ /እንደሚታይ መገለጹን አስታውሰዋል፡፡


የተወካዩ ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ መመለስ እንደሚገባው ያስረገጡት ብፁዕነታቸው፣ ትኩረት ያደረጉት በቤተ ክህነቱ አዘውትሮ ይነሣል ባሉት የአገልጋዮች እና ሠራተኞች አስተዳደራዊ በደል ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ “ሠራተኞች በደል ደረሰብን ብለው በፍርድ ቤት አስተዳደሩን እየከሰሱ ገንዘብ ወጥቶ ይሰጥ እየተባለ ይሰጣቸዋል፡፡ የሕግ አገልግሎት ክፍሉ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁል ጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” በማለት በአስፈጻሚው አካል በኩል የሚታየውን የሙያዊ አቅም ክፍተት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡


ብፁዕነታቸው እንዲህ ቢሉም ለጉባኤው በተሰራጨው የ”ዐዋጅ ነጋሪ” መጽሔት በቀረበው የሕግ አገልግሎቱ የሥራ አፈጻጸም ግን ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በሥራ ነገር ክርክሮችና ይግባኞች ከ34 ጉዳዮች ከግማሽ በላዩን አስፈርዶ በተፈረዱበትም ይግባኝ እንደጠየቀ ሰፍሯል፡፡


የሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በበኩላቸው ዋናው ጉዳይ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እንደተባለው ሕጋችንን አለማስከበራችን መሆኑን በራሳቸው ልምድ አስረድተዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 85/65 ተፈቅዶ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም ታትሞ የወጣውን ቃለ ዐዋዲ በመያዝ፣ “አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ /ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም” እያሉ በተደጋጋሚ እንደሚነግሯቸው ብፁዕነታቸው ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡


ብፁዕነታቸው አክለውም፣ “ይሁንና በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ሦስት አንቀጽ አምስት የሰፈረውን በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፤ በጅማው ጉዳይ ስላለፈው አደጋ ርምጃ እንወስዳለን ተብሎ ትንኮሳው ግን እስከ አሁን አልቆመምም፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም እንቅልፍ በዝቷል” ሲሉ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ በጋራ መክሮ አቋም እንዲይዝበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳው አካትቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍበት አሳስበዋል፡፡


በሌላ በኩል ከዚህ ጥያቄ ጋራ በተከታታይ ከቀረቡት ውስጥ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት ተሠርተዋል ተብለው የሚቀርቡ ተግባራት በእውነትም ስለ መኖራቸው ማረጋገጥ ስለሚቻልበት ሥርዓት፣ ስለ ሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በምዕራብ ጎጃም - ባሕር ዳር የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ እንደሌለ ተደርጎ በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት መነገሩ ይገኝበታል፡፡


የምዕራብ ጎጃም ሀ/ስብከት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ በሀ/ስብከቱ እንደሌለ ያቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ በማኅበረ ቅዱሳን እና በአርማጌዶን ቪሲዲዎች ላይ በፕሮቴስታንቶች አዳራሽ ሲጨፍሩ የሚታዩት ‹የተቀሰጡ መሪጌቶች› ከባሕርዳር አካባቢ መሆናቸውን በማስታወስ ይልቁንም አካባቢያዊ ሁኔታው ለጠቅላላው የአማራ ክልል የተሐድሶ መናፍቃን መፈልፈያ እንዳይሆን ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተገልጧል፡፡


ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም በሰጡት አጫጭር ምላሽ፣ “ቤተ ክርስቲያናችን በማኅበራት ስም እየተወረረች ነው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ያልገባቸውና ከዚህ ዓለም ትዝታ ያልተላቀቁ ናቸው፤ ማኅበራት በዘፈቀደ ሳይሆን በቋሚ ሲኖዶሱ ተጠንቶ ነው ዕውቅና የሚሰጣቸው፤ በቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ መላእክት ስም የተቋቋሙ ማኅበራት/ ሰንበቴዎች ከጥንትም ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ ተቆራኝተው የነበሩ ናቸው፡፡ በስብከተ ወንጌል ስም ላሉት ግን ተጠንተው በማእከል ደረጃ ዕውቅና ሊሰጣቸው ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በቃለ ዐዋዲው ዙሪያ የተደረገውን ውይይት ሲያጠቃልሉም “….ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡


ከሁለቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አስተያየት በኋላ በብርቱ የተነቃቃ ከሚመስለው ጉባኤተኛ በርካታ እጆች ወጥተው ቢታዩም ውይይቱ በተጀመረው መልኩ ነገ ጠዋት እንደሚቀጥል በመግለጽ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ከቀትር በኋላ ከተደረገው ውይይት ቀደም ሲል የ21 አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፡- መልካም አስተዳደርን/ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን/ ለማስፈን በሀገረ ስብከት እና በወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በተሰጡ ሥልጠናዎች፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ማኅበራትን በመከላከል፣ ኢ-ጥሙቃንን እና መናፍቃንን አስተምሮ እና አሳምኖ በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በማጥመቅ፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ይዞታ በማስከበር፣ አብነት ት/ቤቶችንንና  መምህራንን በገቢ በመደጎም እና በማጠናከር፣ እጓለ ሙታንንና የሕግ ታራሚ የሆኑ ወላጆች ያሏቸውን ልጆች በመከባከብ ላይ ያተኮረ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡


ከሪፖርቶቹ ይዘት ውስጥ፦
v የከፋ ቦንጋ ሀ/ስብከት ውስጥ በተቀሰቀሰ ሁከት በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ላይ ጥይት እስከ መተኮስ መደረሱ፣
v በአፋር ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለራስ አገዝ ልማት በሚሠሯቸው ሥራዎች ግብር መጠየቃቸው፣
v በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ብር 800,000 የፈጀ የአብነት ት/ቤት ተከፍቶ ዲያቆናትና ካህናት ሠልጥነው እየወጡ ፍሬውን ማየት መጀመሩ፣ በሰሜን ሸዋ በብር 23 ሚሊዮን ወጭ ዘመናዊ ት/ቤት እና የአብነት ት/ቤት ያቀናጀ ተቋም መከፈቱና በተለይም ለደቡቡ የሀገራችን ክፍል መጋቢ የሆኑ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ መገለጹ፣
v በሶማሌ ሀ/ስብከት የሊቀ ጳጳሱ ቶሎ ቶሎ መቀያየር ሀገረ ስብከቱን እያዳከመው መሆኑ፣
v በአንጻሩ የአዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሠራተኞች ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዳይዛወሩባቸው መጠየቃቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን by Deje Selam

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርታዥ

  • ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቤተ ክርስቲያን ወጥ/ማእከላዊ/ የበጀት አስተዳደር በምትከተልበት አሠራር ላይ ጉባኤው ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥሪ አድርገዋል
  • . የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ይሻሻላል፤ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በዕቅድ መሥራት እንዲለመድ ይደረጋል
  • . በ2004 ዓ.ም ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይታተማል፤ በ2000 ዓ.ም በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል አቀማመጥ በሆሄያት አገባብ እና በትርጉም ስልቶች ረገድ የክለሳ ምልክት ተደርጓል፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላትን የያዘ የሆሄያት አገባብ መጽሐፍ ይዘጋጃል
  • . ጉባኤው ለውይይት እና ጥያቄ በተፈቀደው የአንድ ሰዓት ጊዜ አንዳችም ሐሳብ ሳያነሣ አህጉረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት የ35% ፈሰስ /የፐርሰንት ገቢ/ ላይ ያተኮሩ ሪፖርቶችን መስማቱን ቀጥሏል
  • . ያረፉት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ታስበዋል
  • . ‹‹ስማቸውን የጠቀስናቸው ብፁዓን አባቶቻችን አልፈው እኛ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍና ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ቀርተናል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ/
  • . የመናፍቃን እና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ መምጣቱ፣ ፕሮቴስታንቶች የሚፈጥሩት ትንኮሳና የባህል ወረራ፤ በጉራጌ ዞን እስላሞች በሐሰት ‹‹ክርስቲያኖች ስምንት መስጊዶችን አቃጠሉብን›› ብለው ለተወሰነ ጊዜ ክርስቲያኖችን ማሳሰራቸው፣ የቦታ ይገባናል ጥያቄ በማንሣት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ መሞከራቸው፤ በጅማ ‹‹እምነታችሁን ለውጡ›› እያሉ ምእመናንን ማወካቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሦስት አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ሰፈር በሙርሲ ብሔረሰብ በመቃጠሉ ምእመናን አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው፤ በሰሜን ወሎ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ለማክሸፍ ወደ ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ አራት አገልጋዮች በመኪና አደጋ መሞታቸው፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባር ጽላትን በፎርጅድ የመለወጥ ተንኮልና በሶዶ ወረዳ16 አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው፤ በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ 130 ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሰው ሠራሽ አደጋ መቃጠሉ፤ የሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በዘፈቀደ መንቀሳቀስ፣ በተለይም በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሕዝቡን በየቋንቋው የሚያስተምረው ሰባኬ ወንጌል አለመገኘት፣ በአዲስ አበባ የሕገ ወጥ ሰባክያን እንቅስቃሴ፣ በሊቃውንት ያልተመረመሩ መጻሕፍትና ካሴቶች በየዐውደ ምሕረቱ ሲሸጡ መታየታቸው እና 283 ቀሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ባለመመለሳቸው ተጨማሪ ገቢ መታጣቱ በበጀት ዓመቱ ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ተካቷል
  • . ለጉባኤው ከወትሮው በተለየ ከብር 600,000 በላይ ወጪ ተደርጓል
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 7/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 18/2011)፦ 
በየዓመቱ ጥቅምት ወር የሚካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ጠዋት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ባደረሱት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ከ48 አህጉረ ስብከት/ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ/ ከእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ስድስት በመሆን ተወክለው የመጡ ከ300 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት፣ ‹‹ስማቸውን በጸሎት የጠራናቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አልፈው እኛ የቀረነው ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ነው፡፡ እኛ ከእነርሱ የተሻልን ሆነን ሳይሆን ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍ በዚህ ቦታ ተሰልፈናል፡፡ ብዙዎቻችን ከሊቃውንቶቻችን ስንማር ረጅም ዘመን ቆይተናል፡፡ ብዙ ልምድ አካብተናል፡፡ መማራችን፣ ማወቃችን፣ ረጅም ጊዜ መቆየታችን ከሥራ ከተለየ ጥቅም እንደሌለው አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን እንድንሠራ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ምእመኑም ሆነ ትውልዱ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ በደል፣ ፍርሃት እንዳይደርስባቸው እንድንጠብቃቸው ለእኔና እዚህ ላለነው ብፁዓን አባቶች ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ‹በጎቼን ጠብቁ› ተብሎ ከአባታችን ቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ 

እግዚአብሔር እኔ እበልጣለሁ የሚል ሥርዐተ አልበኝነትን አይወድም፡፡ ሰዎችን ከክፉ ነገር ለማዳን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ በሓላፊነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በተጠያቂነት ስሜት መፈጸም ይገባል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡



በመብራት መቋረጥ ምክንያት ካጠረው የቅዱስነታቸው መልእክት በመቀጠል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የልብ ድካም ሕመም እንዳለባቸው በመግለጽ እስከ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ ያለውን የሥራ ክንውን ሪፖርት ብቻ ነው ለማሰማት የቻሉት፡፡ ቀሪው የሪፖርቱ ክፍል ከ15 ደቂቃ ጫን ያለ ‹‹የሻይ ዕረፍት›› በኋላ በጽ/ቤቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ነበር የቀረበው፡፡

ከ48ቱ አህጉረ ስብከት በአጥቢያ ደረጃ ብር 451,996,682.53፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ ብር 90,692,854.51፣ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ብር 43,877,275.34፣ ገቢ ከሚያስገቡ ስምንት አምራች ድርጅቶች እና ስድስት መምሪያዎች ብር 90,766,002.09 በአጠቃላይ በ2003 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዓመት ብር 542,762,684.62 ገቢ መገኘቱን ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ዝርዝር ላይ አመልክተዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ኀይል እንደ አበው ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን በአንድነት ቢያዝና እንደ አስፈላጊነቱ በየደረጃው ለሁሉም ቢተነተን/ቢበጀት/ ችግራችን ሁሉ ተቃሎ፣ አገልግሎታችን ሠምሮ ምንኛ ባማረብን ነበር?›› ሲሉ የጠየቁት ብፁዕነታቸው እስከ አሁን ድረስ ማዕዳችን ‹‹ከአንድ መሶብ እየወጣ ተሠርቶ በአንድነትና በበረከት ልንቋደሰው አለመቻላችን›› እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ማጠቃለያም አጠቃላይ ጉባኤው ከተጀመረ 30 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ግባችን በቂ ነው የሚባል ባለመሆኑ ገና እጅን አጣጥፎ የሚያስቀምጥ አለመሆኑን በማስታወስ፣ ‹‹…ይህ ዐቢይ እና ወሳኝ ጉባኤ በብርሃነ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ በጥልቅ መክሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር እንዲቃና፣ አገልግሎታችን እንዲሟላ፣ እኩልነት እንዲሰፍን የበጀት ማእላዊነት እንዲኖር በቅን ልቡና አስቦበት ጥናታዊ ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ አክብሮት በተሞላ ልቡና አሳስባለሁ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስለተከናወነው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንዳተተው፣ የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ 26,187 ሐዲስ አማንያን በወንጌል ትምህርት በማመን ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ገብተዋል፤ ወደ ሌላ እምነት ሄደው የነበሩ 241 ጥንተ ኦርቶዶክሳውያን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነዋል፡፡ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰባክያን እየተዘዋወሩ እንዲሰብኩ ከመደረጉም በላይ በብፁዓን አባቶች እና ሰባክያነ ወንጌል በየወረዳውና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ሥምሪቶች ተደርገዋል፤ ታላላቅ ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡ በየማሠልጠኛው ለሰለጠኑ ካህናት፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት እና ለንስሐ አባቶች በሠለጠኑ መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በማእከል ታውቀው ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና ማኅበራት እንሰብካለን እያሉ ምእመናንን ግራ እንዳያጋቡና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያፋልሱ ጥበቃ፣ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል፡፡ ‹‹እምነታችሁን ትታችሁ የእኛን እምነት ተከተሉ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ የተገኙ መናፍቃን ተከሰው በገንዘብና በእስራት ተቀጥተዋል፡፡

በአንጻሩ የተለያየ ቋንቋ የሚናገረውን ወገን በሚሰማው ቋንቋ የሚያስተምረው በቂ የመምህራን ቁጥር አለመኖሩ፣ ከሦስቱም ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት በየዓመቱ ቢመደቡም በተመደቡበት አለመገኘትና የበጀታቸው አብሮ መቅረት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎ የተጋበዙ ‹ሰባክያን› ከብር 30,000 - 40,000 ድረስ ክፍያ ካልተከፈለን እያሉ በአገልግሎት ላይ አለመገኘታቸው፣ የመናፍቃንና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየሰፋ መምጣትና የስድስት ካህናት እና የ109 ምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መግባት፣ እንደ ሰሜን ወሎ እና መተከል ባሉት አህጉረ ስብከት መናፍቃኑ ያስከዷቸውን ካህናት በማሰለፍ የሥራ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ከዚህም አኳያ በተያዘው የበጀት ዓመት የአብነት መምህራንንና የካህናት ማሠልጠኛዎችን ለማጠናከር/በዚህ ዓመት በተለይም በሰሜን ሸዋ መምህራን ከብር 400 - 2000 በሚደርስ ደመወዝ እንደተቀጠሩት፣ ለአብነት መምህራን የጡረታ ዋስትና እንደተጠበቀላቸው/፣ ሰባክያነ ወንጌልን በማብዛት የተለያየ ቋንቋ የሚሰማውን ኅብረተሰብ ለማስተማርና ለማስተባበር የየአካባቢውን ተወላጆች በየቋንቋቸው በማሠልጠን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ እና ነባሮቹም እንዲታደሱ/ከዚህም መካከል በጆርዳን በነጻ በተገኘው 3000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በኢየሩሳሌም ገዳም የሚሠራውን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ/፣ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች እንዲከበሩ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር/ካርታ/ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ቃለ ዐዋዲውን ለማሻሻልና የማጠናከሪያ ሥምሪት ለማካሄድ ዕቅድ ስለ መያዙ፣ በአጠቃላይ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ለማብዛትና ለመጠበቅ፣ በምእመናን አስተዋፅኦና በልማት ውጤት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ፣ ማእከላዊነትን የጠበቀ መልካም አስተዳደር ከላይ እስከ ታች በማስፈን የካህናትን ኑሮ ለማሻሻልና ድህነትን ለማጥፋት መታቀዱ በብፁዕነታቸው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡

ለዚሁ ጉባኤ የተዘጋጀው ‹‹ዐዋጅ ነጋሪ›› የተሰኘው የሰበካ ጉባኤ መመሪያ መጽሔት በአራተኛ ዓመት ቁጥር ሰባት እትሙ፣ 48ቱ አህጉረ ስብከት እያንዳንዳቸው ያሏቸውን የምእመናን ብዛት፣ የገዳማት እና አድባራት ብዛት፤ በስብከተ ወንጌል፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ገዳማትን እና ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከር፣ በራስ አገዝ ልማት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ በተደረጉ አስተዋፅኦዎችና ሌሎችም ተግባራት ዙሪያ የተፈጸሙ ክንዋኔዎችን በተመለከተ የተላኩ ሪፖርቶች በአሕፅሮት ተካተውበት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰራጭቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ማሽኖች በእርጅና ምክንያት ከሚሠሩበት የሚቆሙበት ጊዜ የበለጠ እንደሆነና ለእድሳትም ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይኸው መጽሔትም በሌላ የግል ማተሚያ ቤት መታተሙ ታውቋል፡፡ ለጉባኤው ዝግጅት ቅርበት ያላቸው የቤተ ክህነቱ ምንጮች እንዳስረዱት፣ ለመጽሔቱ ኅትመት ፣ በጉባኤው ላይ ይታያል ተብሎ ለሚጠበቀው የፓትርያርኩ ከ1984 - 2003 ዓ.ም መዋዕለ ዜና የሚዘክር ዶክመንታሪ ፊልም ዝግጅት፣ ለጉባኤው አባላት አበልና መስተንግዶ በሚል የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ሁለት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አባሎች የሚገኙበት የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ብር 600,000 ወጪ አድርጓል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የጉባኤው ዝግጅት ወጭ ግን ከብር 100,000 አይበልጥም ነበር - እንደ ምንጮቹ መረጃ፡፡

የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በንባብ ቀርቦ ከተሰማ በኋላ በቀጥታ ወደ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ሽግግር ተደርጎ፣ በደቡብ ሱዳን ባለባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ሳቢያ ቅድሚያ የተሰጣቸው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀ/ስብከት የሆነው የጋምቤላ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተመጠነ ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በመጽሔቱ በተገለጸው ሪፖርት መሠረት በሀ/ስብከቱ 39 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤ 327 ካህናት በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፤ የምእመናኑ ቁጥር አልተገለጸም፤ በቅኔ፣ በአቋቋም፣ በቅዳሴ እና በመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 47 የክልሉ ተወላጆች በዲቁና እና ቅስናም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት አምነው ተጠምቀዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሀ/ስብከቱ ካስገባው ብር 1,176,115.50 ውስጥ የመንበረ ፓትርያርክ 35 በመቶ ብር 82,796.91 ገቢ ማድረጉ ተገልጧል፡፡

በዚህ መልኩ የጅማ፣ የመቐለ፣ የኢሉ አባቦራ፣ ድሬዳዋ፣ ጋሞጎፋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ባሌ፣ ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች በተከታታይ ሪፖርታቸው ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ፣ የጅማ እና የኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት ከአክራሪ እስልምና የተነሣ ያለባቸውን ተግዳሮት ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋው ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ገሪማን ‹‹ንዑድ፣ ክቡር›› እያሉ ደጋግመው በማወደሳቸው በጉባኤተኛው ተሥቆባቸዋል፡፡


በአህጉረ ስብከቱ የሪፖርት አቀራረብ ሥራ አስኪያጆቹ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በ‹ዐቃቤ ሰዓትነት› በሰጡትና በጥብቅ በሚቆጣጠሩት ከ5 - 10 ደቂቃ ባለው ጊዜ ሪፖርታቸውን በችኮላ ያቀርባሉ፡፡ ከዚሁም ላይ እንደ ወትሮው ሁሉ ለመንበረ ፓትርያርክ በሚደረገው የዘመኑ የ35 ከመቶ ፈሰስ ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የሰሰሱ መጠን የአህጉረ ስብከቱ ጥንካሬ እና ዋናው የሥራ ፍሬያቸው መለኪያ መስሎ ታይቷል፡፡

ከቀትር በኋላ ከ10፡30 - 11፡25 ባለው ጊዜ በቀረቡት ሪፖርቶች፣ (በተለይም የሰበካ ጉባኤ እና የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ) ላይ ውይይት እና ጥያቄ እንደሚኖር በተገለጸው መሠረት መድረኩ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለተሰብሳቢው ክፍት መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም አንዳችም ጥያቄ ይሁን ውይይት ሳይነሣ ቀርቷል፡፡ የፍርሃት ይሁን የፍላጎት ማጣት? ብለው ሲጨነቁ ለነበሩት በጉባኤው የደጀ ሰላም ታዛቢዎች ምላሽ የሰጠው ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ጥያቄ እና አስተያየት ከሌለ ሪፖርቱ ይቀጥል›› ብለው ከመናገራቸው ቤቱ በተሰብሳቢዎቹ ለየት ያለ የጭብጨባ ዘይቤ የተናጋበት ሁኔታ ነው - አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡

በጉባኤው ላይ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የየራሳቸው ሪፖርት የሚያቀርቡበት ቀን ያላቸው ሲሆን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ዛሬ ያቀረቡትን የማእከላዊ ጽ/ቤቱን ሪፖርት ሙሉ ቃልና የ48ቱን አህጉረ ስብከት የተጨመቀ ሪፖርት ‹‹ቃለ ዐዋዲ›› መጽሔት እንዳገኘነው ከዚህ በታች አቅርበንላችኋል፡፡

30ኛው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ጥቅምት 12 ቀን ለሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካስተላለፉትና በመጽሔቱ ላይ ከታተመው መልእክታቸው የሚከተለውን ይገኝበታል፡- ‹‹ይህን መሰል ጉባኤ ስናካሂድ የአሁኑ ጉባኤያችን ለሠላሳኛ ጊዜ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው፡፡ በየጉባኤያቱ የሚዘጋጁ አርእስተ ጉዳዮችና የሚወጡ ዕቅዶች፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ እየቀረቡ ከተመከረባቸው በኋላ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ስብሰባችን የጉባኤውን ሪፖርት አንብበን የምንለያይበት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዕቅድ የምናቅድበትና የምንወያይበት ስብሰባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡››
እውን ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራስ እስከ እግሯ በአንድ አዳራሽ የተገኘችበት ስብሰባ በሆነውም ባልሆነውም የሪፖርት ጋጋታ ከመጨናነቅ፣ በረባ ባልረባው የውዳሴ ዝናም ከማጭበጨብ፣ ጫን ባለ የእህል ውኃ ግብዣ ከመደንዘዝ ተርፎ፡- የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን በሚያሤሩት የውስጥ አደጋ፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በደቀኑብን የውጭ ስጋት፣ እንደተባለው ጥናትና ሥር ነቀል ርምጃ በሚሻው የፋይናንስ፣ የሰው ኀይል እና የሌሎች ሀብቶች አስተዳደሯና ልማታዊ ክንውኗ ዙሪያ ይመክር ይሆን? ከቀደመውና ከዛሬው ውሎ አኳያ የሚሆን አይመስልም፡፡ ርግጡን ግን በጉባኤው የአምስት ቀናት ቆይታ የምናየው ይሆናል፡፡ 
by deje selam