Monday, December 19, 2011

ገዳመ አስቄጥስ

ጉብኝት ወደ ገዳመ አስቄጥስ

አባ መቃርዮስ

በአንድ ወቅት አባ መቃርዮስ ይህንን ታሪክ ተናግሮ ነበር። ወጣት ሆኘ በአንዲት በዓት ውስጥ ስኖር መንደሩ ጸሐፊ ሊያደርጉኝ ፍለጉ። ይህንን ክብር መቀበል ስላልፈለኩ ሸሽቼ ወደ ሌላ መንደር ገባሁ። ሸሽቼ ስሔድም አንድ ሰው አብሮኝ ነበረ። ያም ሰው እኔ በእጄ የምሰራውን እየሸጠልኝ ያገለግለኝ ነበር። በዚህ መሐል በዚያ መንደር የምትኖር አንዲት ድንግል የነበረች ሴት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አርግዛ ተገኘች። ማርገዟም በታወቀ ጊዜ ከማን እንደጸነሰች ቤተሰቦቿ አጥብቀው ጠየቋት። እሷም የደፈረኝ እና የጸነስኩትም ከዛ መናኝ ሰው ጋር ብላ ነገረቻቸው። ቢዚህን ጊዜ መንደርተኞችም ሲሰሙ በፍጥነት መጥተው ያዙኝ። በጣም ጥቁር የመሰለ ማሰሮ እና ሌሎችንም የወዳደቁ ነገሮች በአንገቴ ዙሪያ አጠለቁብኝ ከዛም ወደ መንደሮችና አደባባዮች እያዳፉ ወሰዱኝ። በጣምም አብዝተው ይደበድቡኛል። ደግሞም « ይህ መነኩሴ ልጃችንን አበላሸ፤ ያዙት፤ በሉት እያሉ ይቀጠቅጡኛል» ብዙም ክፉ ቃላትን ይናገሩ ነበር።
እስከ ሞት ድረስ ደበደቡኝ። ከሽማግሌዎች አንዱ ወደ እኔ ቀረበና « ምን እያደረጋችሁ ነው ምንስ መስራታችሁ ይህን እንግዳ መነኩሴ መከራውን የምታሳዩት ደግሞስ እስከ ሞት ድረስ እንደዚህ የምትደበድቡት» ምክኒያታችሁስ ምንድን ነው ብሎ ጠየቃቸው። እኔን ያገለግለኝ የነበረ ሰው በሃፍረት ስሜት ውስጥ ሆኖ በኋላየ ይከተለኝ ነበር። እሱም እኔን እንደሚያገለግለኝ ያውቁ የነበሩ ሰዎች እርሱን ይሰድቡት ነበር። « ተመልከት ይህንን አብዝተህ ታምነውና ታገለግለው የነበረው መነኩሴ እንደዚህ አሳፋሪ፤ ዘግናኝ እና አስነዋሪ ስራ በንጹህ ልጃችን ያደረገውን ስራ? አያሳፍርም? ምን እንደሰራ አየህ? ይሉት ነበር። የልጅቱም ወላጆች « ልጃችንን ለመንከባከብ ቃል እስኪገባ ድረስ እንዳትለቁት» ብለው ትዕዛዝ አስተላለፉ። እኔም ያንን ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ እንደምፈጽምላቸው ቃል ከገባሁላቸው በኋላ ወደ ቤተ እንድሄድ ፈቀዱልኝ። እኔም ከዛ መከራ፤ ስቃይና እንግልት እንደተላቀኩ ባየሁ ጊዜ አምላኬን አመስግኜ ወደ በኣቴ ተመለስኩ። ከዚያም የሚያገለግለኝን ሰው « ያለኝን ቅርጫቶች ሽጥና ለዚያች ሴት ስጥልኝ» አልኩት እርሱም እንዳልኩት አደረገ። ለራሴም መቃርዮስ ሆይ ለራስህ ሚስት አግንተሃል፤ እርሷን መንከባከብ ትችል ዘንድ ካለፈው የተሻለ ስራ መስራት አለብህ ብየ ለራሴ ነገርኩት። ከዚያም ሌትና ቀን መስራት ጀመርኩ። ያፈራሁትንም ገንዘብ ለልጅቷ እየላኩ መርዳት ጀመርኩ። ለብዙ ጊዜ እንደዚህ እያደረኩ መውለጃዋ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እረዳት ነበር። የመውለጃዋ ቀን በደረሰ ጊዜ ምጡ በዛባት ለብዙ ቀናት ብታምጥም መውለድ ግን አልቻለችም ነበር። « መንደርተኞችም ተሰባሰቡ፤ ተጨነቁ ደግሞም እርስ በእርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር ምንድን ነው ችግሩ እያሉ። የልጅቷ ምጥም እየበዛ፤ እየተሰቃየች በመጣች ጊዜ ምንድን ነው ችግሩ? ብለው እሷን ጠየቋት። እሷም « ምክኒያቱን አውቄዋለሁ፤ ያንን መናኝ ባልፈጸመው ድርጊት ስለ ወነጀልኩት ነው የጸነስኩት ከሱ አልነበረም፤ የጸነስኩት ከእገሌ ነው ብላ እውነቱን ከእንባ ጋር ነገረቻቸው። በዚህን ጊዜ ያገለግለኝ የነበረው ሰው በጣም ከመደሰቱ የተነሳ እይሮጠ ወደ እኔ ፈጥኖ መጣና የምስራች ብሎ ሁሉን ነገር ገልጦ ነገረኝ። ያች ሴት የጸነስኩት ከመነኩሴው አይደለም እስክትልና እውነቱን እስክትናገር ድረስ መውለድ አልቻለችም ስለዚህ እንደዚያ ሲያሰቃዩህ የነበሩት መንደርተኞች በሙሉ መጥተው ይቅርታ ሊጠይቁህ በዝግጅት ላይ ናቸው አለኝ። ነገር ግን ይህንን ስሰማ ሕዝቡ ስለ እኔ መልካም በማውራት ነብሴን በውዳሴ ያዝሏታል ብየ በመፍራት ሸሸሁ ወደ ሌላ ገዳምም ሄድኩ። ስለዚህ እኛ ከዚህ ምን እንማራለን? ሰውን በሃሰት ከመክሰስ፤ ከመውንጀል መታቀብ ይኖርብናል። ለዚህም እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን። የአባታችን የመቃርዮስ በረከታቸው እና ረድኤታቸው አይለየን አሜን።




Friday, December 16, 2011

ስለ ታቦተ ጽዮን የማናውቀው


የአኩስም ጽዮን ያለቺበት እና እቴጌ መነን ያሠሩት መቅደስ


 ሰሞኑን የአኩስም ጽዮን ያለቺበት እና እቴጌ መነን ያሠሩት መቅደስ እያፈሰሰ ነው የሚል ዘገባ በመውጣቱ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ታቦተ ጽዮንን ለማየት ዕድል ይፈጥራል እያሉ ማውራት ጀምረዋል፡፡

እስቲ መረጃ የኢሳትን ያድምጡ

 
ይህ ሁሉ የተዛባ ዘገባ የአኩስም ጽዮንን እና የአኩስም ሕዝብን ጠባይ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በዘመናዊ ታሪካችን የአኩስም ጽዮን ከነበረችበት መቅደስ ስትንቀሳቀስ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡ በዐፄ ፋሲል ዘመን ከተሠራው ማረፊያዋ እቴጌ መነን ወዳሠሩት ማረፊያ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ተንቀሳቅሳለች፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች እንዳሉት ያን ጊዜ ለመታየት አልቻለችም፡፡
የአኩስም ጽዮን አቀማመጥ፣ አጠባበቅ እና አነዋወር እጅግ ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ምሥጢራዊ ሕግ እና ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ለአንድ ጉዳይ ወደ አኩስም ጽዮን በሄድኩ ጊዜ እዚያ ካሉት ሽማግሌዎች ጋር በአፈ ንቡረ ዕዱ በኩል የመነጋገር ዕድል ነበረኝ፡፡ እኔ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ልዩ ስሜት የተሰማኝ፣ እግዚአብሔርንም ያመሰገንኩት ያኔ ነው፡፡
አፈ ንቡረ ዕደ እንደነገሩኝ የታተ ጽዮንን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ ጉባኤ አለ፡፡ የዚህ ጉባ አባላት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ ሥርዓት የሚመጠሩ ናቸው፡፡ ሃይማተኞች፣ በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ምሥጢር ጠባቂዎች፣ ቤተሰቦቻቸው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሰጡ፣ በምንም ነገር የማይታለሉ እና በእድሜ የጠኑ አረጋውያን ያሉበት ነው ጉባኤው፡፡
ይህ ጉባኤ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ይወያያል፣ ይወስናል፡፡ ለምሳሌ 1982 ዓም በኢሕአዴግ እና በደርግ መካከል በነበረው ውጊያ ጊዜ ማንም ሳያይ እና ሳይሰማ ታቦተ ጽዮንን እጅግ ጥብቅ ወደሆነ ቦታ ወስዶ ያስቀመጣት፤ በኋላም አገር ሲረጋጋ ወደ መንበርዋ የመለሳት ይህ ጉባኤ ነው፡፡
አፈ ንቡረ ዕድ እንደሚሉት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜም ቢሆን ጣልያን ታቦቷን ሊተናኮል ይችላል ብለው በማሰብ (አንዳንደች እንደሚሉት እንዳ አባ ገሪማ ወደሚባል አካባቢ) ወስደው ከጠባቂዋ ጋር በአንድ ዋሻ በማስቀመጥ እዚያ ሀገር ሰላም ሲሆን እንድትመለስ አድርገዋል፡፡ ይህ ሲወሰን እና ሲተገበር ግን ከዚህ ጉባኤ አባላት ውጭ ማንም አያውቅም፡፡ ጣልያንም አልደረሰበትም፡፡
በዐፄ ፋሲል ዘመን ተሠራው ማረፊያዋ
ታቦቷን የሚጠብቁት አና የሚያጥኑት ሰው ሲደክሙ ወይንም ሲያርፉ ተተኪውን ፈልጎ፣ መዝኖ እና ፈትኖ በቦታው የሚተካው ይህ ጉባኤ ነው፡፡ ያንን ተተኪ ለማምጣት በድብቅ በጉባኤው አባላት ዘንድ ሱባኤ ይያዛል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይደርሳል፡፡ በመጨረሻም ለአንዳቸው በራእይ ተገቢው ሰው ይገለጣል፡፡ ከዚያም በቦታው እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡
ለመሆኑ የቅርቡ ይቅርና በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ ታቦቷ የት ነበረች? ብዬ ሽማግሌዎቹን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በግራኝ ወረራ ጊዜ በወቅቱ የነበረው ጉባኤ በወሰነው መሠረት ታቦቷን ይዘው ወደ ኤርትራ ምዕራባዊ ክልል ነበር የሄዱት፡፡ በዚያ ቦታ አሥራ ሰባት ዓመት ቆይታለች፡፡ ወደ ቦታው ሲኬድ ከፊሉ የጉባኤው አባላትም አብረው ሄደው ነበር፡፡
አሥራ ሰባት ዓመት እዚያ ስትቆይ ታቦቷን ያገለግሏት የነበሩት አባት ዐረፉ፡፡ ጉባኤውም ሌላ ሰው ተካ፡፡ ሀገር ተረጋግቶ ሰላም ሲሆን ታቦቷ ትመለስ ዘንድ ጉባኤው ወሰነ፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ልትንቀሳቀስ አልቻለችም፡፡ በኋላም ሱባኤ ተያዘ፡፡ በመጨረሻም ለአንድ አባት «ታቦቷን ያገለገሉትን አባት ዐጽም እንዴት ትታችሁ ትሄዳላችሁ?» ስትል እመቤታ ተናገረቻቸው፡፡ እነርሱም ዐጽማቸውን አፍልሰው በሳጥን ሲያደርጉት ታቦቷ ተነሣችላቸው፡፡ እርሳቸውንም አምጥተው በቀድሞው ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር አጠገብ ቀበሯቸው፡፡ ብለውኛል፡፡
ታቦተ ጽዮን በሁለት መልኩ ነው የምትጠበቀው፡፡ አንደኛው በማይመረመር ጥበቡ እግዚአብሔር ባዘዘላት ጠባቂዎች ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደነገሩኝ ለአንዳንዶቹ ብቻ የሚታዩ ሰማያውያን መላእክት ጠባቂዎች አሏት፡፡ በሥውር ከገዳማት ታዝዘው መጥተው የሚያጥኗት እና የሚጠብቋት ቅዱሳንም አሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በልዩ ልዩ መንገድ ይጠብቃል፡፡ አንዳንዱ ነዳይ መስሎ፣ ሌላው ተሸካሚ መስሎ፣ ሌላው የቡና ቤት አስተናጋጅ መስሎ፣ ሌላው ካህን መስሎ፣ ሌላው ተሳላሚ መስሎ፣ ሌላውም ጠላ ሻጭ መስሎ ይጠብቃል፡፡ እነዚሀን ሰዎች ከሽማግሌዎቹ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በዚያ አካባቢ የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእነዚህ ጠባቂዎች ዓይን ሥር ነው፡፡ ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ እና ከሚያስጎበኙ መካከል መረጃ የሚሰበስቡ እና ጥበቃ የሚያደርጉ አያሌ ናቸው፡፡
የአኩስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሌሊት እና ቀን ስብሐተ እግዚአብሔር የማይቋረጥባት ናት፡፡ እንደ አንዳንዶቹ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የማይኖርበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህም የተነሣ አካባቢው በካህናቱ እና አገልጋዮቹ እይታ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ይኼ በግቢው ውስጥ እና ዙርያ ጥግ ይዞ ሸለብ ያደረገው ምስኪን እንዲሁ ምስኪን እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳታዩት ጋቢውን ገለጥ እያደረገ አካሄዳችሁን ያያል፡፡ ምናልባት ቸግር የምትፈጥሩ ከመሰለውም በምሥጢራዊ የድምጽ ምልክት ጥሪ ያቀርባል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በምዕራባውያን ዓይን ብቻ እያየን እንዳንሳሳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያን ስለ ታቦት ያላቸው አመለካከት ከእኛ ጋር በእጅጉ ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ከዛሬው የባሱ አስቸጋሪ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ መረጃ እንደልብ በሌለበት ዘመን ኖራለች፡፡ በአንድ አካባቢ የሚደረገውን ነገር በሌላው አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ለመረዳት በማይችሉበት ዘመን ኖራለች፡፡ በእነዚህ ዘመን ያልጠፋች ታቦተ ጽዮን በዚህ ዘመን የትም አትሄድም፡፡ እግዚአብሔር ፈጽሞ ተጣልቶን ካልሆነ በቀር፡፡
እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእነዚህ ጠባቂዎች ዓይን ሥር ነው
 ኢሕአዴግ ታቦተ ጽዮንን ከሀገር ያወጣል ብዬ ፈጽሞ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ዘመን ይልቅ ትግራይን ነጻ ባወጣበት እና በአካባቢው የሚደረጉት ነገሮች ሁሉ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርብ ባልሆ ኑበት 1982 ዓም ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ ሰውን በሚያደርገው ነገር መውቀስ እንዲታረም ያደርገዋል፡፡ ባላደረገው ነገር መውቀስ ግን እንዲያደርገው መገፋፋት ነው፡፡ አቶ መለስ «እንኳን ለሰው ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ይገባል» እንዳሉት፡፡
አቡነ ጳውሎስ ሮም ተገኝተው ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ በአጋጣሚ እኔም ለጉባኤ ሄጄ ሮም ነበርኩ፡፡ «ታቦተ ጽዮንን በሙዝየም እናሳያታለን» ፈጽሞ አላሉም፡፡ «ስለ ታቦተ ጽዮን ዓለም የተሻለ መረጃ የሚያይበት ዘመን ይመጣል» ነበር ያሉት፡፡ ጋዜጠኛው ግን በዚያ መልኩ ተረጎመውና ዓለምን አነቃነቀው፡፡
ፓትርያርኩ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ሥርዓቱ የሚያዝዘውን እንጂ እርሳቸው የፈለጉትን የማድረግ መብት የላቸውም፡፡ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ገብቼ ልይ ባሉ ነበር፡፡ የአኩስም ጽዮን ሥርዓት ጥብቅነት ለፓትር ያርክ እንኳን የማይመለስ መሆኑን ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ በአኩስም በንግሥ ጊዜ ታቦት አይወጣም፡፡ ሥዕል እና መስቀል እንጂ፡፡ የአኩስም ሽማግሌዎች ታቦት ከመንበሩ፣ ሰው ከሀገሩ የሚወጣው ችግር ሲኖር ብቻ ነው ብለውኛል፡፡ ለዚህ ነው ታቦቱን ከመንበሩ ሰውንም ከሀገሩ አታውጣው ብለን የምን ጸልየው ነው ያሉት፡፡ በየወሩ የመጀመርያው ሰባት ጠዋት ጠዋት ምሕላ እየደረሰ ታቦት ተይዞ ከተማው ይዞራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ታቦቷን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ያለው በየዘመናቱ በሚቀያየሩት ንቡራነ ዕድ እጅ አይደለም፡፡ ሕዝቡ በፈጣሪ ርዳታ በምሥጢራዊው ሥርዓት በመረጣቸው የሽማግሌዎቹ ጉባኤ እጅ እንጂ፡፡
አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ ነውና ተረቱ ነገሮችን በጥንቃቄ ማየቱ መልካም ነው፡፡ ፈረንጆቹ የሚሉትን ብቻ እየሰሙ እግዚአብሔር የለለ አድርጎ መቁጠሩ ግን ደግም አይደል፡፡ ይልቅስ መፍራት ያለብን ታቦተ ጽዮንን ከእሥራኤል ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ያደረጋት የእሥራኤል ዐመጽ እና በደል በእኛ ዘንድ እንዳይገኝ ነው፡፡ ከሆነ አምላክም ጥበቃውን ያነሣል፤ እኛም ጠብቀን አናድናትም፡፡
ዲ/
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንነ ይጠብቅ