Friday, April 15, 2022




ሁሌም ቢሆን ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ እያየን ዝም የሚል ልብ የለንም፡፡ በተለይ በመድረክ አገልግሎት ላይ በመናያቸው ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ ማየተ ደግሞ በጣሙን የቆስላል፡፡ መቼም ሳይገባው የቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ለመውጣት የሚደፍር አለ ብለን አናስብም ትንሽም ቢሆን ሚስጠራትን የተማረ እና የስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያወቀ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ስርዓትማ ካየንው አንድ ሰው ወደ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት በፈሪሐ እግዚአብሔርለቅረብ መወሰን በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ። ዘዳ.12:28፤ እንደተባልንው ስንመላለስ  እግዚአብሔርን በመፍራት መሆን ይኖርብናል  እግዚአብሔርን የሚፈራ ትውልድ ደግሞ ለእግዚአብሔር ቃል ይገዛል  በእግዚአብሔርም የባረካል፡፡ በንስሃ ህይወቱም ሁል ጊዜ ተጠብቆ መኖርም ይገባል እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ ራእ.3:3 ንስሃ የሚገባ ሰው ደግሞ ህይወቱ በፀሎት የመሰረታል ሁል ጊዜም ይሰግዳል ይጾማልም ለአገልግሎቱም መቃናተ ፈቃደ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ይሆናል፡፡ እነኝህ ያነሳናቸው በጣም ጥቂቱን ግዴታዎች ነው  ይህቺን ትንሻን ህይወት የሌለው ክርስቲያን አገልጋይ አይደለም ክርስቲያን ለመሆኑም ጥርጣሬ ውስጥ ይገባል፡፡
ይሁንና ይህቺን በጥቂቱ ያልነው  የዘማሪት ዘርፌ አይን ያወጣ ጋብቻ ነው፡፡ ዘማሪት ዘርፌ ከበደ ማናት በዘፋኝነት  ህይወት እያለች ምን አይነት ህይወት ነበራት የሚሉትን ሁሉ እንተወውና በቤተ ክርስቲያናችን ወደ አገልግሎት ከመጣች ብኋላ በኢትዮጵያ እያለች ከፕሮትስታንት ተሃድሶ አራማጆች ጎን ብዙ ጊዜ ስሟ ሲነሳ የነበረ ሲሆን ወደ አሜሪካም ከሄደች ወዲህ ከአባ ወልደተነሳይ ጋር በአንድ ጉባኤ ለአገልግሎት እንደምትሳተፍ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ዘማሪት ዘርፌ በኢትዮጵያም እያለች ከጋምቤላ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ  ረዳት የሆነውን ዲ/ን አይናለምን ከጋምቤላ ከተማው ውጪ በለ አድባር በቅዱስ ቁርባን ማግባቷ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ከዚየም ወደ አዲስ አበባም ሲመጣ አብረው እንደነበሩም የሚታወቅ ሲሆን ከኢትዮጵያ ከወጣች ብኋላ ደግሞ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ እሰጢፋኖስ የነበረው ዲ/ን ዘገብርኤል ጋራ በስርዓተ ተክሊል ሁለተኛዋን ጋብቻ ፈፅማለች፡፡ መጀመሪያ በስርዓተ ቁርባን ሁለተኛውን ደግሞ በስርዓተ ተክሊል ልብ በሉ በቤተ ክርስቲያናችን  ስርዓት ጋብቻ ሲፈፀም ከቤተ ክርስቲያን ከወጣ ብኋላ ምን አይነት አለባበስ  የኖረዋል የሚለውን ለእናንተ ትተን ስርዓተ ተክሊል በቤተ ክርስቲያን ስርዓት መስረት እንዴት ይፈፀማል የሚለውን ጥቂት እንመልከት፡፡
በሚታየው አገልግሎት የማይታየውን ፀጋ ከምናገኝባቸው ውስጥ ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ የማይደገም  ምስጢረ ተክሊል ነው ፡፡    ምስጢረ ተክሊል የሚፈፀመው በፍትሃ ነገስት አንቀፅ 24፡ 906 ላይ እንደተገለጣ የመጀመሪያው ሥጋው ድንግልና ነው ፡፡  ከሁለት ተጋቢዎች አንዱ ድንግልናውን ያጣ እንደሆን በድንግልና ላለው ስርአተ ተክሊሉ ተፈፅሞለት ተክሊል የሚያደርግ ሲሆን ድንግል ላልሆነው ግን ፀሎተ ንስሃ ተነቦለት ቅዱስ ቁርባኑን ተቀብለው ጋብቻቸው ይፈፀማል ፡፡
ልላው ድንግልናቸውን በተለያዩ ምክነያቶች ላጡ ለምሳሌ በሕክምና የተነሳ፤ በተፈጥሮ ሲወለዱ የድንግልና ምልክት የሌላቸው፤ ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ ተገደው የተደፈሩ፤ ከአቅም በላይ የሆነ ስራ በመስራት ድንግላናቸውን ያጡ ስርዓተ ተክሊል ሊፈፀምላቸው ይችላል፡፡ ይህ በዚሁ እንዳለ ስርአተ ተክሊል የሚፈፀመው የሃየማኖት አንድነት ላላቸው 2ኛ ቆሮ. 6፡ 14-18፤ ፍቃደኝነታቸውን ለገለፁ ተጋቢዎች እና ከ 20 አመት እድሜ በላይ  ለወንዱ ፡ከ15 እድሜ ኣመት በላይ ለሴት ከሆኑ እንድሆነ ሰረዓተ ተክሊል ይፈፀምላቸዋል፡፡ ይህንንማ ፍትሐ ነገስት አንቀፅ 24 ፤883-884፤894 እና 906 ላይ በስፋት ተዘርዝሯል፡፡
በድንግልና ለመኖር ወስኖ ቃልኪዳኑን ትቶ አፍርሶ ያለ አንድ ሰው ፀሎተ ተክሊል ሳይፈፀምለጽ በቁርባን ብቻ ማግባት  የተፈቀደ ነው፡፡ ፍትሐ ነገስት አንቀፅ 24፤ 834 ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።ዘኊ.30:2፤
በስዓርተ ተክሊል ተጋብተው ባል ወይም ሚስት አንዱ የሞተ እንድሆን እና በሕይወት ያለው ለማግባት ቢፈልግ ግን ሚስቱ የሞተችበት  ከአንድ ዓመት ብኋላ፤ ባሏ የሞተባት ከ10 ወር ብኋላ ከሐዘናቸው ተፅናንታ ማግባት ይችላሉ ይህም በፍትሐ ነገስት አንቀፅ24 ፤ 916 ተገልጧል፡፡
በጥቂቱ  ስለ ስርዓተ ተክሊል ካየን  ዘማሪት ዘርፌን ከላይ ከጠቀስንው የሚገልፃት የቱ ነው፡፡
1.    በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀሟ
2.    ከበፊቱ ባሏ ወደ ልላ ካህን ባል ማግባቷ
3.    የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት በአደባባይ መጣሷ እና ማስጠሷ
4.    አርአያ በመሆን ፋንታ ብጣሽ ጨርቅ ለብሶ ገላን እያሳዩ ከበሮ መምታቷ
5.    ማህተብ ሳታስር መታየቷ
ሌላም ሌላም ሌላም ብቻ ሁሉም ስርአተ ቤተ ክርስቲያን ለምን አልተከበረም ዋናው ጥያቄ ነው ለአንድ አገልጋይ ነኝ ባይ ደግሞ ይህቺን ጥቂቷን የቤተ ክርስቲያን ግዴታ መወጣት ግዴታው ነው ባዮች ነን፡፡ የእኛ ድርሻመሆን ያለበት እንዲህ መሰሉን ኢሰርአተ ቤተ ክርስቲያን ሲፈፀም ተመልክተን ማለፍ ሳይሆን እንዳይደግም የራሳችንን ጥረት ማድረግ የጠበቅብናል፡፡

ለቤተ ክርስቲያናችን ስርዓት መከበር ያለሰለሰ ጥረት እናድርግ ፡፡
ይህን እንድናደርግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

                                                                                                          

ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩት አባላት በእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ተወያዩ

ከጥቅምት 6-11 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሠላሳ አንደኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይካሔዳል፡፡ 
የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋናው ስባሰባ ደግሞ ጥቅምት 12  እንደሚጀመር እየተጠበቀ ሲሆን በአሁን ሰዓት እንዱና አንገብጋቢው አጀንዳ የፓትርያርክ ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከውጪው ሲኖዶስ ጋር ያለውን እርቀ ሰላ በተመለከተ ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው አቡነ መልከፄዴቅ ጋር ብቻ ውይይት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩ ሰባ አባላት    ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ወይይት ማድረጋቸው ተነግሯል ፡፡

በውይይቱም አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ በፊት እንደሚገመተው ሁሉ በገዳም መኖርን እንደሚመርጡና አንድ  ጊዜ የተጣሰው ስርዓት እሳቸው በህይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ እንዲመረጥ እንደማይፈቅዱና እሳችው እስኪያርፉ አሁን እንዳለው ቤተ ክርስቲያኗ በመንበረ ፓትርያርክ እየተመራች እንድትቆይ እንደሚሹ ማስታወቃቸውን ምንጮቻችን ዘግበውልናል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤  አሜን፡፡

†ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ቅዱስ አቡነ ሲኖዳ†



በስመ ሥላሴ
ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ቅዱስ አቡነ ሲኖዳ መርህ ለመንግስተ ሰማያት”
“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)
አቡነ ሲኖዳ የተባሉት አንዳንድ ፀሒፍያን ሀገራቸው ሸዋ ነው ይላል። ሀገራቸው ግን ጎጀም ደብረ ጽሞና ምስራቅ ከተባለው አሁን ገዳማቸው ከሚገኝበት ቦታ ተወለዱ። በ፲፬ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ይስሐቅ ጊዜ የነበሩ ጻድቅ ናቸው። በዚህ በጎጀም በደብረ ጽሞና የነበሩት ሕዝቦች በዘንዶ ያመልኩ ነበርና ያንን የሚያመልኩትን ዘንዶ በመስቀላቸው ሲባርኩ ከሁለት ተሰንጥቆ ሞቷል። የሀገሩንም ሕዝብ አስተምረው አጥምቀው ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን ስም ሰርተው ሰጥተዋቸዋል። እነሱም “ሲኖዳ ቅዱስ አቡነ መርህ ለመንግስተ ሰማያት” ብለዋቸዋል። በዚህም ጌታችን አስደናቂ ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸዋል።

Sunday, October 18, 2020

“የሚያየኝን አየሁት”
በትዕግሥት ታፈረ ሞላ
04/11/2003
የክረምት ብርድ በተለያየ ምክንያት ከቤቱ የወጣውን መንገደኛ ፊት አጨፍግጎታል፡፡ ሰጥ አርጋቸው ደርጉም ከቡድኖቹ ጋር የዕለት እንጀራውን ለመጋገር ታክሲ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሱም ሆነ ጓደኞቹ የማውራት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሌሊት በእርሱ አጠራር “ግዳጅ” የሚሉት የተደራጀ የሌብነት ሥራ ሲሠሩ ስላደሩ እንቅልፍ በማጣት ዐይኖቻቸው ቀልተው አብጠዋል፡፡ የወረዛው የታክሲው መስታወት ላይ የእነሱ ትንፋሽ ተጨምሮበት በጉም ውስጥ የሚሔዱ አስመሰላቸው፡፡

“ወራጅ” አለ፤ ሰጥ አርጋቸው፤ መስታወቱን በእጁ ጠረግ ጠረግ አድርጎ ወደ ውጭ እየተመለከተ፡፡ እጁ ላይ ውፍረቱ እጅግ የሚደንቅ የወርቅ ካቴና አድርጓል፡፡ ባለታክሲው ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበው ሕዝብ ግርግር ስለፈጠረበት አለፍ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ ስድስት ወንዶችና ሁለት ነጠላ መስቀለኛ ያጣፉ ሴቶች እንደኮማንደር በየተራ ዱብ ዱብ አሉና ሰጥ አርጋቸውን ከበቡት፡፡ 

“ሄይ! ጊዜ አናጥፋ፤ ባለፈው ዓመት እንዳደረግነው ቶሎ ቶሎ ሒሳባችንን ዘግተን ውልቅ፡፡” ሲል፤ አንደኛዋ ሴት “አዎ በእናታችሁ መታ መታ እናድርግና ከዚህ እንጥፋ፤ ዛሬ የምንቅመው ጫት መቼም…” ስትል የቡድኑ መሪ አቋረጣትና “ዲሞትፈርሽን ይዘሻል?” አላት፡፡ በነጠላዋ ደብቃ ስለቷ የበዛ ትንሽ ምላጭ በኩራት አሳየችው፡፡ “በቃ እኔ አምና ከቆምኩበት ከመቃብር ቤቱ ጎን እቆማለሁ፡፡ ዕቃ ከበዛባችሁ እያመጣችሁ አስቀምጡ፡፡ የቡድናችንን ሕግ በየትኛውም ደቂቃ እንዳትረሱ፡፡” አላቸው፡፡ ሕጉ ከመካከላቸው አንድ ሰው ቀን ጥሎት ቢያዝ፤ ብቻውን ይወጣዋል፡፡ ስለቡድኑ መረጃ ከመስጠት ይልቅ አንገቱን ለሰይፍ ቢሰጥ ይመርጣል፡፡ 

ሰጥ አርጋቸው ረጋ ባለ ድምፅ “ዳይ… ዳይ እግዚአብሔር ይርዳን” ሲላቸው ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እግራቸውን አፈጠኑ፡፡ እሱም ከኋላቸው የጨዋ መልክ ተላብሶ ተከተላቸው፡፡ የእጁን ካቴና፣ የአንገቱን ገመድ መሳይ ሀብል ያየ ሁሉ ለእሱ በመስጋት ያዩታል፡፡ ሐሳባቸውን ቢረዳ “ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው” የሚለውን ተረት ይተርትባቸው ነበር፡፡ 

ቅዳሴው አልቶ ታቦት እየወጣ ነው፡፡ እልልታው ይቀልጣል፡፡ ወንዶች ፊታቸውን አብርተው ወደ መድረኩ ቁመታቸው በፈቀደላቸው መጠን እያዩ እጃቸው እስኪቃጠል ያጨበጭባሉ፡፡

ሰጥአርጋቸው እግረ መንገዱን አንድ ዘመናዊ ሞባይል በተመስጦ በሚያጨበጭብ ወጣት ኪስ ውስጥ ሲያይ በተለመደው ፍጥነቱ ወስዶ ጓደኞቹን ወደ ቀጠረበት ቦታ ለመድረስ በሰው መሐል ይሹለከለካል፡፡
አሁን እልልታውና ጭብጨባው ጋብ ብሎ ለዕለቱ የሚስማማ ስብከተ ወንጌል እንዲያቀርቡ የተመደቡት ሊቀ ጠበብት መድረኩን ይዘውታል፡፡ 
    “…. ዛሬ እንደሚታወቀው የሁለቱ ዐበይት ሐዋርያት ክብረ በዓል ነው፡፡ ትምህርታችን ግልጥ እንዲሆንልን በወንጌል እጅግ ብዙ ፍሬ ከማፍራታቸው በፊት ስለነበራ    ቸው ሕይወት እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተቀመጠ ጊዜ “ጌታ ሆይ ሁሉም ቢክዱ እንኳን፤ እኔ ግን እስከመጨረሻው እከተልሃለሁ” ሲለው በራሱ እጅግ ተመክቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዶሮ ሳይጮኸ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡” አለው፡፡ ጴጥሮስ ተሟገተ፡፡ 


 

    “ነገር ግን ክርስቲያኖች ታሪኩን እንደምታውቁት የመጀመሪያውን አንዲት ሴትን ፈርቶ ካደ፡፡ እየቀጠለ ሦስት ጊዜ ሲክድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ የመከራ እጅ እንዳለ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስ እይታ እንደ መርፌ ወጋው፡፡ ባዶ ትምክህቱ ተገለጸለት፡፡ ከዛ ዘወር አለና አንጀቱ፣ ሆድ ዕቃው እሰኪናወጽ ይንሰቀሰቅ ገባ፡፡ ጌታ እንዳየው ጴጥሮስ ራሱን በራሱ ከሰሰ፡፡ እንባዎቹ እሳት ሆነው በጉንጮቹ ላይ ይጎርፉ ጀመር…” 
የሰጥ አርጋቸው ቡድን አባላት እየቀናቸው ነው፡፡ የአንገት ሀብል፣ የተቀንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎ፣ የገንዘብ ቦርሳዎች ሰብስበው ለዳግም ሙከራ ተሰማርተዋል፡፡ 

መምህሩ በተመስጦ ትምህርታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ “….ወዳጆቼ እኛንም እኮ በተለያየ ኃጢአት ውስጥ ስንመላለስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንና ምድርን የፈጠረ አባት የማያየን ይመስለን ይሆን? አንዳንዶቻችን  ፈጣሪ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ስለሚኖር፤ ይኼ የምናየው ሰማይ እግዚአብሔርን እንደመጋረጃ የሚጋርደው መሰለን እንዴ?...” እያሉ በሚስብ አንደበታቸው በተመስጦ ይናገራሉ፡፡ 

የሰጥአርጋቸው ጓደኞች እየተመላለሱ የሚያሲዙትን ዕቃ በትልቅ ጥቁር ፌስታል አቅፎ ቁጭ ባለበት ጆሮው የዐውደ ምሕረቱን ትምህርት እያመጣ ያቀብለዋል፡፡ ጆሮ ክዳን የለው፡፡ 

“…. ቅዱስ ጴጥሮስ ግን…..” ቀጥለዋል አባ፤
    “…. በፀፀት እንባው ኃጢአቱን ሁሉ አጠበ፡፡ ትርጉሙ “ሸንበቆ” የነበረ “ስምዖን” የተባለ ስሙን ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ለውጦ ጴጥሮስ አለው፡፡ ጴጥሮስ ማለት “ዐለት” ማለት ነው፡፡እንደገናም ጌታችን ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ደጋግሞ አንድ ጥያቄ ጠየቀው “ጴጥሮስ ትወደኛለህን?” “አዎን ጌታ ሆይ” አለ፤ “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” “አዎን ጌታ ሆይ” “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” ሲለው ለሦስተኛ ጊዜ ጴጥሮስ አንዲት ኃይለ ቃል ተናገረ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ፡፡” አለው፡፡ በንስሐው ጊዜ ራስን ዝቅ ማድረግን ተምሯልና፡፡ እንደቀደመው ጊዜ በራሱ ትምክህት “እንዲህ አደርጋለሁ፤ እንዲህ እፈጥራለሁ” አላለም፡፡ በኋላም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ባደረገው ክርስቲያናዊ ተግባር ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር አሳየ የክርስቲያን ጠላቶች ሰቅለው ሊገድሉት በያዙት ጊዜም “እኔ እንደጌታዬ እንዴት እሰቀላለሁ? ራሴን ወደ ምድር ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ፡፡ በማለት እንደ ዐለት የጠነከረ እምነቱን ገለጸ፡፡ 
የሰባኪ ወንጌሉ ድምፅ ለአፍታ ተገታና መርሐ ግብር መሪው በእልህ መናገር ጀመረ፡፡ “….ምእመናን እባካችሁ ከሌቦች ራሳችሁን ጠብቁ በጣም ብዙ አቤቱታ እየደረሰን ነው፡፡ ሞባይል ስልኮች በሴቶች በኩል ቦርሳቸው በምላጭ እየተቀደደ እየተወሰደ ነው፡፡ ወንዶችም ኪሶቻችሁን ጠብቁ፡፡ በረት የገባው ሁሉ በግ አይደለም!” አለና ይቅርታ ጠይቆ ድምፅ ማጉያውን ለሊቀ ጠበብት ሰጣቸው፡፡ 

ሰጥ አርጋቸው የፕሮግራም መሪውን የእልህ ንግግር እየሰማ ፈገግ ለማለት ሞከረና አንዳች ነገር ሽምቅቅ አደረገው፡፡ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ተመለከተ፡፡ ሰማዩ እንደ ድሮው ነው፡፡ 
ሊቀ ጠበብት የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ማስተማር ቀጥለዋል፡፡ 
    “ሰማዕቱ ቅዱስ እሰጢፋኖስ ሲወገር ልብሳቸውን ከወጋሪዎቹ ጋር ተስማምቶ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሴት ወንዱን እያስያዘ እስር ቤቶችን ሁሉ ሞላ፡፡ በኋላም የጠለቀ ክርስቲያኖችን ለመያዝ እንዲያመቸው የድጋፍ ደብዳቤ ለማምጣት ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ዳመና ጋረደውና “ሳ..ውል…ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” አለው፡፡ በአምላካዊ ድምፅ ጌታ እኮ ሳውልን ማጥፋት ወይም መቅጣት አቅቶት አይደለም፡፡ ምስክር ሲሆነው ምርጥ ዕቃው አድርጎ መርጦታልና፡፡ 


 

    “ጌታ ሆይ አንተ ማን ነህ?” አለ ቅዱስ ጳዉሎስ ግራ ገብቶት 


 

    “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ አለው፡፡” “ተመልከቱ እንግዲህ” አሉ አባ እጅግ ተመስጠው፡፡ 
አንዳንድ እናቶች ከንፈራቸውን በተመስጦና በሐዘን ሲመጡ ከሚያሰሙት ድምፅ ሌላ ሁሉም በያለበት ቆሞ ጆሮውንና ልቡን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሥራ ላይ ከተሰማሩት የሰጥአርጋቸው ቡድኖች በቀር፤ “…. ቅዱስ ጳዉሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን እኮ በአካል አላገኘውም፡፡ ታዲያ እንዴት ለምን ታሳድደኛለህ አለው? ክርስቲያን ማለት በክርስቶስ ያመነ ማለት አይደለም ወገኖቼ? አይደለም ወይ?” ሲሉ ከፊት ያሉ ሕፃናት ድምፃቸውን ከሌሎች አጉልተው “ነው!” ብለው መለሱ፡፡ 
    “ሳውልም ያሳድድ የነበረው ክርስቲያኖችን ነበርና ነው፡፡ ዛሬ እኛም ስንቶችን አሳደድን ወገኖቼ! አሁን መርሐ ግብር መሪው የተናገረውን ሰምታችኋል አይደል? እዚህ መድረክ ላይ ብዙ ምእመናን ንብረታቸውን ተገፈው እያለቀሱ ነው፡፡ ማን ነው ከዚህ መሐል በክርስቲያኖች ላይ እጁን የዘረጋው? ዛሬም መድኃኔዓለም “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ? ቅዱስ ጳዉሎስስ የኦሪት ሊቅ ነበርና ማሳደዱ ስለ አምልኮቱ ቀንቶ እንጂ ስለ ሆዱ አልነበረም፡፡ እሱን ሦስት ቀን የዐይኖቹን ብርሃን በመጋረድ የቀጣ አምላክ እኛንማ እንዴት ባለ ጨለማ ይቀጣን ይሆን? እሱን አምነው በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ደክመው ያፈሩትን በመስረቅ በማታለል ልጆቹን እያሳደድን ነው፡፡ ይኽን ያደረክ ወንድሜ! ይኽን ያረግሽ እኅቴ ሆይ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለምን ታሳድጅኛለሽ? ይልሻል፣ ይልሃል፡፡…” 
ሲሉ ሰባኪው፤ ሰጥአርጋቸው እጆቹ መንቀጥቀጥ ጀምረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብት በሰውኛ ባህርያቸው ሁሉንም እያዩ ያስተምራሉ፡፡ በእሳቸው አካል ላይ ግን ለሰጥአርጋቸው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐይኖች ታዩት፡፡ የተጨነቁ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ላካቸው፡፡ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ ወደ መሬት አቀረቀረ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ “ለካ እስከ ዛሬ ክርስቶስ ያየኝ ነበር፤ ያላየሁት እኔ ነኝ” አለ በልቡ፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው “ወገኖቼ የእኛ አምላክ የቀደመውን በደላችንን ሳይሆን የኋላውን ብርታታችንን የሚመለከት ነውና፤ ቅዱስ ጳዉሎስ ጨርቁ እንኳን ድውያንን ይፈውስ ዘንድ እጅግ ብዙ ጸጋ በዛለት፡፡ ሐዋረያው ጳዉሎስም እውነት ለሆነው በፍፁም ፍቅር ሊጠራው ለእኛም ሳይገባው ቁስላችንን ለቆሰለልን፣ እሱ ታሞ ለፈወሰን፣ ተጠምቶ ላረካን፣ ተርቦ ላበላን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር አንገቱን በሰይፍ ተቆረጠ፡፡ ሰማዕትነትን በዚህች ቀን ተቀበለ፡፡ ዛሬ ሐምሌ አምስት ቀን የምናከብረው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ወገኖቼ እኛስ አንገታችንን የምንሰጠው ለማን ነው? ለዘላለም ሕይወት ለሚሰጠን ለአምላካችን ነው ወይስ በተንኮል ለሚተባበረን ባልንጀራችን? …” 

ሰጥአርጋቸው ጥቁሩን ፌስታል እንደያዘ ድንገት ብድግ አለና በሰዎች መሐል ወደ ፊት ይገሰግስ ጀመር፡፡ አንዱ ባልንጀራው ያገኘውን ይዞ ወደ እሱ ሲመጣ በሰው መሐል ሲሹለከለከ ያየውና “ለእኔ በጠቆመኝ ይሻል ነበር፡፡” እያለ በዐይኑ ይከተለዋል፡፡ የቡድናቸው መሪ ግን ግቡ ቅርብ አይመስልም፡፡ አሁንም በሰዎች መሐል ወደፊት እየተሹለከለከ ነው፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው፡፡ “ቅዱስ ጳዉሎስ አሳዳጅ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱሱ ክርስቶስ ፍቅር በዝቶለት ልሔድ ከእርሱ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ..” እያለ በሙሉ ልቡ ይናገር የነበረው ስለ ስሙ ታስሮ ተገርፎ ተሰቃይቶ…” እያሉ ሲናገሩ አንድ ሰውነቱ ሞላ ያለ ወጣት እግራቸው ሥር ተንበርክኮ ከፌስታል ውስጥ ብዙ ቦርሳዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ወርቆች ዘረገፈ፡፡ 
ሊቀ ጠበብት ግራ ተጋብተው ወደ ልጁ ተጠጉና “ልጄ ሆይ! ምንድን ነው?” አሉት፡፡

ሰጥአርጋቸው አንገቱ ላይ ያለውን ወርቅ እየፈታ ቀና ብሎ አያቸው፡፡ እሳቸው ዐይን ውስጥ የኢየሱሱ ክርስቶስን ዐይን አየ፡፡ ዐይኖቹ በእንባ ተሞሉና በለሆሳስ “የሚያየኝን አየሁት” አላቸውና እግራቸው ሥር ተደፋ፡፡ 

ሊቀ ጠበብት በርከክ አሉና በፍቅር አቀፉት “ልጄ ስምህ ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ 

“ሰጥአርጋቸው” አለ አንገታቸው ውስጥ እንደተሸጎጠ፡፡ ሕዝቡ ገና ግራ በመጋባት ማጉረምረም ጀምሯል፡፡ ሊቀ ጠበብት በፍፁም ፍቅር ግንባሩን ሳሙና “እኔስ “ምሕረት” ብዬሀለሁ” አሉት፤ የእጁን የወርቅ ካቴና ሊያወልቅ ሲታገል እያገዙት እግዚአብሔር ይፍታህ ልጄ እግዚአብሔር ይፍታህ ይላሉ፤ ደጋግመው፡፡ 

/ምንጭ፦ ሐመር 17ኛ ዓመት ቁጥር 6/ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር




ቤተ ክርስቲያን
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ወገኖች፣ ለጸሎትና ለምስጋና ለስግደትና ለቁርባን የሚሰበሰቡበት ታቦትና መስቀል፣ ሥዕልና ንዋየ ቅዱሳን ያለበት የክርስቲያን ቤት ናት። ይችውም ባለሦስት ክፍል ሕንጻ ቤተክርስቲያን ስትሆን እኒህም ቅኔ ማህሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ ናቸው።   
በክርስቶስ ያመነ ያመነች  ምእመን ምእመንት ሰውነት ቤተ ክርስቲያን (መቅደሰ እግዚአብሔር) ይባላሉ።  ጉባኤ ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን። ቤተ ክርስቲያን ተተበብለሎ የተተረጎመው አቅሌሲያ የሚል የግሪክ ቃል ነው። “አቅሌሲያ” ማኀበር ወይም ጉባኤ ተብሎ ይተረጎማል።
“ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል...” ማቴ. ፳፩፡፲፫ (21፡13)
ስለ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጽሐፍትና ቅዱሳን አባቶች በብዙ መንገድ ተርጉመውታል።
“ቤተ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ የምታደርገን የልዑል እግዚአብሔር ደጅ ናት።” (መ/ዲዲስቅሊያ)   
“የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በመስቀል ላይ ነው፤ ስለሆነም ፈተና ይበዛባታል። ስለዚህ ከግል ሕይወታችሁ ይልቅ የቤተ ክርስቲያናችሁን አቋም አጠናክሩ።” (አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ)
“በሃይማኖት ሙቀት ቤተ ክርስቲያንን ያጋላት የመንፈስ ቅዱስ እሳት ነው።” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ)
“ለቤተ ክርስቲያን ስትል በአደባባይ  በጥፊ የተመታህ አቤቱ ይህን ማድረግህ እርሷን በከበረ ደምህ ትቀድሳት ዘንድ ነው።” (ቅዱስ ያሬድ)
“ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት አንድ የሆኑ የክርስቲያኖች የትንሳኤያቸውና የደኀነታቸው ምንጭ የክርስቶስ አካል ናት።” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

ምስክርነት
በአርባ ሰማንያ
በክብር አጥምቃ
በሜሮን ያተምሽኝ፣
ብታመም አክመሽ
ብራብ የመገብሽኝ፣
ባገባ አክሊል ጭነሽ
ፍጹም ያከበርሽኝ፣
ስሞት አስፈትተሽ
በመልካሙ ደጅሽ
የምታሳርፊኝ፣
ልመስክረው እንጂ
ቤተ ክርስቲያን ሆይ
ስንዱነትሽን፤
ፍጹምነትሽን።
ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ። መዝ. ፻፲፯፡ ፳ (117፡20)


የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት


ቅዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡

ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡

ለዛሬ ከስድስቱ የመጀመሪያውን እነሆ፡-

1ኛ. መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡

ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›.፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8.44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

አሁን ከዚህ ቦታ ከርእሳችን አንጻር እኛ የምንፈልገው ቆመ የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም ይዞ መገኘቱን መረዳት ነው፡፡ መቆም ሲባል ማማለድ የሚል ትርጓሜ እንዳለው ለመረዳት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተጻፈውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጣዖት በማምላክ ፈጣሪቸውን አስቆጡት፡፡ እርሱም ሊያጠፋቸው ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሙሴ እነዚህን ሕዝቦች ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስኝ በማለት በራሱ ፈርዶ አማለዳቸው፡፡ ፈጣሪም የሙሴን ልመና ሰምቶ መዓቱን በትዕግሥት መለሰ፡፡ ይህ ታሪክ በዘፀአት የኦሪት ክፍል ተመዝግቧል፡፡ (ዘፀ32.32)

ይህንን የሙሴ ምልጃ ቅዱስ ዳዊት በሌላ ጊዜ በድጋሚ ተርኮታል፡፡ ይኸውም በዳዊት መዝሙር የምናገኘው ነው፡፡ ነገር ግን አተራረኩ መቆም ማማለድ መሆኑን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፡፡ እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ፡፡›› የተሰመረበትንና ደምቆ የተጻፈውን ኃይለ ቃል ልብ ብለህ ተመልከት፡፡ (መዝ015.23) ባይቆም ኖሮ ሲል ባያማልዳቸው፣ ባይለምንላቸው፣ ባይጸልይላቸው ኖሮ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም እንደሚኖረው እንረዳለን፡፡

ዳግመኛም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች (መላእክት) በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ›› ይለናል፡፡ ‹‹ለመቆም›› ሲል ለመለመን፣ ለማማለድ ማለት ነው፡፡ አብሮአቸውም ሰይጣን መምጣቱን ልብ በል፡፡ ሰይጣን የመጣው ለምን ነበር? ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ፈጣሪውን ለመለመን አልነበረምን? የመላእክትም አመጣጥ ፈጣሪቸውን ስለሰው ለመለመን እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ ይህን ሲገልጥ ‹‹ለመቆም መጡ›› ይለናል፡፡ መቆም መለመን፣ ማማለድ ማለት ነውና፡፡ (ኢዮ1.6)

መቆም ማለት መጸለይ፣ ማማለድ የሚል ፍቺ እንዳለው ካስጨበጡ በኋላ ይህንን ቃል በመጠቀም የመላእክትን አማላጅነት ማስረዳት ቀላል ይሆናል፡፡

ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከምናውቀው ውጭ አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒ አቅጣጫም እንኳን ፍቺ ይዘው ይገኛሉ፡፡ አገባባቸውን እንደመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤና ምሥጢር መማር የሚያስፈልገው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ ቃላትን ትክክለኛ መንፈስ አለመረዳት የመላእክትን አማላጅነት እንዳይረዱ አድርጓቸዋልና፡፡

ለምሳሌ፡- ቅዱስ ገብርኤል ራሱ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል የተጻፈ ኃይለ ቃል ሲሆን አብዛኞቻንን እናውቀዋለን፡፡ ልዩ የሚሆነው ግን የቃሉን ትክክለኛ አገባባዊ ትርጉም ባለማወቃችን ምክንያት መልአኩ ይህን ባለ ጊዜ ‹‹እኔ አማላጅ ነኝ›› እንዳለን አድርገን አለመረዳታችን ነው፡፡ መቆም ማለት ማማለድ የሚል ትርጉም ካለው ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆም›› ማለት ደግሞ ‹‹የማማልድ›› ማለት መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነቱን ራሱ ግልጽ በሆነ መንገድ ነግሮናል ማለት ነው፡፡

እስኪ እናንተ ፍረዱ! በዚህ ስፍራ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅ ነኝ ማለቱን ካላመንን ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ማለቱን ምን ብለን እንረዳዋለን? የእግዚአብሔር ፊቱ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ነው እንጂ እንደፍጡር ወደ አንድ ገጽ የተወሰነ አይደለም፡፡ መላእክት ደግሞ በተፍጥሯቸው እንደ ሰው ልጅ የሚታጠፍና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ ስለሌላቸው አይቀመጡም፤ አይተኙምም፡፡ ታዲያ አማላጃችሁ ነኝ ማለቱ ካልሆነ በቀር መልአኩ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ሲል ምን ማለቱ ነው? መልአኩ እግዚአብሔርን እንደ ምድራዊ ንጉሥ ራሱን ደግሞ እንደ ንጉሥ ወታደር ቆጥሮ በንጉሡ ፊት ቀጥ ብዬ የምውል ዘበኛ ነኝ ማለቱ ነውን? በፍጹም አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ደጅ አፍ መቆምና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምሥጢራቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ (ራእ21.12፤ ዘፍ3.24) ይልቅ ሊሆን የሚችለው እኔ በፊቱ ባለሟልነት ያለኝ ሁሉ ጊዜ ስለ እናንተ የማማልድ ነኝ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

መልአኩ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ለምንድን ነው? ለማመስገን ነው እንዳንል ይህንን ሐሳብ ለካህኑ ለዘካርያስ መንገር ለምን አስፈለገው? የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ትርጉሙ እንዲህ ቢሆን ወደ ካህኑ ወደ ዘካርያስ ከመጣበት ጉዳይ ጋር ንግግሩ ምንም ግንኙነት አይኖረውምና ይህን መናገር አያስፈልገውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እኔ ሰዎችን ሁሉ ለማማለድ በእግዚአብሔር የምቆም ባለሟልነት ያለኝ መልአክ በመሆኔ የለመንከው ልመና መድረሱን የምሥራች ልነግርህ ብመጣ ቃሌን እንዴት ትጠራጠራለህ? ለማለት ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ›› በማለት መልአኩ ይህን ተናገረ ብንል ከሁሉ በላይ የሚያስኬድና ለአእምሮ የሚመች ትክክለኛ ትርጓሜ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡ ‹‹በዚያ ወራት ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› ይላል፡፡ (ዳን12.1) በዚህ ጥቅስ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ተብሏል፡፡ እረ ለመሆኑ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ‹‹የሚቆመው›› ለምንድር ነው? ለማማለድ አይደለምን? ይህን ካልተቀበልን ቃሉን ምን ብለን እንተረጉመዋለን? ለማመስገን ይቆማል እንዳንል ቃሉ የሚለው ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ነው፡፡ ስለ እኛ ጥብቅና ይቆማል እንዳንል ወደ ባሰ ስሕተት ይወስደናል፡፡ ሚካኤል በእግዚአብሔር ፊት ጥብቅና አይቆምምና፡፡ እግዚአብሔርም በጠበቃ የሚሟገቱት አምላክ አይደለምና፡፡ ጥብቅና ይቆማል ከማለት ይልቅ ትክክለኛውና የሚስማማው ወደ ፈጣሪ ሊለምንልን ወይም እኛን ለማማለድ ይቆማል የሚለው ትርጓሜ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተመለከትነው ‹‹መቆም›› የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም አለውና፡፡

ይህ ለምሳሌ ያህል ተጠቀሰ እንጂ በፈጣሪ ፊት እልፍ አእላፋት መላእክት ለምልጃ ይቆማሉ፡፡ ቅዱስ ዳንኤል ‹‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፡፡›› በማለት የገለጸው ይህንን እውነት ነው፡፡ (ዳን7.9-11)

ከዚህ በላይ ከብሉይ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከሐዲስ ደግሞ ስለ ቅዱስ ገብርኤል የተጻፉት ለማስረጃነት ተጠቅሰዋል፡፡ የተማሩትንና ያነበቡትን በልብ ለመክተብ መላልሶ ማንበብና ማጥናት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ብትሻ የቅዱስ ገብርኤል ዝክረ በዓል ወር በገባ በአሥራ ዘጠኝ እንደሚውል ታውቃለህ፡፡ ስለ እርሱም የተጠቀሰው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1.19 መሆኑን ልብ በልና ጥቅሱ ከወርኃዊ በዓሉ ጋር ያለውን ዝምድና መርምር፡፡ ማለትም ቁጥር 19 ላይ መጻፉን አስተውል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲሁ አድርግ፡፡ ጥቅሱ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ወርአዊ ክብረ በዓሉም በ12ኛው ቀን ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህንንና ይህን የመሰለ የራስህን የማጥኛ ዘዴ በመጠቀም ጥቅሶቹን በቃልህ ለማጥናት ሞክር፡፡

ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ

ጽንሰ ሐሳብ፡- መቆም ማማለድ ማለት ይሆናል፡፡ የዚህ ማስረጃው (መዝ105.23፤ ኢዮ1.6) ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ በፈጣሪ ፊት ይቆማሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡
በቃል የሚጠኑ ጥቅሶች

  • 1ኛ.ሉቃ1.19
  • 2ኛ.ዳን12.1
  • 3ኛ.ዳን7.9-11


  • እነዚህን ማጥናት አያቅትምና አጥንቶ ለልጆች በማስጠናት የወላጅነት ግዴታችንን በዚህ መንገድ እንወጣ!



     ይቆየን!

    በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ