- ምእመናን “ቅዱስ አባታችን” ብለው በሙሉ ልብና በፍቅር የሚታዘዙት አባት ይፈልጋሉ፤
- ቤተ ክርስቲያን “እንቁላልና ቲማቲም የሚወረወርበት ሌላ ፓትርያርክ” አያስፈልጋትም፤
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 9/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 18/2012)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን መንበረ ፕትርክና በ5ኛው ፓትርያርክ አረፍተ ሞት ባዶ ከሆነ ወዲህ ላለፉት 20 ዓመታት ሲያከራክር
የነበረው ርዕሰ ጉዳይ እንደገና፣ እንደ አዲስ መወያያ መሆን ጀምሯል። በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃም፣ በግል ደረጃም
የተለያዩ ሐሳቦችም በመንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ። በምእመኑ ደረጃ “ነገረ ፓትርያርክ”ን ከማንሣት በፊት ዕርቀ ሰላሙ
መቅደም አለበት የሚለውን አበክሮ በማቅረብ ላይ ይገኛል። የተለያዩ ደብዳቤዎችንም ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ
አቅርበዋል። በሁሉም በኩል ሥጋት የሆነው ግን ክንደ-ፈርጣማው፣ እጀ ረዥሙ የኢሕአዴግ መንግሥት ለእምነቱ ተከታዮች
ፍላጎት ሳይገዛ “የራሱን ፓትርያርክ” እንዳያስቀምጥ ነው።
በጥቅምት 6/2005 ዓ.ም ዘገባችን እንደገለጽነው በመንግሥት በኩል የመጀመሪያ የፓትርያርክ ምርጫው የምሥራቅ
ሸዋ ሀገር ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጎርጎርዮስ ሲሆኑ ይህ ካልሆነ በሁለተኛ ደረጃ የያዛቸው በኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የታመነ ነገር ሆኗል፡፡ የቀድሞው
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለአንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደ እንደራሴያቸውም
እንደተተኪያቸውም አስተዋውቀዋቸው ነበር የተባሉት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
ስድስተኛ ፓትርያርክ ይኾኑ ዘንድ መንግሥት ወስኖ መግፋት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ ምንጮቻችን
ማብራሪያ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ወደ ፕትርክናው መንበር መገፋታቸው÷ “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አቋም እና አሠራር (እነርሱ ራእይ ይሉታል) ያስቀጥላሉ፤ ለመንግሥት ለመታዘዝና ፍላጎቱን ለማስፈጸም ይመቻሉ” በሚል ሐሳብ ነው ተብሏል፡፡