ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, June 23, 2011

እውን ‹‹ተሐድሶ›› የለምን?

ሰሞኑን በተደጋጋሚ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ወሬ ነው!›› የሚል ንግግር በመስማቴ ይህንን አጭር ማሳሰቢያ ለመጻፍ ተነሳሣው፡፡ በእርግ...ጥ ንግግሩን ቀደም ሲልም ሰምቼው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን መደጋገሙ ሲበዛ በተለይም ግምት የሰጠዋቸው ሰዎች ነገሩን ተቀብለዉት ስመለከት ለካ የሚናቅ ሐሰት የለም አሰኘኝ! ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ወሬ ነው!›› ለሚለው ለምን ፈጠረው? ይህን ሐሳብ ፈጥሮ ምን ይጠቀማል? ቢፈጥረውስ እናንተ ተሐድሶ ካልሆናችሁ ምናችሁ ይነካል?  የሚል የራሴን ጥያቄ ፈጥሮ ከመጠየቅ በቀር እኔን ስለማይመለከተኝ የማኅበሩ የቤት ሥራ ነውና ራሱ ይጨነቅበት ብዬ አልፌዋለሁ፡፡ ትንሽ ማብራሪያ ለመስጠት የምሞክረው ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› በሚለው አመለካከት ላይ ነው፡፡ በእርግጥ አንድን ነገር እያለ ‹‹የለም›› ማለት አንድም ሐሰት ዳግመኛም የጥፋት ስልት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአጥፊዎች ሁሉ አውራ የሆነ ሰይጣንም ይህን ስልት በተለያየ መንገድ ሲጠቀምበት ይታያል፡፡ ሰይጣን በሰዎች ልቡና ያድርና ራሱን ደብቆ ክፉ ሥራ ሲያሠራቸው ይኖራል፡፡ በወንጌል እንደተነገረው በጾም፣ በጸሎትና በመንፈሳዊ ሥራ እንዲሁም በተቀደሰ ውሃና አፈር (በጸበል) ኃይሉ ሲደክምበት ‹‹ተቃጠልኩ›› እያለ ይለፈልፋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን መንፈሳዊ ሥርዓት በማከናወን ያንን ሰው ለቆ እንዲወጣ ይገሠጻል፤ ይረገማል፤ ይገዘታል፡፡ ወዲያውም ለቆ ይሄዳል፡፡ ክርስቲያኖች ይህን የሰይጣን ክፋትና አሠራር ያውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር መኖር የማያምኑ ከሃዲዎች በሰይጣን መኖርም አያምኑም፡፡ ሰይጣን እነዚህን ሰዎች እኔ ‹‹የለውም›› እያለ ይዘብትባቸዋል፤ ይዋሻቸዋል፡፡ እነርሱም በጸበል ሲለፈልፍ አይተው በሥራህ ተገለጥክ፤ አወቅንብህ እንዳይሉት እንኳን ይህ እኮ ጭንቀት ነው፤ ቅዠት ነው፤ ኢሉዥን ነው /illusion/፤ ኮንፍዩዥን ነው /Confusion/ ወዘተ እያለ ምክንያት በመደርደር አለመኖሩን ሊያሳምናቸው ይጥራል፡፡ በዚህም ሐሳቡን የተቀበሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ይገርማል! ሥራው እየታየ፤ ንግግሩ እየተሰማ የለውም ማለቱ አቤት የሰይጣን ድርቅና! የተሐድሶ አራማጆች ሥራ ዓይኑን አፍጥቶ ጥርሱን አግጥጦ በሚታይበት በዚህ ዘመን ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የፈጠራ ወሬ ነው እንጂ በእውን ያለ ነገር አይደለም›› ማለት አንድም አይኔን ግንባር ያድርገው ከማለት ይቆጠራል፡፡ ወይም ደግሞ ከላይ በምሳሌ እንደተጠቀሰው አቅጣጫ የማስቀየር የቅሰጣ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሌላው ቢቀር ፊደል የለየና ማንበብ የሚችል ሰው ከአንድ አሥር ዓመት ወዲህ የወጡትን በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳዮች የተጻፉትን የሕትመት ውጤቶች ከሁሉም አቅጣጫ ቢከታተል ‹‹ተሐድሶ›› በቀናች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማ ቀኖና እና ትውፊት ላይ ያነጣጠረ በጥናት የተቀነባበረ የጥፋት ስልት እንጂ  ጭራቅን የመሰለ የፈጠራ ወሬ አለመሆኑን በቀላሉ ይረዳል፡፡ ‹‹ተሐድሶዎች›› ራሳቸው የቁርጥ ቀን መድረሱን እያወጁ ወደ አደባባይ ሲመች በቃልና በጽሑፍ ሳይመች ደግሞ በጉልበት ጭምር እየተጋፉ ለመውጣት በሚሽቀዳደሙበት በዚህ ጊዜ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር›› የለም ማለት ከ‹‹ተሐድሶነት›› የከፋ የሐሰት ምስክርነት ነው፡፡ በአገራችን የከተማና የገጠር ጎዳናዎች ላይ ሲመላለስ ‹‹…የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን›› የሚል ጽሑፍ እያነበበ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› የሚል ሰው ምን ሊባል ይችላል? የማያውቅ ሰው የዚህኛው ከዛኛው ልዩነቱ ምንድር ነው? አንድ ናቸውን? እያለ ይጠይቃል እንጂ በማያውቀው ነገር ደፍሮ ምስክርነት አይሰጥም፡፡ በዛሬ ጊዜ ‹‹ተሐድሶአዊ እንቅስቃሴ የለም›› ማለት በሚቃጠል ቤት ውስጥ ጭስ አፍኖት እየሳለ በር ዘግቶ እንደመቀመጥ ይቆጠራል፡፡ ዛፍ በፍሬው እንደሚታወቅ ‹‹የተሐድሶ እንቅስቃሴም›› መገለጫዎች አሉት፡፡ እነዚያን እየመረመሩ ‹‹እንግድዳ ትምህርት›› (ዕብ13.9) ሲያገኙ መለየት እንጂ ‹‹ተሐድሶ የት አለ?›› ‹‹ተሐድሶዎቹስ እነማን ናቸው?›› የሚል ዓይነት ያልበሰለ አጠያየቅ ከእውነታው እንድንርቅ ሊያደርገን ይችላል፡፡ በየመንፈሳዊ መድረኮች ላይ ሁለት ዓይነት ልሣን ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል፡፡ የቱ ‹‹እንግዳ ትምህርት›› እንደሆነ የእረኛቸውን ድምፅ የሚሰሙ እውነተኛ በጎች ለይተው ያውቁታል፡፡ የሴት ድምፅ ከወንድ እንደሚለይ ልዩነቱ ጉልህ ነውና፡፡ ዕረፍት የማይሰጡ፤ የቃላት ድርደራዎችና ጩኽቶች ከማሳመን እና ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ ሌላ ጥያቄ የሚያጭሩ፣ የሚያጠራጥሩና የሚያስጨንቁ ስብከቶችና ‹‹መዝሙሮች›› የምን ነጸብራቅ ናቸው? ከአንድ የተሰወረ ምንጭ ካልቀዱትስ በቀር ብዙ ሰዎች አንድ ዓይነት ዘይቤ፣ ቃላት፣ ድምፅና እንቅስቃሴ ሊኖራቸው እንዴት ይችላል? በዚሁም ላይ ይህ ሁሉ ደግሞ ከመናፍቃኑ ጋር አንድ መሆኑ ምን ይጠቁማል? ‹‹ከተሐድሶ›› ስልቶች አንዱ በስውር መንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ በጥናትና በዓላማ የሚተገበር በመሆኑ በማስተዋል ካልሆነ በፍጥነት ለመለየት ያስቸግር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን ተክል ምንነት ለይቶ ለማወቅ ቅጠሉንና ፍሬውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለዚህም ገበሬ መሆን አይጠይቅም፡፡ ይህ ኮክ ነው፤ ይህ ወይን ነው፤ ይህ በለስ ነው! ለማለት ቆፍሮ ሥሩን የሚያይ የለም፡፡ ሥሩ በምክንያት ከመሬት ውስጥ መቀበሩ ይታወቃልና፡፡ ሥሩ ምንም ይሁን ምን የተክሉን ዓይነት ለይቶ ለማወቅ ቅጠሉንና ፍሬውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እንደዚሁም የ‹‹ተሐድሶ እንቅስቃሴ›› መራራ ፍሬው በስሎ አዝመራውም ነጥቶ እየታየ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል! ‹‹ተሐድሶ የሚባል የለም›› እያሉ ስለማያውቁት ነገር ምስክርነት ከመስጠት፤ ለጥፋትም ሥራ ተባባሪ ከመሆን፤ ራስንና ሌሎችንም ከመጉዳት የሚቀድመው አፍን መሰብሰብና ራስን መመርመር ነው፡፡ ‹‹የተሐድሶ›› ሴራ ስውር እንደመሆኑ መጠን የዚህ የጨለማ ሥራ ሰለባ ከሆኑና ያላመኑበት ጉዳይ ከሆነ ይህንንም እውነት ዘግይተው ከተረዱ የሚሻለው ቶሎ መመለስ ነው፡፡ ‹‹ተሐድሶ የሚባል የለም›› ማለት ራስን የሚያድን መንገድ ስላልሆነ ከወዲሁ ንስሐ መግባት ይገባል፡፡ እንዲያውም ሌሎች እንዳይጠፉ መረጃ መስጠትና ካገኙት ልምድ በማካፈል አካሄድን ማሳመር እንጂ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነቱ ድርቅና የሚበጅ አይሆንም፡፡ ነቢዩ እንደተናገረ ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉና›› (1ሳሙ2.10) ስንዴ ከእንክርዳድ ጋር በመመሳሰሉ እንደ አረም ተቆጥሮ አብሮ ቢነቀል እህል ስለሆነ ግዕዛን የለውምና አይፈረድበትም፡፡ ማለትም ማን ከእንክርዳድ ጋር ተሰለፍ አለህ? አይባልም፡፡ ክርስቲያን ግን ከመናፍቃን ጋር ቢሰለፍና አብሮ ቢቆጠር ራሱን አልለየምና ወቀሳ አይቀርለትም የሚገባው ነውና፡፡ ከክፉዎች ጋር አብሮ እንዳይፈረድበት የፈለገ እንደሎጥ ተለይቶ መውጣት ይገባዋል፡፡   በነገራችን ላይ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› የሚለውን ሐሳብ ይዞ ሙጭጭ ማለት ምእመናንን እንዳይነቁ የማደናገሪያና የማዳከሚያ ስልት ካልሆነ በቀር ለምን ይጠቅማል? እንኳን ኖሮ ባይኖር እንኳን የሰባኪና የካህን ድርሻው እንዲህ ያለ ፈተና ሊከሠት ወይም ሊኖር ይችላልና ተጠንቀቁ እያሉ ምእመናንን ማንቃት እንጂ ‹‹ምንም የሚመጣ ችግር የለም›› እያሉ ማስነፍ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገሃድ የሚታየውን እንቅስቃሴ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ አይደለም፡፡ ‹‹ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ›› ዕብ13.9 ይቆየን! by Hibret Yeshitila

አበው ይናገሩ

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ

የምንኩስና ግብር ምን ነበር ሚስጢሩ

የክርስቲያን ህይወት ምን ነበር ተግባሩ

መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና

ወልድ ዋህድ ብሎ በእምነቱ የፀና፡፡

ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ

ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ

ነቢያት በመጋዝ የተሰነጠቁት

ሀዋርያት ቁል ቁል የተዘቀዘቁት

ሰማእታት በእሳት የተለበለቡት

ቅዱሳን ገዳም ደርቀው የተገኙት

ሚስጥሩ ምን ነበር አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ጊሸን ላሊበላ

የቅዱሳንን አጽም ለምን እንዳልበላ፡፡

ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር

እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡

ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት

ወይስ ሃብት ንብረት የተሟላ ቤት

ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት

እናንተ ገዳማት ምስጢሩን አውሩት፡፡

ጎበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና

ምግባር ሃይሞኖቱን በእጅጉ ያቀና፡፡

እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት

ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡

የጊዮርጊስ ወዳጂ የት ነው የሚገኘው

በመሃል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው

ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ አይኔን ሰው አማረው

የሃይማኖት ጀግና የት ነው የማገኘው?

ልጋባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት

ማህበረ ስላሴ ከቅዱሳ ቤት

አክሱም ጊሸን ማርያም ከቃልኪዳን ቦታ

ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ፡፡

ፈርሃ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ

ቤተክርስቲያንን ያልተዳፈረ

የት ነው የሚገኘው ለሃይማኖቱ ሟች

ለተዋህዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች

የወገን መመኪያ የከሃዲ መቅሰፍት

ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሳ ቀስቅሱት

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ

የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምስጢሩ

የክርስቲያን ህይወት ምን ነበር ተግባሩ

መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ አይኔን ጀግና አማረው

በእምነት የፀና የት ነው የማገኘው፡፡

ወልድ ዋህድ ብሎ በእምነቱ የፀና

ብቅ ይበል እንየው እሱ ማን ነው ጀግና

በጎችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ

መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ

የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ

እንደዚያ እንደጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ፡፡

የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው

የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው

የዓለም ደስታዋ ልቡን ያልማረከው

የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?

ምስጢርን ከምስጢር አንድ አድርጎ ተምሮ

ወልድ ዋህድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ

እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ

ከጳውሎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር

መሆኗን የሚያምን ማህደረ እግዚአብሔር

ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን

ትንታግ ምልስ ጭንግፍግፍን

ልሣነ ጤዛ መናፍቅን

ወልደ አርዮስነ ዲቃላውን

በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ

ጀግና ማን ነው ብቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት

እስኪ ጎርጎርዮስ ይምጣና ጠይቁት፡፡

ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ

ምስጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ

የክርስቶስ ባሪያ የአጋንንት መቅሰፍት

ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት

ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት

የፀሎት ገበሬ ገብረመንፈስ ቅዱስንም ይነሳ ቀስቅሱት

ይነሳ ጊዮርጊስ ይመስክር ምስጢር

የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ

ዲያቢሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ

ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ

እመር ብለው የወጡት ከስጋ ገበያ

ፆም ፀሎት ነበር የሃይማኖት ጋሻ

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት

አላማው ምንድን ነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና፡፡

ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ

ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡