ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, June 23, 2011

አበው ይናገሩ

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ

የምንኩስና ግብር ምን ነበር ሚስጢሩ

የክርስቲያን ህይወት ምን ነበር ተግባሩ

መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና

ወልድ ዋህድ ብሎ በእምነቱ የፀና፡፡

ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ

ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ

ነቢያት በመጋዝ የተሰነጠቁት

ሀዋርያት ቁል ቁል የተዘቀዘቁት

ሰማእታት በእሳት የተለበለቡት

ቅዱሳን ገዳም ደርቀው የተገኙት

ሚስጥሩ ምን ነበር አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ጊሸን ላሊበላ

የቅዱሳንን አጽም ለምን እንዳልበላ፡፡

ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር

እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡

ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት

ወይስ ሃብት ንብረት የተሟላ ቤት

ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት

እናንተ ገዳማት ምስጢሩን አውሩት፡፡

ጎበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና

ምግባር ሃይሞኖቱን በእጅጉ ያቀና፡፡

እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት

ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡

የጊዮርጊስ ወዳጂ የት ነው የሚገኘው

በመሃል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው

ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ አይኔን ሰው አማረው

የሃይማኖት ጀግና የት ነው የማገኘው?

ልጋባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት

ማህበረ ስላሴ ከቅዱሳ ቤት

አክሱም ጊሸን ማርያም ከቃልኪዳን ቦታ

ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ፡፡

ፈርሃ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ

ቤተክርስቲያንን ያልተዳፈረ

የት ነው የሚገኘው ለሃይማኖቱ ሟች

ለተዋህዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች

የወገን መመኪያ የከሃዲ መቅሰፍት

ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሳ ቀስቅሱት

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ

የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምስጢሩ

የክርስቲያን ህይወት ምን ነበር ተግባሩ

መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ አይኔን ጀግና አማረው

በእምነት የፀና የት ነው የማገኘው፡፡

ወልድ ዋህድ ብሎ በእምነቱ የፀና

ብቅ ይበል እንየው እሱ ማን ነው ጀግና

በጎችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ

መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ

የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ

እንደዚያ እንደጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ፡፡

የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው

የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው

የዓለም ደስታዋ ልቡን ያልማረከው

የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?

ምስጢርን ከምስጢር አንድ አድርጎ ተምሮ

ወልድ ዋህድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ

እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ

ከጳውሎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር

መሆኗን የሚያምን ማህደረ እግዚአብሔር

ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን

ትንታግ ምልስ ጭንግፍግፍን

ልሣነ ጤዛ መናፍቅን

ወልደ አርዮስነ ዲቃላውን

በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ

ጀግና ማን ነው ብቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት

እስኪ ጎርጎርዮስ ይምጣና ጠይቁት፡፡

ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ

ምስጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ

የክርስቶስ ባሪያ የአጋንንት መቅሰፍት

ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት

ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት

የፀሎት ገበሬ ገብረመንፈስ ቅዱስንም ይነሳ ቀስቅሱት

ይነሳ ጊዮርጊስ ይመስክር ምስጢር

የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ

ዲያቢሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ

ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ

እመር ብለው የወጡት ከስጋ ገበያ

ፆም ፀሎት ነበር የሃይማኖት ጋሻ

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት

አላማው ምንድን ነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና፡፡

ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ

ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡

2 comments:

  1. እውን ይናገሩ!!!! አዎ ይናገሩ የሚታይ ስራቸው ደግሞም ይናገሩ እውኑ የሚታይ ስራቸው አበው ይናገሩ

    ReplyDelete
  2. constantly i used to read smaller articles
    or reviews that as well clear their motive, and that is also happening
    with this post which I am reading at this time.
    Feel free to surf my website - hcg weight loss

    ReplyDelete