ደቂቀ ናቡቴ

Friday, July 29, 2011

ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤተ ክህነቱ ሰው


ሦስቱ ጠባየ ጳጳሳት

ቤተ ክህነቱ በየዘመናቱ ሦስት ዓይነት ጠባየ ጳጳሳትን አስተናግዷል፡፡ የመጀመሪያው እና የአብዛኛዎቹ የሆነው አድርባይነት ነው፡፡ የዚህ ምንጩ ደግሞ በዓላማ ለዓላማ የመላእክትን አስኬማ አለመድፋት ነው፡፡ የመላእክት አስኬማ /ምንኩስና/ ንጽሕናን ይጠይቃል፣ ብዙዎቹ ንጽሕናቸውን አጉድፈዋል፡፡ የመላእከት አስኬማ የዚህን ዓለም ጣዕም ይንቃል፤ ብዙዎቹ ዓለማዊነትን ኑሮ አድርገውታል፡፡ የመላእክት አስኬማ የራሴ የሚለው ዘውግ እና ንብረት የለውም፡፡ ብዙዎቹ ግን የዘውግ ብል የበላቸው፤ የዚህ ዓለም ሀብትና ንብረት ያማለላቸው ናቸው፡፡ ይኽ ደግሞ ጥብዓት የጎደላቸው፤ ትጋሀ ሌሊት የማያውቃቸው፣ የመንኖ ጥሪት መዓዛ የማይሸታቸው አድርባዮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በምስጢር የፈጸምናቸው ስህተቶች ከአሁን አሁን ተደረሶባቸው እንጋለጥ ይሆን በሚል የሚደነብሩ እና የማፍያው ቡድንም ይኽን የጎደፈ ገመናቸውን ለምእመኑ እገልጣለሁ እያለ የሚያስፈራራቸው እና ከፍርሃታቸውም የተነሣ ለዚህ ቡድን ፈቃድ እንዲያድሩ አድርጓቸዋል፡፡

ሁለተኛው እና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ጳጳሳት ጠባይ ደግሞ ቸልተኝነት ነው፡፡ የእነዚዎቹ ቸልተኝነት ከጠባቂነታቸው እና ከስንፍናቸው የሚመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን የመላእክት አስኬማ መለያ የሆነው ቅድስና፣ ዘውግ አለመለየት፣ የዓለምን ፈቃድ ማሸነፍን ገንዘብ ቢያደርጉም የጠባቂነት እና የስንፍና ቅንቅን ወሯቸዋል፡፡ ለቤተክርስቲያን የሚሆነውን ሠርተው ከማለፍ ይልቅ ሌሎች እንዲሠሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ መስዋዕት ከሚከፍሉ በሌሎች መስዋዕትነት የቤተክርስቲያንን ዕድገት ማየት ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ የጎደለውን ከሚያሟሉ፤ የጠመመውን ከሚያቀኑ ሌሎች በሚያሟሉት እና በሚያቀኑት ፍኖት መጓዝን ይመርጣሉ፡፡ እነርሱ ተናግረው ከሚያሳምኑ ይልቅ ሌሎች ተናግረው እንዲያሳምኑላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ ታሪክ ሠርተው ከማለፍ ይልቅ የተሠሩ ታሪኮችን እያመነዠጉ የታሪክ ግብ ይቅርና ምዕራፍ ሳይኖራቸው ያለፉ፤ የሚያልፉ ሰነፎች ናቸው፡፡ እነርሱ የተጣለባቸውን ሓላፊነት በቆራጥነት ከመወጣት ይልቅ ቅዱስ ፓትርያርኩ «ከተስማሙበት ምን አገባን» የሚሉ፤ ቤተክርስቲያን በሰላም ማጣት፣ በመናፍቃን ሴራ፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ስትታመስ እየተመለከቱ እነዚህ ሁሉ ችግሮች በአንድ ጀንበር በፓትርያርኩ ሞት የሚፈታ ይመስል ሞት ናፋቂዎች ሆነዋል፡፡ ይኽ መሆኑ ደግሞ ቤተክህነቱን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላተኞች እንድትወረር፣ ቅሰጣ እንዲደረግባት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሦስተኛው ጠባየ ጳጳሳት እና በቤተክህነቱ በጥቂቱም ቢሆን ትላንት የነበረ፤ ዛሬ ግን ያጣው ጴጥሮሳዊነት ነው፡፡ ጴጥሮሳዊነት ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ላይ የቆመ ነው፡፡ ይኽ ደግሞ ስለ እውነት በእውነት መሞት ልዩ ግብሩ ነው፡፡ ጴጥሮሳዊነት ከላይ እንደተመለከትነው ሁለቱ ጠባየ ጳጳሳት ሳይሆን በእግዚአብሔር አምኖ የራስንም ሓላፊነት እየተወጡ ውጤቱን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ መቀበል ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም «ኢትዮጵያ ከየት ወዴት)» በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ጴጥሮሳዊነት እንዲህ ብለዋል፡፡

«. . .ጴጥሮሳዊነት በመሠረቱ መንፈሳዊነት በመሆኑ የሚመካበትም ኀይል መንፈሳዊ እንጂ አካላዊ ወይም ጠመንጃ አይደለም፡፡ የጴጥሮሳዊነት ዓላማ አስፈላጊ ከሆነ ለእምነቱ፣ ለሀገሩና ለወገኑ ለመሞት እንጂ ለመግደል አይደለም፡፡. . . ለመሞት መዘጋጀትና ለእውነትና ለእምነት መሞት ግን ወኔን ይጠይቃል፡፡ መንፈሳዊ [ጴጥሮሳዊ]ወኔ፡፡» /ገጽ.44/

ሦስቱ የጴጥሮሳዊነት ምንጭ

ጴጥሮሳዊነት በመንፈሳዊነት ላይ የቆመ የመላእክት አስኬማ ነጸብራቅ እንደመሆኑ ከሦስት ነገሮች ይመነጫል፡፡

1 አደራን ለመጠበቅ ዝግጁ ከመሆን

አደራ ክቡር፣ ውድ፣ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደ ሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤ አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡

ለሀገራቸውና ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡ «ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡» /መርሻ አለኸኝ /ዲያቆን/፣ 1986 ዓ.ም፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ ገጽ.80/

ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ እኔም የጴጥሮሳዊነት አንዱ ምንጩ አደራን ለመጠበቅ ዝግጁ ከመሆን ይመነጫል የምለው ለዚህ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡

የጴጥሮስን ሥልጣን የያዙ፣ አስኬማውን የደፉ፣ ካባውን የደረቡ፣ መስቀሉን ከእነ በትረ ሙሴው የጨበጡት «ዘመነኞቹ» ጳጳሳት ከቤተክርስቲያን የተቀበሉትን የእረኝነት የአደራ ቃል በመተው ለቤተክርስቲያን ከሚታገሉላት ይልቅ የሚታገሏት ሆነዋል፡፡ ጵጵስናውን ሲቀበሉ የገቡትን ቃለ አደራ በመዘንጋት በጴጥሮሳዊነት ለአገርና ለወገን ሊቆሙ ይቅርና ክብርን ለአጎናጸፈቻቸው እናት ቤተክርስቲያን የማይሆኑ እርባና ቢስ ሆነዋል፡፡ ፍርሃት ድሩን ሠርቶባቸው ትምእርተ ምንኩስናቸውን ሸፍኖታል፡፡ ሹመታቸው የዖዝያን ሹመት እስኪመስል ድረስ የጽድቅ ፈሪዎች፤ የኃጢአት ደፋሮች አስመስሏቸዋል፡፡

2. አባታዊ ሓላፊነትን ከመወጣት

የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን በቆራጥነት ለመወጣት ካደረጉት ተጋድሎ ይመነጫል፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው «ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ)» ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው በሰማዕትነት አለፉ፡፡ / መርሻ አለኸኝ/ዲያቆን/፣ 1996ዓ.ም፣ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ገጽ.77/

ዛሬ ቤተክርስቲያንም ሆነች ቤተክህነቱ ያጣው ጴጥሮሳዊነት ይኽ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ይኽን የጽድቅ ፍኖት ይዘው መጓዝ ሲሳናቸው አይተናል፡፡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ የድህነት ቀንበር ለተጫነው፣ በችጋር አለንጋ ለተገረፈው፣ በሀዘን ለተቆራመደውና ለጎበጠው ሕዝባችን ሊቆረቆሩ ይቅርና አባታዊ ሓላፊነት ለሰጠቻቸው እናት ቤተክርስቲያን ጠበቃ መሆን ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ሁሉም በሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዘመን እንደነበሩት ግብዊ ጳጳስ ሆነውባታል፡፡ በእርግጥም እውነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የአሜሪካ እና የካናዳ ዜግነት ኖሯቸው በአሜሪካ እና በካናዳ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የግላቸው ቤተክርስቲያን የከፈቱ ባዕዳን ናቸው፡፡ እዚው ያሉት በየስድስት ወሩ ከዲያስፖራው ምእመን በተወካዮቻቸው አማካይነት የተሰበሰበውን ገንዘብ ለመተሳሳብ እና የድርሻቸውን ለመውሰድ ወደ አሜሪካ ያመራሉ፡፡ በገንዘቡም ከአንድ አባት የማይጠበቅ ኢ-ሥነምግባራዊና ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ እንዴት ጴጥሮሳዊ ወኔ ይኖራቸው)

ሌሎቹም የቤተክርስቲያን አባት መሆናቸው እስኪጠፋን ድረስ ሀገረ ስብከታቸውን ትተው አዲስ አበባ በዘመናዊ ቪላ የሚሽሞኖሙኑ፤ እነርሱ በሀገረ ስብከታቸው ተቀምጠው የሚሆነውን ከመሥራት ይልቅ፤ ባለጉዳዮችን በየመኖሪያ ቤታቸው የሚያንከራትቱ፤ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝባዊ አለኝትነታቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ፤ ዘመናዊ ቤት የሠሩበትን፣ ዘመናዊ መኪና የገዙበትን፣ በየሳምንቱ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ማር፣ በግ የሚያማርጡበትን ገንዘብ የሰጣቸውን ምእመን «ቤተክርስቲያን ተሳልመህ ከመመለስ ውጭ ምንም አያገባህም» ብለው የሚመጻደቁ ፊውዳሎች ናቸው፡፡ /ነጋድራስ ጋዜጣ፣ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም፣ቅጽ.07፣ቁጥር 240፣ገጽ.2/

አንዳንዶቹም ከቤተክርስቲያን ልዕልና እና መታፈር ይልቅ ራሳቸውን በአገረ ስብከቶቻቸው ልዑላን በማድረግ የሾሙ፤ የአክሊለ ሦክ ምሳሌ የሆነውን ቆብ ማድረጋቸውን ዘንግተው ዘውድ የደፉ ይመስል በዙርያቸው «እራት አግባዎችን» አደራጅተው ለቤተክርስቲያን የማኅፀን እሾኽ የሆኑ፤ የትኛውም አካል እነርሱን እስካልነካ ድረስ ቤተክርስቲያን ላይ «ቤንዚል አርከፍክፎ፣ ክብሪት ጭሮ እሳት ቢለቅ» አባታዊ መዓዛ የማይታይባቸው፤ ጴጥሮሳዊነት እጅጉን የራቃቸው ሥጋውያን ናቸው፡፡ እናም አንዱ ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤ ተክህነት ጴጥሮስ እና ጴጥሮሳዊነት ይኽን ነው፡፡

3. ከመንኖ ጥሪት
መንኖ ጥሪት በዚህ ዓለም ያለን ማንኛውም ሀብትና ንብረት ንቆ መተው ነው፡፡ «ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም» እንዲል ሉቃ.14.33፡፡ እንግዲህ የዚህን ዓለም ጣዕም ማጣጣም ያልተወ መንፈሳዊ አባት የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሊሆን ይቅርና ጥሩ ክርስቲያንም አይሆንም፡፡ እርሱ ምውት ሕሊና ነውና፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት ጥብዓት ምንጩ ይኸው መንኖ ጥሪት ነው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን የእርሱ አቋም የራሳቸው አቋም፤ የእርሱ የጭቆና አገዛዝ የእርሳቸው አገዛዝ፣ የእርሱ ተራ ፕሮፓጋንዳ የእርሳቸው እውነት አድርገው እንዲቀበሉ መደለያ /ገንዘብ፣ መኪና በዘመኑ ዘመናዊ የሚባል ቤት/ ልስጦት ሳይላቸው ቀርቶ ነውን) ለሕዝባቸው፣ ለሀገራቸውና ለቤተክርስቲያናቸው ሰማዕት የሆኑት) እርሳቸው ግን መንኖ ጥሪትን ገንዘብ ያደረጉ አባት በመሆናቸው ሌሎቹ የቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ለፋሺስት ጣሊያን ሲያድሩ መደለያው ሳያንበረክካቸው በመንፈሳዊ ወኔ ሰማዕት ሆነዋል፡፡

የዛሬዎቹ አንዳንድ ጳጳሳት የመንኖ ጥሪትን ሕይወቱን ይቅርና ቃሉን ማወቃቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ዛሬ፣ ዛሬ አንዳንዶቹ ለመኪና ስጦታ፣ ለገንዘብ መደለያ፣ ለውዳሴ ከንቱ ብለው እናት ቤተ ክርስተያንን ዋጋ እያስከፈሏት ይገኛሉ፡፡ ዶግማዋን በላንድ ክሩዘር፣ ቀኖናዋን በG+1,2,3,4 . . . . ቤቶች ለውጠዋል፡፡ ሥርዐተ አበውን አመድ ላይ የወደቀ ሥጋ አድርገዋል፡፡ ወርቅና ብር ለመዘነላቸው አጽራረ ቤተክርስቲያን ሁሉ የሚያድሩ እንዲሁም ጥብቅና የሚቆሙ፣ ጥሩ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

አንዳንዶቹም የጴጥሮሳዊነት ምንጭ የሆነው መንኖ ጥሪት እጅግ ስለራቃቸው በየገዳማቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ የገዳማቱን እና የየአድባራቱን መሠረታዊ ችግር ከሚፈታ ይልቅ እነርሱ ኪስ ሲገባ የሚያስደስታቸው፤ በየሀገረ ስብከቶቻቸው ያሉ ሊቃውንት በችጋር ሲሰደዱ፣ ወንበር ሲያጥፉ እነርሱ ግን መደለያ ያቀረቡላቸውን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ሲከባከቡ፣ ሽርጉድ ሲያበዙላቸው ይታያል፡፡ ከቤተክርስቲያኗ የአስተዳደር ሕግ እና ሥርዐት ውጭ በየሀገረ ስብከቶቻቸው የእኅት እና የአክስት ልጆቻቸውን የሚቆጥሩ፡፡ እነርሱም በአቅማቸው ቤተሰባዊ አስተዳደርን ያሳፈኑ ናቸው፡፡ ለምን) «ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ» ነውና፡፡ ከዚህ እውነታ ተነሥተን እነርሱ በፓትርያሪኩ ላይ ያነሡትን የቤተሰብ አስተዳደራዊ በደልን ስንፈትሽ ሞራላዊ ብቃት እንደሌላቸው ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ እነርሱም ቤተሰባዊ አስተዳደር ደዌ የተጣባቸው ናቸው፡፡

ለዚህም ነው፡- እኛ እያለን አጽራረ ቤተክርስቲያን አይነኩም ባዮች የሆኑት፡፡ እነርሱ ለቤተክርስቲያን መከራ ከሚቀበሉ ቤተክርስቲያን መከራ መቀበሏን የፈቀዱት፡፡ እነርሱ ሞት ከሚቀምሱ ሥርዓቷን፣ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን ለሞት የዳረጉት፡፡ በአንድ ጀንበር የበር መሰበር ብትንትናቸው ወጥቶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍያው ቡድን ያስረከቡት፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ እና ሰማያዊ ሥልጣን መከበር ይልቅ የአባ እገሌ መሻር እና የአባ እገሌ መሾም ጉዳይ ሆኖባቸው በፍቅረ ሢመት /በሥልጣን ጥም/ አብደው በቤተክህነቱም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማየት የሚገባንን የአስተዳደር ለውጥ እንዳናይ ግርዶሽ ሆኑብን፡፡

እንግዲህ ቤተክህነቱም ያጣው የቤተክህነቱ ሰው ጴጥሮስ እና የእርሱ ተክለ ሰብእና ነው፡፡ የእያንዳንዳችንም ውሳኔ የሚጠይቀው ይኽንን ለመመለስ ዝግጁ መሆን ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ሆነች ቤተክህነቱ ከገቡበት ማጥ ልናወጣቸው የምንችለው በጴጥሮሳዊነት ነው፡፡ አምላከ ጴጥሮስ ባዶዋን ለቀረችው ቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም የሰው ያለህ ለሚለው ቤተክህነት ያጣውን ሰው እስኪመልስለት እርሱ እንደፈቀደው ይሁን ከማለት ባሻግር ሁሉም ስለሁሉም በሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡

Wednesday, July 20, 2011

“አን ዱ” የለም እንጂ “አን ዱ” ማ ቢኖር?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብዙ ብዙ ፈተናወችን አልፋ እዚህ ለመድረሷ ጥርጥር የሌለው ሀቅ ነው በዘመናችን ያለው ፈተና ግን ስትራቴጂዎች በመቀየስ እስከ አሁን ካለው ኑፋቄያዊ አስተምሮ በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያኗን ባለችበት ከእነ ምእመኗ እና ሕንፃዋ ሙሉ በሙሉ ፕሮቴስታንታዊ አድርጎ መውረስ የስልቱ የመጨረሻ ግቦች ነው የተለመዱ የተሐድሶ ስትራቴጂዎች፡ ‹‹አባቶችን መከፋፈል እና የአንዱ ደጋፊ የሌላው ነቃፊ መምሰል፣ የጥላቻ ጽሑፎችን በማሰራጨት ምእመናንን ማደናገር፣ ፖለቲካዊ ክሶችን ማቅረብ፣ ከገዳማት እናቶችን ማስኮብለል፣ የነጋዴዎች እና የብፁዓን አበው ደጋፊ መስሎ መቅረብ፣ ብዙ ውስጠ ወይራ የሆኑ የጽዋ ማኅበራትን መመሥረት፣ ጉባኤያትን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዲካሄዱ እገዛ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን የውስጥ ለውስጥ(Underground) ሥራዎችን በይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል(ለዚህም ከገድላት የተወሰኑ መቀበል)፣ የፎርጅድ ጽላት ዝግጅት፣ የሙዳየ ምጽዋት ብርበራ፣ የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ እና ንዋየ ቅድሳት ዘረፋ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ በግለሰብ ስም ማዛወር፤ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባል በመሆን፣ በከተሞች ታላላቅ ጉባኤያትን በማዘጋጀት በገዳማት እና አድባራት ስም ገንዘብ ማሰባሰብ እና ለግል ጥቅም ማዋል፣ ፎርጅድ ማኅተሞችን በማዘጋጀት በአባቶች ስም ልመና ማካሄድ፣ በባሕታዊነት ስም መነገድ እና አስነዋሪ ድርጊቶችን በአደባባይ እና ሰዉ በሚያይባቸው ቦታዎች በመፈጸም ሕዝቡ ባሕታዊ እና መነኩሴ እንዲጠላ ማድረግ፣ ገዳማት ውስጥ እየገቡ በተለያዩ ሰንካላ ሰበቦች ሁከት መፍጠር እና ጠብ አስነሥቶ የተወሰኑትን አስወጥቶ ይዞ በመጥፋት እነዚያን የመናፍቃን ሰለባ ማድረግ፣ ገዳማትንም መፍታት›› ምን አለ “ አን ዱ“ ቢኖር ይህን ኩሉ ጉድ ለመፈፀም የተዘጋጁትንና እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫ ሁሉ አንድ ወደ ኋላ ብለንው የአባቶቻችንን አሰተምሮ እንዲሰብኩ ፎረማት ባረግናቸው ነበር ፡፡
“አን ዱ” ያው እንደምታውቁት በኮምፒውተር አጠቃቀም ለይ የ “አን ዱ” ጥቅም የማይረዳ የለምና አንድ ነገር ስንሳሳት የ “አን ዱ” ኮማንድ በመጠቀም የነበረውን እንዳልነበረ የደርገዋል ታዲያ ይሄ “አን ዱ” የሚባል ነገር እንደ ኮምፒውተር በኑራችንም ቢኖር ምናለበት ታዲያ ይህን አንዱ ተጠቅመን ኑፋቄውን እነዳለነበር ያለፉትን አበው ለእምነት ለተዋህዶ የቆሙትን እነደ ቅዱስ ቄርሎስ ያሉትን መልሰናቸው “ሥላሴ አትበሉ” ለሚሉት ለእነበጋሻው አይነቱ ይህን ምስጢረ ሥላሴን ከ ሀ ጀምረው ያስረዱት ነበር እንዲህም ብለው ምስጢረ ስላሴን “እግዚአብሄር በአካል ሶስት በባህርይ አንድ ብለን እናምናለን፡፡ይሄውም ፦ አንድ መለኮት ፣ አንድ ባህርይ ፣ አንድ ልእልና ፣ አንድ ጌትነት ፣ አንድ ክብር ፣ ከጥንት አስቀድሞ የነበረ አንድ ቀዳማዊነት ነው ፤ ደግሞም በሶስት አካላት ፣ በ ሶስት ገፃት ፍፁማን ናቸው ፣ ግዙፋን አይደሉም ፣ ያልተፈጠሩ ናቸው ፣ ድካም የማይስማማቸው የማይለወጡ ናቸው ፣ ለመገኘት ጥንት ለዘመን ፍፃሜ የላቸውም፡፡ ወልደ እግዚአብሄር ዳግመኛም ከአብ ባህርይ የተገኘ አምላክ ፣ ቃል ፣ ወልድ ፣ ያልተፈጠረ ፣በመለኮት አንድ ከሚሆኑ ከሶስቱ አካላት አንድ አካል ፣ ከአብ ጋር ትክክል የሚሆን ፣ አለም ሳይፈጠር በመለኮታዊ ልደቱ ከአብ የተወለደ ፣ ፍፁም እግዚአብሄር አብን በመልክ የሚመስለው ፣ በባህርይ የሚተካከለው የማይመረመረ የጌትነቱ መታወቂያ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በገፁ በአካሉ ልዩ የሚሆን የአብ ልጅ ፣ አምላክ ፣ ቃል በአባቱ ፈቃድ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ለእኛ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ያልተፈጠረ ፣ ስጋ ያልነበረው ፣ የማይለወጥ እርሱ እግዚአብሄር ቃል በማይመረመር ግብር በመልኩ ፣ በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ሰወችን ለማዳን ከአብ አንድነት ሳይለይ ከሰማይ ወረደ፡፡ ቃል ስጋ መሆን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን ሰው ሆነ ፤ ከጌትነቱ ክብር ፈፅሞ አልተለየም ፤ ምንም ሰው ቢሆን እርሱ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ነው ፤ በመለኮቱ ህግን የሰራ ሲሆን እነሆ ህግን በመፈፅም ተገኘ ፤ ህግን ሲሰጥ በነበረበት ባህርይውም ፀንቶ ኖረ፡፡ በመለኮቱ ገዢ ሲሆን የተገዢ ባህርይን ገንዘብ አደረገ ፣ ግን የጌትነት ክብር ከእርሱ አልተለየም ፤ አንድ ሲሆን ለብዙወቹ ምእመናን በኩር ሆነ ፤ በአንድነቱም ፀንቶ ኖረ፡፡ በማይመረመር ምስጢር እንደ እኛ በመሃፀን መፀነስን ወደደ ፤ እርሱ ሰው እንደመሆኑ በመሃፀን ሳለ በባህርይ መለኮቱ በሰማይ በምድር ፣ ከምድርም በታች ምሉእ ነው ፤ በማይመረመር በማይነገር ጌትነቱም በአብ እሪና ይኖር ነበረ ፤ የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው ሁሉ በላይ በታች ያሉ ፍጡራንም ሁሉ በመሃል እጁ ናቸው ፤ አሽናፊ ፈጣሪ እርሱ እንደ ከሃሊነቱ ሁሉን ያዝዛቸዋል፡፡ መለኮትና ትስብእት በተመለከተ እግዚአብሄር ወልድ በድንግል መሀፀን ሳለ በሰማይም በምድርም ከአባቱ ጋር አንድ ባህርይ መለኮት ህልው ነውና ከሃጢአት በቀር በመሀፀን ሆኖ ከተፈጠረ ከፍፁም ትስብእት ጋርም በማይመረመር ባንድ ባህርይ መለኮት መቸም መች አንድ ነውና፡፡ እግዚአብሄር አብን በመልክ የሚመስለው ፣ በባህርይ የሚስተካከለው እርሱ ቀምቶ እግዚአብሄር የሆነ አይደለም ራሱን አዋርዶ የተገዥን ባህርይን ገንዘብ አደረገ እንጂ ፤ መለኮትስ እንደሰው በድንግል መሀፀን ያለ የእለት ፅንስ በመሆን በድንግል ማህፀን ሳለ በሰማይ በምድር ምሉ ነው፡፡ ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥቂት በጥቂት ማደጉን ወንጌላውያን ፃፉልን ፦ በየጥቂቱ ያደገ ግን መለኮት አይደለም ፡ በሰማይም በምድርም የመላ ነውና ፤ በሁሉ በሰማይ በምድር የመላው እንዴት ያድጋል? ከተዋሃደው ስጋ ጋር አንድ አካል አንድ ባህርይ ነውና በየጥቂቱ ማደግን ገንዘብ አደረገ፡፡ ከሃጢአት ብቻ በቀር እንደ እኛ በስራው ሁሉ ተፈተነ ፣ ተራበ ፣ ተጠማ ፣ ደከመ ፣ አንቀላፋ ፣ በላ ፣ ጠጣ ፣ አለቀሰ ፣ ተከዘ ፣ አዘነ ፣ ታመመ ፣ ሞተ ፣ ተገነዘ ፣ በመቃብርም ተቀበረ ፤ ይህስ እንዴት ለመለኮት ይነገራል? ነገር ግን እግዚአብሄር ቃል በተዋሃደው ስጋ ስለእኛ ይህን ሁሉ ገንዘብ አደረገ፡፡ መለኮት ግን ከመከራ ሁሉ የራቀ ነው፡፡ (ወይንስ) በባህር ላይ ተራመደ ፣ ሙታንን አስነሳ ፣ ድውያንን ፈወሰ ፣ ከሞት ተነሳ ፣ በዝግ ቤት ገባ ፣ ወደ ሰማይ አረገ እንደምን ይባላል? ይህ የትስብእት ገንዘቧ አይደለምና ፣ ነገር ግን ሰውን ሰለመውደዱ የቃል ገንዘብ ለትስብእት ሆነ እንጂ ፤ እኛም ሰው አምላክ ሆነ ስለዚህ እንላለን፡፡ እንግዲህስ እግዚአብሄር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው ሞተ እንላለን እንጂ በባህርይው (በመለኮቱ) ከሞተስ እነሆ አብም ሞተ ደግሞ እንላለን ፣ እነሆ መንፈስ ቅዱስ ሞተ ደግሞ እንላለን ፤ ነገር ግን መለኮት ህማም ሞት ስለሌለበት እግዚአብሄር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው ሞተ እንላለን፡፡
አበው ባስረዱት ነበር ምን ያረጋል ታዲያ “አን ዱ“ በህይወታችን የለም እነጂ የቄርሎስ ትምህርቱ እንዲህ እንየው ታዲያ አልዛርን ከሞት ያስነሳው ማን ነው? ወይንስ እግዚአብሄር የሚለው ስም ከሶስቱ አካላት የማን ነው? እናንተ አልዛርን ከሞት ያስነሳው ኢየሱስ ነው እግዚአብሄር አይደለም የምትል እስኪ መልስልኝ ፦ ይህ ስም የአብ ብቻ ነውን? አባቶች እንዳስተማሩን ይህስ የሶስቱም የአንድነት ስማቸው ነው፡፡ እኛም እግዚአብሄር ስንል ፦ እግዚአብሄር አብ ፣ እግዚአብሄር ወልድ ፣እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ ማለታችን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እስኪ መልሱልኝ ፦ አልዛርን ከሞት ያስነሳው ኢየሱስ ብቻ ነው የምትሉ መለኮትን ትከፍሉት ዘንድስ ማን አስተማራችሁ? ወይንስ ለስላሴ ስንት መለኮት አለው? ስላሴ ግን በባህርይው አንድ መለኮት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ወይንስ ኢየሱስ ክርስቶስ አልዛርን ከሞት ያስነሳው በቃል ገንዘብ ነውን? ወይንስ በትስብእት ገንዘብ? ይህንስ የኢየሱስ ክርስቶስን ባህርይ ትከፍሉ እንደሆነ ጠየቅኳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሄር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋህዶ አንድ እንደሆነ እኛ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እናምናለን፡፡ እንግዲህ የቃል ገንዘብ ለትስብእት እንደሆነ በመለኮቱ ሰማይና ምድርን የመላ ፣ በስልጣኑ ሁሉን የፈጠረ እርሱ በመለኮቱ ስልጣን አልአዛርን ከሞት አስነሳው እንላለን ፤ የስላሴ መለኮትም አንድ ነውና ስላሴ ደግሞ አልአዛርን ከሞት አስነሳው እንላለን ፣ ይህም መለኮት የእግዚአብሄር አብ ነውና እግዚአብሄር አብ አልአዛርን ከሞት አስነሳው ደግሞ እንላለን፤ ለመንፈስ ቅዱስም ይህ ይነገር ዘንድ ይሆናል፡፡ መለኮት ከ ትስብእት ለአይን ጥቅሻ እንኳን እንዳልተለየው ፦ አንድ በሆነው መለኮት አብም መንፈስ ቅዱስም ወልድን በስራው ሁሉ አልተለዩትም ፤ እግዚአብሄር ወልድም ምንም ስጋን በመልበሱ በምድር ቢሆን በመለኮቱ ግን ከዙፋኑ አልተለየም፡፡እንዲህ ስንል ግን እግዚአብሄር አብ ሞተ እንላለንን? ወይንስ እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ ተሰቀለ እንላለን? እስኪ መልሱልኝ መለኮት ይሞታልን? ይሰቀላልን? አይሞትም አይሰቀልምም ፤ ስለዚህም እግዚአብሄር አብ ፣ እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ ፣ ወይንም ስላሴ ሞቱ አንልም፤ ነገር ግን እግዚአብሄር ወልድ በተዋሃደው ስጋ ስለእኛ ይህን ሁሉ ገንዘብ አደረገ ብለን እናምናለን ፡፡ እንግዲህስ ይህን አባቶች አስተማሩን ፤ እናንተ ግን አዲስን ትምህርት ከየት አመጣችሁት? እኛ ግን አልአዛርን ባስነሳው እግዚአብሄር እናምናለን፡፡ አበው ባስረዱት ነበር ምን ያረጋል ታዲያ “አን ዱ“ የለም እንጂ “አን ዱ“ ቢኖር እንደ በጋሻው ያለውን መምህር አበው አቃንተውት ልጁንም ፎርማት ባደረጉት ነበር፡፡
ያንን ወንድሞች በቅንነት እውነተኛ መስሎአቸው እናገለግልበታለን ብለው የገቡበትን ‹‹የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበርም እነ በጋሻውና የሬድ አደመ ባልፈጠሩት ነበር ‹‹የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር›› - ይህ ማኅበር በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ(እነ በጋሻው ደሳለኝ እና ያሬድ አደመ በዋናነት የሚሳተፉበት) ሲሆን የተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች፡- (1)የትምህርት አሰጣጡን ይዘት ከመሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይልቅ ግራና ቀኝ ወደማያስለይ እና መሠረታዊ ቁም ነገር ወደማያስጨብጥ ተራ ወግ እና ተረት መለወጥ ነው፤ የዚህ ተግባር ዓላማም ምእመኑ መሠረታዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያኑን አስተምህሮ እንዳያውቅና እንዲህ ከሆነም የሚጫንበትን ኑፋቄ ሳያቅማማ እና ሳይለይ እንዲቀበል ለማድረግ ነው፡፡ (2)የስብከተ ወንጌሉን አቅጣጫ ለቤተ ክርስቲያናችን ወካይ ዓርማ (Icon) የሚባሉትን ነገሮች የሚያጥላላ እና የሚያናንቅ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን አክብሮት እንዲቀንስ እና እንዲጥል ከዚያም በውስጡ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠላ ማድረግ ነው፡፡ (3)ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን ማጥፋት፤ ይህም ፕሮቴስታንታዊውን አስተምህሮ አሾልኮ በማስገባት ‹‹አንድ ነን፣ እዚህም እዚያም የሚሰበከው ጌታ ነው፤. . . ወዘተ›› በማለት ከውስጥ ሆኖ መለወጥ ነው፡፡ (4)የተለያዩ ማኅበራትን በሕዋስ(Cell) ደረጃ በየጉራንጉሩ መመሥረት እና ማቋቋም፤ እነዚህን ጥቃቅን ማኅበራት አህጉረ ስብከት ስለማያውቋቸው እና የሚቆጣጠሩበትም መንገድ ስለ ሌላቸው እነዚህ የሚያዘጋጇቸው ጉባኤያት፣ የሚጋብዟቸው ሰባክያን እና በዚያም የሚሰጠው ትምህርት ለዓላማቸው የተመቸ ይሆናል፤ እየሆነም ነው፡፡ (5) በስብከቶቻቸው እና በጽሑፎቻቸው የፕሮቴስታንቶችን ምንጮች መጠቀም፣ ለዚህም በቅርብ ጊዜ ያሳተሙት መጥሐፍ ሐሳቡ ብቻ ሳይሆን ርእሱ ሳይቀር የፕሮቴስታንት ፓስተር ከጻፈው መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ ታዲያ “አን ዱ “ በህየወታችን ቢኖር ኖሮ ሰለስቱ ምዕት አቕጣጫውን በእነሱ መስመር ባቃኑት ነበር ትምህርት ጤፉ በጋሻው ይህን ወደ መሰለው የ”እኔ ከሞትሁ ሠርዶ አይብቀል” ግዙፍ ድምዳሜ ለመድረስ በንጽጽሩ ምን ያህል ቦታዎችን በመነሻነት እንደወሰደ አይታወቅም፡፡ የሚታወቅ ነገር ቢኖር መምህረ ሃይማኖት ባሕታዊ ኀይለ ጊዮርጊስ የተባሉ ሰባኬ ወንጌል እንደተናገሩት፣ በጋሻው እና “የሞንታርቦ ወንድሞቹ” ትውልዱ ማንነቱን ለይቶ በማያውቅበት የምሽት ጉባኤዎች ድብልቅልቅ በማደንዘዝ ሀብቱን እየበዘበዙ፣ እናት ቤተ ክርስቲያኑን በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አዳክሞ ለመውረስ አልያም ከፍሎ ለመረከብ ላሰፈሰፉ ኀይሎች በሎሌነት እያገለገሉ መሆናቸው ነው፡፡ ታዲያ ይባስ ብለው ሰዎች በአውደ ምህረትህ ላይ ለፀሎት ተሰብስበው በ "እግዚኦ መሃርነ ክርስቶስ" አንተን በሚማፀኑበት ወቅትም፥ ፍፁም በሚያውክና በእልህ በተሞላ ድምፅ መዝሙር ለመባል ስርዓት በጎደለው ጩኧት ቤትህን አመሱት። አማኙንም ከአምልኮ ስርዓቱ ለማስተጓጎልና ቤትህ በመታደስና በመፅዳት ላይ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ለማኖር አፀድህን በሚቃጠል ቆሻሻ ጢስ አጠኑት። “አን ዱ “ ቢኖር ኖሮ! በሰጠሀቸው ፀጋ በፊትህ ተመፃደቁ፤ ትምክህታቸውም ፈር ለቀቀና በሀሰት ትምህርታቸው ህዝብህን አደናገሩት። በመንደር ወሬና ስድብ አስመርረውም አስለቀሱት። በገዛ ደምህ የዋጀሀትን ቤተ ክርስቲያን ‘አርጅታለች’ አሉና ለእድሳቱ ሚስማርና መዶሻ ለመዋዋስ ከመናፍቃን ጋር መከሩ። አረጀች ያሏትን ቤተክርስቲያንም በሣራ መሰሏት፤ እነሱም በስተርጅና የተወለዱ የሣራ ልጆች መሆናቸውን አበሰሩን። “አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፥ በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል።” (መጽሐፈ ምሳሌ 20:20) የሚለውን የወንጌል ቃል ስተውት ይሁን ንቀውት፥ በ40 እና በ80 ቀን የእግዚአብሄር ልጅነትን ያገኙና ቤተክርስቲያንን ያውቁ ዘንድ እንኳን ያልከለከሉዋቸውንና፥ ሀገርንና ሀይማኖትን ከጠላት ጠብቀው ያቆዩላቸውን አባቶች "የእንጨት ሽበቶች፣ ፍንዳታዎች" ብለው ለቀለለ ስድብ አፋቸውን ከፈቱ መንፈስ እንዳዘዘን እናስተምራለን” ከሚል “የዘመኑ ሐዋርያ ነኝ” ባይ ምእመኑ ምን ይማራል? “ንጉሣችን ቅልጥ አድርጎ ይዘምራል፤ አባባ ሲተኛ እኛ እንነቃለን፣ እኛ ስንተኛ እርሱ ይሠራል፤ ሥላሴ ሲያጫውቱ ያሥቃሉ፣ እሺ፤ በጣም ነው የሚያጫውቱት፤ ተባበሩኝ ብለው የሚያሥቁ ኮሜዲያን አሉ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደዛ አይደሉም፤ ለማርያም ከበሮ አይመታም ለጌታ እንጂ፤ ከጸበሉ ይልቅ የሚያጽናናቸው ቃሉ ብቻ ነው፤ በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስ እና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ…ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ፤ እኛ ሕዝቡን ጨፍረን እናምጣው፣ እናንተ መዝሙር አስተምሩት፤ እኛ ሕዝቡን ደንሰን እናምጣው፤ እናንተ ሥርዐት አስተምሩት፤ እኛ ሕዝቡን ጨፍረን እናምጣው እናንተ ሃይማኖት አስተምሩት፤ ይሄ ሕዝብ እኛ ሳንወድቅ ወድቋል፤ እኛ የምናምነው በፈውስ፣ በዝማሬ በጸጋ ነው፤ ‹በተሰጠኝ ጸጋ ሰይጣን ፎቶዬን ሲያይ መጮህ ጀምሯል› [ጋሞጎፋ ሳውላ ኪዳነ ምሕረት]” የሚል ሰባኪ ነኝ ባይ ዋልጌ የግል ተክለ ሰብእናውን ከመገንባት ውጭ እንደምን ምእመኑን በሃይማኖቱ ለማጽናት ይቻለዋል? ታዲያ ምን ያረጋል በዚህ ሁሉ ነገር “አን ዱ” ቢኖር ኖሮ አበውም በመጡ ታሀድሶም በጠፋ ነበር አምላክ ሆይ በጎችህ በተኩላዎች እንዳይነጠቁብህም የተኩላዎቹን አፍ ዝጋ፤ የበጎችህንም ንቃት አብዛ። የአሳቾቹም የጨለማ ጉዞ “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው።” (ወደ ሮሜ ሰዎች 1:28) እንደሚለው ያንተው ፈቃድ ከሆነም፤ እባክህ ስለቅዱሳን ብለህ የዚህችን ቤተክርስቲያን ጥፋት አታሳየን ልቦናቸውንም አብርተህ ዳግም አንተን ያውቁ ዘንድ ይሁን።