ደቂቀ ናቡቴ

Friday, July 29, 2011

ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤተ ክህነቱ ሰው


ሦስቱ ጠባየ ጳጳሳት

ቤተ ክህነቱ በየዘመናቱ ሦስት ዓይነት ጠባየ ጳጳሳትን አስተናግዷል፡፡ የመጀመሪያው እና የአብዛኛዎቹ የሆነው አድርባይነት ነው፡፡ የዚህ ምንጩ ደግሞ በዓላማ ለዓላማ የመላእክትን አስኬማ አለመድፋት ነው፡፡ የመላእክት አስኬማ /ምንኩስና/ ንጽሕናን ይጠይቃል፣ ብዙዎቹ ንጽሕናቸውን አጉድፈዋል፡፡ የመላእከት አስኬማ የዚህን ዓለም ጣዕም ይንቃል፤ ብዙዎቹ ዓለማዊነትን ኑሮ አድርገውታል፡፡ የመላእክት አስኬማ የራሴ የሚለው ዘውግ እና ንብረት የለውም፡፡ ብዙዎቹ ግን የዘውግ ብል የበላቸው፤ የዚህ ዓለም ሀብትና ንብረት ያማለላቸው ናቸው፡፡ ይኽ ደግሞ ጥብዓት የጎደላቸው፤ ትጋሀ ሌሊት የማያውቃቸው፣ የመንኖ ጥሪት መዓዛ የማይሸታቸው አድርባዮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በምስጢር የፈጸምናቸው ስህተቶች ከአሁን አሁን ተደረሶባቸው እንጋለጥ ይሆን በሚል የሚደነብሩ እና የማፍያው ቡድንም ይኽን የጎደፈ ገመናቸውን ለምእመኑ እገልጣለሁ እያለ የሚያስፈራራቸው እና ከፍርሃታቸውም የተነሣ ለዚህ ቡድን ፈቃድ እንዲያድሩ አድርጓቸዋል፡፡

ሁለተኛው እና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ጳጳሳት ጠባይ ደግሞ ቸልተኝነት ነው፡፡ የእነዚዎቹ ቸልተኝነት ከጠባቂነታቸው እና ከስንፍናቸው የሚመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን የመላእክት አስኬማ መለያ የሆነው ቅድስና፣ ዘውግ አለመለየት፣ የዓለምን ፈቃድ ማሸነፍን ገንዘብ ቢያደርጉም የጠባቂነት እና የስንፍና ቅንቅን ወሯቸዋል፡፡ ለቤተክርስቲያን የሚሆነውን ሠርተው ከማለፍ ይልቅ ሌሎች እንዲሠሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ መስዋዕት ከሚከፍሉ በሌሎች መስዋዕትነት የቤተክርስቲያንን ዕድገት ማየት ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ የጎደለውን ከሚያሟሉ፤ የጠመመውን ከሚያቀኑ ሌሎች በሚያሟሉት እና በሚያቀኑት ፍኖት መጓዝን ይመርጣሉ፡፡ እነርሱ ተናግረው ከሚያሳምኑ ይልቅ ሌሎች ተናግረው እንዲያሳምኑላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ ታሪክ ሠርተው ከማለፍ ይልቅ የተሠሩ ታሪኮችን እያመነዠጉ የታሪክ ግብ ይቅርና ምዕራፍ ሳይኖራቸው ያለፉ፤ የሚያልፉ ሰነፎች ናቸው፡፡ እነርሱ የተጣለባቸውን ሓላፊነት በቆራጥነት ከመወጣት ይልቅ ቅዱስ ፓትርያርኩ «ከተስማሙበት ምን አገባን» የሚሉ፤ ቤተክርስቲያን በሰላም ማጣት፣ በመናፍቃን ሴራ፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ስትታመስ እየተመለከቱ እነዚህ ሁሉ ችግሮች በአንድ ጀንበር በፓትርያርኩ ሞት የሚፈታ ይመስል ሞት ናፋቂዎች ሆነዋል፡፡ ይኽ መሆኑ ደግሞ ቤተክህነቱን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላተኞች እንድትወረር፣ ቅሰጣ እንዲደረግባት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሦስተኛው ጠባየ ጳጳሳት እና በቤተክህነቱ በጥቂቱም ቢሆን ትላንት የነበረ፤ ዛሬ ግን ያጣው ጴጥሮሳዊነት ነው፡፡ ጴጥሮሳዊነት ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ላይ የቆመ ነው፡፡ ይኽ ደግሞ ስለ እውነት በእውነት መሞት ልዩ ግብሩ ነው፡፡ ጴጥሮሳዊነት ከላይ እንደተመለከትነው ሁለቱ ጠባየ ጳጳሳት ሳይሆን በእግዚአብሔር አምኖ የራስንም ሓላፊነት እየተወጡ ውጤቱን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ መቀበል ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም «ኢትዮጵያ ከየት ወዴት)» በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ጴጥሮሳዊነት እንዲህ ብለዋል፡፡

«. . .ጴጥሮሳዊነት በመሠረቱ መንፈሳዊነት በመሆኑ የሚመካበትም ኀይል መንፈሳዊ እንጂ አካላዊ ወይም ጠመንጃ አይደለም፡፡ የጴጥሮሳዊነት ዓላማ አስፈላጊ ከሆነ ለእምነቱ፣ ለሀገሩና ለወገኑ ለመሞት እንጂ ለመግደል አይደለም፡፡. . . ለመሞት መዘጋጀትና ለእውነትና ለእምነት መሞት ግን ወኔን ይጠይቃል፡፡ መንፈሳዊ [ጴጥሮሳዊ]ወኔ፡፡» /ገጽ.44/

ሦስቱ የጴጥሮሳዊነት ምንጭ

ጴጥሮሳዊነት በመንፈሳዊነት ላይ የቆመ የመላእክት አስኬማ ነጸብራቅ እንደመሆኑ ከሦስት ነገሮች ይመነጫል፡፡

1 አደራን ለመጠበቅ ዝግጁ ከመሆን

አደራ ክቡር፣ ውድ፣ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደ ሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤ አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡

ለሀገራቸውና ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡ «ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡» /መርሻ አለኸኝ /ዲያቆን/፣ 1986 ዓ.ም፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ ገጽ.80/

ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ እኔም የጴጥሮሳዊነት አንዱ ምንጩ አደራን ለመጠበቅ ዝግጁ ከመሆን ይመነጫል የምለው ለዚህ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡

የጴጥሮስን ሥልጣን የያዙ፣ አስኬማውን የደፉ፣ ካባውን የደረቡ፣ መስቀሉን ከእነ በትረ ሙሴው የጨበጡት «ዘመነኞቹ» ጳጳሳት ከቤተክርስቲያን የተቀበሉትን የእረኝነት የአደራ ቃል በመተው ለቤተክርስቲያን ከሚታገሉላት ይልቅ የሚታገሏት ሆነዋል፡፡ ጵጵስናውን ሲቀበሉ የገቡትን ቃለ አደራ በመዘንጋት በጴጥሮሳዊነት ለአገርና ለወገን ሊቆሙ ይቅርና ክብርን ለአጎናጸፈቻቸው እናት ቤተክርስቲያን የማይሆኑ እርባና ቢስ ሆነዋል፡፡ ፍርሃት ድሩን ሠርቶባቸው ትምእርተ ምንኩስናቸውን ሸፍኖታል፡፡ ሹመታቸው የዖዝያን ሹመት እስኪመስል ድረስ የጽድቅ ፈሪዎች፤ የኃጢአት ደፋሮች አስመስሏቸዋል፡፡

2. አባታዊ ሓላፊነትን ከመወጣት

የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን በቆራጥነት ለመወጣት ካደረጉት ተጋድሎ ይመነጫል፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው «ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ)» ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው በሰማዕትነት አለፉ፡፡ / መርሻ አለኸኝ/ዲያቆን/፣ 1996ዓ.ም፣ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ገጽ.77/

ዛሬ ቤተክርስቲያንም ሆነች ቤተክህነቱ ያጣው ጴጥሮሳዊነት ይኽ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ይኽን የጽድቅ ፍኖት ይዘው መጓዝ ሲሳናቸው አይተናል፡፡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ የድህነት ቀንበር ለተጫነው፣ በችጋር አለንጋ ለተገረፈው፣ በሀዘን ለተቆራመደውና ለጎበጠው ሕዝባችን ሊቆረቆሩ ይቅርና አባታዊ ሓላፊነት ለሰጠቻቸው እናት ቤተክርስቲያን ጠበቃ መሆን ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ሁሉም በሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ዘመን እንደነበሩት ግብዊ ጳጳስ ሆነውባታል፡፡ በእርግጥም እውነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የአሜሪካ እና የካናዳ ዜግነት ኖሯቸው በአሜሪካ እና በካናዳ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የግላቸው ቤተክርስቲያን የከፈቱ ባዕዳን ናቸው፡፡ እዚው ያሉት በየስድስት ወሩ ከዲያስፖራው ምእመን በተወካዮቻቸው አማካይነት የተሰበሰበውን ገንዘብ ለመተሳሳብ እና የድርሻቸውን ለመውሰድ ወደ አሜሪካ ያመራሉ፡፡ በገንዘቡም ከአንድ አባት የማይጠበቅ ኢ-ሥነምግባራዊና ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ እንዴት ጴጥሮሳዊ ወኔ ይኖራቸው)

ሌሎቹም የቤተክርስቲያን አባት መሆናቸው እስኪጠፋን ድረስ ሀገረ ስብከታቸውን ትተው አዲስ አበባ በዘመናዊ ቪላ የሚሽሞኖሙኑ፤ እነርሱ በሀገረ ስብከታቸው ተቀምጠው የሚሆነውን ከመሥራት ይልቅ፤ ባለጉዳዮችን በየመኖሪያ ቤታቸው የሚያንከራትቱ፤ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝባዊ አለኝትነታቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ፤ ዘመናዊ ቤት የሠሩበትን፣ ዘመናዊ መኪና የገዙበትን፣ በየሳምንቱ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ማር፣ በግ የሚያማርጡበትን ገንዘብ የሰጣቸውን ምእመን «ቤተክርስቲያን ተሳልመህ ከመመለስ ውጭ ምንም አያገባህም» ብለው የሚመጻደቁ ፊውዳሎች ናቸው፡፡ /ነጋድራስ ጋዜጣ፣ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም፣ቅጽ.07፣ቁጥር 240፣ገጽ.2/

አንዳንዶቹም ከቤተክርስቲያን ልዕልና እና መታፈር ይልቅ ራሳቸውን በአገረ ስብከቶቻቸው ልዑላን በማድረግ የሾሙ፤ የአክሊለ ሦክ ምሳሌ የሆነውን ቆብ ማድረጋቸውን ዘንግተው ዘውድ የደፉ ይመስል በዙርያቸው «እራት አግባዎችን» አደራጅተው ለቤተክርስቲያን የማኅፀን እሾኽ የሆኑ፤ የትኛውም አካል እነርሱን እስካልነካ ድረስ ቤተክርስቲያን ላይ «ቤንዚል አርከፍክፎ፣ ክብሪት ጭሮ እሳት ቢለቅ» አባታዊ መዓዛ የማይታይባቸው፤ ጴጥሮሳዊነት እጅጉን የራቃቸው ሥጋውያን ናቸው፡፡ እናም አንዱ ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤ ተክህነት ጴጥሮስ እና ጴጥሮሳዊነት ይኽን ነው፡፡

3. ከመንኖ ጥሪት
መንኖ ጥሪት በዚህ ዓለም ያለን ማንኛውም ሀብትና ንብረት ንቆ መተው ነው፡፡ «ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም» እንዲል ሉቃ.14.33፡፡ እንግዲህ የዚህን ዓለም ጣዕም ማጣጣም ያልተወ መንፈሳዊ አባት የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሊሆን ይቅርና ጥሩ ክርስቲያንም አይሆንም፡፡ እርሱ ምውት ሕሊና ነውና፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት ጥብዓት ምንጩ ይኸው መንኖ ጥሪት ነው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን የእርሱ አቋም የራሳቸው አቋም፤ የእርሱ የጭቆና አገዛዝ የእርሳቸው አገዛዝ፣ የእርሱ ተራ ፕሮፓጋንዳ የእርሳቸው እውነት አድርገው እንዲቀበሉ መደለያ /ገንዘብ፣ መኪና በዘመኑ ዘመናዊ የሚባል ቤት/ ልስጦት ሳይላቸው ቀርቶ ነውን) ለሕዝባቸው፣ ለሀገራቸውና ለቤተክርስቲያናቸው ሰማዕት የሆኑት) እርሳቸው ግን መንኖ ጥሪትን ገንዘብ ያደረጉ አባት በመሆናቸው ሌሎቹ የቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ለፋሺስት ጣሊያን ሲያድሩ መደለያው ሳያንበረክካቸው በመንፈሳዊ ወኔ ሰማዕት ሆነዋል፡፡

የዛሬዎቹ አንዳንድ ጳጳሳት የመንኖ ጥሪትን ሕይወቱን ይቅርና ቃሉን ማወቃቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ዛሬ፣ ዛሬ አንዳንዶቹ ለመኪና ስጦታ፣ ለገንዘብ መደለያ፣ ለውዳሴ ከንቱ ብለው እናት ቤተ ክርስተያንን ዋጋ እያስከፈሏት ይገኛሉ፡፡ ዶግማዋን በላንድ ክሩዘር፣ ቀኖናዋን በG+1,2,3,4 . . . . ቤቶች ለውጠዋል፡፡ ሥርዐተ አበውን አመድ ላይ የወደቀ ሥጋ አድርገዋል፡፡ ወርቅና ብር ለመዘነላቸው አጽራረ ቤተክርስቲያን ሁሉ የሚያድሩ እንዲሁም ጥብቅና የሚቆሙ፣ ጥሩ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

አንዳንዶቹም የጴጥሮሳዊነት ምንጭ የሆነው መንኖ ጥሪት እጅግ ስለራቃቸው በየገዳማቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ የገዳማቱን እና የየአድባራቱን መሠረታዊ ችግር ከሚፈታ ይልቅ እነርሱ ኪስ ሲገባ የሚያስደስታቸው፤ በየሀገረ ስብከቶቻቸው ያሉ ሊቃውንት በችጋር ሲሰደዱ፣ ወንበር ሲያጥፉ እነርሱ ግን መደለያ ያቀረቡላቸውን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ሲከባከቡ፣ ሽርጉድ ሲያበዙላቸው ይታያል፡፡ ከቤተክርስቲያኗ የአስተዳደር ሕግ እና ሥርዐት ውጭ በየሀገረ ስብከቶቻቸው የእኅት እና የአክስት ልጆቻቸውን የሚቆጥሩ፡፡ እነርሱም በአቅማቸው ቤተሰባዊ አስተዳደርን ያሳፈኑ ናቸው፡፡ ለምን) «ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ» ነውና፡፡ ከዚህ እውነታ ተነሥተን እነርሱ በፓትርያሪኩ ላይ ያነሡትን የቤተሰብ አስተዳደራዊ በደልን ስንፈትሽ ሞራላዊ ብቃት እንደሌላቸው ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ እነርሱም ቤተሰባዊ አስተዳደር ደዌ የተጣባቸው ናቸው፡፡

ለዚህም ነው፡- እኛ እያለን አጽራረ ቤተክርስቲያን አይነኩም ባዮች የሆኑት፡፡ እነርሱ ለቤተክርስቲያን መከራ ከሚቀበሉ ቤተክርስቲያን መከራ መቀበሏን የፈቀዱት፡፡ እነርሱ ሞት ከሚቀምሱ ሥርዓቷን፣ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን ለሞት የዳረጉት፡፡ በአንድ ጀንበር የበር መሰበር ብትንትናቸው ወጥቶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍያው ቡድን ያስረከቡት፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ እና ሰማያዊ ሥልጣን መከበር ይልቅ የአባ እገሌ መሻር እና የአባ እገሌ መሾም ጉዳይ ሆኖባቸው በፍቅረ ሢመት /በሥልጣን ጥም/ አብደው በቤተክህነቱም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማየት የሚገባንን የአስተዳደር ለውጥ እንዳናይ ግርዶሽ ሆኑብን፡፡

እንግዲህ ቤተክህነቱም ያጣው የቤተክህነቱ ሰው ጴጥሮስ እና የእርሱ ተክለ ሰብእና ነው፡፡ የእያንዳንዳችንም ውሳኔ የሚጠይቀው ይኽንን ለመመለስ ዝግጁ መሆን ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ሆነች ቤተክህነቱ ከገቡበት ማጥ ልናወጣቸው የምንችለው በጴጥሮሳዊነት ነው፡፡ አምላከ ጴጥሮስ ባዶዋን ለቀረችው ቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም የሰው ያለህ ለሚለው ቤተክህነት ያጣውን ሰው እስኪመልስለት እርሱ እንደፈቀደው ይሁን ከማለት ባሻግር ሁሉም ስለሁሉም በሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡

No comments:

Post a Comment