ደቂቀ ናቡቴ

Friday, November 4, 2011

የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ 12ኛ ቀን ስብሰባ ዋና ዋና ዜናዎች



 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 24/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 4/2011)፦
  • አቡነ ፋኑኤል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በሽምግልና በመጠቀም በዋሽንግተን ዲሲ እና በካሊፎርኒያ የሚጠብቃቸውን መሬት አንቀጥቅጥ ተቃውሞ ለማብረድ እና የአሜሪካ ሹመታቸውን ለማደላደል እየተጣጣሩ ነው፤
  • ቅ/ሲኖዶስ በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች ላይ የቀረበው የዳሰሳ ምልከታ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚመራ የባለሞያዎች ኮሚቴ እንዲገመገም ወሰነ፤
v  በኤፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የፌዴራል መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀት እና ለማጠናከር የተዘጋጀውን ዐዋጅ ረቂቅ መርምሮ በማስተካከል በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሕግ ዕውቅና እንዲያገኝ ይላክ ዘንድ መርቷል፤ መንፈሳዊ ፍ/ቤቶቹ የመንግሥትን የፍትሕ አካላት ላጨናነቁት የቤተ ክህነት ጉዳዮች እፎይታ እንደሚሰጡ ተስፋ ተደርጓል፤
v  የጋብቻ፣ ፍቺ፣ ቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ሞግዚትነትና በቤተሰብ ተዛምዶ ላይ የሚነሡ ጥያቄዎች፣ የውርስ፣ የኑዛዜና የስጦታ ጉዳዮች፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ በሚቀርቡ ክሶች ኪሳራ መወሰን የፍ/ቤቶቹ የወል ዳኝነት ሥልጣን ክልል የሚሸፈኑ ናቸው፡፡
v  በፍ/ቤቶች ጉዳያቸው የሚታየው በቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ሥርዐት በፍ/ቤቶቹ ለመዳኘት ተስማምተው በፈቃዳቸው የቀረቡ አገልጋዮች እና ምእመናን ናቸው፡፡
v  ፍ/ቤቶቹ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የሚቋቋሙ ሲሆን መሪዎቹ ‹‹ርእሰ ፍትሕ›› የሚል ማዕርግ ይሰጣቸዋል፤
  • ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በአጀንዳ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ተጠምደዋል - አቡነ ሳሙኤልን ስለ ወነጀሉበት ክስ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ስለ ማሻሻል እና ስለ ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ ቀደም ሲል በምልአተ ጉባኤው ውድቅ የተደረጉባቸውን ጉዳዮች በተለያየ ቀለም መልሰው ቢያነሡም ዳግመኛ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፤
  • አባ ሰረቀ ‹‹ከሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሐላፊነታቸው እንዲነሡ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፈውን ውሳኔ ለመቃወም›› በሚል የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሠልጣኞች በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት መካከል የተቃውሞ ፊርማ እያሰባሰቡ ነው፤ የደቀ መዛሙርቱን የጋራ ጥያቄዎች ለሽፋንነት ይጠቀማሉ የተባሉት ተቃዋሚዎቹ በአባ ሰረቀ ላይ በተላለፈው ውሳኔ ሁነኛ ሚና ተጫውተዋል ባሏቸው ማረፊያ ቤታቸው በቅጽሩ በሚገኘው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ሌሎች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይም እንዳነጣጠሩ ተጠቁሟል፤ እንቅስቃሴውን አባ ሱራፌል የተባሉት የፓትርያርኩ ዘመድ እና ከአራት ያላነሱ “የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጭፍሮች ናቸው” የሚባሉ (ዲ.ን አብርሃም ይገዙ - ከነገሌ ቦረና፣ ዲ.ን በረከት ታደሰ - ከአሰበ ተፈሪ፣ ዲ.ን መስፍን ታዬ - ከሐዋሳ፣ ዲ.ን አሳምነው ዐብዩ - ከአምቦ የመጡ እና በልደታ አካባቢ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መደበኛ ሥልጠና የወሰዱ) እና ዲ.ን መንግሥቱ - ከባሕር ዳር የተመደበ ያስተባብሩታል፤ ፓትርያርኩ አጋጣሚውን በመጠቀም የአባ ሰረቀን ጉዳይ መልሰው ሊያነሡ እንደሚችሉ ተገምቷል፤
  • በ17ኛ ተራ ቁጥር በተመለከተው ልዩ ልዩ አጀንዳ ሥር ፓትርያርኩ ለውይይት ያቀረቡትና “ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ ከሐዋሳ መጥተዋል በተባሉ ሰዎች ቀርቧል የተባለውን ክስ” ቅ/ሲኖዶሱ ውድቅ አድርጎታል፣      
  • በተመሳሳይ “በልዩ ልዩ” ሥር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ አክሱም ጽዮን ማርያም፣ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም እና ቅዱስ ላሊበላ ደብር በጳጳሳት እንዲመሩ ያቀረቡት ሐሳብ በምልአተ ጉባኤው አባላት ተቀባይነት አላገኘም፤ በዚሁ አጀንዳ ሥር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ደርበው የሚመሩት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀውስጦስ የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሏል፤
  • ከወትሮው በተለየ ለተከታታይ 13ኛ ቀን ቀጥሎ የሚገኘው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቃለ ጉባኤዎቹንና የስብሰባውን መግለጫ ረቂቅ  በመናበብ ይፈራረማል፤ የምልአተ ጉባኤው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው።

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

No comments:

Post a Comment