ደቂቀ ናቡቴ

Friday, December 16, 2011

ስለ ታቦተ ጽዮን የማናውቀው


የአኩስም ጽዮን ያለቺበት እና እቴጌ መነን ያሠሩት መቅደስ


 ሰሞኑን የአኩስም ጽዮን ያለቺበት እና እቴጌ መነን ያሠሩት መቅደስ እያፈሰሰ ነው የሚል ዘገባ በመውጣቱ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ታቦተ ጽዮንን ለማየት ዕድል ይፈጥራል እያሉ ማውራት ጀምረዋል፡፡

እስቲ መረጃ የኢሳትን ያድምጡ

 
ይህ ሁሉ የተዛባ ዘገባ የአኩስም ጽዮንን እና የአኩስም ሕዝብን ጠባይ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በዘመናዊ ታሪካችን የአኩስም ጽዮን ከነበረችበት መቅደስ ስትንቀሳቀስ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡ በዐፄ ፋሲል ዘመን ከተሠራው ማረፊያዋ እቴጌ መነን ወዳሠሩት ማረፊያ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ተንቀሳቅሳለች፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች እንዳሉት ያን ጊዜ ለመታየት አልቻለችም፡፡
የአኩስም ጽዮን አቀማመጥ፣ አጠባበቅ እና አነዋወር እጅግ ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ምሥጢራዊ ሕግ እና ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ለአንድ ጉዳይ ወደ አኩስም ጽዮን በሄድኩ ጊዜ እዚያ ካሉት ሽማግሌዎች ጋር በአፈ ንቡረ ዕዱ በኩል የመነጋገር ዕድል ነበረኝ፡፡ እኔ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ልዩ ስሜት የተሰማኝ፣ እግዚአብሔርንም ያመሰገንኩት ያኔ ነው፡፡
አፈ ንቡረ ዕደ እንደነገሩኝ የታተ ጽዮንን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ ጉባኤ አለ፡፡ የዚህ ጉባ አባላት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ ሥርዓት የሚመጠሩ ናቸው፡፡ ሃይማተኞች፣ በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ምሥጢር ጠባቂዎች፣ ቤተሰቦቻቸው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሰጡ፣ በምንም ነገር የማይታለሉ እና በእድሜ የጠኑ አረጋውያን ያሉበት ነው ጉባኤው፡፡
ይህ ጉባኤ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ይወያያል፣ ይወስናል፡፡ ለምሳሌ 1982 ዓም በኢሕአዴግ እና በደርግ መካከል በነበረው ውጊያ ጊዜ ማንም ሳያይ እና ሳይሰማ ታቦተ ጽዮንን እጅግ ጥብቅ ወደሆነ ቦታ ወስዶ ያስቀመጣት፤ በኋላም አገር ሲረጋጋ ወደ መንበርዋ የመለሳት ይህ ጉባኤ ነው፡፡
አፈ ንቡረ ዕድ እንደሚሉት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜም ቢሆን ጣልያን ታቦቷን ሊተናኮል ይችላል ብለው በማሰብ (አንዳንደች እንደሚሉት እንዳ አባ ገሪማ ወደሚባል አካባቢ) ወስደው ከጠባቂዋ ጋር በአንድ ዋሻ በማስቀመጥ እዚያ ሀገር ሰላም ሲሆን እንድትመለስ አድርገዋል፡፡ ይህ ሲወሰን እና ሲተገበር ግን ከዚህ ጉባኤ አባላት ውጭ ማንም አያውቅም፡፡ ጣልያንም አልደረሰበትም፡፡
በዐፄ ፋሲል ዘመን ተሠራው ማረፊያዋ
ታቦቷን የሚጠብቁት አና የሚያጥኑት ሰው ሲደክሙ ወይንም ሲያርፉ ተተኪውን ፈልጎ፣ መዝኖ እና ፈትኖ በቦታው የሚተካው ይህ ጉባኤ ነው፡፡ ያንን ተተኪ ለማምጣት በድብቅ በጉባኤው አባላት ዘንድ ሱባኤ ይያዛል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይደርሳል፡፡ በመጨረሻም ለአንዳቸው በራእይ ተገቢው ሰው ይገለጣል፡፡ ከዚያም በቦታው እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡
ለመሆኑ የቅርቡ ይቅርና በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ ታቦቷ የት ነበረች? ብዬ ሽማግሌዎቹን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በግራኝ ወረራ ጊዜ በወቅቱ የነበረው ጉባኤ በወሰነው መሠረት ታቦቷን ይዘው ወደ ኤርትራ ምዕራባዊ ክልል ነበር የሄዱት፡፡ በዚያ ቦታ አሥራ ሰባት ዓመት ቆይታለች፡፡ ወደ ቦታው ሲኬድ ከፊሉ የጉባኤው አባላትም አብረው ሄደው ነበር፡፡
አሥራ ሰባት ዓመት እዚያ ስትቆይ ታቦቷን ያገለግሏት የነበሩት አባት ዐረፉ፡፡ ጉባኤውም ሌላ ሰው ተካ፡፡ ሀገር ተረጋግቶ ሰላም ሲሆን ታቦቷ ትመለስ ዘንድ ጉባኤው ወሰነ፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ልትንቀሳቀስ አልቻለችም፡፡ በኋላም ሱባኤ ተያዘ፡፡ በመጨረሻም ለአንድ አባት «ታቦቷን ያገለገሉትን አባት ዐጽም እንዴት ትታችሁ ትሄዳላችሁ?» ስትል እመቤታ ተናገረቻቸው፡፡ እነርሱም ዐጽማቸውን አፍልሰው በሳጥን ሲያደርጉት ታቦቷ ተነሣችላቸው፡፡ እርሳቸውንም አምጥተው በቀድሞው ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር አጠገብ ቀበሯቸው፡፡ ብለውኛል፡፡
ታቦተ ጽዮን በሁለት መልኩ ነው የምትጠበቀው፡፡ አንደኛው በማይመረመር ጥበቡ እግዚአብሔር ባዘዘላት ጠባቂዎች ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደነገሩኝ ለአንዳንዶቹ ብቻ የሚታዩ ሰማያውያን መላእክት ጠባቂዎች አሏት፡፡ በሥውር ከገዳማት ታዝዘው መጥተው የሚያጥኗት እና የሚጠብቋት ቅዱሳንም አሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በልዩ ልዩ መንገድ ይጠብቃል፡፡ አንዳንዱ ነዳይ መስሎ፣ ሌላው ተሸካሚ መስሎ፣ ሌላው የቡና ቤት አስተናጋጅ መስሎ፣ ሌላው ካህን መስሎ፣ ሌላው ተሳላሚ መስሎ፣ ሌላውም ጠላ ሻጭ መስሎ ይጠብቃል፡፡ እነዚሀን ሰዎች ከሽማግሌዎቹ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በዚያ አካባቢ የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእነዚህ ጠባቂዎች ዓይን ሥር ነው፡፡ ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ እና ከሚያስጎበኙ መካከል መረጃ የሚሰበስቡ እና ጥበቃ የሚያደርጉ አያሌ ናቸው፡፡
የአኩስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሌሊት እና ቀን ስብሐተ እግዚአብሔር የማይቋረጥባት ናት፡፡ እንደ አንዳንዶቹ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የማይኖርበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህም የተነሣ አካባቢው በካህናቱ እና አገልጋዮቹ እይታ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ይኼ በግቢው ውስጥ እና ዙርያ ጥግ ይዞ ሸለብ ያደረገው ምስኪን እንዲሁ ምስኪን እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳታዩት ጋቢውን ገለጥ እያደረገ አካሄዳችሁን ያያል፡፡ ምናልባት ቸግር የምትፈጥሩ ከመሰለውም በምሥጢራዊ የድምጽ ምልክት ጥሪ ያቀርባል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በምዕራባውያን ዓይን ብቻ እያየን እንዳንሳሳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያን ስለ ታቦት ያላቸው አመለካከት ከእኛ ጋር በእጅጉ ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ከዛሬው የባሱ አስቸጋሪ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ መረጃ እንደልብ በሌለበት ዘመን ኖራለች፡፡ በአንድ አካባቢ የሚደረገውን ነገር በሌላው አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ለመረዳት በማይችሉበት ዘመን ኖራለች፡፡ በእነዚህ ዘመን ያልጠፋች ታቦተ ጽዮን በዚህ ዘመን የትም አትሄድም፡፡ እግዚአብሔር ፈጽሞ ተጣልቶን ካልሆነ በቀር፡፡
እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእነዚህ ጠባቂዎች ዓይን ሥር ነው
 ኢሕአዴግ ታቦተ ጽዮንን ከሀገር ያወጣል ብዬ ፈጽሞ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ዘመን ይልቅ ትግራይን ነጻ ባወጣበት እና በአካባቢው የሚደረጉት ነገሮች ሁሉ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርብ ባልሆ ኑበት 1982 ዓም ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ ሰውን በሚያደርገው ነገር መውቀስ እንዲታረም ያደርገዋል፡፡ ባላደረገው ነገር መውቀስ ግን እንዲያደርገው መገፋፋት ነው፡፡ አቶ መለስ «እንኳን ለሰው ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ይገባል» እንዳሉት፡፡
አቡነ ጳውሎስ ሮም ተገኝተው ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ በአጋጣሚ እኔም ለጉባኤ ሄጄ ሮም ነበርኩ፡፡ «ታቦተ ጽዮንን በሙዝየም እናሳያታለን» ፈጽሞ አላሉም፡፡ «ስለ ታቦተ ጽዮን ዓለም የተሻለ መረጃ የሚያይበት ዘመን ይመጣል» ነበር ያሉት፡፡ ጋዜጠኛው ግን በዚያ መልኩ ተረጎመውና ዓለምን አነቃነቀው፡፡
ፓትርያርኩ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ሥርዓቱ የሚያዝዘውን እንጂ እርሳቸው የፈለጉትን የማድረግ መብት የላቸውም፡፡ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ገብቼ ልይ ባሉ ነበር፡፡ የአኩስም ጽዮን ሥርዓት ጥብቅነት ለፓትር ያርክ እንኳን የማይመለስ መሆኑን ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ በአኩስም በንግሥ ጊዜ ታቦት አይወጣም፡፡ ሥዕል እና መስቀል እንጂ፡፡ የአኩስም ሽማግሌዎች ታቦት ከመንበሩ፣ ሰው ከሀገሩ የሚወጣው ችግር ሲኖር ብቻ ነው ብለውኛል፡፡ ለዚህ ነው ታቦቱን ከመንበሩ ሰውንም ከሀገሩ አታውጣው ብለን የምን ጸልየው ነው ያሉት፡፡ በየወሩ የመጀመርያው ሰባት ጠዋት ጠዋት ምሕላ እየደረሰ ታቦት ተይዞ ከተማው ይዞራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ታቦቷን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ያለው በየዘመናቱ በሚቀያየሩት ንቡራነ ዕድ እጅ አይደለም፡፡ ሕዝቡ በፈጣሪ ርዳታ በምሥጢራዊው ሥርዓት በመረጣቸው የሽማግሌዎቹ ጉባኤ እጅ እንጂ፡፡
አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ ነውና ተረቱ ነገሮችን በጥንቃቄ ማየቱ መልካም ነው፡፡ ፈረንጆቹ የሚሉትን ብቻ እየሰሙ እግዚአብሔር የለለ አድርጎ መቁጠሩ ግን ደግም አይደል፡፡ ይልቅስ መፍራት ያለብን ታቦተ ጽዮንን ከእሥራኤል ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ያደረጋት የእሥራኤል ዐመጽ እና በደል በእኛ ዘንድ እንዳይገኝ ነው፡፡ ከሆነ አምላክም ጥበቃውን ያነሣል፤ እኛም ጠብቀን አናድናትም፡፡
ዲ/
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንነ ይጠብቅ

4 comments:

  1. እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያና ችንነ ይጠብቅ

    ReplyDelete
  2. hemmee.... mene endemel gera selegebagn newe, egna be akababiachen yalewen bete kristian eytebeqenat newe ene? berget ende aqemachen awo, KEZIEH YEBELETE meqenajet yelebenem hoy?... D/Daniel ante bezu eyeserah behonem TESEMI-NETEHEN meteqem yaleben yemeslegnal; endet? telegn endehone... SEBAKYANEN (PREACHERS)HULUNEM BE ANDE TELA SER bemesebseb bezowchen beteqenaj melku medres yechal zend betesera!

    ReplyDelete
  3. This seems to me a very high classified information and be kept secret only among the trustees. I don't see the point of revealing it to the public at large. Wonder why the Nebure Ed has to share such a security issue with you, in the first place, unless he wants to invite a problem?

    ReplyDelete
  4. enanete tewu!
    yalhone tarik kemtaweru ewenetun tsafu!
    taote tseyon ye askusm sew new yemitebkat??????

    1 msmer becha egziabhere new alachu?????

    menale be mulu tshufu Egziabhere fekdo endametat ersu new yemitebekat belachu be 4 netb(::) betezegu
    daniel endehone kentu wedase ena awaki ene becha neggn enzihn negroch tedemero mengedun eysate new::
    kemtsfeu wede sera gebu
    esti balfew yetekatelchew ye arseman betekerstyan lemaserat genzeb asebasebu sew hedo yegobegnachew enbachewn enabeseee ehe new sera
    copy past useless athunu!!!

    tnx

    ReplyDelete