ደቂቀ ናቡቴ

Wednesday, February 29, 2012

ጌታቸው ዶኒ እንደገና ወደ ዜና ብቅ ሲል

(ምንጭ፡- የካቲት 21/2004 ዓ.ም ከአማናዊቷ ደጀ ሰላም)

  • ዳግመኛ በተሾመበት ደብር የተቀሰቀሰው የምእመናን ተቃውሞ ተጠናክሯል።
  • የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እስርና ማስፈራሪያ እየተፈጸመባቸው ነው።
 በግንቦት 2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ራሳቸውን “ወንጌላውያን” ብለው ከሚጠሩ የፕሮቴስንታት አብያተ እምነት ጋር ያለው የዓላማ ግንኙነት በማስረጃ የተረጋገጠበት፣ በሕገ ወጥ የማጥመቅ ሥርዐትና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ጉልሕ ሃይማኖታዊ ሕጸጽ የፈጸመው ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ቀደም ሲል በአበው ካህናት እና ምእመናን ከፍተኛ ተቃውሞ ወደተባረረበት የቃሊቲ ደብረ ገነት ቁስቋም ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ አጥቢያውን እንዲያስተዳደር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ መሾሙ ተሰምቷል፡፡
ጌታቸው ዶኒ ከሁለት ዓመት በፊት በተባረረበት ደብር የቀድሞውን የአለቅነት ሥልጣኑን ይዞ እንዲመለስ የተደረገው ከታኅሣሥ ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን የሥፍራው ምንጮች በጽሑፍ ያደረሱን መረጃ ያመለክታል። ሊቀ ካህናት ጌታቸው በድጋሚ መመደቡ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮም በአጥቢያው ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ዘንድ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለት በመጠናከር ላይ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ጥር 6 ቀን 2004 ዓ.ም የሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒን ወደ ደብሩ መመለስ የሚቃወም ጽሑፍ /ትራክት/ ለምእመናን ተሰራጭቷል፡፡ የአቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ አንዳንድ የአጥቢያውን ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በመጥራት “አካባቢውን ሰላም ነስታችኋል” በማለት ቢያስጠነቅቅም ተቃውሞው እንዳልቆመ ነው ምንጮቹ የተናገሩት፡፡
በተለይም በበዓለ ጥምቀት በተከናወነው ጸሎተ ቅዳሴ፣ ሥርዐቱ ከተጀመረ በኋላ ቅዳሴውን የሚመሩት ካህን የለበሱትን ልብሰ ተክህኖ አስወልቆ በመልበስ ቅዳሴውን ለመምራት መሞከሩ ካህናቱንና ምእመናኑን አስደንግጧል፡፡ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የተፈጸመው ይኸው የጌታቸው ዶኒ ድፍረት ውስጥ ለውስጥ ተሰምቶ ጥር 12 ቀን 2004 ዓ.ም ታቦታቱ ወደ መንበራቸው ለመመለስ በዐውደ ምሕረቱ በቆሙበት ወቅት ‹ምክር እና ቡራኬ እሰጣለሁ› ብሎ በተነሣበት ወቅት ምእመናኑ በከፍተኛ ድምፅ ዝማሬና እልልታ በማሰማት ከመናገር እና ከመደመጥ ተከላክለውታል፡፡
በበዓሉ አከባበር ወቅት በርካታ የፖሊስ ኀይል በሥፍራው መታየቱ ውጥረት ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ‹ሊቀ ካህናት› ጌታቸው ዶኒ ወጣቶቹን በዐመፅ ቀስቃሽነት በመክሰስ ፖሊስ እንዲያስታግሣቸው ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጧል፡፡
ቁጥራቸው ከ400 በላይ የኾኑ ምእመናን ጌታቸው ዶኒ ቀደም ሲል የደብሩን አገልጋይ ካህናት በጎጥ (ተወላጅነት) በመከፋፈል እንዳይግባቡ ማድረጉን፣ ከጠበልተኞች ብጽዓት እና በአጥቢያው በሚፈጸመው ተኣምር የተነሣ ከሩቅም ከቅርብም ከሚሰበሰቡ ምእመናን የሚገኘውን ሀብት በአስተዳደራዊ መንገድ ለሙስና በማመቻቸት ሀብቱን ለምዝበራ ማጋለጡን፣ ምእመኑን ለማስተማርና አባታዊ ሓላፊነትን ለመወጣት ያለበትን ውስንነት በመጥቀስ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፤ በግልባጭም በክፍለ ከተማ እና ወረዳ ደረጃ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት አካላት አሳውቀዋል፡፡
ይሁንና የምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ አቤቱታ በግልባጭ የደረሰው ፖሊስ የካቲት አንድ ቀን 2004 ዓ.ም ሁለት የሰንበት ት/ቤቱን የሥራ አመራር አባላትንና ሦስት ምእመናንን ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በማለት ጠርቶ በማሰሩ የተፈጠረው ተቃውሞ እንዲባባስ አድርጓል፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የወረዳው (05) አስተዳደር ጽ/ቤትም የካቲት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም የአጥቢያውን ምእመን በጽ/ቤት በመጥራት ምእመናኑ ጉዳዩን ኮሚቴ በማዋቀር እንዲከታተሉ፣ የክፍለ ከተማው ፖሊስ በምእመናኑ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ከመፈጸም እንዲቆጠብ በማግባባት ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል፡፡ የታሰሩት ምእመናንም የካቲት ሁለት ጠዋት ፍ/ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው የብር 350 ዋስ ጠርተው እንዲፈቱ ተደርጓል፤ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በተደረሰበት መግባባት መሠረትም ጉዳዩን የሚከታተሉ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ይህም ሆኖ በማናለብኝ ድርጊቱ የቀጠለው ጌታቸው ዶኒ በምእመኑ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑትን የደብሩን ስብከተ ወንጌል ሓላፊ እንዲታሰሩ አልታቀበም - ቆይቶ የስብከተ ወንጌል ሓላፊው በዋስ ቢለቀቁም፡፡
በፈውስ ተኣምራትና ሌሎች ድንቅ ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቀው የቃሊቲ ደብረ ገነት ቁስቋምና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተ ስምንት ዓመት ያህል አስቆጥሯል፡፡ ሥፍራው ከአዲስ አበባ ወጣ ያለና የአጥቢያው ምእመናን ቁጥርም አነስተኛ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በሚያድሩበት ቦታ የደብረ ገነት ቁስቋም ማርያም ታቦት ከቦታው ባለመነሣቷ እዚያው ቦታ ላይ ማደርያ እንደተሠራላት፣ በጠበሏ እና እምነቷ ፈዋሽነት የተነሣም በርካታ ምእመናን ከየማእዝናቱ እየመጡ መሻታቸው እንደሚፈጸምላቸው ተዘግቧል፡፡
ጌታቸው ዶኒ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሲዳሞ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በፓትርያርኩ ከተሾመበት ሥልጣኑ ምእመናን ባቀረቧቸው ማስረጃዎችና ተቃውሞዎች መነሻነት እንዲወገድ ከተደረገ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሓላፊ ሆኖ ተመድቦ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት የደብረ ገነት ቁስቋም ማርያምን ጨምሮ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል፣ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም፣ በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ እና በአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ችግር የታየ ሲሆን አለመግባባቱ አስቸኳይ እልባት እንዳያገኝ አስተዳደሮቹ ከሀ/ስብከቱ አንዳንድ ሓላፊዎች እና በፓትርያርኩ ዙሪያ የፈጠሩት የጥቅም ግንኙነት ዕንቅፋት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

No comments:

Post a Comment