ደቂቀ ናቡቴ

Monday, May 14, 2012

አቡነ ጳውሎስ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ጋራ ማበራቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ገለጹ

 (ምንጭ ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 5/2004 ዓ.ም፤ May 13/ 2012)፦



  • ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጣይ ለሚኖረው አመራር የመላው ካህናትና ምእመናን ጸሎትና ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲደረግለት ተጠይቋል 
  • በአባ ጳውሎስ፣ አባ ፋኑኤልና ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ምክርና ኮሚሽን አድራጊነት የተጻፈው የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ እና ዘገባ በፈጠረው ቁጣ ሳቢያ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተቋረጠ 
  • ጋዜጣው በስብሰባ መካከል መሰራጨቱና ባተኮረበት ይዘት ብፁዓን አባቶችን ለማሸማቀቅ ተብሎ መዘጋጀቱን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተናግረዋል 
  • የጋዜጣው ርእሰ አንቀጽና ዘገባዎች አባ ጳውሎስ በስብሰባው እንዲያዙላቸው የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች ከአባ ጳውሎስ “የፓትርያርክነት ዐምባገነንነት” ፍላጎት አንጻር የማብራራት ግብዝነት የሚታይበት ነው
  • አባ ጳውሎስን ከፓትርያርክነት ማዕርጋቸው በሚያወርዷቸው የቃለ መሐላ ጥሰትና የታማኝነት መታጣት ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ውይይት ተጀምሯል
  • የአባ ጳውሎስ ግብረ በላዎች ትንት ማምሻውንና ዛሬ ቀን በአባቶች ማረፊያ ቤት እየተዘዋወሩ በማስፈራራት ጽናታቸውንና አንድነታቸውን ለማላላት እየሞከሩ ነው፤ እጅጋየሁ በየነ፣ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንና ለጊዜው ስማቸው ያልተጠቀሱ ግለሰቦች ይገኙባቸዋል
  • መደበኛ ስብሰባው ነገ ሰኞ ይቀጥላል
  ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በፊት በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ርእሰ መንበሩ አባ ጳውሎስ በምልአተ ጉባኤው ስምምነት የተደረሰባቸውን አጀንዳዎች ባለመቀበል ኾነ ብለው በያዙት ግትርነት የተነሣ ብዙኀኑ አባላት ከቀትር በኋላ ሌላ ሰብሳቢ መርጠው ውይይታቸውን ለመቀጠል ወስነው ነበር የተነሡት፡፡
በዚህ መሠረት የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ከቀትር በኋላ ስብሰባውን ለመቀጠል ወደ አዳራሹ ሲገቡ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በየመቀመጫቸው አንጻር ተቀምጦ ያገኛሉ፤ ፓትርያርኩም በኮሚቴው የተዘጋጁትን አጀንዳዎች እንደሚቀበሉ መስለው ተላስልሰው በመቅረባቸው ምልአተ ጉባኤው በእርሳቸው ርእሰ መንበርነት እየተመራ በተ.ቁ (2) ላይ የተመለከተውን የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን ሪፖርት አዳመጠ፤ እግረ መንገዳቸውንም ጋዜጣውን እንደ ዋዛ መመልከታቸውን አላቆሙም ነበር፡፡
ሪፖርቱ በንባብ ተሰምቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ውይይት ከመጀመሩ በፊት ለሻሂ ዕረፍት የተነሡት አባቶች ግን ጋዜጣው በያዘው ‹ቁም ነገር› ላይ መመካከር ያዙ፤ ምክክሩም አቡነ ጳውሎስ ከስብሰባው ቀደም ብለው ከዋሽንግተን ወደ አገር ቤት ከመጡት አባ ፋኑኤል እና ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ጋራ በማበር የጋዜጣውን አዘጋጆች እና ጋዜጣው በሚዘጋጅበት መምሪያ ውስጥ በሓላፊነት የሚገኙ ሌሎች ግለሰቦችን በቅጥረኝነት በመጠቀም የሠሩት መኾኑን ይደርሱበታል፡፡
ከሻሂ ዕረፍት መልስ ጋዜጣው ምን እንደጻፈ፣ ስለምን እንደጻፈ ሊያውቅና ሲቆጣጠርም ይገባ የነበረው  የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ስለ ጋዜጣው ዝግጅት ምንም እንደማያውቁና ሌሎች አጀንዳዎች ወደ ኋላ ቀርተው ምልአተ ጉባኤው በዚሁ ጉዳይ እንዲነጋገር ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በቤቱ የነበረው ድባብ በፓትርያርኩ እና በአባ ፋኑኤል ላይ ባነጣጠረ የተግሣጽ መአት የተሞላ ነበር፡፡ አባ ጳውሎስም ይኹኑ አባ ፋኑኤል የሠሩትን ያውቃሉና አንገታቸውን አቀርቅረው ተግሣጻቸውን ከመቀበል ውጭ ትንፍሽ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡
በተግሣጹ አባ ጳውሎስ ከተሐድሶ መናፍቃን ጋራ በግልጽ በማበር አባቶች በወቅታዊ ጉዳዮች በተቀረጹት አጀንዳዎች ዙሪያ ያላቸውን አንድነት እና የዓላማ ጽናት በመሸርሸር ለማሸማቀቅ (በግብር የሚመስሏቸው የመፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች እንደሚያደርጉት) አስበው እንዲፈጸም በማዘዝ እጃቸው እንዳለበት ተነግሯቸዋል፤ አባ ፋኑኤልም “መወገዝ ያለብኽ ሕገ ወጡ አንተ ነኽ፤ በሌላው ሊቀ ጳጳስ ሀገረ ስብከት ገብተኽ ክህነት የምትሰጥ፤ አንተ ብሎ ክህነት ያዥ¡” በሚሉና ሌሎችም ኀይለ ቃላት የድርሻቸውን አግኝተዋል፡፡
በ56ኛ ዓመት ቁጥር 126፣ ሚያዝያ ግንቦት 2004 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ‹‹የአባቶች ገበና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጋለጥ›› በሚል ርእስ ስለ ሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያንንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ከግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ የህልውና ውሳኔ›› በሚል ርእስ ስለተዘጋጀው ሐተታ አስተያየታቸውን የተጠየቁት ዋና አዘጋጁ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ‹‹እኔ ማንንም አልፈራም፤ ጽሑፉ አያስጠይቀኝም እንጂ ብጠየቅበት አልፈራም፤ በይዘቱ አዲስ አይደለም፤ የተለያዩ ግለሰቦች በየራሳቸው አቀራረብ ሲጽፉት የቆዩት ነው፤ እኔ ለመጻፍ የሞከርኹት የቤተ ክርስቲያን ህልውና እየተነካ ነው ብዬ በማምንበት ስለ ጳጳሳት ንብረት ጉዳይ ነበር፤ አባ ጳውሎስ ግን በሲኖዶስ ስብሰባ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይሻሻል አሉ፤ እውነቱን ለመናገር  ጽሑፉ ከውጭ የመጣ እንጂ በዝግጅት ክፍሉ የተጻፈ አይደለም፤ በስሜ እየተነገደብኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዋና አዘጋጁ ጽሑፉ ከውጭ ተዘጋጅቶ እንደመጣ የተናገሩትን መነሻ በማድረግ አዘጋጁን አካል ለማወቅ በተደረገ ጥረት÷ ‹‹አባ ጳውሎስን ደግፋችኹ ከጻፋችኹ ማንም አይነካችኹ፤ ከተነካችኹም እኛ አለንላችኹ፤ ሁሉም ወንጀለኛ ነው›› በሚል የጥቅም ማበረታቻ የተቀበሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ፣ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊነት ባለው ሥልጣን ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያንን ከመድረክ እያገለለና በየአህጉረ ስብከቱ በመዞር ከፕሮቴንታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና አቀንቃኞች ጋራ ያለውን ግንኙነት እያጠናከረ የሚገኘው አእመረ አሸብር፣ እንደ ቀበሮዋ ዘለው ዘለው የሻቱትን ማዕርገ ጵጵስና ቢያጡት የተሾሙትን አባቶች በማሸማቀቅና አንገት በማስደፋት ለመሾም የቋመጡት አባ ሰረቀ፤ ለዚህም የገንዘብ ድጋፍ የሰጡት አባ ፋኑኤልና ዦቢራው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን መኾናቸው እየተነገረ ነው፤ የአባ ጳውሎስ አይዟችኹ ባይነት (ቡራኬ) ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡ ይኹንና የዝግጅት ክፍሉም በጽሑፉ ላይ ማሻሻያ በማድረግና እንዲታተም በመፍቀድ፣ ምናልባትም የጥቅሙም ተካፋይ በመኾን መጠየቁ እንደማይቀር ግልጽ ነው፡፡

         ነገ ሰኞ በሚቀጥለው ስብሰባ ቀዳሚው አጀንዳ የጋዜጣው አዘጋጆች ተጠርተው የሚጠየቁበት እና ለዝግጅቱ ሓላፊነት የሚወስደው አካል ተለይቶ አስፈላጊው ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሚኾን ተጠቁሟል፡፡ ጋዜጣው ከመሰራጨት እንዲታገድ፣ አባ ጳውሎስን ጨምሮ አዘጋጆቹና ተባባሪዎቻቸው በቅዱስ ሲኖዶስና በሕግ አግባብ የሚጠየቁበትም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
        የጋዜጣው ዝግጅት ቤተ ክህነቱ በአባ ጳውሎስ ዙሪያ በተሰበሰቡ ጥቅመኞች እና የተሐድሶ መናፍቃን ለመወረሩ ማስረጃ እንደ ኾነ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ቁም ነገር የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክህነቱ በተሐድሶዎችና ጥቅመኞች ለመወረሩና በእነርሱ ተጽዕኖ ሥር ለመውደቁ ከዚህ በላይ ማስረጃ አያስፈልገንም፤›› ብለዋል አንድ አባት፡፡ ስብሰባው በጋዜጣው ሳቢያ ያለሰዓቱ መቋረጡን ተከትሎ ሁሉም አባቶች በየማረፊያ ቤታቸው ትላንት ማምሻውንና ዛሬ ቀን እርስ በርስ መመካከራቸውን ቀጥለዋል፡፡
          ‹‹በአባቶች መካከል በተፈጠረው አንድነትም ይኹን በግቢው የአባ ጳውሎስ ግብረ በላዎች በሚያደርጉት መራወጥ 2001 . የነበረው ኹኔታ ተመልሶ የመጣ ይመስላል፤›› ያሉ አስተያየት ሰጭዎች ብፁዓን አባቶች የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን በመጠቀም በስብሰባዎች ላይ አባ ጳውሎስ የሚፈጥሯቸውን የማዘናጊያ አካሄዶች ወጊድ እያሉ ጉዳዮች በሚገባቸው ጥልቀት እየተብላሉና በውሳኔ እየታሰሩ መሄዳቸውን እንዲያረጋግጡ መክረዋል፡፡


ጋዜጣው ርእሰ አንቀጽ እና ዜና ዘገባ የሚከተሉትን ዋና ዋና ሐሳቦችለማንሣት ይሞክራል፦
  • . አባ ጳውሎስ በሌላቸው ሃይማኖትና ምግባረ ጽድቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በማሻሻል የፓትርያሪክነት ዐምባገነንነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሹ በጉልሕ ያሳያል፡፡ ለዚህም ርእሰ አንቀጹ ‹‹በ1991 ዓ.ም ተሻሻለ ተብሎ የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን . . .አልፎ ተርፎ የቤተ ክርስቲኒቱን ርእስ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን መብት የሚጋፋ ነው፤›› የሚለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኧረ እንዲያው ለመኾኑ አባ ጳውሎስ ራሳቸውን በአምሳለ ንጉሥ እስኪመለከቱ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት እንዳሻቸው እያባከኑ ባሉበት ኹኔታ የትኛው መብታቸው ነው የተገፋው? ወይስ በጣዖትነት መመለክ አማራቸው?
  • በብፁዓን አባቶች ላይ ደግሞ በሥርዐተ ሢመት (ምርጫ፣ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ)፣ በሀብት ክምችትና ውርስ እንዲሁም በውጭ ዜግነት ከጊዜው በጣም የዘገየ፣ አባ ጳውሎስን ከተመሳሳይ ወቀሳ ነጻ ያደረገ የጩኸቴን ቀሙኝ ክስና ግብዝነት የተሞላበት ጽሑፍ አቅርቧል፡፡
  • የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ፕሮጀክት መንገድ ጠራጊ የኾነው “የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት” ተብዬ ከቃለ ዐዋዲውና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የሚፃረር መዋቅር በመኾኑ እንዲዘጋ ያሳለፈውን ውሳኔ በመናቅ ነውረኛውን ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን “በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙሉ ሥልጣን ዋና ሓላፊ” በማለት ይጠራዋል (በጋዜጣው የፊት ገጽ የወጣውንና አባ ፋኑኤልና ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ‹በአጭር ጊዜ ስላሳዩት የሥራ ፍሬ› የሚናገር ‹ዜና› ራሱ እንዳረቀቀው ይነገራል፡፡)
  • ከግማሽ ምእት በላይ በሰሜን አሜሪካ ሲከናወን የቆየውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመዘንጋት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተላልፈው በሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት አህጉረ ስብከት ክህነት በመስጠትና ማእከላዊ አሠራርን በመናድ የሚታወቁትን አባ ፋኑኤልን “በሰሜን አሜሪካ ሥራ አሁን ገና ሥራ እንደተጀመረ እና የታሪክ እመርታ እንደታየ” በመተረክ ይቀጥፋል፡፡
  • የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት wana የኾኑትን ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ “በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ ሲሠሩ ዛሬ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸውን ግለሰቦች በድርጅቱ ውስጥ በመሰግሰጋቸው ተነቅቶባቸው እንደተባረሩ” በመጥቀስ ‹ክስና ማስረጃው› የማይገናኝ ውንጀላ ይናገራል፤ አያይዞም በቤተ ክህነቱ ሠራተኞች አገላለጽ አባ ጳውሎስና ግብረ በላዎቻቸው መጥምጠው እንዳዳከሙት ለተገለጸው ኮሚሽን “የተሳሳተ መረጃ ለለጋሽ ድርጅቶች በመስጠት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ እንዲዘጋ ያስደረጉት ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ናቸው፤” በሚል ክሱን ይቀጥላል፤ ሊቀ ጳጳሱ በሌላቸው ሥልጣን በቀሲስ ዶ/ር መስፍን ላይ አስተላልፌዋለኹ ለሚሉት ከንቱ ‹ውግዘት›ም አጽድቆት ይሰጣል፡፡
  • በጋዜጣው ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ‹‹ጋዜጣው የደገፈውንና የነቀፈውን አያውቅም፤ ለምሳሌ አባ ፋኑኤል ስለ ራሳቸው እያወሩና ቀሲስ ዶ/ር መስፍንን ከስሰው የከበሩ ቢመስላቸውም በውስጥ ገጽ በተጻፈው ጽሑፍ ደግሞ ‹በእግዚአብሔር ገንዘብ የግል ቪላ ገንብተው ያከራያሉ፤ እንደ ዓለማዊ ሰው ለአባት የማይገቡ ዘመናዊና ከፍተኛ ዋጋ ያለው መኪና ገዝተው ያሽከረክራሉ፤ ሌላም፣ ሌላም ተብለው የተወነጀሉት ዋነኛው ራሳቸው ናቸው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡




በአጠቃላይ ጋዜጣው በአቡነ ፋኑኤል ጉቦ እንደተዘጋጀ ምንም አላጠራጠረም። በተግሳጽ መዶሻ ሲወቀሩ ያመሹት አቡነ ፋኑኤልም አልካዱም። ጥያቄው ፓትርያርኩ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሊፈቅዱ ቻሉ የሚለው ተመሳሳይ ጥያቄ ነው። ራሳቸው የሚመሯቸውን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጎን በጋዜጣ ማስደብደብ ምን የሚሉት “ፓትርያርክነት” ነው? ፓትርያርክነታቸውስ ለማን ነው? በ2001 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ የተቃወሟቸው አባቶች ቤታቸው በሌሊት ከመሰባበበሩ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ይህ ሕገ ወጥ ጋዜጣ አዘገጃጀት ግልጽ አያደርገውምን?
ፓትርያርኩ ቅ/ሲኖዶሱን ባለመስማት ካመጹ ቆይተዋል። የዚህ ሕገ ወጥነታቸው ምልክት ደግሞ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የተደነቀረው ሀውልታቸው ነው። ቅ/ሲኖዶስ እንዲነሣ ቢወስንም በርሳቸው አምባገነንነት ይኸው እንደተገተረ አለ። ውሳኔያቸውን በተግባር ለመግለጽ ምንም አቅም ያጡት አባቶች ከዚህ በኋላ ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑ ይፈረድባቸዋልን? የወሰኑትን ውሳኔ ቤተ ክህነቱ ለማስፈጸም የማይፈልግ ከሆነ ምእመናን ሊያግዟቸው አይገባምን? ይህንን ጣዖት መሰል ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ሀውልት ምእመናን ነቃቅለው ሊጥሉ፣ አባቶቻቸውን ሊያጠቋቸው ከሚመጡ ወንበዴዎች እና “ዶላር-አምላኩ” የዲሲ ጆቢራዎች ሊከላከል አይገባውምን?


 ከአባቶቻችን ጋር በመቆም ቤተ ክርስቲያናችንን እንታደጋለን። እግዚአብሔር ይርዳን።

No comments:

Post a Comment