ደቂቀ ናቡቴ

Monday, October 22, 2012

†♥†አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ†♥†


በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብዬ በማመን ምንም እንኳን በስም በአካል በግብር ሦስት ቢሆኑም በመለኮት ዓለምን በመፍጠርና በማሳለፍ በህልውና በመፍረድ አንድ አምላክ ብዬ በማመንና በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በመታመን ስለ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከብዙ በጥቂቱ ለመጻፍ እንዲህ እንጀምራለን።
“…. ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ ኪያየ ይጸንሑ  ጻድቃን እስከ ሶበ ተዐስየኒ።” (“ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።”) መዝ.፻፵፩፡፯ (141፡7)
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
ትውልዳቸው ከዘርዐ ጌዴዎን ገበዘ አክሱም ነው። አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተማርያም ይባላሉ። ለመምህር ሰጥቷቸው ሲማሩ አድገው ኋላ ወላጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ደብረበን ኮል ስገብተው ስርዓተ ምንኩስናን ከአበው እያጠኑ ለትልቁም ለትንሸሹም በትህትና እየታዘዙ ውሃ እየቀዱ እንጨት እየሰበሩ በትኀርምትና በጸለሎት ይኖሩ ነበር። ሰይጣን በውዳሴ ከንቱ ጾር ቢመጣባቸው ከማኀበረ መነኮሳቱ ተለይተው በተባሕትዎ ለመኖር ሽተው ወጥተው ሲሄዱ ተከዜ ደረሱ። ወንዙ ሞልቶ የማያሻግራቸው ቢሆን ውሃውን በትምህርተ መስቀል ባርከው በአንድ እጃቸው መጽሐፍ በአንድ እጃቸው መብራት እንደያዙ ገብተው መብራቱ ሳይጠፋ መጽሐፉም ሳይበላሽ ተሻግረዋል። ዋልዲባ ሲደርሱ ጌታ እዚህ ተቀመጥ  ስላላቸው ገዳም ገድመው ሥርዓተ ምንኩስናን እያስተማሩ ተቀመጡ።
ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህን እየጸለዩ ሲሄዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታቱ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ሲባርኩት ኀብስተ ሕይወት ሆነላቸው። ከነ ደቀመዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል። እመቤታችን የፍቅር መግለጫ ነጭ ዕጣንና ዕንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት (የሕይወት ቦታ) አስገበዋለሁ ብላ ተስፋ ሰጥታቸዋለች። ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታ በስብሐተ መላዕክት ተገልጾ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን ዜና ገድልህን የጻፈ፣ ያጻፈ፣ የያነበበ፣ የተማረ፣ የያስተማረውን፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ። አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋት በገዳመ ዋሊ ታኀሳስ ፲፪ (12) ቀን ዐርፈዋል። የአባታችን ረድኤትና በረከታቸው በሁላችን ላይ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር አሜን።
“በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።“ ፊሊ.፫፡፩­-፫ (ፊሊ.3፡1­-3
ምንጭ፡­- በማኀበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል የተዘጋጀ ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ሁለት መጽሐፍና የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ የተዘጋጀ።
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡ እድሜ ለንሰሐ ዘመን ለፍሰሃ ሰጥቶኝ ይህችን ታህል ስለ አባታችን እንድመሰክር የረደኝ አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡

የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡

1 comment: