ደቂቀ ናቡቴ

Monday, November 26, 2012

†አባ ገሪማ ዘመደራ†

አባ ገሪማ ዘመደራ  (“ኦ ወልድዬ ግሩም ገሪማ ገረምከኒ”)

የተሰዓቱ ቅዱሳን ሐዋርያዊ ተልእኮ መቅድም
ተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አልአሜዳ በነገሰ በአምስት ዓመት ነው። እንደመጡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በአክሱም ዐስራ ሁለት ዓመት ኖረዋል።     
ተሰዓቱ ቅዱሳን በስም አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጵሕማ፣ አባ አፍአባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ፣ አባ ጉባ ይባላሉ። እኚ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ዝም ብሎ አልተቀመጡም፤ ለሥራቸው በር ከፋች የሆነውን ቋንቋ፣ የሕዝቡን ባህል ጠንቅቀው ካወቁ በኋላ ላይ በአንድ አከባቢ ከመኖር ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በመደባቸው ቀጥታ ማስተማርን መርጠው መንፈሳዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የአክሱምን ነገስታት እርዳታና ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር። እኚው ተሰዓቱ ቅዱሳን የመጡበት ሀገራት ሮም፣ እስያ፣ አንጾኪያ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ቂሳርያ፣ ኪልቂያ ሲሆን በነበሩበት ጊዜያትም፡­-
፩. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጽንቶልናል።
፪. መጽሐፍትን ተርጉሞልናል።
፫. ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል።
፬. ብዙ ገዳማትን መስርተዋል።
፭. ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል።

Sunday, November 18, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል ሁለት

                                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13.6-9/ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል አንድ


                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡
ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡ 
1ኛ. መቆም:- መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡
ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›.፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8.44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

Tuesday, November 13, 2012

✙የእመቤታችን የስደት ምሳሌ✙



በስመ ሥላሴ
ፈጣን ደመና  
 ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈ እግዚአብሔር እየተቃኘ ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ዐማኑኤልን ይዛ ወደ ግብጽ የመሰደዷን ነገር ተገልጦለት፤   
“እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።” ኢሳ. ፲፱፡፩ በማለት ከገነት የተሰደድነውን እኛን ወደ ቀደ  ርስታችን እንደመጣ ለማጠየቅና፣ ጠላታችን ዲያብሎስን ከሰዎች ልብ አውጥቶ ለመስደድ፤ ክብር ይግባውና ወልደ እግዚአብሔር ልመናዋ ፈጥኖ በሚሰማላት “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር አስቀድሞ ገልጾታል።
ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ንጉሡ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾለት “ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጉየይ ውስተ ብሔረ ግብጽ” (ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ”) ባለው ጊዜ ይኽ ኢሳያስ የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ምልጃወዋ ፈጥነኖ በሚደርስላት   “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ በሄደ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ሁሉ እይተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱ አድሮ ያስቱ የነበሩት አጋንንት ሁሉ ሸሽተዋል። በመሆኑም እመቤታችን “ደመና መፍጠኒት” ወይም ደመና ኢሳያስ ተብላ ተጠርታለች።

Monday, November 12, 2012

መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት ስሕተት ነውን?

ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
 ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዕድሜ ይስጠን እንጂ ራሱን በቻለ ርእስ በሌላ ጊዜ በሰፊው እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬ የመላእክትን ማዳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ እየጠቀስን እንመልከት፡፡

ቅዱስ ዳዊት በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?

በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡

Friday, November 9, 2012

እምሊባኖስ ትወፅእ መርዓት


 ኦ ድንግል አኮ በፍተወተ ደነስ ዘተጸነስኪ ፡፡ ድንግል ዘርዕ ዘይወጽእ እምስካበ ተዓዳዌ ሕግ ይከውን ለቅጥቃጤ ወለሙስና ባለው ፈቃድ የተፀነሽ አይደለሽም፡፡ አላ በሩካቤ ዘበህግ እምሐና ወኢያቄኒም ተወለድኪ ክቡር አውስቦ በኵለሄ ወለምስካቦሙኒ አልቦቱ ስዕበት ባለው ፈቃድ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡ አንድም እስመ ናሁ በኃጢአት ተፀነስኩ፡፡ ወበአመፃ ወለደተኒ እ...ምየ እንዲል፡፡ በልተው ጠጥተው በሚያደርጉት ፈቲው ጽነት የተፀነስሽ አይደለም፡፡ ብዝኁ ወተባዝኁ ባለው ፈቃድ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡ ታሪክ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ ፤ ብእላቸውም የወርቅ ፤ የብር የፈረስ ፤ የበቅሎ የሴት የባርያ የወንድ ባርያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሳ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ ይህን ያህል አቅርንተ ብሩር ተብሎ ይቆጠር ነበር እንጂ የቀረው አይቆጠርም ነበር፡፡ ከእለታት ባንዳቸው ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ ቴክታ እኔ መካን’ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል አላት እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል ፤ አግብተህ አትወልድምን አለችው ይህስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ ወዲያው ራእይ አይተዋል ፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ ፤ እንቦሳቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው በሃገራቸው መፈክረ ሕልም አለና ሂደው ነገሩት ፤ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን፡፡ በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም አንደ ነቢይ አንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አላቸው ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች ፤ ወለደች ስሟን ሄኤሜን ዴርዴን ዴርዴ ቶናን ቶና ሲካርን ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መተን ስታደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት ፤ ምክነት ወርዶ እንደ አያቶችዋ ሁናለች ብዕሉ ግን በመጠን ሁኑዋል፡፡ ከጎረቤትዋ በዝሙት የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች ሐና ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እስማለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን የምለብሰው ልብስ የለኝም አለቻት፤ እርሱዋም ልብስማ የኔ ካንድ ሁለት ሦስት ልብስ ያለልሽ አይደለም የንን ለብሰሽ አትሄጅም አለቻት፡፡

Wednesday, November 7, 2012

‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!››


ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ዘወትር ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ በምናደርሰው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› በተሰኘው የጸሎት ክፍል ውስጥ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ›› የሚል የምስጋናና የምስክርነት ቃል ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በመልክዓ ማርያም ውስጥም ‹‹ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ ወገቢረ ምሕረት መፍቅዱ›› ማለትም ‹‹ምሕረት ማድረግ ለሚወድ መልካም መልካሙን ማሰብ ልማዱ ለሆነ ሕሊናሽ ሰላም እላለሁ!›› የሚል የምስጋና ቃል አለ፡፡
የተአምረ ማርያም መቅድም ደግሞ የድንግል ማርያምን ሕሊና ከመላእክት ሕሊና ጋር ያስተያይና በልጦ ሲያገኘው በመደነቅ እንዲህ እያለ ያመሰግናል፡፡ ‹‹ሥጋዊ ነገር ከማሰብ መጠበቅ ከአዳም ልጆች ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፡፡ በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና፡፡›› ከዚህም ጋር አያይዞ ‹‹የእመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› ይህም አሳብዋ ንጹሕና መልካም ብቻ መሆኑን ያስረዳናል፡:
እኛ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔርን እንድንመስል›› ታዘናል፡፡ (1ጢሞ4.7-8፤ 1ቆሮ11.1) ይህም በመልክ አይደለም፡፡ በሥራና በአመለካከት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን በአመለካከት መምሰል የማይቻል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔርን ምሰሉ አንባልም ነበር፡፡ በመልክ ስለመምሰል የሚናገር ቢሆን ኖሮ ደግሞ መልክን የሚፈጥረው ፈጣሪ ስለሆን ‹‹ምሰሉ›› አንባልም ነበር፡፡ የሚደንቅ ነው! እኛ ፈጣሪን በአሳብና በአመለካከት እንድንመስለው ታዘዝን፡፡ ድንግል ማርያም ግን መስላ ስለተገኘች ‹‹አሳብዋ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› የሚል ምስክርነት ተሰጠላት፡፡
ቀደም ሲል ስለ ድንግል ማርያም ፍጹም የሕሊና ድንግልናና በጎነት ከአዋልድ መጻሕፍት ያስቀደምኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፈው ማሳየት ያስፈልጋልና እነሆ!
ብዙ ሰዎች ስለ ድንግል ማርያም የሕሊና ንጽሕና ስንናገር በምን አውቃችው ነው? ለማለት ይዳዳቸዋል፡፡ በእርግጥ እኛ እንኳን የድንግል ማርያምን ሕሊና የኃጥአንንም ሕሊና የምናውቅበት ችሎታ የለንም፡፡ የጻድቃን ሕሊና ከኃጥአን ይልቅ እጅግ ይጠልቃል፡፡ የድንግል ማርያም ሕሊና ደግሞ ከሁሉ ይልቅ ጥልቅ ነው፡፡ ‹‹መንፈሳዊ ሰው በማንም አይመረመርም እርሱ ግን ሁሉን ይመረምራል›› ከተባለ ሰው ፍጹም መንፈሳዊት ድንግል ማርያምን ሊመረምር እንዴት ይችላል? (1ቆሮ2.15)

Tuesday, November 6, 2012

አባ ጽጌ ድንግል




“በስመ ሥላሴ”

ወበዛቲ ዕለት አእረፈ አባ ጽጌ ድንግል ጥቅምተ 27
“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ለአባ ጽጌ ድንግል እንዲሁም ለአቡነ መብዓ ጽዮን በዓለ እረፍታቸው በሠላም አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)
አባ ጽጌ ድንግል
ሀገራቸው ወሎ ቦረና ሲሆን ደራሲና ማህሌታዊ ናቸው። ጻድቁ አባታችን ማህሌተ ጽጌን የደረሱ ሲሆን እንጀራ ሳይበሉ ባቄላ እየበሉ ውሃ እየጠጡ 9 ዓመት የቆዩ ትልቅ አባት አባት ሲሆኑ በስማቸው የተሰራ የአለት ፍልፍል የተሰራ ከወቅር የታነጸ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከጋስጫ አጠገብ አላቸው። ቤተ ክርስቲያናቸው በረሃ ውስጥ ነው ያለው። ድሮ ጧት አንድ በ6 ሰዓት አንድ ማታ አንድ በድምሩ በ3 መነኮሳት ይታጠን ነበር። ዛሬ ግን ማዕጠንትም ቅዳሴም የለም። ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 4 ሰዓት መንገድ ተሂዶ የአባ ጽጌ ድንግል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። መቃብራቸውም በዚሁ ቦታ እራሳቸው ባነጹት ነው ያለው። ዛሬ መነኮሳቱ ትተውት ከተማ ስለገቡ ተዘግቶ ነው የሚኖረው እጅግ በጣም ያሳዝናል። በሳምንት ብቻ አንድ ጊዜ ይታጠናል። ጻድቁ እመቤታችንን ስለሚወዱ ማህሌተ ጽጌን ደረሱ። ሌላም አስደናቂ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል። ገድልም አላቸው። ታቦትም በስማቸው ተቀርጿል። ቤተ ክርስቲያንም ከአለት የተወቀረ አላቸው። ጻድቁ አባታችን በብዙ ተጋድሎም ዛሬ ማለትም ጥቅምተ 27 ቀን አርፈዋል። በዚህ በአባ ጽጌ ገዳም ታላላቅ ታላላቅ የሆኑ የብራና መጽሐፍቶች ከ130 በላይ ይገኛሉ። በሐረግ ያሸበረቁ ናቸው። ነጮችና የእጅ ባለሙያዎች ያልደረሱባቸው ጠባቂዎቹ ይመሰገናሉ። የአባታችን በረከት በሁላችን ላይ ይደር።

†♥†ነገረ ቅዱሳን†♥†



“በስመ ሥላሴ”
ወበዛቲ ዕለት አእረፈ አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ለአቡነ መብዓ ጽዮን፣ ንዲሁም ለአባ ጽጌ ድንግል በዓለ እረፍታቸው አደረሳችሁ አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡(እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው። በአባታቸው ስም ሀብተ ጽዮንም ብሎ ይጠራቸዋል። እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው። አባታቸው ንቡረ ዕድ ሀብተ ጽዮን እናታቸው ሂሩት ይባላሉ። ደገኛ ጻድቅ ሲሆኑ ከታወቁበት ግብራቸው በሳምንት ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጌታ ሐሞት እንዳጠጡት ያንን እያሰቡ። አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚ፣ ቡናና ትርንጎ አፈርቷል፤ ጻድቁ ሌላ አስደናቂ ታሪክ አላቸው አርብ አርብ ሲዖል እየገቡ እልፍ እልፍ ነፍሳትን ያወጡ፤ በገበያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ካስተማሩ በኋላ ይመግቡ ነበር። በየወሩ የመድኃኔ ዓለም በዓል እየዘከሩ የወጣ የወረደውን ሁሉ የገበያውንም ሰው ሁሉ ያበሉ ይመግቡ ነበር። ዛሬም ሲዖል እየገቡ ያወጣሉ። “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”ዮሐ.3፡12  እንዳለ ጌታ ዛሬም ይህንን የሚጠራጠሩ ብዙዎች አሉ። እኛ ግን በዚህ እናምናለን እንታመናለን። በጥቅምት 27 ብዙ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ቀንም ነው።  አባታችን በጥቅምት 27 ቀንም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባታችንን አንድ ገበያ የሚያህል ሰው ይከተላቸው ነበር። የአባታችን አባ መባ ጽዮን በራሳቸው ገዳም ማጢቆስ በተባለ ገዳም አፅማቸው ይገኛል። በትግራይ ሽሬ አሎጊንም የሚባል ትልቅ ገዳም አላቸው። የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድኃኔ ዓለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው። እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በዓብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች። ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ክብሩ ከጻድቁ አቡነ መበዓ ጽዮንና ከአባ ጽጌ ድንግል በረከት ረድኤትን ያድለን አሜን።