ደቂቀ ናቡቴ

Tuesday, November 13, 2012

✙የእመቤታችን የስደት ምሳሌ✙



በስመ ሥላሴ
ፈጣን ደመና  
 ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈ እግዚአብሔር እየተቃኘ ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ዐማኑኤልን ይዛ ወደ ግብጽ የመሰደዷን ነገር ተገልጦለት፤   
“እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።” ኢሳ. ፲፱፡፩ በማለት ከገነት የተሰደድነውን እኛን ወደ ቀደ  ርስታችን እንደመጣ ለማጠየቅና፣ ጠላታችን ዲያብሎስን ከሰዎች ልብ አውጥቶ ለመስደድ፤ ክብር ይግባውና ወልደ እግዚአብሔር ልመናዋ ፈጥኖ በሚሰማላት “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር አስቀድሞ ገልጾታል።
ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ንጉሡ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾለት “ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጉየይ ውስተ ብሔረ ግብጽ” (ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ”) ባለው ጊዜ ይኽ ኢሳያስ የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ምልጃወዋ ፈጥነኖ በሚደርስላት   “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ በሄደ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ሁሉ እይተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱ አድሮ ያስቱ የነበሩት አጋንንት ሁሉ ሸሽተዋል። በመሆኑም እመቤታችን “ደመና መፍጠኒት” ወይም ደመና ኢሳያስ ተብላ ተጠርታለች።
ኢትዮጵያዊ የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይኽነን የኢሳይያስ ትንቢት በጥልቀት ሲተረጉም ”ሄሮድስ ኀሠሠ ዘኢይትረከብ  ወእግዚእ ትግሕሠ ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል ፤ በከመ ይቤ ኢሳይያስ ናሁ እግዚአብሔር ይወርድ  ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል  አንቲ ክመ ኦ ቅድስት ድንግል ሄሮድስ ፈተወ ይዕዱ ነፋሰ ውስተ ጽርሑ በአይቴ ይትከሀል ዐዲወ ነፋስ፤ . . . . . . ( ሄሮድስ የማያገኘውን ፈለገ፤ ጌታ በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብጽ ኼደ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ  “እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” ብሎ እንደተናገረ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ  ፈጣን ደመና መችም መች ቢሆን አንቺ ነሽ፤ ሄሮድስ በአዳራሹ ውስጥ ነፋስን ሊዘጋ ወደደ፤ ነፋስን መዝጋት ወዴት ይቻላል? ሄሮስ የፀሐይን ብርሃን በእጁ ሊጨብጥ ወደደ። የፀሐይን ብርሃን መጨበጥ ወዴት ይቻላል? እግዚአብሔር በጀርባሽ ታዝሎ በግብጽ ምድር እንግዳ ሆነ) በማለት ምስጢሩን አምልቶ አጉልቶ አብዝቶ አስፍቶ ተንትኖታል።
ማኀሌታዊው ቅዱስ ኤፍሬም በመዋሥዕት መጽሐፉ ላይ ይኽንን ምስጢር ሲተረጉም “ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ ሀገር ሄደ፤” “ከነቢያት ይልቅ ድምጸ ታላቅ የሞሆን ነቢዩ ኢሳያስ አሸናፊ እግዚአብሔር ወደ ግብጽ ምድር ይወርዳል ብሎ አሰምቶ ተናገረ” (ኢሳይያስ ቀላል ደመና ብሎ የተናገረላት የእግዚአብሔር የባሕርያ ልጁን በማሕፀኗ የወሰነችው ድንግል ማርያም ናታ።) በማለት ሙሉ ትርጓሜን ሰጥቶታል።
ምንጭ፡­- ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ክፍል ፪፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን ዘሰኑይ ፣ ቅዱስ ያሬድ መዋሥዕት ዘፀአት ግብጽ ገጽ ፵፭
የእመቤታችን ረድኤቷ በረከቷ ከሁላችን ጋር ይሁን ከልጇ ስደትና ከስደቷ በረከት ረድኤትን ይክፈለን አሜን ይቆየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡


2 comments:

  1. I was more than happy to find this page. I want to to thank you
    for your time for this particularly wonderful read!!
    I definitely loved every part of it and i also have you book-marked to look at new things on your website.


    Feel free to surf to my weblog: Dre Beats Headphones

    ReplyDelete