ደቂቀ ናቡቴ

Tuesday, August 28, 2012

ቅዱስ ነአኩቶለአብ



ቅዱስ ነአኩቶለአብ ከአባቱ ከቅዱስ ገ/ማርም ከእናቱ ከንግሥት መርኬዛ ለ1164 ዓ.ም ታህሣሥ 29 ቀን ተወለደ ነአኩቶለአብ ማለት የሰማይ አባታችን እናመሰግነው ማለት ነው፡፡ ልደቱም ቅዱስ  ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን እንዳበሰረው  እሱም የተወለደው በብስራተ ገብርኤል ነው፡፡ ከ11 ነገስታት አንዱ ከ4ቱ ነገስታት(ቅዱስ የምርሐነ ክርስቶስ ቅዱስ ገብረማርያም ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነዓኩቶለአብ) ቅዱስ የሚባል ስም የተሰጠው ካህን ወንጉስ ቅዱስ ነአኩቶለአብ እስካሁን ድረስ በህይወት ያለ ለወደፊት በሀይማኖቱ እንደኤልያስና እንደሄኖክ ስለቅዱሳን አማላጅነት መስክሮ የሚሞት እስከ አሁን በብሄረ ህያዋን ያለ በንግስና 40 ዓመት የቆየ ስውር ጻድቅ ነው፡፡ እናትና አባቱ በህፃንነቱ ነበር የሞቱበት፡፡ ነገር ግን የቃልኪዳን አባት ቅዱስ ላሊበላ ከቤተ መንግስቱ ወስዶት በጥሩ ሁኔታ ስርዓተ መንግስቱን እየተመለከተ አደገ፡፡ በዚህ ሁኔታ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ አባ ይስሀቅ የተባሉ መምህር ተቀጥረውለት የቤተክርስቲያን ትምህርቱን ተምሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ስርዓተ መንግስቱን እንዲከታተልና በደንብ እንዲያውቅ ገ/ክርስቶስ የሚባል ከጎኑ ሳይለይ ስርዓተ መንግስቱን እንዲማር ተደርጓል፡፡ በዚህ እንዳለ ዲቁና በመቀበል በንፅህና ያገለግል ነበር፡፡ ሀሳቡም በአርምሞ በድንግልና በስርዓተ ፀሎትና በቀኖና ለመኖር ፈልጎ እንዳለ የአምላክ ትዕዛዝ ስላለ በፍቃደ እግዚአብሄር አምባ ጽዮን ከተባለው ቦታ ስመ ጥሩ ከሆኑት ከቀሲስ እስጢፋኖስና ቅድስት አቅለሲያ ከተባለችው የተወለደችውን ንጽሂት የምትባል ሴት ታጭቶለት በስርዓተ ቤተክርስቲያን በስጋ ወደሙ አንድ አካል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጻድቁ ከመላዕክት ጋር ለመነጋገር አያቋርጥም ነበር፡፡ በቅ/ላሊበላ ዘመነ መንግስት አልገዛም ብሎ ሲያምጽ የነበረ አንድ ከሀዲ ፀረ ቅሞስ የሚባል ሽፍታ ነበር፡፡ ይህ ሽፋታ ምታተኛ የሆነ ኑሮውን በጎጃም ክ/ሀገር ያደረገ አሻፈረኝ ባይ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ታላቅ ፃድቅ የፈጣሪውን ስም እየጠራ ኃይለኛ ባዩ በግጥሚያ ላይ እያሉ የፀረ ቅምስ ልጅ አባቱን ለመርዳት ጦሩን ወደነአኩቶለአብ ቢወረውረው ከቅዱሱ ጎን የማይለየው መላአ አለና ጦሩ ተመልሶ ልጁን ወግቶት ሞቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ፃድቁ ፀረ ቅምስን ማርኮ ወደ ቅ/ላሊበላ አምቶታል፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ለምን ለኔ አልገዛም አልክ ብሎ ቢጠይቀው እኔ አልገዘም አልገብርም አልልም አሁንም ቢሆን ለወደፊት እኔ ቀርቶ እኔን መሰሎችን እንዲገብሩ አደርጋለሁ ብሎ በቄስ መካከል ምሎ ወደሀገሩ ሲመለስ ፊትን ሳይሆን ልብን የሚያይ እግዚአብሄር ከልቡ እንዳላደለ  አውቆታልና በአመፅ ላይ እንዳለ እግሩን እሾህ ወግቶት ሞቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ ቅዱስ ነአኩቶለአብን መንግስቱ መንግስቱን እንደሚቀበለው ያውቃልና አሁን ህንፃው ካለበት አካባቢ ቦታ ከፍሎ እንዲገዛ አድርጎታል፡፡ በዚህ ወቅት ስለግዛት ምንነት ከህዝቡ ጋር የሚግባባበትን ችሎታውን እያደበረ እንዳለ የቅዱስ ላሊበላ የንግስና ዘመኑ 40 ዓመት ስለሞላ ከእንግዲህ እኔ በቃኝ ተራውና ወቅቱ ያንተ ነው፡፡ ስልጣንህን ተረከብ ፈጣሪ ፈቅዶልኃል ሰውን እንዳትበድል፡፡ ፍቅርን ገንዘብ አድርግ ትህትና የተሞላበት ፍርድን ፍረድ የማታዳላ ሁን ከዛሬ ጀምሮ ፈጣሪ ካንተ ጋር ይሁን ብሎ መርቆ ከመንበረ ክብሩ አስቀመጠው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ነአክቶለአብ አምላክን እያመሰገነ አርብ አርብ ጦር ተክሎ ከጦር ላይ እየሠገደና እየወደቀ እየተነሣ በጾም በፀሎት በቀኖና ተወስኖ ይኖር ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ ተአምራትን እየሠራ ለህሙማን ፈውሰን ለደካሞች ብርታትን ለኃጢያተኞች ምህረትን ያካፍል ነበር፡፡ ይህ ፃድቅ ከባለቤቱ ከንግሥት ንፅሂት በሃይለ መስቀል የሚባል ልጅ ወልዶ ነበር፡፡ ይህም ህፃን ውበቱ ደምግባቱ ያማረ ነበርና ልጄ አድጎ ኃጢያት ከሚሰራ አምላክ ሆይ እባክህ ወደአንተ ውሰድልኝ ብሎ ልመናውን ወደፈጣሪው አቀረበ፡፡ ፈጣሪውም በተወለደ በ3 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለይ አድርጓል፡፡
ይህን ዘመን የቅዱሳኑ ምልጃ ያስታግስልን ቅዱስ ነአኩቶለአብ በዘመነ መንግስቱ ትህትና በተመላበት ፍርድ ሰውን እያስተዳደር ሌሊት ደግሞ የአምላኩን ስቅለትና መከራ እያሰበ ይሰግዳል፡፡ ጾሙንም እየዋለ መራራ ነገር የተቀላቀለበት ውሃ ውስን ምግብ ይወስድ ነበር፡፡
የቅዱስ ናኩቶለአብ ቤተክርስቲያን  የሚያገኘው ወደ ቅ/ላሊበላ አካባቢ ለመግባት ቢያንስ 7 ኪ.ሜ ሲቀረው ወደቀኝ በመታጠፍ በእግር ጉዞ 300 ያህል ሜትር ከተጓዙ በኋላ ነው፡፡ ቀና ብለው ሲመለከቱ  ከቤተክርስቲያኑ በላይ ዘመናትን ባስቆጠሩ ወይራዎች ተሸፍኖ አካባቢው ይታየዎታል፡፡ ከዚህ በኋላ ቀጥታ ወደቤተክርስቲያኑ መግባት ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ በር እንዳሉ ቀኝዎን አሻግረው ሲመለከቱ  ንፅሂት የምትባ ፀበል ይታያል፡፡ ከዚህ በኋላ ጫማዎን አውልቀው ሲገቡ ወደ ግራ የሚያዩት ማህሌቱ ነው ወደቀኝ በመሄድ ወደቅድስቱ ይግቡ፡፡ ከቅድስቱ ፊት ለፊት ባለው በር ሲገቡ ፀበሉን ያገኛሉ፡፡ ከጸበሉ ሲገቡ እፅብ ድንቅ ተአምሩን በማየት ይደነቃሉ ከአምላክ የተሰጠው ፈውስን የሚያሰገኘው የፀጋ ፀበል ክረምት ቢበዛ የማይጨምር ቢቀንስ የማያንስ አመቱን በሙሉ እንደእምባ በመንጠባጠብ የነጠብጣቡ መቀበያ ጎድጓዳ ሳህን የመሰሉ ድንጋዮች ያገኛሉ፡፡ እነዚህም ድንጋዮች ሲመለከቷቸው ከ 5 ሊትር በላይ የሚይዙ አይመስሉም፡፡  ነገር ግን ቃል ኪዳን ስላላቸው የሄደውን ህብረተሰብ ሲያስተናግዱ ይታያሉ ፀበሉ ከድንጋዮቹ ቢሞላ እንደ ጉም እየተቆለለ ሲቀዱት መጎደል እንጅ ወደጎን አይፈስም፡፡  ታዲያ የዚህ ተአምር ምን ይሆን፡፡ ከማህሌቱ ስማጎንደሬ የሚባል ትልቅ ከበሮ ይገኛል፡፡ የፃድቁ መስቀል ታላላቅ የብራና መፃህፍትና አልባሳት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቤተክርስቲያን ጀምሮ እስከ አሸተን ውስጥ ለውስጥ የሚየስኬድ መንገድ አለ፡፡
በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥም የድንጋይ ደውል የሚገኝ ሲሆን ጩኅቱም ዘመናዊውን ደወል ያስንቃል የእግዚአብሄር ደንቅ ስራው ብዙ ነው ድንጋዩ አፍ አውጥቶ ምእመናንን እንዲጣራ አድርጎታል፡፡ በጠቅላላው  ይህ ቦታ ብዙ ታላላቅ ተአምራት የሚታይበት መሆኑን ተገንዝበናል እርሶም ህደው ይመልከቱት:: ከብዙ በጥቂቱ የቅዱስ ናአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያን በቦታው ተገኝቼ ባሁት እና ከአነበብኩት የወሰድኩት ነው የቅዱሱ በረከት አይለየን አሜን፡፡

4 comments:

  1. Please can you write about KEFALE-BAHIR ABUNE EWOSTATEWOS?

    ReplyDelete
    Replies
    1. መስከረም ፲፰ ዕለት አዕረፈ ጻድቅ (ቅዱስ) ኤውስጣቴዎስ) (1215-1313)
      †♥†”ከቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር /“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”†♥† መዝ.፻፲፭/፻፲፮፡፲፭/ መዝ.115/116፡15
      “ቅዱሳን በመለኮታዊ ማዕጠንት የተቀጣጠሉ ዕጣን ሲሆኑ የተቀጣጠሉበትም በፈጣሪያቸው ፍቅር ነው።” (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
      አባታቸው ክርስቶስ ሞአ እናታቸውስነ ሕይወት ይባላሉ። በብስራተ መልአክ ወልደዋቸዋል። ዘካርያስ ለሚባል መምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ ሲያገለግሉ አደጉ። ኋላም መዓርገ ምንኩስናን ተቀብለው በትኅርምት የሚኖሩ ሆነዋል። አንድ ቀን የነግህ ተግባራቸውን አድርሰው ከመካነ ግብራቸው ተቀምጠው ሳሉ ጌታ እንዲረዳቸው ሆኖ ተገልጾ ለኢትዮጵያና ለአርመንያ ሐዋርያ እንድትሆን መርጬሃለሁና ዙረህ አስተምር ”አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን ያልሰማ እኔንም አልሰማም” አላቸው። “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ማቴ.፲፡፵ (10፡40) እንዲል። መዓርገ ቅስና ተቀብለው ማስተማር ጀመሩ።
      አንድ ቀን ቅዱሳት መካናትን እጅ ለመንሳት ስድስቱን ቀን እየተጓዙ ሰንበትን እያረፉ ኢየሩሳሌም ደርሰው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ወደ አርመንያ ሲሄዱ ባሕረ ኢያርኮ ደረሱ። መርከበኛ አግኝተው እንዲያሳፍራቸው ጠይቀውት ትቷቸው ሄደ። የለበሱትን አጽፍ ከባሕሩ ላይ አንጥፈው ልጆቼ ጥበበ እግዚአብሔርን እመረምራለሁ ሳትሉ ተሳፈሩ አሉ። ተሳፍረው ሲሄዱ ተጠራጥሮ የነበረ አንድ ደቀ መዝሙር የመርፌ ቀዳዳ በምታህል ቀዳዳ ሾልኮ ሰጥሟል። እርሳቸው ግን ከነደቀመዛሙርቶቻቸው ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በግራ በቀኝ ሆነው እየቀዘፉ አሻግሯቸዋል። ኋላ ግን ያን ደቀመዝሙር ጸልየው አድነውታል። “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። ማቴ.፲፬፡ ፴፩-፴፪ (14፡31-32)
      “ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” ማቴ.፲፯፡፳ (17፡20)
      ”……ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።” ዮሐ.፳፡፳፯ (20፡27) እንዲል ጌታ በወንጌል።
      ከዚያም ደርሰው አሕዛብን አስተምረው ከቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ “ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት” እንዲሉ ምንም ሙት ቢያስነሱ ተዓምራት ቢያደርጉ ሥጋ ከለበሱ ዘንድ ሞት አይቀርምና በዚህ ዕለት አርፈዋል። መቃብራቸውም በገዳመ “መርምህናም” ነው። የአባታችን በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን::
      †♥† “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ…” (የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል::)†♥†
      መዝ. ፻፲፩፡፮ (111፡6)

      Delete
  2. እግዚአብሔር ይስጥልን።
    ቃለ ህይወት ያሰማልን።
    መካሪ ዘካሪ አያሳጣን።

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን አባቶችን ከቦታው አያጥፋብን

    ReplyDelete