ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, September 20, 2012

ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል ሁለት



1500 ዓመት የቅዱስ ያሬድን በዓል ምክነያት በማድረግ በክፍል አንድ ስለ ቅዱስ ያሬድ "ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል አንድ" በሚል ርእስ አስነብበናችኋል፡፡ ዛሬ ደግሞ በክፍል ሁለት የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት በሚል ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ እንድትሆን ያደረጋት የልጆቿ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነትን የተመላው ባህሏ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የሥነ ዜማ ሀገር መሆኗም መጻሕፍተ ታሪክን ባነበቡ ሊቃውንት አንደበት ብቻ ሳይሆን በማዳመጥ  ትውፊት /ርክክብ/ ለኅብረተሰቡ ኀቡእ ያልሆነ ነገር መሆኑ ነው ፡፡
  ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ.74:14 ለኢትዮጵያ ከተሰጡት ታላላቅ ሀብቶች መካከል አንድ በልዩ ስጦታ ከሰማያት ከመላእክት በቀር የትም የማይገኝ እና የተም የሌለ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት ነው፡፡  የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት ግዕዝ ዕዝልና አራራይ በሚባሉ ሦስት የዜማ መደቦች ይመደባሉ፡፡ የሦስቱ መደቦች የዜማ ድምፃቸው አንድ ሲሆን አንድ መሆናቸው የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ነው ፡፡ የዜማ ስልቶች
  •        ግዕዝ- ግዕዝ ማለት ገአዘ ነፃ ወጣ ማለት ሲሆን በዜማነቱ ሲተረጎም የመጀመሪያ አንደኛ ስልት የቀና ማለት ይሆናል ዜማው ፀባይ ደረቅ ያለና ብዙ እርክርክታ የሌለው ለጉሮሮ ጠንካራ ኃይለኛ በመሆኑ ሊቃውንቱ ደረቅ ዜማ ይሉታል                  
  •    ዕዝል፡- የግዕዝ ድርብና ታዛይ ነው ምሳሌነቱ የወልድ ሲሆን ትርጓሜው ፅኑ ማለት ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ጽንዑ የሆነ መከራን ተቀብሎ እኛን የአዳም ልጆች ማዳኑን ያስረዳናል፡፡ አንድም የመለኮትና የትስብእት ተዋህዶ ረቀቅ ስለሚል  ቀስ በቀስ ሊማሩት እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡
  •       አራራይ- የሚያራራ፣ ጥዑም ልብን የሚመስጥ ማለት ነው፡፡ የዜማው ስልት ልብን የሚያራራ በመሆኑ ስያሜውን አግኝቷል፡፡ ሐዋርያትን ከበዓለ ጴንጤቆስጤ በኋላ ያረጋጋ ያጽናና እና ጥበዓተ ድፍረት ሰጥቶ  ዓለምን እንዲያጣፍጡ ስላደረገ  አራራይ ዜማ   በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል፡፡      
    በቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ምስጋና በሙሉ በሦስቱ የዜማ  ዓይነቶች ነው ፡፡ ማንኛውም ሰው በቤተ ክርስቲያናችን መዝሙር የሚያቀርበው  የቅዱስ ያሬድን የዜማ ምልክቶችና ዓይነቶች /ስልቶች/ ተከትሎ ነው ፡፡ ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች እራሳቸውን ችለው የሚዜሙ ቢሆኑም አንዱ የዜማ ዓይነት በሌላው የዜማ ዓይነት ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ወቅ አለበት ፡፡ ለምሳሌ ያህል ግዕዝ ከሚባለው ዜማ ዓይነት ዕዝልና የአራራይ ዜማ ይወጣሉ ፡፡ ይህም በአሐዱ አብ ዜማ ይታወቃል፡፡ ምሥጢሩ ከአብ እምቅድም ዓለም ወልድ ለመወለዱ ከመንፈስ ቅዱስ ለመስረፁ ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም ጋር የንባቡና የድምጹ ቃና አንድ መሆን የሥላሴን አንድነት ሲያስረዳ  የዜማው ሦስት ዓይነት መሆን የሦስትነታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አንዱ ሌላውን ይተካል ማለት ሳይሆን አንዱ የዜማ ዓይነት በሌላው የዜማ ዓይነት ውስጥ በተወሰነ መጠን ተመሳስሎ ይገኛል ለማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ የቅዳሴ ጸሎት በሦስቱ የዜማ ዓይነቶች የተቀመረ ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡
  ቅዱስ ያሬድ በግዕዝ፣ በዕዝል በአራራይ ዜማውን እያስማማ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን ያመሰገነው 22 አርእስተ ዜማ እያቀናበረ ነው ይኸውም 22 ስነ ፍጥረት ምሳሌ ነው፡፡ የስነፍጥረት ምሳሌ የሆኑት 22 አርእስተ ዜማ የሚከተሉት ናቸው::
1.    ዋዜማ                                        2.   በሐምስት
3.   እግዚአብሔር ነግሠ                    4.   ይትባረክ
5.   ሠለስት                                       6.   ሰላም
7.   መዝሙር /መሐትው አቡን/       8.   ዘአምላኪየ
9.   ሚበዝኁ                                    10.  አርባዕት
11.     ብጹዕ ዘይሌቡ                          12.       መወድስ
13.       ኩልክሙ                                 14.         ዕዝል
15.       ዘይእዜ                                   16.      እሰመ ለዓለም
17.       እሰመ ለዓለም                       18.      አርያም
19.      ክብር ይእቲ                            20.       ስብሐተ ነግሕ
21.       ዝማሬ                                   22.       ዕጣነ ሞገር

   ይቆየን…….ይቀጥላል ከአንድ ቀን ብኋላ ቀጣዩን ክፍል እናቀርባለን
++++++የቅዱስ ያሬድ በረከት ረድኤት አይለየን፡፡ አሜን::+++++++++++

No comments:

Post a Comment