ደቂቀ ናቡቴ

Tuesday, September 25, 2012

" ካልጠፋ ገላ ዓይን ጥንቆላ "

(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 15/2005) “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።”ያዕ.5:16 በዋልደባ ገዳም መንግስት በጀመረው የስኳር ፋብሪካ ብዙ በጣም ብዙ በደሎች በመነኮሳቱ ደርሷል እየደረሰም ነው፡፡ እስከአሁንም ችግሩ እልባት ሳያገኝ በመነኮሳቱ ላይ ደብደባ እንግልት እና ከገዳሙ እንዲሰደዱ እየተደረገ ነው ፡፡ 
መነኮሳቱ ግን መፍትሄው እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ እንባቸው ወደ አምላክ እየረጩ አምላክን ከመማፀን አልቦዘኑም፡፡ እንባን የሚያብስ አምላክ ግን ሁሉን ነገር በጊዜው ያደርጋል እያደረገም ነው የሚማር እና ከጥፋቱ የሚመለስ የለም እንጂ፡፡ ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያደረሱን “ፍቅር ይሄይስ ” የተሰኙ ፀሐፊ ሲሆኑ እኛም ጽሁፉ የያዘውን ቁመ ነገር ለእናነተም ልናካፍላችሁ ወደድን ፀሀፊውን አምላክ በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን፡፡ መልካም ንባብ፡፡ አምላካችን ሃገራችንን ይጠብቅልን፡፡  ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።                     
  " ካልጠፋ ገላ ዓይን ጥንቆላ "
  የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እርስ በርሱ፣ በሀሳብና በድርጊቱ መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ለዚህም የአዳምን ልጆች የአቤልንና የቃዬልን ህይወት ማንሳት የሰው ልጅ በተፈጠረ ማግስት አለመግባባትና የጥቅም እንደራሴነት አንደተጀመረ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በዘመናችን ከጉንጭ አልፋ ክርክርና ንትርክ አስከ ከፋ ግጭትና ሞት የሚያበቁ አለመግባባቶች የሚከሰቱት አንድም በስልጣን ወይም በጥቅም ይገባኛል የተነሳ ነው፡፡በነዚህ የግጭት ሰበቦች የተነሳ አለማችን ብዙ ሚለዮን ሰወችንና ብዙ ሀብትን አላግባብ አጣለች፡፡ ምናልባት የሰው ልጅ የአስተሳስብ አድማሱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ግን ልዩነቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ሂደቱ እየጨመረ መምጣቱ ለመጭዋ ዓለም አበረታች ተስፋ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሶስት ነገሮች ጋር ሊጣላ ይችላል፡፡
  • 1.    ከሰው ልጅ ጋር
    2.   ከተፈጥሮ (ከእንስሳት፣ከእፅዋትና ከአየር ንብረት) ጋር እና
    3.   ከፈጣሪ ጋር

የመጀመሪያወቹ የጠብ አይነቶች  በመነጋገርና የማሸሻያ አርምጃ በመውሰድ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፤ምንም አንኳ የፈጣሪ ኃይል አብሮ ቢኖርበትም፡፡ሶስተኛው ጠብ ውስጥ ግን የሰው ልጅ ከገባ በምንም አይነት ሁኔታ ድርድር ውስጥ መግባት አይችልም፡፡ ያለው አማራጭ የታዘዘውን ተቀብሎ መኖር ብቻ ነው፡፡ ከትዕዛዙ ከወጣ እንኳ ቶሎ ብሎ ከስህተቱ መታረምና ለአጠፋው ጥፋት በንስሃ መመለስ አለበት፡፡ካልሆነ ግን ለአጠፋው ጥፋት የሚሰጠውን ቅጣት መቀበል ግድ ይለዋል፡፡ሀብት ፣ስልጣንና ወታደር የመሳሰሉት ተራ ነገሮች ከፈጣሪ ቅጣት ሊታደጉት አይችሉም፡፡ቢሞክረውም እንደ ሰናዎር ሰዎች ተንኮታኩቶ ከመውደቅ አያድነውም፡፡በርግጥ አሁን ዓለም ሀልወተ ፈጣሪን እየካደ የመጣበት ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቅጣቱ አይነትም እየበረከተ መጥቷል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ  አንዲሁም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ እግዚአብሔርን የምታመልክ ብቸኛ አገር አንደሆነች ታሪክ አይኑን አፍጥጦ የሚመሰክርላት አገር ናት፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንኳ ለስደቱ መሸሻ፣ ለቅዱሳን መጠጊያ፣ለስሙ መጠሪያ አድርጎ የባረካት ሃገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች የድንግል ማርያም የአስራት አገር ኢትዮጵያ፤ ለዘመናት ብዙ መከራና ስቃይ አሳልፋለች፡፡ እያሳለፈችም ነው፡፡ ወደፊትም ብዙ ፈተና ይጠብቃታል፡፡
ውድ ወገኖቼ አሁን "የባሰ አታምጣ" ብለን ባንዘምርም "የባሰ አታምጣ" ብለን የምንፀልይበትና ከስህተቶቻችን የምንማርበት ጊዜ ነው፡፡ አንድ አባባል አለ "ጥዋት ያደናቀፈህ ድንጋይ ከሰዓት ከደገመህ አሁን ድንጋዩ አንተ ነህ"፡፡ በእርግጥ የሰው ልጅ ሰው ነውና ይሳሳታል፡፡ነገር ግን ከስህተቱና ከሁኔታዎች ደግሞ መማር አለበት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአገራችን ብሎም በአጉራችን በዚህ ክፍለ ዘመን ታላቅ ራዕይ የነበራቸው ፣ታታሪና ትጉህ ሰው ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአብያተ አምነቶች ጋር እፈጠሩ የነበሩት ጣልቃ ገብነት በህዝብ ዘንድ በተለይም በገዳም መነኰሳትና መናንያን ዘንድ ታላቅ ተቃውሞ እያስነሳባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ ሟችን ለመውቀስ አይደለም፡፡እሳቸው አለሙም አጠፉም አልፈዋል፣እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር፤አፈሩን ያቅልልላቸው፡፡ ኣላማዬ ግን እኛም ወደ አሳቸው ከመሄዳችን በፊት ካለፈው ስህተታችን ምን መማር እንዳለብን ለማስገንዘብ ነዉ፡፡ በአርግጥ ይህ ስህተት እንደ ግለሰብ ከታየ የመለስ ብቻ አይደለም-አገሪቱን እየመራ ያለው የኢሕአዲግ ፓርቲ አንጂ፡፡ አውነቱን ለመናገር ይህች ሀገር አድጋ ፣በልፅጋ፣ ለምልማና ከልመና ተላቃ ማየት አይደለም ደሙ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሁሉ ቀርቶ በጥላቻ ዓይን ለሚያዩን ለምዕራባውያኑም ቢሆን ታላቅ የምስራች ነው-አንዳንዴ ከሚበትኑልን ስንዴ ያርፋሉና፡፡
ስለዚህ የኢህአዲግ ፓርቲ እንደ ሀገር መሪነቱ የልማት ስራዎችን ከመጀመሩ በፊት ከህዝቡ ጋር በቂ የሆነ ውይይት ማድረግ አለበት፡፡መቼም ብዙዎቻችን ሀገር በፋብሪካ ሀብታም ልትሆን ትችላለች አንጂ በፋብሪካ ብቻ ታድጋለች የሚል እምነት ያለን አይመስለኝም፡፡ ሀገር የምታድገው የማህበረሰቡን ባህል፣ታሪክ፣ ስርዓትና መስተጋብር ጠብቃ ዘመናዊነትን ከራሷ አገራዊ እሴቶች ጋር ሳይጋጩ መቀበል ስትችል ነው፡፡ ለምሳሌ ፡- የላሊበላን ግንብ ወይም የፋሲልን ግንብ አፍርሰን ፋብሪካ እንገንባ ብለን ብናስብ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ፋሲልና ላሊበላ ግንብ ማንነት፣ አሰራር፣ለሀገሪቱ ያለውን ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ለወደፊት የሚኖረውን ጥቅም ፣ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ መስተጋብር፣ብናፈርሰው ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ገፅታ፤አንዲሁም ፋብሪካውን በመስራታችን ሊያመጣ የሚችለውን ሀገራዊ ጥቅም ተጨባጭ  በሆነና ህዝብን ባሳመነ መልኩ ማቅረብ አለብን፡፡ይህ ሳይሆን ግን በስሜት እና በማን አለብኝነት ተነሳስቶ ታሪክን ገልብጨ የራሴን ታሪክ አስቀምጣለሁ ማለት ለሁላችንም አይበጅም-ፍፃሜው አጥፊና ጠፊ ከመሆን በቀር፡፡
በዚህ ሰዓት በጣም አወዛጋቢ የሆነውና እየሆነው ላለው ነገር ሁሉ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ያለው የዋልድባ ገዳም ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ምናልባት ዋልድባን ከፋሲል ማወዳደሩ ለብዙ ሰው ላይዋጥ ይችላል፡፡ቢሆንም አይገርመኝም፤ ከቱባ ባለስልጣን  እሰከ ተራው ሰው ስለ ዋልድባ ገዳም ታሪክና ማንነት ያለን ግንዛቤ በጣም አናሳ ነውና፡፡ከወሬ በቀር(ከኢቲቪ) ቦታውን እንኳን በአካል ሂዶ ያየው በጣም ትንሽ ሰው ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የህዝቡን አቤቱታ ለማዳመጥና ሁኔታዎችን ለመመርመር አንኳን ጊዜ አልነበረንም -የምናስተዳድረው ህዝቡን ሁኖ ሳለ፡፡
ምን አልባት ይህ ሁሉ ነገር የመጣው ምን ያመጣሉ ከሚል አስተሳሰብ ከሆነ በጣም ተሳስተናል፡፡ አንድ ነገር እናንሳ አንድ በርጌድ ያማይሞላ የኢህአዲግ ሰራዊት በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረውን የደርግን ሰራዊት ያሸነፈው በብቃት ወይም በምታት አይደለም፡፡ ነው ብሎ የሚያምን ካለም ሞኝ ነው፡፡ይህ ማለት ታጋዮች አልታገሉም ማለት አይደልም፡፡ ውጤቱ የመጣው ግን በነሱ ትግል ብቻ አይደለም፡፡ እሺ እሂን አንተወውና በአድዋ ጦርነት ወቅት  ኢትዮጵያውያን በድንጋይና በጦር ተዋግተው በዘመናዊ መሳሪያ የገጠማቸውን ጣሊያንን ዱቄት ያደረጉት በብቃታቸው ብቻ ነው? እኔ በአንድ ነገር አምናለሁ፤ኢትዮጵያውያን ጦር ከሚወረውሩና ጥይት ከሚተኩሱ አንድ ዘለላ እንባ አፍሰው ስለ እውነት ፍረድ ብለው ወደ አምላካቸው ቢፀልዩ ታምር መስራት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ እናንተ አለማመን መብታችሁ ነው ያውም ዲሞክራሲያዊ፡፡በደርግ ዘመን በነበረው መራሔ መንግስትም የሆነው ይሄ ነው፡፡ህዝቡ እንባውን አነባ ፣ወደ አግዚአብሔርም ደረሰ፣አግዚአብሔርም የህዝቡን እንባ ተመለከተ፤በጦር ኃይሉ ይመካ የነበረውን አምባገነን ገዥ ዳግም በሀገሩ እንኳ እንዳይኖርባት አድርጎ የሙሴን ስልጣን በእምነት ለኢህአዲግ ሰጠ፡፡ኢህአዲግም በተራው ይህን አደራ ተቀብሎ ለሃያ አመታት ህዝብን እየመራ ህዝብም እየተመራ ከዚህ ደረስን፡፡አሁን ግን አካሄዱ በእኔ አማርኛ "ካልጠፋ ገላ ዐይን ጥንቆላ"እየሆነ መጣ፤ተው ተመለስ ተሳስተሃል ቢባል እንኳን ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡በጣም የሚገርመው ነገር ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ሌት ከቀን የሚፀልዩ መናንያን ጥለዋት ወደ ሄዱዋት ዓለም ተመልሰው አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ከቤተመንግስቱ እስከቤተክህነቱ ድረስ ቁጭ አድርጎ አንኳን ያናገራቸው አካል አልነበረም፤በወከባና በማስፈራሪያ ከማንገላታት በቀር፡፡አነሆ የምዕመናን እንባ ፈሰሰ ፤ከእግዚአብሔር ዘንድም ደረሰ፣ እግዚአብሔርም ከመንገዱ ወጣችኋል ብሎ በአንድ ሳምንት ያውም በሱባኤ ወቅት ሁለት ታላላቅ መሪዎችን አጣን፡፡በተለይ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን በዚህ ሰዓት ማጣት ያልነበረብን እንኳን እኛ አፍሪካውያንም ጭምር ከልብ ያዘኑበት ክስተት ሁኖ አልፏል፡፡ግን ምን ዋጋ አለው"ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ"ትል ነበር አያቴ፡፡አሁን እንባ ቀርቶ ደም ብናለቅስ ያለፈውን መመለስ አንችልም-የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በፀጋ  ከመቀበል ውጭ፡፡
እኔን የገረመኝ ነገር ግን አሁንም ከሁኔታዎች አለመማራችንና አለማመናችን ነው፡፡በእርግጥ አለማመን ይቻላል እውነታውን ግን በፍፁም መካድ አይቻልም፡፡ይህች አገር ለዘመናት ብዙ ታሪክና ታምራት የተሰራባት ልዩ አገር ናትና፡፡ቢያንስ ባናምን እንኳ ይህ ነገር ለሞታቸው ምክንያት እኮ ሊሆን ይችላል ብለን ማሰብ በተገባን ነበር፡፡ይባስ ብሎ የዋልድባ መነኰሳትን በፊት መሪ አሳመማችሁ፤ አሁን ደግሞ ሁለት መሪ ገደላችሁ በማለት  ለእስራት፣ ለድብደባና ለስደት ዳረግናቸው፡፡በእርግጥ ለእነሱ መልካም እያደረግንላቸው ነው፡፡ "ስለ እኔ መከራን ትቀበላላችሁ፣ያስሯችኋል፣ይገድሏችኋል" የሚለውን ቃል አምነው ተቀብለው የዚህን ዓለም ጣዕም፣ ደስታና ክብር ጥለው አንድ ጊዜ በረሃ ገብተዋልና፡፡
በአንድ ወቅት በገዳሙ ያገኘኋቸው በምህንድስና ትምህርት ተመርቀው  ለ 17 አመታት በዋልድባ ገዳም የቆዩ አባት አንደዋዛ ይነግሩኝ የነበሩ ነገሮችን በማስተዋል ሳያቸው ሁሉም እየሆኑ ነው፡፡ ምናልባት ትልቁ ችግር የሚመስለኝ እነሱን ኋላቀር አነደሆኑ፣ልማት የማይዋጥላቸው፣ስልጣኔ ከነትርጉሙ የማይገባቸው አድርገን ማሰባችን ይመስለኛል፡፡አውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡የምነናውን ቆብ ከመጫናቸው በፊት አለማዊውን ቆብ እኛ በምንመካባቸው ዩኒቨርስቲዎች የጫኑ መናንያን ቁጥር ቀላል አይደለም-እንደኛ በዚህ ዲግሪ ፣በዚህ ዶክትሬት አለኝ ብለው ስለማያወሩ እንጂ፡፡ ስለዚህ ችግሩ እነሱን በእኛ አስተሳስብ ብቻ መመዘናችን ነው፡፡በመሰረቱ ቤተክርስቲያንም ልማትን አትነቅፍም ታሪክ ማጥፋትን ግን አትደግፍም፡፡ታዲያ እነሱንና እኛን አላግባባን ያለ አውነታ ምንድን ነው? አውነታውማ እነሱ የሚያውቁት እኛ የማናውቀው (አውቀንም ችላ ያልነው)ሌላ የህይወት፣የታሪክና የሀገር ፍቅር ምስጢር ነው፡፡ ይህ ነው  ወደ በረሃ ስቦ የወሰዳቸው፡፡አኛ ግን ለመስማትም ፈቃደኛ አይደለንም፡፡
እኔ የምለው እንዲህ ችግር እንደሚያመጡብን ካወቅን ቀድመው ቤታችን ድረስ መጥተው ሲያናግሩን ለምን በአግባቡ መልስ አልሰጠናቸውም-ከሰውነት በታች አዋርደንና ሰድበን ከመስደድ ይልቅ፡፡በእርግጥ መነኰሳቱ ለዓለም ሰላምን ለመለመን እንጂ የማንንም ጥፋት ለማየት ወደ በረሃ አልወጡም፡፡ፅዋው የተሰጠን ግን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ፈርኦን ልቡ ደንድኖ እስራኤላውያንን ልቀቅ ቢባል እምቢ አለ፣ታምራት እግዚአብሔር ቢያሳያውም አላምን አለ፤በኋላ የደረሰበትን ሁላችንም እናውቃለን፡፡በእኛ ሀገርም በዚህ አመት የሆነው ይሄ ነው፡፡ለዘመናት የእግራቸውን ትቢያ ከመላስ በቀር አንኳን መነኰሳቱን ጎብኝዎችን እንኳ ተተናኩለው የማያውቁ በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩ አውሬዎች የመከላከያ አባላትንና ሰራተኞችን ሲበሉ ፣ሌሎች ታምራትም ሲፈፀሙ፣ህዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲጮህ መንግስትም ሆነ ቤተ ከህነት ለመስማትም ቆም ብለው ለማሰብም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ማን ነበር "ለጥፋት የታዘዘች ከተማ ነጋሪት ቢጎሰም አትሰማም"ያለ፡፡
አሁንም የመሸ ቢመስለም አልጨለመም፡፡ቢያንስ ስለዚህ ጨዋ፣የዋህ፣ሩህሩህና ሆደ ባሻ የኢትዮጵያ ህዝብ ብላችሁ አንኳ ቆም ብላችሁ ነገሮቸን መርምሩ፡፡መደባበቁ፣መተቻቸቱ፣መለያየቱና መናቆሩ ለእኛ አይጠቅመንም፡፡ህዝቡ የወደደውንና የመረጠውን አብረን እንስራ፣አብረን እንብላ፣አብረን እንሙት፣አብረን አናልቅስ ያን ጊዜ ያምርብናል-ልክ እነደ ሰሞኑ፡፡ማንም ኢትዮጵያዊ የልማት ፀር አይደለም፤ ነገር ግን ባህሉ፣እምነቱ ፣የአባቶቹ ርስትና ታሪካዊ ቦታዎች ሲነኩበት ማንም ኢትዮጵያዊ አይወድም (ከእነንተና በቀር)፡፡ ዓለም ያልደረሰበት፣ተመራምረው የማያገኙት በእምነት የምንቀበለው ከጥንት የወረስነው የኢትዮጵያ የሆነ ብቸኛ የታሪክና የእምነት ምስጢር አለና፡፡አሁንም አደግመዋለሁ አለማመን ይቻላል ፤አውነታውን ግን መካድ አይቻልም፡፡
የሀገር እድገት የሚመጣው የሀገርን ማንነት ጠንቅቆ በማወቅና ከውስጥ በመነጨ የሀገር ፍቅር ተነስተን ጠንክረን ስንሰራ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ስለሃገርና ስለወገን ማሰብ እንጀምራለን፡፡ እናታቸውን እንዳጡ ልጆች፤ከዳሃ እስከ ሃብታም፣ከማይም እስከ ምሁር ፣"ከሰፈር ልጅ እስከ ወንዝ ማዶ ልጅ"፣ከላሜቦራ እስከ ዲያስፖራ፣ከጀሌ እስከ ቱባ ባለስልጣን ድረስ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ያለቀሰው በጠ/ሚኒስተር መለስ ሞት ብቻ አይደለም፡፡ለኢትዮጵያና ለባህሉ ካለው ክብር በመነጨ ውስጣዊ ስሜት ጭምር እንጂ፡፡ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ህዝቡ ያለቀሰው በመለስ ሞት አዝኖ እንጂ የኢህአዲግን ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ደግፎ አይደለም-አነዳንድ ሰዎች በመከረኛው ኢቲቪ የተሳሳተ ነገር ሲናገሩ ስለሰማሁ ነው፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም መለስ ዜናዊ፤ መንግስቱ ኃይለማርያምም ቢሆን አልቅሶ ይቀብረዋል፤ትሁት፣ይቅር ባይና ባህሉን አክባሪ ህዝብ ነውና፡፡
ይህ ክስተት "ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ አይቻለውም" የሚለውን መፅሃፍ ቅዱሳዊ ቃል በተግባር ያስመሰከረ፣ ኢትዮጵያውያን በቁርጥ ቀን የማይለያዩ የአንድ እናት ሀገር ልጆች መሆናቸውን በበቂ ሁኔታ ያሳየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዘርና በሃይማኖት ሰበብ ሊከፋፍሉን ለሚያስቡ የቁራ መልክተኞች አስደንጋጭ ክስትት ነው፡፡ እናም ወገን ሆይ መለያየትን ቀብረን ልክ እንደ ለቅሶው በአንድነት እንነሳ፣በልዩነታችን እንቻቻል፤ ለአንድ ኢትዮጵያ እጅ ለእጅ ተያይዘን በህብረት እንጓዝ፡፡ ትልቅ ተስፋ አለኝ መሪዎቻችን ከዚህ ክስተት መማር ብቻ ሳይሆን የተማሩትን በተግባር ፈፅመው ከጎናቸው ያለውን ህዝባቸውን እንደሚያስደስቱ፡፡ቤተክህነቱም እንደዚሁ፡፡
እናም ቆም ብለን እናስብ፣ያለፈውን እንመርምር፣የተሳሳተውን እናስተካክል፣የወደፊቱን በማስተዋል እናቅድ፡፡ጌታ በወንጌል እነደተናገረው "የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም" እንዳለው ኢትዮጵያውያንም የሚኖሩት"በስኳር ብቻ" አይደለም፤ ይልቁንስ በባህላቸው፣በእምነታቸው፣በታሪካቸው፣በፀሎታቸውና በፍቅራቸውም ጭምር ነውና በመነኰሳት ላይ እያደረስነው ያለነውን ግፍ በቃህ እንበለው፡፡ አሊያ ሁሉም ነገር ይቀጥላል-የህዝብ ሀዘንም የእግዚአብሔር ቁጣም፡፡ ለሁላችንም ለመጭው ዘመን እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን፡፡ይቆየን፡፡
   "ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር"
        ሁሉም ያልፋል ፍቅር ያሸንፋል !!!
         ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!! 
በፍቅር ይሄይስ (fikir.yiheyis@gmail.com)

6 comments:

  1. EPRDF wiha wist nekrachihu bitnegrut aysemam. Atilfu. Esu yemiyawqew quanqua andi ena andi bicha new. KLASHNKOP!!!

    ReplyDelete
  2. Bezih guday lay Yebetekirstian Abatoch ena mengist tekeraribew liweyayu yigebal.Minalibat zimitaw hizibun wedaltefelege akitacha endayimeraw esegalehu.Abatochim ke mengist gar teweyayitew le hizbu ewinetawin masawek yitebekibachewal!Beterefe hulunim yemiyawikew Amlakachin mefitihe yisetenal!!!

    ReplyDelete
  3. አሁንማ ሰሚ አጣን እኮ ምን ይሻል ይሆን? እኔ በበኩሌ ቦታው ላይ ሁላችንም ተንቀሳቅሰን አንድ አስገራሚ ነገር ብንፍጥር ሳይሻል አይቀርም? ብዬ አስባለሁ ፡፡ ግን ደግሞ የእኔ ጣልቃ መግባት ምንድነው? እላለሁ ምክነያቱም እግዚአብሔር በጊዜው ስራውን እየሰራ ይመስለኛል ኧረ እንዲያውም በዚህ ብቻ የሚቆምም አይመስለኝ የዛኔ እጃቸውን ያነሱ ይሆናል፡ ማን ያውቃል አምላክ እየቀጣም ያስተምራል አህዛብ የሚማሩ ከሆነ፡ከሆነ፡፡

    ReplyDelete
  4. MENE WEYANEA YEGEBAWALE BELACHEHU NEWE ENDE FEREONE BEZU WEYANEA MOTO MAYETE YEFELEGALE

    ReplyDelete
  5. EGZIABIHER YITEBIKACEW! ABATOCIYACININ YIDEGIFILIN.
    LELA MINIM MADREG ANICILIM. HAYIALU GETACIN ENATU EMEBIRHAN TILA KELELA HONEW KEKIFU HULU KALGAREDUN MADREG YEMINICILEW MINIM YELEM.
    BETHAM BETHAM YASAZINAL.
    Sara

    ReplyDelete
  6. ኢትዮጵያ የድንግል ማሪያም የአስራት ሀገር መሆኗን በምን ማስረጃ ማረጋገጥ እንችላለን ?
    ስለዚህ ጉዳይ የምታውቁ ሰዎች እባካችሁን ብታስረዱኝ/ብትገልጹልኝ/
    አመሰግናለሁ

    ReplyDelete