ደቂቀ ናቡቴ

Friday, September 14, 2012

መስቀልና እመቤታችን

በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ 
  • መግቢያ 
በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለእያንዳንዱ የቤተሰብእ አባል የራሱ የሆነ ቦታ ወይም ደረጃ አለው፡፡ እናት ያላት ቦታ አለ፡፡ አባት ያለው ቦታ አለ፡፡ ልጆች ያላቸው ቦታ ደግሞ ይኖራል፡፡ የልጆች ቦታ እንኳን እንደ እድሜያቸውም ሆነ እንዳላቸው የትምህርት፣ የሥራና የሥነ ምግባር ሕይወት የተለያየ ነው፡፡ የታላቅ ልጅ ቦታ ከታናሽ ይለያል፡፡ይህ ዓይነቱ የመዋቅር ልዩነት በየትም ቦታ ይታያል፡፡ በወታደር ቤት ይህ ልዩነት አለ፡፡ በቢሮና በማናቸውም መድረክ ይህ ዓይነቱ ልዩነት የተጠበቀ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ሰው ውስጥም በአካል ብልቶች መካከል ይህ ልዩነት አለ፡፡ ልዩነቱ የኃላፊነት፣ የወሳኝነትና የአስፈላጊነት መጠንን ይገልጣል፡፡ ይህን ልዩነት ተከትሎ የሚመጣ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ይኸውም የክብር ልዩነት ነው፡፡
ንዋያተ ቅድሳትም ሁሉ ክብራቸው የተለያየ ነው፡፡ የሥዕል ክብር ከመስቀል፤ የመስቀል ከታቦት የታቦት ከመንበር፤ የመንበር ከአጎበር፤ የመጻሕፍት ከኩስኩስት፤ የጻሕል ከጽዋዕ ወዘተ የተለያየ ነው፡፡  
ወደ ቅዱሳን ምእመናን ስንመጣ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ምእመናን በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ሲኖሩ የራሳቸው የሆነ አሰላለፍ አላቸው፡፡ ይህም በዕድሜና በሌላ ሥጋዊ መመዘኛ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሚዛን ነው፡፡
ቅዱሳን አንዳቸው ከአንዳቸው በመንፈሳዊ ጸጋና ማዕርግ፣ በክብርም የተለያዩ ናቸው፡፡ ወንጌል እንደገለጠችው ባለ ሠላሳ ፍሬ አለ፤ ባለ ስልሣ ፍሬ አለ፤ ባለ መቶ ፍሬ ደግሞ አለ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ይህን የማዕርግ ልዩነት ሲያስረዳ ‹‹በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና፡፡›› ብሏል፡፡ (1ቆሮ15.41) አበው ‹‹ከጣት ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ፡፡ ስለ ክብርና ልዩነት ይህን ሁሉ ያተትነው መስቀልና እመቤታችን በክብር እኩል ናቸውን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መንደርደሪያ እንዲሆነን ነው፡፡

ከቀድሞ ጊዜ አንሥቶ ‹‹መስቀልና እመቤታችን እኩል ናቸው፡፡›› ብለው የሚያምኑና የሚሰብኩ ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ አሉም፡፡ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ክርክሮችም ተካሂደዋል፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ ክርክር አይጠፋ ይሆናል፡፡
በቂ ማስረጃ የሌላቸውና በስሕተት የተጠቀሱ ማስረጃዎችን ያነገቡ ቢሆኑም መስቀልና እመቤታችን እኩል ናቸው የሚሉ ጥቂት መጻሕፍትም ተጽፈዋል፡፡
መስቀልና እመቤታችን በክብር እኩል ናቸው አይደሉም ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከማስቀመጣችን በፊት እኩል ናቸው ብለው የሚናገሩ ሰዎች ‹‹ከምን ተነሥተው ነው?›› የሚለውን መመልከት ያሻል፡፡ 
  • በ‹‹መስተብቁዕ ዘመስቀል›› መጽሐፍ
ይህ መጽሐፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጽሐፍ ነው፡፡ ለበርካታ መቶ አመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተሐድሶ መናፍቃን ጠንካራ ትችትና ነቀፋ ቢደርስበትም አሁንም አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለቅዱስ መስቀል በተጓዳኝ አንሥቶ ይናገራል፡፡ ስለ መጽሐፉ ይዘት እና ታሪክ እናንተ በስፋት እንድትመረምሩ እየጋበዝኩ ከርእሳችን አንጻር ተጻፈውን መስመር በመስመር እያነሣን ትርጓሜው እንመልከት፡፡
መጽሐፉ ጉዳዩን የሚጀምረው ‹‹ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን›› በማለት ነው፡፡ ይህም ‹‹ለእነዚህ ሁለት ፍጥረታት›› ማለት ነው፡፡ ለድንግል ማርያምና ለመስቀል ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሲናገር የመጣው ስለእነርሱ ነውና፡፡
እነዚህ ሁለቱ ፍጡራን ድንግል ማርያምና ክቡር መስቀል በምን ምክንያት እንደሚመሰገኑ ካስረዳ በኋላ ‹‹እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ›› ይላል፡፡ ይህም ‹‹በክብር ተመሳስለዋልና›› ማለት ነው፡፡ ባላስተዋሉት ሰዎች ዘንድ ግን ትልቅ እንቅፋት በመፍጠር መስቀልና እመቤታችን በክብር እኩል ናቸው ለማለት ያደረሳቸውም ይህ ቃል ነው፡፡
ይኸውም በመስተብቁዕ ዘመስቀል ላይ የሚገኘው ‹‹እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ›› የሚለው የግዕዝ ዐረፍተ ነገር ወደ አማርኛ ‹‹በክብር ተመሳስለዋልና›› ተብሎ መተርጎም ሲኖርበት ወደ አማርኛ የመለሰው ክፍል ‹‹በክብር ተካክለዋልና›› ብሎ ስለተረጎመው አንባቢን የሚያሳስት ሊሆን ችሏል፡፡ ስለዚህ ዋናው ችግር የመጽሐፉ ሳይሆን ከግዕዝ ወደ አማርኛ የመለሰው ሰው ነው፡፡
በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ቃል ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግሥ ነው፡፡ ‹‹ዐረየ›› ሁለት ፍቺ አለው፡፡ አንደኛው ‹‹ተካከለ›› ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ተመሳሰለ›› የሚል ነው፡፡ ሁለቱም ፍቺዎች በአግባቡ መቀመጥ የሚኖርባቸው ቦታ ቦታ አለ፡፡ ይህንን ከዚህ በታች በምሳሌ እናያለን፡፡
1ኛ. በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ስለ ወልድ የተሰጠ የምስክርነት ቃል እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር ‹‹ዐረየ›› ከሚለው ቃል የተገኘውን ‹‹ዕሩይ›› የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፡፡ አገባቡ ግን ‹‹ተካከለ›› ተብሎ የሚተረጎም ነው፡፡ ስለዚህ በአማርኛው ስንጸልይ ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል›› እያልን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ‹‹የሚተካከል›› የሚለውን ‹‹የሚመሳሰል›› ብለን ብንተረጉመው ትልቅ ክህደት ይሆናል፡፡ ይህ ማስረጃ ‹‹ዐረየ›› የሚለው ቃል ተካከለ ተብሎ እንደሚተረጎም የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡
2ኛ. በውዳሴ ማርያም የዐርብ ምንባብ ውስጥ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያደረገውን ሲያዘክር ‹‹ወረሰየነ ዕሩያነ ምስሌሁ በብዝኀ ኂሩቱ›› ይላል፡፡ እንደላይኛው ሁሉ በዚህም ዐረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹ዐረየ›› ከሚለው ግሥ የተገኘው ‹‹ዕሩያነ›› የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ይሁን እንጂ አገባቡ ‹‹ተካከለ›› በሚለው መንገድ ሳይሆን ‹‹መሰለ›› በሚለው ነው፡፡ በአማርኛም በጸሎት ስንደግመው ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በቸርነቱ ብዛት መሳዮቹ አደረገን›› እያልን ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ‹‹መሳዮቹ›› የሚለውን ‹‹ተካካዮቹ›› ብለን ለመተርጎም እንደፍራለንን? በዚህ መልክ ብንተረጉመው እኛ ሁላችን ራሳችንን የአምላክ እኩዮች አደረግን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ክህደት ነው፡፡
ስለዚህ በሃይማኖት መጻሕፍት ውስጥ ‹‹ዐረየ›› የሚል ግሥ በዝርዝር ያለበት ዐረፍተ ነገር ሁሉ ቃሉ ሁለት ፍቺ ስላለው እንደ አገባቡ ታይቶ በየትኛው መንገድ መተርጎም እንደሚገባ መለየት ያስፈልጋል፡፡ በዘፈቀደ መተረጎም ወይም በአንደኛው ትርጉሙ ብቻ መጓዝ አስቀድሞ እንደተመለከትነው ዓይነት ከባድ የክህደት ዐዘቅት ውስጥ ይጥላል፡፡
በመስተብቁዕ ዘመስቀል ላይ የሚገኘው ዐረፍተ ነገርም ይህ ዓይነት የትርጉም ችግር የተፈጠረበት ነው፡፡ ችግሩ ወደ አማርኛ የመለሰው (የተረጎመው) ሰው እንጂ የኃይለ ቃሉ ወይም የደራሲው አይደለም፡፡ ደራሲው ምንም ፍጡር ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ብእሴ እግዚአብሔር ሰው ነውና፡፡
ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያምና መስቀል በክብር ‹‹ይመሳሰላሉ›› እንላለን እንጂ ‹‹ይተካከላሉ›› አንልም፡፡ መመሳሰል ደግሞ ከመተካክል ልዩ ስለሆነ መስቀልና ድንግል ማርያም ቢመሳሰሉም በክብር ግን አይተካከሉም፡፡ ድንግል ማርያም ከመስቀል በእጅጉ ትበልጣለች፡፡ ይህ መስቀልን መንቀፍና ማዋረድ ሳይሆን ማክበር ነው፡፡ ስለ መስቀል ሐሰት መናገር እንጂ ትክክለኛ ማዕርጉን መናገር መንቀፍ አይባልምና፡፡
ይህን ዐውቀን እኛ ክርስቲያኖች ከድንግል ማርያም ቀጥለን ለመስቀል እንሰግዳል፤ እናከብረውማለን፡፡ በቀኝ እጃችን ወይም በክብር እንይዘዋለን በአንገታችንም እናስረዋለን፡፡
  • ንጽጽር 
ድንግል ማርያም ከመስቀል እጅግ ትበልጣለች፡፡ በሁለቱ ማለትም በዕፀ መስቀልና በድንግል ማርያም የተደረገውን አምላካዊ ሥራ አኩል ነው ብለን ብንነሣ እንኳን በተፈጥሮ ሰው ከዕፅ እንደሚበልጥ ሁሉ ድንግል ማርያምም ከመስቀል ትበልጣለች፡፡ ድንግል ማርያም በተፈጥሮ ሰው በመሆኗ መስቀልን ከመብለጧም በላይ ምግባርና ትሩፋቷ ሲጨመርበት መስቀልን በክብር መብለጧ የላቀ ይሆናል፡፡
እኛ ክርስቲያኖች የፈጣሪን ሥራ ለማመን ችግር የለብንም፡፡ ምንም ሐተታ ባይሰጥና ንጽጽር ባይደረግ እንኳን ቅዱስ መስቀል ከድንግል ማርያም ጋር በክብር ትክክል መሆኑ የተጻፈበት የቅዱስ መጽሐፍ ማስረጃ በግልጽ ቢኖር የተባለውን ለማመን ተጨማሪ ምክንያት አንፈልግም ነበር፡፡ ፈጣሪ የወደደውን ማድረግ እንደሚችል እናምናለንና፡፡ እርሱ ዘወትር የማይሳሳት ትክክል ሲሆን ሥራው ሁሉ ለበጎ ነው፡፡ ነገር ግን ከተመሰከረላቸው መጻሕፍት መስቀልና እመቤታችን በክብር የተካከሉ መሆናቸውን የሚያስረዳ መረጃ አናገኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ የምናገኘው የድንግል ማርያምን የበላይነት ነው፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም ከመስቀል ትበልጣለች፡፡
ድንግል ማርያም ‹‹መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ›› ናት፡፡ ይህም ‹‹ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች›› ናት ማለት ነው፡፡ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከሆነች ከመስቀልም በላይ ናት፡፡ ምክንያቱም መስቀልም ፍጡር ነውና፡፡ በዚህ ምክንያት በየትኛውም የጸሎት ክፍል ድንግል ማርያም ከመስቀል በፊት ስግደትና አክብሮት ይሰጣታል፡፡
ሀ. ምክንያታዊ አቀራረብን ስንከተል ደግሞ መስቀል ክርስቶስን ከተሸከመው በላይ ድንግል ማርያም ተሸክማዋለች፡፡
ለ. ዳግመኛም በመስቀል ላይ ፈሶ መስቀልን ያከበረው ደመ ክርስቶስ ራሱ አማኑኤል ከድንግል ማርያም የነሣው ነው፡፡
ሐ. መስቀል ግዕዛን (ሕይወት፣ ዕውቀትና ነጻ ምርጫ) የለውምና መክበሩ በፈጣሪ ምርጫ እንጂ የእርሱ ፈቃድና ግብር የለበትም፡፡ ለድንግል ማርያም የክብሯ መነሻ የሚሆን የሚጠቀስላት ግዕዛን (ሕይወት፣ ነጻ ፈቃድና ዕውቀት) አላት፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ንጽሕት፣ ቅድስት፣ ድንግል፣ ማእምንት (የታመነችና የምታምን) ስለሆነች ላላት ክብር በቃች እንጂ በአድልዎ ወይም የሚያስመርጣት ነገር ሳይኖር የተመረጠች አይደለችም፡፡ ስለዚህ በፈቃዷና በሥራዋ የተመረጠች በመሆንዋ ከመስቀል እጅግ ትለያለች፡፡ መለየት ብቻ ሳይሆን እጅግ ትከብራለች፡፡ 
  • ‹‹የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል››
መስተብቁዕ ዘመስቀል በመባል የሚታወቀው የቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት መጽሐፍ ‹‹ለእነዚህ ለሁለቱ ፍጥረታት›› ማለትም ለመስቀልና ለእመቤታችን ‹‹ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ›› ይላል፡፡ ይህም ‹‹የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡›› ማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ፍጡርን ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ማመስገን ተገቢ ነውን?
እንደሚታወቀው ምስጋና ሁሉ የፈጣሪ ነው፡፡ በአጭሩ እግዚአብሔር የምስጋና ባለቤት ነው፡፡ የእርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ‹‹የእግዚአብሔር ቤት፣ የእግዚአብሔር ሰው፣ የእግዚአብሔር መላእክት … ወዘተ›› እያልን እንደምንገልጽ ሁሉ ምስጋናም የእርሱ የባሕርይ ገንዘብ ነውና ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› እንላለን፡፡
ሁላችን ቀንና ሌሊት በምንደግመው የአቡነ ዘበሰማያት ጸሎት ውስጥ ይህ ሐቅ ተቀምጧል፡፡ ‹‹እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም›› ይህም ‹‹መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ምስጋናም ለዘላለሙ አሜን!›› ማለት ነው፡፡ (ማቴ6.13) በዚህ ጥቅስ መሠረት መንግሥተ ሰማያት የማን ናት? ስንባል የፈጣሪ እንደምንለው ሁሉ ምስጋና የማን ነው ስንባልም የፈጣሪ ነዋ! እንላለን ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እውነት ቅዱሳት አዋልድ መጻሕፍትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተባብረው መስክረዋል፡፡ የቅዳሴና የሰዓታት መጻሕፍት ‹‹ስብሐቲሁ ዘእምኀቤሁ ወውዳሴሁ እምዚአሁ›› ይላሉ፡፡ ይህም ‹‹ክብሩ ከእርሱ የሚገኝ ነው፡፡ ምስጋናውም ከእርሱ ነው›› ማለት ነው፡፡ ምስጋና ከእርሱ የሚገኝ ነውና ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ይባላል፡፡
ስለዚህ የጸሎት መጽሐፉ ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ሲል ከፈጣሪ የተገኘ፣ ገንዘብነቱ የእርሱ የሆነ ምስጋና ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ለቅዱሳን ይቀርብ ዘንድ እርሱ የፈቀደው ምስጋና ማለትም ይሆናል፡፡ በዚህ ጥቅስ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምና ለመስቀል ‹‹የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል›› ማለት በተብራራው መሠረት እርሱ የፈቀደውና ገንዘብነቱ የእርሱ የሆነ ማለት ነው እንጂ ለእርሱ የሚቀርበው ዓይነት ምስጋና ይገባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ እርሱ አምላክ ነውና የአምልኮ ልዩ ምስጋና ይቀርብለታል፡፡ ለፍጡራን ደግሞ እርሱ የፈቀደውና ከእርሱ የተገኘ የጸጋ ምስጋና ይቀርብላቸዋል፡፡  

ፈጣሪ ገንዘቡ ከሆነ ምስጋናው ለቅዱሳንና ለጻድቃን በፈቃዱ እንዲመሰገኑ ይሰጣቸዋል፡፡ እርሱ ለጋስ ጌታ ነውና፡፡ ‹‹ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ›› የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐረጋት ይህን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ (2ጴጥ1.4) ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ የዚህ ጊዜ እነርሱ የሚመሰገኑበት ምስጋና ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ይባላል፡፡
እግዚአብሔር በእውነቱ ለቅዱሳን ያልሰጠው ምን አለ? ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሎ ሰላሙን ሰጣቸው፡፡ ፍቅሩን ሰጣቸው፡፡ ‹‹ትፈርዳላችሁ›› ብሎ ፍርድን ሰጣቸው፡፡ ታዲያ ምስጋናውን የማይሰጥበት ምን ምክንያት አለ? ቅዱስ ጳውሎስ የገዛ ልጁን ሊሰጠን ያልሳሳው አምላካችን ‹‹ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም›› ያለው ስለዚህ ነው፡፡ (ሮሜ8.32) ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ምስጋናውን ሰጣቸው ስንል ቅንጣት ታህል አንጠራጠርም፡፡

ቅዱሳን የሚመሰገኑት ምስጋና ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ካልተባለ ታዲያ የማን ሊባል ነው? የቅዱሳን የራሳቸው ምስጋና ነው እንዳንል ፍጡር ከባሕርይው የሚገኝ ምስጋና የለውም፡፡ ሰይጣናዊና የሐሰት ምስጋናም አስጸያፊ ነውና ለቅዱሳን የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ምስጋና ጊጉያን (በደለኞች ሰዎች) ለጠንቋዬችና ለአስማተኞች ለራሱም ለሰይጣን የሚያቀርቡት ምስጋና ነው፡፡ ስለዚህ ለቅዱሳን እግዚአብሔር ራሱ ፈቅዶ የሰጣቸውን ‹‹የፈጣሪ ምስጋና›› ለእነርሱ ማቅረብ ተገቢ ነገር ነው፡፡
አንዳንዶች ግን የቅዱሳንን ምስጋና ለመቃወምና እርሱም ፈቅዶ ያልሰጣቸው አስመስሎ ለመናገር ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።›› የሚለውን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡ (ኢሳ42.8) ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ምስጋናዬን አልሰጥም የሚል አንድምታ ፈጽሞ የለውም፡፡ ነገር ግን የሚል አስመስሎ መጥቀስ ጥቅሱን በትኩረት አለመመልከትና ክህደትን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጥቅሱ በግልጽ የሚለው ‹‹ምስጋናዬንም ለተቀረጸ ምስል አልሰጥም›› ነው፡፡ ታዲያ እኛስ ብንሆን እግዚአብሔር ምስጋናውን ለቅዱሳን ሰጥቷል አልን እንጂ ለተቀረጹ ምስሎች ምስጋናውን ሰጥቷል መች አልን? ይህን ጥቅስ ጠቅሶ ለቅዱሳንም ምስጋና አልተሰጠምና ልናመሰግናቸው አይገባም ብሎ መከራከር ክብር ይግባቸውና ቅዱሳንን ‹‹የተቀረጹ ምስሎች›› ብሎ መስደብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ምስጋናውን ሲሰጥ ለተቀረጹ ምስሎችና ለጣዖታት ግን የማይሰጥ መሆኑን የሚያስረዳ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ተፈጸመ በረድኤተ እግዚአብሔር!

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ!
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኃኒትነ!
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ! አሜን!

11 comments:

  1. egziabher yibarkh betam des yemil new.......hulem endezih ayinet tshufochin btasnebebun endene lalut bzu tmhrt yisetal.......kechalachihu degmo yemetshaf kidus tinat bemil btetsfuln betam destegnoch nen egziabher yistlgn.

    ReplyDelete
  2. Girum mabrarya new! Kalehiwet yasemaln memhr!!

    ReplyDelete
  3. Egziaber yistelen endezih aynet tsuhufochen aberktulen. Dn. Hibret yeshitila kale hiwot yasemalen hulgize tenker yalu ena tiyken yemimelsu timhrtochen newe yemitastemeren ahunem yekidusan amlak yabertah ewketihen yichemirleh edme ketena gar yisteh.

    ReplyDelete
  4. Kale hiwot yasemalin!!

    ReplyDelete
  5. Kalehiwet yasemaln memhr!!

    ReplyDelete
  6. ቃለህይወት የሰማልን

    ReplyDelete
  7. ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ ጸጋውን ያብዛልህ+++!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  8. ቃለ ህይወትን ያሰማልን እግዚአብሔር ይባርክህ! ዲያቆን ኅብረት

    ReplyDelete
  9. Gobez lij.... berta ( You know you are the only modern and well educated young scolar for the church)

    ReplyDelete
    Replies
    1. Beergit Dn Hibret Betam Besal new gin only Yemilew yistekakel. kale hiwot yasemalin lewendimachin

      Delete
  10. Kalehiwet yasemaln Dn Hibret y

    ReplyDelete