ደቂቀ ናቡቴ

Friday, September 28, 2012

ዕረፍቱ ለቅዱስ ኤውስጣቴዎስ



በስመ ሥላሴ
መስከረም ፲፰
ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ጻድቅ (ቅዱስ) ኤውስጣቴዎስ) (1215-1313)
†”ከቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር  /“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።” መዝ.፻፲፭/፻፲፮፡፲፭/ መዝ.115/116፡15
“ቅዱሳን በመለኮታዊ ማዕጠንት የተቀጣጠሉ ዕጣን ሲሆኑ የተቀጣጠሉበትም በፈጣሪያቸው ፍቅር ነው።” (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)
አባታቸው ክርስቶስ ሞአ እናታቸውስነ ሕይወት ይባላሉ። በብስራተ መልአክ ወልደዋቸዋል። ዘካርያስ ለሚባል መምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ ሲያገለግሉ አደጉ። ኋላም መዓርገ ምንኩስናን  ተቀብለው በትኅርምት የሚኖሩ ሆነዋል። አንድ ቀን የነግህ ተግባራቸውን አድርሰው ከመካነ ግብራቸው ተቀምጠው ሳሉ ጌታ እንዲረዳቸው ሆኖ ተገልጾ ለኢትዮጵያና ለአርመንያ ሐዋርያ እንድትሆን መርጬሃለሁና ዙረህ አስተምር ”አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን ያልሰማ እኔንም አልሰማም” አላቸው። እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ማቴ.፲፡፵ (10፡40) እንዲል። መዓርገ ቅስና ተቀብለው ማስተማር ጀመሩ።
አንድ ቀን ቅዱሳት መካናትን እጅ ለመንሳት ስድስቱን ቀን እየተጓዙ ሰንበትን እያረፉ ኢየሩሳሌም ደርሰው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ወደ አርመንያ ሲሄዱ ባሕረ ኢያርኮ ደረሱ። መርከበኛ አግኝተው እንዲያሳፍራቸው ጠይቀውት ትቷቸው ሄደ። የለበሱትን አጽፍ ከባሕሩ ላይ አንጥፈው ልጆቼ ጥበበ እግዚአብሔርን እመረምራለሁ ሳትሉ ተሳፈሩ አሉ። ተሳፍረው ሲሄዱ ተጠራጥሮ የነበረ አንድ ደቀ መዝሙር የመርፌ ቀዳዳ በምታህል ቀዳዳ ሾልኮ ሰጥሟል። እርሳቸው ግን ከነደቀመዛሙርቶቻቸው ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በግራ በቀኝ ሆነው እየቀዘፉ አሻግሯቸዋል። ኋላ ግን ያን ደቀመዝሙር ጸልየው አድነውታል። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። ማቴ.፲፬፡ ፴፩-፴፪ (14፡31-32)
ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” ማቴ.፲፯፡፳ (17፡20)
”……ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።” ዮሐ.፳፡፳፯ (20፡27) እንዲል ጌታ በወንጌል።
ከዚያም ደርሰው አሕዛብን አስተምረው ከቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ “ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት” እንዲሉ ምንም ሙት ቢያስነሱ ተዓምራት ቢያደርጉ ሥጋ ከለበሱ ዘንድ ሞት አይቀርምና በዚህ ዕለት አርፈዋል። መቃብራቸውም በገዳመ “መርምህናም” ነው። የአባታችን በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ይቆየን።!   
“ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ…” (የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል::)
መዝ. ፻፲፩፡፮ (111፡6)

ቅዱሳንን እንደየቅድስናቸው ተቀብለን በረከታቸውን እንድናገኝ እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፡፡
   ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

1 comment:

  1. Tsadiku armaniya hager besemaetinet marefachewn lib yilual!bezihem Kahin Dingel wonebiy, TSadik wosemaet nachew.

    ReplyDelete