ደቂቀ ናቡቴ
▼
አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?
" በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። " ዮሐ.2:1-11
አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ? ማለት ምን ማለት ነው ? በውኑ ይህ ስድብ ነውን ? ብዙዎች የዚህን ቃል ትርጉም ባለመረዳት ሲስቱ
ይስተዋላል:: የቃሉን ትርጉም እና ምንነት ከማየታችን በፊት
ስለእመቤታችን ድንግል ማርያም ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ክብር እንዳላት ጥቂት እንበል:: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንግልና ላይ እናትነት፣ በክብረ
ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጠው ከእርሷ በቀር ማንም
የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለው ፍጥረት የለም፡፡ በሉቃስ
ወንጌል ትርጓሜው ላይ እንደገለጸው ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያውቀው የሚቻለው የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ
የደረሰችው እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪው ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለው
እያወቀች ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር››‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችው ፍጡር ሊረዳው የሚቻለው
የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡
በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ
ሊደርስ የሚቻለው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተውም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባው ለዚህ የመጨረሻ
ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለውን የተወደደውንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀውን
ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለው? ልዩ የሆነውን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት:: ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነው፡፡እርሷንም በቤቱ
ማስተናግድ የሚቻለው ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለው ጌታ የሰጠው
ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነው፡፡ መላእክት ሲጠብቋት ከኖሩ በኋላ መልአክ
ለመሰለ ሰው ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለውም የለም፡፡በተለይ በሉቃስ
ወንጌል ትርጓሜው ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤
ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳይፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ
የተገኘው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/
እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረው ጌታ ነው፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ››
ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰው ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ
የተቀበላትም ራሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለው የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እንኳንስ
የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠው ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም
ፈጽሞ ይካድ :: የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳን
መታመን የማይቻላቸው የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊውን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸው ይችላል? ”አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም“ ብሏታል። ስለዚህ አንዳንዶች ማርያም ማርያም አትበሉ
ሲሉ ብዙ ጊዜ ሰምተናል ። አንድን ጹሑፍ ላልተጻፈበት ዓላማ ማዋል አለመታደል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ “ከአንቺ
ጋር ምን አለኝ” ማለት “ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?” ማለት እንደሆነ ግልጽ በሆነ መልክ ተቀምጧል"
እርስዋም ኤልያስን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ ? ሐጢያቴን ታሳስበኝ ዘንድ ልጄንስ ትገድል
ዘንድ ወደ እኔ ዘንድ መጥተሀልን ? አለችው :: ቅዱስ ኤልያስ ይህን ባለችው ጊዜ የሴትየውን ልጅ ከሞት
አስነሳላት ይላል : : መጸሀፈ
ነገስት ቀዳማዊ ምህራፍ 17 : 17 - 24 :: አንቺ
ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ወይም አንተ ሰው ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለት :የትህትና አነጋገር ነው :: የትህትና አነጋገር ባይሆን ኖሮ ቅዱስ ኤልያስ ልጅዋንም ከሞት ባላስነሳላት
ነበር ::
" ኤልሳእም የእስራኤልን ንጉስ :- እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ አለው " ይላል መጸሀፈ ነገስት ካልእ ምህራፍ 3 : 13 -20 ለንጉሱ ጥሩ ዜና ነገረው "" ንጉስ ሆይ ሞአባውያንን እግዚአብሔር በእጃችሁ ይጥልላቹሀል ብሎ ነገረው " :: ተመልከቱ
አንተ ሰው ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለት የትህትና ነው :: እንጂ የስድብ ቢሆን ኖሮ የእግዚአብሔር ታላቅ ነቢይ
ቅዱስ ኤልሳእ እንዴት ይጠቀመዋል ? ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለት ግን የትህትና ስለሆነ ነቢዩ ቃሉን ተጠቅሞበታል
:: ንጉሱንም ከነበረበት ፍርሀት እና ጭንቀት እንዲወጣና ደስታን በልቡ ውስጥ አስርጾለታል :: ስለዚህ መጸሀፍቅዱስ እንደሚነግረን አንተ ሰው ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለት ንጉስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን ጸብ አለኝ
የፈለግከውን አደርግልሀለው ማለት ነው ::
"በምኩራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው
ነበረ በታላቅ ድምጽም ጮሆ :- የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን ? ልታጠፋን መጣህን "" አሉት
ይላል ሉቃስ
ምህራፍ 4 : 31 - 35:: በሰዬው ላይ የነበሩት አጋንንትም የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን ?
አታጥፋን እባክህን ማለታቸው ከአንተ ጋር ምን ጸብ አለን ሲሉ ነው :: ከአንተ ጋር ምን አለን ማለታቸው
ከአንተ ጋር ምንም ጸብ የለንም አታጥፋን :: ሲሉት ነው ::
"ሴት" የሚለው ቃል ደግሞ ስጋሽ ከስጋዬ አጥንትሽ ከአጥንቴ ማለት ነው "
እግዚብሄር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሰራት : ወደ አዳምም አመጣት :: አዳምም አለ :-
ይህች አጥንት ከአጥንቴ ስጋዋ ከስጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል "" ኦ. ዘፍ. 2 : 22 ::
ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ
እግዚአብሔርም አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ብሎ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲጠይቃት
እናቴ ሆይ ከአጥንትሽ አጥንት ወስጃለሁ (ነስቻለሁኝ ) ከስጋሽ ስጋን ነስቻለሁኝ ከአንቺ ጋር ምንም ጠብ የለኝም
የፈለግሸውን ጠይቂኝ ሲላት ነው :: ለዚህም ነው ልመናዋን ሰምቶ አማላጅነትዋን ተቀብሎ ውሀውን ጣፋጭ የወይን ጠጅ
ያደረገው :
በአጭሩ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ? ማለት የትህትና
አነጋገር ነው እንጂ የስድብ አይደልም :: መልአኩ “ጌታ
ከአንቺ ጋር ነው”ይላታል። “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” የሚለው የእግዚአብሔር መልእክተኛ ከሆነ “ጌታ ከእርሷ ጋር ምን አለው?” የሚለውስ
የማን መልእክተኛ ነው ትላላችሁ? ጌታ ከእርሷ ጋር ባይሆን ዛሬ እኛ ከእርሱ ጋር አንሆንም ነበር፣ የእርቃችን
ሰነድ፣ የአብሮነታችን ምስጢር፣ የመገናኛ ድንኳናችን ናት። አማኑኤል ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተባለው
ከእርሷ ሰው ሆኖ አይደለምን? (ማቴ.1÷23)። ፍቅርን እየወደደ የፍቅርን ሀገር የሚጠላ ማነው? ፍቅር ጌታን እየወደደ ሀገረ ፍቅር
ድንግል ማርያምንስ የሚጠላ ማነው? እርሱ ይመለካል፣ እርሷን ብጽዕት እንላለን! እርሱ ታላቅ ገናና ነው፣ እርሷ ታላቅ ሥራ ተደርጎባታል
(ሉቃ.1÷49)። እርሱ አምላክ ነው፣ እርሷ እናቱ ናት። የልባችን መሻት እንዲሞላ እርሱ ከእርሷ ጋር እንደሆነ
እርሷም ከእርሱ ጋር ናት።
እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ ላዳነበት ጥበቡ ምስጢር መፈጸሚያ መቅደስ፣ የመለኮት
ማደሪያ ለመሆን የበቃች ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ እመቤታችን ንጽሕተ ንጹሕን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተለዩ የተለየች፣
ከተመረጡም የተመረጠች፤ መትሕተ ፈጣሪ፣ መልእልተ ፍጡራን፣ ከፈጣሪ በታች፣ ከፍጡራን በላይ እየተባለች የምትመሰገን
ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና አላት፡፡
የወላዲተ አምላክ ንጽሕናና ቅድስና ልዩ ነው፡፡ ‹‹ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል
በተገባ ተገኝታለችና መላእክት የሚፈሩትን ትጉኀን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኀጸኗ ተሸከመችው፡፡
ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፣ ከሱራፌልም ትበልጣለች፣ ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና፡፡›› እያሉ ሊቃውንት
ያመሰገኗትም ድንቅ ከሆነ ቅድስናዋና ንጽሕናዋ የተነሣ ነው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ፤ ራዕ.4፥7-9/፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በምስጋናው ‹‹ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ … ዓይኖቻቸው ስድስት ከሆኑ
ከሱራፌል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፡፡ እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ .. ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው
እሳት ይድኑ ዘንድ፣ አንቺ ግን ለመለኮት ማደሪያ ሆንሽ የመለኮት ባሕርይም አላቃጠለሽም፡፡ የእሳት ነበልባልን
ተሸከምሽ፡፡›› በማለት ንጽሕናዋን ከመላእክት ንጽሕና ጋር እያነጻጸረ እጹብ ድንቅ እያለ ያመሰግናታል፡፡
የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና በቅዱሳን አንደበት ሲመሰገን ድንቅ ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ምልዕተ ጸጋ››
ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት›› እያሉ ያመሰገኗት ምስጋና ድንቅ ነው፡፡ ከሰው ወገን እንዲህ ያለውን ምስጋና
የተቀበለ የለምና፡፡ የእግዚአብሔር እናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም የንጽሕናዋን የቅድስናዋን ድንቅነት ሊቁ ቅዱስ
ኤፍሬም ሶርያዊ ‹‹ከቅዱሳን ሁሉ ክብር ይልቅ የማርያም ክብር ይበልጣል …›› ሲል በብዙ ምሳሌ ያመሰገናት ሊቁ አባ
ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹በምን በምን ልመስልሽ›› በማለት ምሳሌ የታጣላት ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና ያላት መሆኑን
መስክሯል፡፡
የንጽሕናዋ የቅድስናዋ ምስክር ስሟ ድንቅ ነው፡፡ ማርያም ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ፍጽምት ማለት ነውና፡፡ ለጊዜው
መልክ ከደምግባት ያላት ስለሆነ ውበቷ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ነውርም የለብሽም፡፡››
እንዲል /መኃ.መኃ 4፥7/፡፡ ሔዋን ንጽሐ ጠባይ ሳያድፍባት እንደነበረችው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥበቃ
ከጥንት ጀምሮ በጥንተ ተፈጥሮ ንጽሐ ጠባይ ሳያድፋባት ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ተጠብቃ የኖረች ድንቅ ናት፡፡ ነቢዩ
‹‹ንጉሥ ውበትሽን ወደደ›› ያለበት ምክንያቱ ከዚህ ድንቅ ንጽሕናዋ የተነሣ አይደለምን? ከአካላዊ ውበቷ ይልቅ
ውስጣዊ ንጽሕናዋ ቅድስናዋ ምን ይደንቅ!
የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና አፍአዊ ብቻ አይደለም፡፡ ንጉሥ እግዚአብሔር የወደደው ውበት እመቤታችንንም ድንቅ
የሚያሰኛት ሌላም አለ፡፡ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ልቡናና ንጽሐ ነፍስን አስተባብራ የያዘች ፍጽምት መሆኗ፡፡ ስለዚህ
ከቅዱስ ዳዊት ጋር ሆነን በአማን ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ፣ በእውነት በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው ልንላት
ይገባል፡: መዝ.86፥3፡: ስለ ቅድስት እናታችን ፍፁም ንጽሕና ቅድስና ታናግረን አንጨርስም ፡፡ ታዲያ ይህችን ቅድስት እናት ስለ ንጽሕዋ
ቅድስናዋ ሊቃውንቱ ተናግረው ያልጨረሱትን፡፡ አንዳንዶች ባለማወቅ
ጌታ እንዳቃለላት አድርገው መውሰዳቸው ፍፁም የዲያቢሎስ ግብር ቢጸናወታቸው እንጂ እናትነቷ እንዲህ ቢገባቸው ኖሮ ባለቤቱ ያከበረውን ባላቃለሉ
ነበር፡፡ ከእግሯ ስር ተደፍተው ምልጃዋ እንዳይለያቸው በተማፀኗት ነበር፡፡
ይቆየን
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳንና የጻድቃን የሰማእታት: የቅዱሳን መላእክት ተራዳይነት እና አማላጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን ::
No comments:
Post a Comment