ደቂቀ ናቡቴ

Friday, October 19, 2012

ሳይቃጠል በቅጠል

(የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ) አንጋፋዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ተከታይ ምእመናን እንዳሏት ይታመናል፡፡ ይህች አንጋፋና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ጥንተ ሥልጣኔ መሠረት ስትኾን ለኢትዮጵያ የቱሪስት መዲናነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እና መሠረት እንደኾነችም ማንም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነቱን እንዲያከብር፣ ባህሉንና ቅርሱን እንዲከባከብ በሥነ ምግባር በግብረ ገብነት የታነጸ እንዲኾን ያበረከተችው አስተዋፅኦም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖቱን ጠባቂነትና ባህሉን አክባሪነት በምስክርነት እንድትጠቀስ አድርጓታል፡፡ በዚህ መስክም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ውጭ የኾኑ ወገኖችንም በፍቅርና በክብካቤ በመያዝ ፍቅርን፣ አንድነትንና መቻቻልን በተግባር የሰበከች ስትኾን በውጤቱም ለኢትዮጵያ የእምነቶች መቻቻል ቁልፍ ሚና የተጫወተች አንጋፋና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡

ብሔራዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን ለመላው ሕዝብ ከማዳረስ አንጻር በከተማ ያልተወሰነች፣ በየገጠሩ የሚገኙ ሕዝቦችን በስብከተ ወንጌል በመማረክ ተከታዮቿ ያደረገች በውጤቱም በመላ ሀገሪቱ ለመስፋፋት የቻለች ስትኾን በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ ወገኖችም በሰላም፣ በመፈቃቀርና በመቻቻል ከሌሎችም ወገኖች ጋራ መኖር እንዲችሉ ያስተማረች እናት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡
ይህም ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በብሔር ትምክህተኝነት የምትገለጽ ስትሆን ለኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት መሆን የምትችል ብሔራዊት እናት ነች፡፡ ይኹንና የቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ተምሳሌትነት ያልተመቻቸውና ከመጠን በላይ መስፋፋቷ ያሰጋቸው አንዳንድ ወገኖች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመበታተን፣ ለማዳከም አቋራጩ መንገድ በብሔር፣ በጎጥ በዘርና በመንደር እንድትከፋፈል በማድረግ ማዳከም እንደሚቻል በመገመታቸው በዚህ ስሌት አንዳንድ የዋህ ሰዎችን በመቀስቀስና በማስተባበር ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማመስና ለመበታተን ታጥቀው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡

ይህ ቀላል የሚመስል ነገር ግን እጅጉን አደገኛ የኾነው የመበታተንና የማፈራረስ ስትራቴጂ ለጥቅመኞች፣ አሉባልተኞች እና ሥራ ፈቶች እጅግ የሚመች ሲሆን ለምስኪኑ ምእመን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንዲህ ከኾኑ እኛ ምን አገባን? ብለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥለው እንዲኾኑ ጥቂቶቹም ከመናፍቃን ጎራ እንዲሰለፉ ሰበብ ኾኗቸዋል፡፡

ይህ በዘርና በጎጥ የመከፋፈል ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰው አልባ የሚያደርጋት መኾኑን በመረዳትም በዚህ መሠሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማስተማር፣ በማረምና በመምከር መመለስ ግድ ይላል፡፡ በተለይ ካለፉት ኻያ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መሰባሰብ፣ መደራጀትና መንቀሳቀስ የጀመሩት የተሐድሶ መናፍቃን ስብስብ ይህን የመሰለ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፈራረስ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህንኑ በመረዳት ቡድኑ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች፣ ያቀጣጠላቸውን እሳቶች በማጥፋት ከዚህ እኵይ ዓላማው እንዲታቀብ ማድረግና የማያዳግም ርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን ከጥቅምቱ 31ኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ ጉባኤ ተሳታፊዎችም የሚጠበቅ ይኾናል፡፡

በተለይም ከአምስተኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ኅልፈተ ሕይወት ወዲህ በቀጣይ የፓትርያርክ ምርጫና በምርጫው መመረጥ ይገባቸዋል በሚሏቸው አባት ዙሪያ በየሆቴሉ፣ በየመናፈሻውና በየግለሰቡ ቤት በመዞር÷ ‹የእገሌ ዘር፣ የእገሌ ዘር› በማለት በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስና በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመረጠው ቅዱስ አባት እንደ ፖሊቲካ ፓርቲ ምርጫ በዘርና በመንደር መመረጥ አለበት በማለት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ፡፡

አንዳንዶቹ በዘር የሚመስሏቸውን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማነጋገር፣ በማደራጀት እና በመቀስቀስ በማይመለከታቸው ጉዳይ እንዲገቡ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ እዚህ ላይ በየትኛውም የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኝ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዲህ ዐይነት አደገኛ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ በእሳት መጫወት እንደማይገባው የቡድን አደራጆቹ ያውቃሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስም የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ውጤቱ ሊመጣጠን የማይችል መኾኑን ማስላት ባለመቻላቸው አልያም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንዲህ ዐይነት እንቅስቃሴ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለው ማሰባቸው በእጅጉ የዋሆች እንደ ኾኑ የሚያመላክት ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሌሎች የዋሆችንና አላዋቂዎችን ሊያስትና ሊያሰናክል ስለሚችል ወሰንና ዳርቻ ተበጅቶለት እዚህ ላይ ይብቃ ሊባል ይገባዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪዎች በመምሰል ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማመስ፣ አባቶችን ከአባቶች በማለያየት መተማመንና መቀራረብ እንዳይፈጠር ሲሠሩ የነበሩ የተሐድሶ መናፍቃን ግንባር ቀደም መሪዎች በአባቶች እርስ በርስ መለያየትና መጋጨት ምንኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳጋበሱ ያውቃሉ፡፡ አሁንም አንዱን ከአንዱ ለማለያየት ጥሩ መንገድ የሚኾነው “አባቶችን በብሔር መከፋፈል ሲቻል ነው” በሚል የአላዋቂነት ስሌት በመንቀሳቀስ “ብፁዕ አቡነ እገሌ ከእነ ብፁእ አቡነ እገሌ ይሻላሉ፤ እርሳቸውን ለማስመረጥ ብንቀሳቀስ መልካም ነው፤ ከብሔርም ከትምህርትም አንጻር የተሻሉ ናቸው” ተሰብስበው ሲያቦኩና ያልበላቸውን ሲያኩ ሰንብተዋል፡፡

እነዚህ ኀይሎች መቼም ቢኾን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ደንታ የሌላቸው፣ በመከፋፈሉና በመለያየቱ መሀል እንዴት መጠቀም እንደሚችሉና እንደሚገባቸው ከማስላት የዘለለ ሕልም የሌላቸው በቀጥታ ከመናፍቃን በሚሰጥ አመራርና ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና እየተንቀሳቀሱ ያሉ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ያለውን የሽግግር ወቅት በመጠቀም የተሐድሶ መናፍቃንና ጥቅመኞች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማመስ፣ ለመበታተንና ሀብት ለማጋበስ ወቅቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር እየተንቀሳቀሱ እንደ ኾነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ስለሆነም ብፁዓን አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ሓላፊዎች፣ የ31ኛው ዓለም አቀፋዊ ሰበካ ጉባኤ ተሳታፊዎች፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎችና የጸጥታ ተቋማት “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በዚህ ደረጃ በውስጥም በውጭም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ነቅቶ መጠበቅ፣ መከታተልና ማረም እንደሚገባ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡

ምንጭ፡- ዐዋጅ ነጋሪ፤ 5ኛ ዓመት ቁጥር 8፤ 2005 ዓ.ም

2 comments:

  1. Kale hiyot yasemalin endih ayinet merja lemimelekatachew hulu madres lagerim lebetekiristianim tekami newuna bertu teberatu elalehu!!!!!

    ReplyDelete
  2. I am sure this piece of writing has touched all the internet users, its really really pleasant paragraph on building
    up new web site.

    Also visit my blog Dr Dre Beats

    ReplyDelete