ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, October 18, 2012

†♥†አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ†♥†



“በስመ ሥላሴ”
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡(እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ

ኢትዮጵያዊው አባት አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባቱ መልዓከ ምክሩ እናቱ ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለደበት ልዩ ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ይባላል፡፡ በዚያች ሀገር እግዚአብሔርን የሚፈራ ስሙ መልዓከ ምክሩ የሚባል ደግ ሰው ባለቤቱም ወለተ ማርያም ሁለቱም ደጋጎች እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው በእግዚአብሔር ህግ ጸንተው የሚኖሩ መልካም ስራን በመስራት እንደ ዘካርያስና ኤልሳጴጥ እውነተኞች ነበሩ፡፡ሁለት ደጋጎች ልጆችም አሏቸው የተባረከ መልካም ፍሬን የሚያፈራ በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔርን የሚያገለግል በጸሎቱ ሰውን የሚጠቅም በጻድቃንም ዘንድ የተመረጠ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ድንግል ማርያም ይለምኑ ነበር፡፡
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ጆሮውን ወደ ልመናቸው አዘነበለ እንዳለ መዝ 3329 እግዚአብሔር አምላክ በዓይነ ምህረት ተመለከታቸው ልመናቸውንም ሰምቶ አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሚያዚያ 8 ቀን ተጸንሶ ታህሳስ 9 ቀን ተወለደ፡፡ በተወለደ እለትም ተነስቶ በእግሩ ቆሞ 3 ጊዜ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብሎ ጣዕም ባለው አንደበቱ ተናገረ፡፡ 9 ጊዜም ህጻናትን ለሚያናግሩ ገዥ ለሚሆኑ ለአጋይዝተ አለምላሴና ለእመቤታችን ለመስቀሉም ሰገደ፡፡ እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ብዙ ሰዎች ከህጻኑ አንደበት የስላሴን ምስጋና ሰምተው ፈጽመው አደነቁ ዳግመኛም በዚህ ህጻን ላይ የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበታል ብለው እየተጨዋወቱ ወደ ሀገራቸው ገቡ፡፡
አባቱና እናቱም መጀመሪያ ስለመወለዱ ዳግመኛም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን ምስጋና በማቅረቡ ደስ አላቸውና እግዚአብሔር ይህን ህፃን ሰጠን እኛ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስዕል ፊትና ለፍጥረት ሁሉ ለምትራራ ከሁሉ በላይ በሆነች አምላክን በወለደች በቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል ፊት ቁመን እንደለመንን ልመናችንን ሰምታ የተመረጠ ልጅ ሰጠችን ብለው አመሰገኑ፡፡የመንጻት ወራት በተፈጸመ ጊዜ 40 ቀን አባትና እናቱ በጸራ ወርቅና ብር ንጉስ ይኩኖ አምላክ ወደ አሰራው እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ወስደው አዳም 40 ቀኑ ወደ ገነት እንደገባ በቤተክርስቲያን ስርዓት ተጠመቀ፡፡ አዳም በአርባ ሄዋን በሰማንያ ቀን ወደ ገነት እንደገቡ ኩፋሌ 49 ካህናትም መንፈስ ቅዱስ እንዳናገራቸው ስሙን እስትንፋሰ ክርስቶስ ብለው ሰየሙት ስጋ ወደሙን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ የስሙም ትርጓሜ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ አንድም የክርስቶስ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቀው አደገ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልቦናውን ብሩህ አድርጎለት 5 ዓመቱ የቅዱሳን መጽሐፍትን፣ ቃላትን ፣ብሉያትንና ፣ሐዲሳትንም፣ድርሳናትንም አወቀ፡፡ ከመምህር ኪራኮስ የመፅሐፍትን ትምህርት ከነትርጓሜው 7 ዓመቱ ጨረሰ፡፡ በማስተዋል ሲመለከት አባቱንና እናቱን ዘመዶቹን የተወ ቃሌን ይጠብቃል መንግስተ ሰማያትን ይወርሳል ይህን ያላደረገ ሊያገለግለኝ አይችልም የሚለውን አገኘ ማቴ 1037 ይህንንም ቃል በልቦናው ይዞ የምነናውን ስርዓት ይጠብቅ ነበር፡፡ 7 ጊዜ በመዓልት 7 ጊዜ በሌሊት በየዕለቱ 150 መዝሙረ ዳዊትን ሲያደርስ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ፊቱን በትምህርተ መስቀል አማትቦ ጸሎት በጀመረ ጊዜ እጆቹን ሲዘረጋ ወጥመዳቸውን ያጠመዱ አጋንንት በነፋስ ፊት እንዳለ ጢስ ተነው ይጠፋሉ እየተሯሯጡም ፈጥነው ይሸሻሉ፡፡
ከዚህ በኃላ ስሙ ማርቆስ ከሚባል ጳጳስ ድቁናን ተቀበለ፡፡ ልጄ ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ወደ ገዳም ብትሄድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ እንዳለ ሲራክ 21 ይህንን አለም ናቀ፡፡ ልዩ ክብር የሚሆን የምንኩስናን ልብስ ይቀበል ዘንድ በተወለደ 14 ዓመቱ ወደ ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደ ከባህር ዳር ቆሞ የሙሴን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ያለመርከብ ባህሩን ተሻግሮ ወደ ቤተክርስቲያን ገባ፡፡የኢየሱስ ሞዐ ልጅ የሚሆን አበምኔቱ በመነኮሳት መጽሐፍ እንደተፃፈ 3 ዓመት ፈተነው፡፡ በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት ለአባቶች መነኮሳት ምግብ ሊሆናቸው ከባህር ውስጥ አሳን በማውጣት ያገለግል ነበር፡፡ከአባ ህንጻ ደብረ ድባ ከሚባል ቦታ የቅስና ስልጣን ተቀበለ፡፡
በጾም በጸሎት በተጋድሎ የአባቶቻችንን ሐይማኖት በማስተማር ህሙማንንና ዓይነ ስውሮችን፣ አንካሶችን፣ በክፉ ደዌ የተያዙትን ቁጥራቸው 80 የሚሆኑትን በአንድ ቀን ፈወሳቸው፡፡አባታችን ጸሎት ሲጸልይ ቆሞ አይደለም ወዙ እንደ ውሃ ነጠብጣብ እስከሚፈስ ድረስ ይሰግድ ነበር፡፡የስግደቱም ልክ ተቆጥሮ አይዘለቅም፡፡ መልካም ምግባሩ በጣም የተትረፈረፈ የበዛ ነውና ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶና የወርቅ መሰላል ስለ ስግደቱና ስለ ጸሎቱ ስለ ትሩፋቱ ብዛት ቅዱሳን እስኪያደንቁ ድረስ ተተክለው ይታያሉ፡፡በዚያን ዘመን ከሰው ሁሉ እንደርሱ የጽድቅን ስራ የሚሰራ አልተገኘም፡፡
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አየዋለሁ ምስጋናውም ዘወትር በአንደበቴ ነው ሰውነቴም ዘወትር በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ ትላለች እንዳለ አባታችንም ሁል ጊዜ ጌታችንን በግልጽ ያያል የፈለገውንም ሁሉ ዘወትር ፈጥኖ ያገኛል ጌታም ከእርሱ አይርቅም ነበር፡፡ብጹዕ አባታችን አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ አርባ ዕለት በተፈጸመ ጊዜ እህል ሳይቀምስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው ለአባታችንም ወደ እርሱ መጥቶ አስሩን ቃላተ ኦሪትና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶችን ሰጠው፡፡ ዘፀ 341
ከዚህ በኃላ ሰውን ሁሉ እንዲያስተምር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከነገረው በኃላ ስለወደድከኝ ፈቃዴን ስለፈጸምክ ስለ ብዙ ድካምህና መከራህ ለኔ ስለተጋደልክ እኔም በአንዲት ቀን አስር ሺህ አስር ሺህ ነፍሳትን እምርልሃለሁ፣በሦስቱ በዓላት በተወለድኩበት በተጠመቅሁበት በተነሳሁበት እንደዚሁ ሰባ ሰባ ነፍሳትን በቀን ሰባት ጊዜ በሌሊት ሰባት ጊዜ እስከ እለተ ምጽዓት ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት ዳግመኛም ዝክርህን ያዘከረ፣ስምህን የጠራ፣የገድልህን መፅሐፍ የጻፈ፣ያጻፈ፣ያነበበ፣የሰማ ፣የተረጎመውን እምርልሃለው አለው፡፡ ማቴ 1041-42
አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ለማስተማር ወደ አባቶቹ ሀገር ወደ አባቱ መቃብር በገባ ጊዜ እዚያው ደርሶ ቤተክርስቲያን ሰራ እለቱን ስንዴ ዘርቶ፣ወይን ተክሎ፣ጽድንም ወይራን ግራርን ተክሎ በአንዲት ቀን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እለቱን አድርሷል፤ስንዴውን ለመስዋዕት ወይኑን ለቁርባን በታምራት አድርሷል፡፡ከእለታት በአንድ ቀን አባታችን በጸሎት ላይ ሳለ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ከብሩህ ደመና ጋር ወደ እርሱ መጥቶ በደመና ጭኖ ከፈጣሪው ዘንድ አደረሰው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቅዱሳኖቹ እንዲባረክ ካደረገ በኃላ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን አዘዘው ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ አድርሰህ አሳየው አለው፡፡መላዕኩም እንደታዘዘው አደረገ፡፡መልሶም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ደብረ ዛብሒል ወደ ምትባል ቦታ አደረሰው፡፡ ከዚያም ደርሶ ድንቅ ታምራትን አደረገ ውሃም ከአለት ላይ እያመነጨ ህሙማንን ፈወሳቸው፡፡
በባህር ውስጥ ጠልቆ ዘወትር በሄደበት ሀገር ሀሉ ሲጸልይ የሚያርፍበትን ቦታና ስጋዬ የሚቀበርበትን ቦታ ግለጽልኝ ብሎ በጸለየ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ተልኮ መጥቶ የአባትህ አባት ከሸዋ ሀገር መጥቶ ታቦተ እግዚአብሔር አብን ወደ አስተከለበት ወደ አባ ሙሴ ደብር ወደ አባትህና እናትህ ቦታ ዳውንት ምትባል ሀገር ሂድ ብሎ የእረፍት ቦታውን ነገረው፡፡ከዚያም ወደ ብዙ ገዳማት በመሄድ ቡራኬን ተቀበለ፡፡ ከአራት ዓመት በኃላ አረጋውያን መነኮሳትን ተሰናበታቸው መርቀውት ተለያዩ፡፡ የኢትዮጵያን ገዳማት ተዘዋውሮ እየጎበኘ ጎዣም ደረሰ ፤በዚያ እያስተማረ፣ እያጠመቀ የታመሙትን እየፈወሰ፣የእውራንን አይን እያበራና ሙታንን እያስነሳ በዚያ ተቀመጠ፡፡በባህር ውስጥም ገብቶ 9 ዓመት ለኢትዮጵያ ጸለየ፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በኃላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ ይህችን ሀገር እና የኢትዮጵያን ህዝቦች ምሬልሃለሁ ከዚህች ባህር ውጣ አለው፡፡ አባታችንም ከባህር ውስጥ ወጥቶ ተንበርክኮ ለጌታችን ሰገደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የማረፊያህ ቦታ ምስራቅ ወደ ምትሆን ወደ ዳውንት ሂድ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ አባታችንም በአስራ ሰባት ዓመቱ ወደ ደብረ አሰጋጅ በሚሄድበት ጊዜ ጸሐይ ልትገባ ደረሰች፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጸለየ አለቀሰ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አውግዤሻለሁ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ አሁን ቀጥ ብለሽ ቁሚ አላት ጸሐይም ወደ ኃላ ተመልሳ በአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቃል ቆመች ደብረ አሰጋጅ እንደገባ ጸሐይም አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ ዘንድ ፍታኝ አለችው እግዚአብሔር ይፍታሽ ባላት ጊዜ ገባች፡፡
እድሜው ሰላሳ ሦስት በሆነ ጊዜ ወደ ደብረ ድባው አበምኔት መጥቶ ሚያዝያ ዘጠኝ ቀን ምንኩስናን ተቀበለ፡፡በዚያ ደንጋይ ፈልፍሎ ዋሻ አዘጋጀ፡፡ ሉቃስ የሳላት ከግብፅ የመጣች የድንግል ማርያምን ስዕል አስገብቶ የዋሻውን በር ዘጋ፡፡ ያለ ደቀመዝሙሩ ልብሰ ክርስቶስ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር አይገናኝም፡፡በዚህ ድንቅ ድንቅ ታምራትን እያደረገ ሁለት መቶ አርባ ነፍሳትን ከሲኦል አወጣ፡፡
አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጻድቃን ሰማዕታት፣መነኮሳት በዘጠና ዘጠኙ ቅዱሳን መላዕክት ልቡና በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ ጸሎት አባታችን ይፀልያል በየፀሎቱ ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት ይደግማል፡፡ ይህንንም ጸሎት በጸለየ ጊዜ 240 ነፍሳትን በቀን ሰባት ጊዜ በሌሊት ሰባት ጊዜ ከሲኦል ያወጣል ይህንን ጸሎት ኃጢያተኛ ሰው እንኳን በጸለየበት ጊዜ አንድ እልፍ (1000 )ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣል ይህቺ ጸሎት አታወጣም ብሎ የሚጠራጠር ቢኖር መንግስተ ሰማያትን እንደማያይ ገድሉ ይናገራል፡፡ መዝ 11/1126
አባታችን እጁን ዘርግቶ ዘወትር ያለማስተጓጎል ይፀልያል፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጽናቱን አይቶ ኢትዮጵያን ምሬልሃለው ይለዋል፡፡የእመቤታችንን የስደቷን መታሰቢያ ጾም ሳያስተጓጉል ከዓመት እስከ አመት ይፆማል፡፡ ይህን እያደረገ ላለበት ደብር ህግና ቀኖናን ስርዓትን አወጣ፡፡በዚያን ዘመን መሀልም የተባለ እንደ አርዮስና መቅደኒዩስ የተወገዘ ሐሰተኛ መናፍቅ ተነሳ፡፡ የጌታን ልደት ሦስት ነው ብሎ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ይህንንም ክህደት ለንጉሱ ለአጼ ኢያሱ አስተማረው ንጉሱም በክህደቱ ጸና፡፡ወታደሮቹንም ልኮ በገዳማት ያሉ ቅዱሳንን አሲያዘና ሐይማኖታቸውን እንዲክዱ አስገደዳችው ቅዱሳኖችም ሰማዕትነትን መረጡ፡፡ አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርሰቶስን ግን አላገኙትም፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በክንፉ ሰውሮታል እረፍቱ በሰማዕትነት አይደለም ወደ ፊት የሚሰራው ብዙ ስራ አለና፡፡
ካሃዲ ንጉስም በአባታችን ጸሎት ንሰሐ ገብቶ መንግስተ ሰማያትን ወረሰ፡፡አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ተሰውሮ ይኖርበት ከነበረበት ገዳም ሰማዕታት ካረፉ በኃላ በአንድ አመት ተመለሰ በሁለተኛውም ዓመት ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ መጥቶ የሚያርፍበትን እረፍተ ሰዓቱን ፣ቀኑን ፣እለቱን፣ ዓመቱንና ወሩን ነገረውና ወደ ላከው ወደ ፈጣሪው ተመለሰ፡፡አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ፈጣሪውን ለኃጣአን የሚሆን አስራት ስጠኝ አለው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ እንዳለው ቃል ኪዳን ገባለት የሚያዝያ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ታመመ፡፡ የእረፍቱ ቀን ደርሷልና ብዙ ባህታውያን ስውራን መነኮሳት ወደ እርሱ መጡ በእርሱ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ አይተው ቅዱሳን አደነቁ፤ በፊቱ ላይ ያለውን ብርሃን አይተው ተገረሙ፤ የራስ ጸጉሩ እንደ በረዶ ነጭ ነበር፡፡በዚያን ጊዜ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመቱ ነበር፡፡
ዳግመኛ አባታችን አገልጋዩ የሆነውን ጻድቁ ልብሰ ክርስቶስን ጠርቶ ከእርሱ በኃላ የሚሆነውን በመጨረሻውም ዘመን የገድሉ መጽሐፍ እንደሚጻፍ ይህም ገድል ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም መታሰቢያ እንደሚሆን ነገረው፡፡ ወንድሞቹን እንዲጠራም አዘዘው፡፡ በተሰበሰቡም ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ በስጋ አታዩኝም ከመንግስተ ሰማያት በስተቀር አንገናኝም አላቸውና በመስቀል አመላክቶ በዚህች ቦታ ላይ ቅበሩኝ በላዩ ቤተክርስቲያን ስሩ፣ የመናፍቃንን ትምህርት አትቀበሉ፣ ሀይማኖታችሁንም ጠብቁ፣ የእመቤታችንን አማላጅነት መስክሩ ብሎ ነገራቸው፡፡ ያን ጊዜ ቅዳሜ ማታ ለእሁድ አጥቢያ ነበር፤ እንደ ነጋሪት ያለ ቃልና እንደ ነጋሪት ያለ ድምጽ ከሰማይ ተሰማ ፡፡በታላቅ ግርማ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት እየተመሰገኑ መጡ፡፡ጌታችንም ለብፁዕ አባታችን ቃል ኪዳን ገባለት ዝክርህን ያዘከሩ መታሰቢህን ያደረጉ እስከ 17 ትውልድ እምርልሃለሁ፡፡ ይህን የገድልህን መፅሐፍ በቤቱ ያስቀመጠ የተለያዩ በሽታዎች፣ችግር፣ረሃብ፣የሰው ሞት፣የእንስሳት ሞት፣ከቤቱ የእህል በረከት አይታጣምይህን ቃል ኪዳን ከሰጠው በኃላ ጌታችንም መልሶ የፈለከውን ጠይቀኝ አለው አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ፈጣሪዬ ሆይ ይህን የሰጠኸኝ ቃል ኪዳን በስራዬ አይደለም በቸርነትህ ነው ስምህ ፈፅሞ የተመሰገነ ይሁን፤ዝክሬን ያዘከረ፣መታሰቢያዬን ያደረገ፣የገድሌን መፅሐፍ የጻፈውን እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ? አለ፡፡ ጌታችንም እስከ 25 ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ዳግመኛ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡
አባታችንም ይህንን ቃል ኪዳን ከተቀበለ በኃላ ልጆቹን መነኮሳቱን አረጋጋቸው፡፡ በቀና በራሱ ስልጣንና በሐዋሪያት ስልጣን እግዚአብሔር ይፍታ አላቸው ልጆቼ አትደንግጡ አትፍሩ ፈጽማችሁ ተደሰቱ ታላቅ ተስፋ በሰማይ አለና ከእኔ ቦታ ወዲያና ወዲህ ፈጽማችሁ አትዘዋወሩ እስከ ዘመናችሁ ፍጻሜ ጸንታችሁ ተቀመጡ ካላቸው በኃላ ሚያዝያ 9 ቀን በእግዚአብሔር ፈቃድ በሰላም አረፈ፡፡ባመላከተው ቦታ መነኮሳቱ ቀበሩት ያን ጊዜ መፍራት ንውጽውጽታ ልቅሶ ሆነ የእርሱ ስጋ መሬት በተቀበለች ጊዜ ተንቀጠቀጠች፡፡
መዝ 115/116 6
+++ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ+++ የጸድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል መዝ.111፡6

የአባታችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ በረከታቸው ይደርብን፡፡ አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን!!!
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስ/ሳር፣ ነገረ ቅዱሳን፣ መዝገበ ታሪና  ገድላቸው ላይ እናገኛለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

15 comments:

  1. "ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።
    ዮሐ. 8:12

    ReplyDelete
  2. "የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።" ያዕ.5፡16

    ReplyDelete
  3. “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ…” (የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል::መዝ. ፻፲፩፡፮ (111፡6)

    ReplyDelete
  4. “ቅዱሳን በመለኮታዊ ማዕጠንት የተቀጣጠሉ ዕጣን ሲሆኑ የተቀጣጠሉበትም በፈጣሪያቸው ፍቅር ነው።” †♥† (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)

    ReplyDelete
  5. †♥† “የቅዱሳን ሕይወት ተርታ ታሪክ ወይም ተረት አይደለም፤ ይልቁንስ እግዚአብሔርን የሚከተሉና በሥራቸው ሁሉ የእርሱ ጥበቃ ያልተለያቸው ሰዎች ታሪክ ነው።” †♥† (ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ)

    ReplyDelete
  6. ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?ማቴ. 16፡26

    ReplyDelete
  7. መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
    ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። ማቴ.10፡38-39

    ReplyDelete
  8. እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ዕብ.፲፩፡፴፫¬-፴፬ (11፡33¬-34)

    ReplyDelete
  9. የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቻቸውም ወደ ጩኸታቸው ናቸው መዝ 33/34፡15

    ReplyDelete
  10. "የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነውና" ምሳ 11፡23

    ReplyDelete
  11. "ጻድቃን እነደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራሉ" ምሳ 28፡1

    ReplyDelete
  12. "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል እንደ ዝግባም ያድጋል" መዝ 91፡12

    ReplyDelete
  13. "እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው" መዝ 67፡35

    ReplyDelete
  14. ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፤ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ።የእግዚአብሔር ምስጋና በጕሮሮአቸው ነው፤ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው፥በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፤ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት፥ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ፤የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ። ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት። ሃሌ ሉያ።” መዝ.149:5 -9

    ReplyDelete
  15. እኝህን ቅዱስ አባት ያወኳቸው ቀፀባ ማሪያም ቤተክርስቲያን ፅላታቸው በመኖሩና በዛቤተክርስቲያን ፀበላቸው አጋንንትን ሲያባርርና ሲያስር ስላየሁ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከቃልኪዳናቸው አንዱ የቅዱሱን አባታችንን ፀበል ፀዲቃቸውን ያደረገ ብቻ ሳይሆን ፀበል ፀዲቁን የበላ የጠጣ ከአምላክ በተሰጣቸው ቃልኪዳን ምህረት ይደረግለታል፡፡ እኝህን ቅዱስ አባት ያወኳቸው ቀፀባ ማሪያም ቤተክርስቲያን ፅላታቸው በመኖሩና በዛቤተክርስቲያን ፀበላቸው አጋንንትን ሲያባርርና ሲያስር ስላየሁ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከቃልኪዳናቸው አንዱ የቅዱሱን አባታችንን ፀበል ፀዲቃቸውን ያደረገ ብቻ ሳይሆን ፀበል ፀዲቁን የበላ የጠጣ ከአምላክ በተሰጣቸው ቃልኪዳን ምህረት ይደረግለታል፡፡

    ReplyDelete