ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, October 4, 2012

ማኅሌተ ጽጌ፡- ምንጩ - ትርጉሙ - መልእክቱ ክፍል ሁለት

(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 24,2005 ዓ.ም ከሐመር መፅሄት የተወሰደ(. ያረጋል አበጋዝ)) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋር አስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት ናት፡፡ 
'ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአግሪሁ ለይሁዳ
ጸቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ
ያለው ይህም ማለት ነቢዩ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮችና ኮረብቶች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል÷ ይመነጫል ያለው በአንቺ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ክርስቶስን በወለደች ዕለት መሪሩ ጥሞ፣ ይቡሱ ለምልሞ ተገኝቷል፡፡ ይህ ለጊዜው ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከእርስዋ በነሣው ሥጋና ደም ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ከልጅነት ተራቁቶ፣ በረሀበ ነፍስና በጽምዓ ነፍስ ተይዞ የነበረውን የሰው ልጅ ከጐኑ ውኃን ለጥምቀት፣ ሥጋውንና ደሙን ምግበ ነፍስ አድርጎ የአምስት ሺህ አምስት መቶውን ዘመነ ረሀብ እንዳስወገደልን ያስረዳል፡፡
አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እምአንክሮ
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ
እለ ያማስኑ ለዓፀደ ወይንነ ወፍሮ
ናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ

ትርጉም
‹‹እመቤታችን ማርያም ሆይ አርምሞሽ ከማድነቅ በላይ ሆነ÷ በማድነቅ የማይፈጸም ሆነ፡፡የወይን ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች ለማጥመድ (ለመያዝ) ፍጠኚ፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው ነበር›› (ሉቃ.2÷51) ሲል የእመቤታችን አርምሞ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ ገልጿል፡፡ እመቤታችን ማንም ፍጡር ያልሰማውን ብሥራተ መልአክ የሰማች÷ ለማንም ያልተደረገውን በድንግልና መጽነስና መውለድ የታደለች÷ ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲመሰገንባት የመላእክትን ቅዳሴ የሰማች ፈጣሪዋን የመገበች፣ ከሰው ወገን ይቅርና ከሱራፌልና ከኪሩቤል የሚበልጥ ክብርና ጸጋ የታደለች ስትሆን እርሷ ግን በዚህ ዓለም ስትኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ከማኖር በስተቀር ይህንን አየሁ÷ ይህንን ሰማሁ አላለችም፡፡ ሔዋን ዕፀ በለስን ወደ መብላትና ጸጋዋን ወደማጣት ያደረሳት ለእርስዋና ለአዳም ብቻ የተነገረውን ምሥጢር አውጥታ ለዲያብሎስ በመናገርዋ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን ሁሉን በልቧ መዝገብ በመያዟ የተመሰገነች ሆነች፡፡

ከክርስቶስም ሆነ ከእመቤታችን የተማርነው አርምሞን ነው፡፡ ክርስቶስን ጲላጦስና ሊቃነ ካህናቱ ከየት መጣህ? ማነህ? ትምህርትህስ ምንድነው? እያሉ ሲጠይቁት ዝም ነው ያላቸው፡፡ ልሰቅልህ ሥልጣን አለኝ ሲለው ብቻ ነው መልስ የመለሰለት፡፡ ስለዚህ እኛም ከአባታችን ከክርስቶስና ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያየነውን አብነት ማንሣት ይገባናል (ዮሐ.19÷2 ማቴ.27÷14)፡፡

የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የእመቤታችንን አርምሞ ከአደነቀ በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞንእሥግሩ ለነ ቈናጽለ ንዑሳነ እለ ያማስኑ ዓፀደ ወይንነ - የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን›› (መኃ.2÷15) እንዳለ የወይን ቦታ የተባለ የሕግ መጠበቂያ ልባችንን ሊያበላሹ ውር ውር የሚሉትን በቀበሮ የተመሰሉ መናፍቃንንና አጋንንትን እንድታስታግስልንና እንድታስወግድልን ይጸልያሉ፡፡

ትመስል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ
ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ
ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ
እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ
ለእለ በሰማይ ወምድር ዘከንኪ ዕረፍተ፡፡

‹‹ማርያም ሆይ እናትሽ (ሐና) ጽጌያት የተፈጠሩባትን ሦስተኛዋን ቀን፣ ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛውን ቀን (ረቡዕ) እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን የፈጸመባትንና ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡››

እግዚአብሔር በዕለተ ሠሉስ (3ኛው ቀን) ዕጽዋትን ፈጠረ (ዘፍ.1÷13)፡፡ ከእነዚህ ዕጽዋት ጽጌያት (አበቦች) ከጽጌያት ደግሞ ፍሬ ይገኛል፡፡ ቅድስት ሐናን ጽጌያት በተፈጠሩበት በዕለተ ሠሉስ÷ እመቤታችንን በጽጌ፣ ጌታን ደግሞ ከጽጌው በተገኘው ፍሬ መስሏቸዋል፡፡ በአራተኛው ቀን (በዕለተ ረቡዕ) ፀሐይንና ጨረቃን፣ ከዋክብትን ፈጠረ፡፡ ሐናን በዕለቱ፣ እመቤታችንን በፀሐይ መሰላቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን (በሰንበት) ለሰው ሁሉ ዕረፍት እንዲሆን ለአብነት እግዚአብሔር አረፈ ተባለ፡፡ በዚህች ዕለት ሰው ሁሉ ከሥጋዊ ድካምና ውጣ ውረድ አርፎ ፈጣሪውን እያመሰገነ ይውላል፡፡ በእመቤታችንም ሰው ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ አርፎ ተግባረ ነፍስ እየሠራ ፈጣሪውንወሠርዓ ሰንበተ ለሰብእ፣ ዕረፍተ ሰንበትን ለሰው ዕረፍት ሠራእያለ ሲያመሰግን ይውላል፡፡

በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ
ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ
ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ
ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ
ወበጸዳሉ አብርሃ ጽልመተ

ትርጉም
‹‹በአንቺ ላይ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ለሰው የአካሉን ሦስትነት ገለጸ÷ አስረዳ፡፡ ድንግል ሆይ ጽጌሽ (ልጅሽ) ተአምራቱን ገለጸ÷ አስረዳ፡፡ በብርሃኑም ጨለማን አራቀ፡፡››

እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን በግልጽ ያሳየው በእመቤታችን÷ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ነው፡፡
/ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበሥራት እንዲህ አላትመንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ፣ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ - መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል÷ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል›› (ሉቃ.1÷35)፡፡

መንፈሰ እግዚብሔር ብሎ መንፈስ ቅዱስን፣ የልዑል ኃይል ብሎ ወልድን፣ ልዑል ብሎ አብን በማንሣት ሦስትነታቸውን አስረዳ፡፡ እመቤታችን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ ሊዋሐድ፣ አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ እናት ለመሆን እንድትበቃ በማድረግ ሦስቱም ተሳትፈዋል፡፡

/ በዮርዳስኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ÷ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነውአለ፡፡ (ማቴ.3÷16-17)፡፡ 
ወልድ በተጠማቂነት÷ አብ በደመና ሆኖ ልጄ ነው እያለ ሲመሰክር÷ መንፈስ ቅዱስ ደግመ በርግብ አምሳል ሲወርድ በአንድ ጊዜ ታይተዋል፡፡ አንድ ገጽ የሚሉ ሰባልዮሳውያን ላይጠገኑ ተሰበሩ፡፡ አንዱ ራሱ በተለያየ ስም ተጠራ እንዳይሉ በአንድ ጊዜ ሦስቱም በየራሳቸው መገለጫ ወልድ በተዋሐደው ሥጋ÷ አብ በደመና÷ መንፈስ ቅዱስ በርግብ ተገለጡ፡፡

/ በደብረ ታቦርም አብ በደመና ሆኖበእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙትበማለት ተናግሮአል (ማቴ.17÷1-8 2ኛጴጥ.1÷17-19)፡፡

ዕፀ ደንጐላ ዘቈላ ወአኮ ዘደደክ
ዘጸገይኪ ጽጌ በማዕከለ አይሁድ አሥዋክ
ተአምረ ድኂን ማርያም ዘልማድኪ ምሒክ
መሐክኒ ለምእመንኪ እምፃዕረ ኵነኔ ድሩክ
ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ

ትርጉም
እሾህ በሆኑ አይሁድ መካከል ያለሽ የደጋ ያይደለሽ የቆላ የሱፍ አበባ ማርያም በአንቺ መታመኔ በከንቱ እንዳይሆንብኝ እኔን ምእመንሽን (የታመንኩብሽን) ከክፉ ኩነኔ አድኝኝ÷ አንቺ ምሕረት ልማድሽ ነውና፡፡

በመኃልይ መጽሐፉ ሰሎሞንወከመ ጽጌ ደንጐላት በማዕከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኅቤየ በማዕከለ አዋልድ፣ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ÷ እንዲሁ አንቺ ነሽይላል (መኃ 2÷2)፡፡

የቆላ ሱፍ ዙሪያውን እሾህ ቢከብበውም ከማበብና ከማፍራት ወደኋላ አይልም፡፡ እመቤታችንም ብዙ ተአምር እያለ በማያምኑና ሁልጊዜ ምልክትን በሚፈልጉ በክፉዎች አይሁድ መካከል መሆኗ በሃይማኖት ከማበብና ፍሬ ትሩፋት ከመሥራት አልከለከላትም፡፡ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግልም የሰሎሞን የትንቢት ቃል እመቤታችን በአይሁድ መካከል ፍሬ ክርስቶስን በማስገኘቷ መፈፀሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህን ትንቢቱንና ፍጻሜውን ካስረዳ በኋላመሐክኒ ለምዕመንኪ እምፃዕረ ኵነኔ ድሩክ፣ ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ - በአንቺ እናትነትና ቃል ኪዳን የምታመን እኔን ከክፉ ፍርድ አድኝኝ፤ በአንቺ መታመኔና አንቺን ተስፋ ማድረጌ ለከንቱ አይደለምና በማለት ጸሎቱን ያቀርባል፡፡

እስከአሁን በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው የማኅሌተ ጽጌ ድርሰት እጅግ በጣም በምሥጢርና በኃይለ ቃል የታጀበና ልዩ የሆነ ውበትና ጣዕም ያለው ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የሚቻለው እንዳለ ግእዙን ማንበብ፣ መረዳት ሲቻል ነው፡፡ እንኳን በግጥም መልክ የተደረሰ ድርሰት ይቅርና ተራ ንባብና ድርሰት እንኳን ሲተረጉሙት መንፈሱን መልቀቁ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ይህ የቅኔ ዓይነት አካሄድ ያለው ድርሰት ሲተረጐም እየተፍረከረከ ትክክለኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ፍዝ ይሆናል፡፡

መልክዐ መልክዖችን መተርጐም ችግሩ ይህ ነው፡፡ የአማርኛው ትርጉም መልእክቱን አልችል ይላል፡፡ ሆኖም የማኅሌተ ጽጌን መንፈሱን ለመግለጽና ስለ ምንነቱ መጠነኛ ግንዛቤ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ለመግለጽ ተሞክሮአል፡፡
ይህም የእግዚአብሐርን ጸጋ ሁላችንም በመቅረብ እንድናውቅና ማኅሌተ ጽጌ በመጸለይና ማኅሌቱን በመቆም የእመቤታችንን በረከትና ረድኤት የልጇን የክርስቶስን ምሕረት ለማግኘት ያበቃናል፡፡ ለዚህም እመ አምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ አትለየን፡፡

ታሪክ
በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሄድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡
እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥእልኪ ድንግል እዘይን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡

ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልቧ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስላዘነባት ልጅ ሳትወልድ ሞተች (ሳሙ 6÷12-23)፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ ‹‹ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ›› ዳዊት ‹‹ለእመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ›› ‹‹ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ፣ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ - ሜልኮል በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ ይሁን›› የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የእመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያክል የተረገሙ ይሆኑ? እነዚህም ‹‹በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ›› (መዝ 30÷18) ባለው ርግማን የተረሙ ናቸው፡፡

እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ሥቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣሕል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ ስዕምተ፡፡
አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ድኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያገኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር ብሎ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባዔ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው (ለአውሎጊስ) እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደሉ የማይፈርድ ጭርሱን ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከሥዕለ ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ እመቤታችን ልጇን ወዳጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡
አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ ‹‹ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ›› ማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባን እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡

ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢተኃሥሢ፣
እመንበረ ላዕክኪ ቢምዕር ከመገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣ 
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡
የእመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው እጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል ‹‹ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው›› ቢሉት ‹‹እኔም እንደርሰ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ፣ ከእርሱ በምን አንሳለሁ?›› በማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ታሪክ ነው፡፡
‹‹ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጂ፣ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ፣ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተበቀልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኵያን ኀጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን (ማለት የልጅሽን) ኀይል ይዘሽ ተነሽ›› በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም እመቤታችን እኛንም ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡

በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒኪ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አጺዋ፣
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጤዋ፡፡

አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋች ገነትን ‹‹እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣ ያለ አንቺ ጽጌ (ያለ ክርስቶስ) በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም›› (ዘፍ 3÷24)፡፡ ‹‹ካንቺ በተገኘ በክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች›› ይላል፡፡

በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ ክርስቶስ ሰው መሆንና በመስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ ክርስቶስ ደግሞ ከእመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት ‹‹መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ›› (ኢሳ 46÷1) እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽዮን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡  
ጸሎት
በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
አንበርኒ ማርያም ውስጥ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሒትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ በጽጌሁ ሕይወት፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ ‹‹እንደ ማኅተም በልብህ፣ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ›› (መኃ 8÷6) ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ ‹‹አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተም ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልትእመቤታችንን ‹‹እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ›› በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ ‹‹በእንተ ርስሒትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት›› ይላል፡፡ ይኽም ማለት ‹‹አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ›› በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ ‹‹መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ›› እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡  
ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረስዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ እኅሊ፣
ሥርዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ ‹‹ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝይላል፡፡ ጌታችን ‹‹እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም›› (ማቴ 17÷20) በማለት ላመነ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ብሎ ባበሰራት ጊዜ ‹‹ይህ እንደምን ይሆንልኛል›› አለች፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› ቢላት በፍጹም እምነት ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ - እንደቃልህ ይሁንልኝ›› በማለት ተቀበለች፡፡ ይህንንም ቅድስት  ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ ‹‹ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት›› (ሉቃ 1÷45) ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልዪልኝ በማለት የለመነው፡፡
 ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት፣
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፅት፣
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡
‹‹ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረ ኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽ በሐመልማል የታየ ማርያም ሆይ በእሳት አምሳል የታየ ጽጌ-ልጅሽ ኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡››
ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ (ዘጸ 3÷3)፡፡ ይህ የምሥጢረ ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ ሐመልማሉ የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱ አምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮት ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረጋጋት የሚያስረዳ ነው፡፡

ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርና የርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ መሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን ‹‹ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀቅ÷ ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ›› በማለት ያቀርባል፡፡ ይኽም ማለት ‹‹ ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴን ያስተስርይልኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ›› ማለት ነው፡፡

ዳዊት ‹‹በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል›› (መዝ 86÷7) ብሎ እንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ 

ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡
 እመ አምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ

No comments:

Post a Comment