ደቂቀ ናቡቴ

Thursday, October 4, 2012

†♥† “ተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንሕነ ወሰብዕሰ ከመሣዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ” †♥†



ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አባዊነ!
ከመስከረም26- ኅዳር 6 - ዘመነ-ጽጌ
“ተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንሕነ ወሰብሰ ከመዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ” (((መዝ.፻፪/፻፫፡፲፬-፲፭ (102/102፡14-15)))
ትርጉም፡- “አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ። ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤” (((መዝ.፻፪/፻፫፡፲፬-፲፭ (102/102፡14-15)))
† ሁሉን ቻይ ታላቅ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ በቀንና በሌሊት የአንተን መኖር አስታውስና፣ አንተን ሁል ጊዜ በፊቴ አደርግህ ዘንድ ልቤን ምራልኝ፤ በኪሩቤል ላይ የምትኖር የቀለያትንም (ጥልቅ ባሕርንም) ጥልቀት የምትመለከት ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ አቤቱ ምስጢርን ግለጽልኝ፤ ቃልህንም እናገር ዘንድ፣ ያለመሰልቸት ስለ አንተ እንድመሰክር አንተ አንደበት ሁነኝ አሜን።”

የተዘሩ አዝርዕት በቅለው የተተከሉ አትክልት ጸድቀው አብበው አፍርተው የሚታዩበት የጽጌ የልምላሜ ወቅት በመሆኑ “አሰርጎኮ ለሠማይ ወከዋክብት ወለምድርኒ በስነ ጽጌያት  ግብረ እደዊከ አዳም እግዚኦ” እያልን ጌታን የምናመሰግንበት ጊዜ ነው።
“ጽጌ” ማለት አበባ” ማለት ሲሆንዘመነ ጽጌ” ማለት የአበባ ዘመን” ማለት ነው፡፡ በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡ በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት በፍቅርና በደስታ ይዘክሩታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማግኘት በርካታ ክርስቲያኖች የአዋጅ ጾም ባይሆንም በፈቃደኝነት ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡

 †ይህ ወቅት የእመቤታችንን ስደት የምናስብበት ጊዜ ነው። ይህስ እንደምን ነው? ቢሉ ጌታ በተወለደ ጊዜ ቤተልሄም በእሳት ተቀጽራ አጋንንት ለማየት ሄደው አቅቷቸው ላለቃቸው ነግረውት እሱም በኪሩቤል አምሳል አራት ተሸካሚዎች አዘጋጅቷልና ተሸክመው ቢወስዱት መላእክተ በሐጸ እሳት እየነደፉ አላስቀርብ አሉት። የኔን ፅልጣን ያንተን መንግስት የሚነጥቅ ንጉስ ተወልዷልና ልብሰ ቀለብ እሰጥሃለሁና ዓመት ዓመት ከመንፈቅ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ሕጻናት ሰብስቡልኝ ብለህ ፍጃቸው ከነርሱ አንዱ ይሆናል ብሎ ላከበት። ሄሮድስ አወሰጁን አስነግሮ ያላቸው ልጆቻቸውን ልጆች የሌላቸው ልብስ ቀለብ ለመቀበል እየተዋሱ ሲሰበሰቡ ፲፬ /14/ እልፍ ከአራት ሺህ ሕጻናት አስፈጅቷል። (((ማቴ.፪፡፲፮ /2፡16/)))
“እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። ማቴ.፪፡፲፫ /2፡13/  
የእመቤታችን ስደት የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ስደት ነው፡፡ ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፈው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ሰብአ ሰገልየተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ?” በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናልእያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፈሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡

ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡ ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡ ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ /በአማካሪዎቹ ግፊት ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት የሚሆን ዕድሜ ያላቸውን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. ፩፡፲፫-፲፰ (1፡13-18)

እነርሱም (ሰብአ ሰገል ) ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡”  /ማቴ. ፪፡፲፫-፲፬ /2፡13 14/ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሔደ፡፡ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያ ኖረ፡፡ /ማቴ ፪፡፲፫-፲፭ /2-13-15/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ፤ ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳድደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስደታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥተው ሀገራችንን ባርከዋል።በኪደተ እግራቸውም ጣና ሐይቅን፤ ዋልድባንና ሌሎችንም ቦታዎች ዞረው እንደባረኩ ድርሳነ ኡራኤልና ተአምረ ማርያም ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/፡፡

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን “.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..” የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡ በኋላ በዚህች ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን በእመቤታችን ስም ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን ተከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ /384-412 ./  ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል

ነቢያት ስለጌታ ትንቢት በመናገራቸው፣ እመቤታችን የጌታ እናት በመሆኗ፣ ሐዋርያት ስለጌታ በማስተማራቸው ተሰደዋል፡፡ የጌታ አገልጋይም እናትም የሆነችው የእመቤታችን ስደት ግን. . . ከሁሉ የሚለይ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት ልዩ የሚያደርገው:-

1.
ሕግን በመተላለፉ ከገነት ተሰዶ የነበረውን አዳምን ለመካስ የተደረገ በመሆኑ
2.
በግብጽ ነግሦ የነበረውን አምልኮት ጣኦት ለማሳደድ የተደረገ ስለሆነ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ግብጽ ስትሰደድ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር አግኝቷታል፡፡ እሾህ እየወጋት እንቅፋት እየመታት ተጉዛለች /ተሰዳለች/ በስደቷም ረሃብና ጥም፣ ችግርና መከራ ደርሶባታል፡፡ በበረሃው ወንበዴዎችን ባየች ጊዜም በስደት ከሄሮድስ ጭካኔ ከሀገር ያወጣሁትን ልጄን ይገድልብኛል ብላ መሪር እንባ አልቅሳለች፡፡በስደቷ ወቅት በደረሰባት ረሐብና ጥም የተነሣ ወደ መንደር ገብታ ብትለምን በችግር ምክንያት የሰው ፊት ማየት ከእሳት የበለጠ ወላፈኑ ስለሚያቃጥል የሰው ፊት ገርፏታል፡፡ የትእማን ቤተሰቦች ዘብተውባታል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሸክማችንን ሊሸከም ነውና ውኃውን ለፍጥረታት የሚሰጥ እርሱ እየጠማው፤ እንስሳትን የሚመግብ እየራበው ምድርን በልምላሜ የሚያለብስ ተራቁቶ፣ የኛን ከገነት መሰደድ የመጣብንን ዕዳ ሊክስልን ከእናቱ ጋር ተሰደደ፤ ድንግል ማርያምም የአምላክ እናት ሆና መከራን ቀመሰች፡፡ ጌታን አዝላ በረሐብ አለንጋ ተገረፈች፡፡ በመጨረሻ ግን ሁሉ የመከራና የስቃይ ስደት ሲያበቃ አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽሲል በመኃልየ ማኀልይ ዘሰሎሞን ተነግሮ የነበረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከዚያ ሁሉ መከራና ስደት በኋላ ልጇን ይዛ ወደ ናዝሬት ተመልሳለች፡፡

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ «ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲነግሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» /ማቴ 5-11/ የሚለውን የስደት ዋጋ ጭምር እያሰብን መሆን ይገባል፡፡

ይህንንም የእመቤታችንን ስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ በማኅሌትና በመዝሙር ትዘክራለች፡፡ ካህናቱም በዕለተ ሰንበት ከምሽት ጀምረው በማኅሌትና በመዝሙር ምስለ ፍቁር ወልዳን /የልጇ እና የእርሷ/ ሥዕል ይዘው ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡ ይህም የእመቤታችንን ስደት ለማጠየቅ ነው፡፡ ሌሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰባቸውን መከራ ለማስታወስ የፍቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በቅድስት ቤተክርስቲያን ተገኝተን በመንፈስ የሩቁን አቅርበን የእመቤታችንን ስደት በእምነት እያየን በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታችን በዜማ «መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ንጹሕ፣ ፀአዳ ፣ቀይህና ብሩህ የሚሆን ልጅሽን ታቅፈሽ ርኅሩኅ የሆነ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትለሽ ከሐዘናችንና ከችግራችን ታረጋጊን ዘንድ ፈጥነሽ ድረሽልን» ልንላት ያስፈልጋል፡፡ በቅዳሴያችንም «ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ፣ ረሃበ፣ መከራ ሁሉ አሳስቢ እንላለን፡፡ አሜን።
ዋቢ መጽሐፍት፡-  መዝገበ ታሪክ ዘኦረቶዶክስ ተዋህዶ፣ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦረቶዶክስ ተዋህዶ፣ መጽሐፈ ስንክሳር።
ስብሐት ወክብር ለእግዚአብሔር
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡ እድሜ ለንሰሐ ዘመን ለፍሰሃ ሰጥቶኝ ይህችን ታህል ስለ አባታችን እንድመሰክር የረደኝ አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

3 comments:

  1. አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡

    ReplyDelete