ደቂቀ ናቡቴ

Wednesday, September 26, 2012

"ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን"



"ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን" (ቤተ ክርስቲያንን ሰሯት)
“ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው።” መዝ.፷፬/፷፭፡፭
 “በኢሩቤል ላይ የምትኖር የቀለያትንም (ጥልቅ ባሕርንም) ጥልቀት የምትመለከት ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ አቤቱ ምስጢርን ግለጽልን፤ ቃልህንም እንናገር፣ እናስተላልፍም ዘንድ ሁኔታዎችን ሁሉ አመቻችልን።”

ይህ ዕለት መስከረም ፲፮ (16) ቀን ብቻ ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን ይባላል:: በዚህ ቀንም እንደ ሌሎቹ ቀናት ሁሉ አምልኮተ እግዚአብሔር በመዝሙር በቅዳሴ ይደገማል።
የመዝሙሩ ርዕስ፡- "ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን" (ቤተ ክርስቲያንን ሰሯት)
በቅዳሴ ጊዜያትም ፩. በዲያቆኑ (ገባሬ ሰናዩ) 1ቆሮ.3፡1-18 ያለውን ፪. ዲያቆን (ንፍቁ ዲ.) ራዕ.21፡10 ፫ ረዳቱ ቄስ (ንፍቁ ካ.) ሐዋ.7፡44-51 ያነባሉ።
ምስባክ፡- በገባሬ ሰናዩ (ዋናው) ዲያቆን የሚሰበከው ምስባክ
ደብረ ጽዮን ዘአፍቀረ
ሐነጸ መቅደሶ በአርያም
ወሰረራ ውስተ ምድር ዘለዓለም
አማርኛ፡- የወደደውን የጽዮንን ተራራ።
        መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥
        ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት። መዝ.77(78)፡69
ምስጢር (ትርጉም) ይህ ምስባክ ደ/ጽዮን (ቤተ መቅደስን፣ እመባታችንን፣ ምዕመንን) የወደደ እርሱ እንደወደደ መመስገኛ የምትሆን ቤተ መቅደስን በልዕልና ሰራት፤ እመቤታችንን ለማደሪያው ፈጠራት፤ ምዕመንንም በሞቱ በደሙ ቀድሶ ማደሪያው አደረጋት፤ በዚህ ዓለም (እመቤታችን በክብር ምዕመናን በሕይወት በክብር አጽንቶ ሰራት የሚያሰኝ ትርጉም የያዘ ነው።
በዚህ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍል (በዋናው ቄስ) ዮሐ.10፡22 እስከ ፍጻሜው ድረስ።

ማስገንዘቢያ፡- ከዚህ በላይ ያየናቸው መዝሙረ ያሬድ፣ ክፍላተ መጻሕፍት፣ ቅዳሴው ሳይቀር ስለ ቤተ መቅደስ ክብር የሚናገሩ፣ የእግዚአብሔር ማደርያ ቤተ መቅደስ ምን እንደሆነ የሚያስገነዝቡ ናቸው።
የእለቱ ትምህርት ርዕስ
“የእግዚአብሔር ማደርያ (የታነጸች ቤተ መቅደስ)
 ቤተ መቅደስ ማለት የእግዚአብሔር ማደሪያ ማለት ነው። ቅዱስ እግዚአብሔ ክብሩ ስለሚገለጥበት፤ ስሙ ስለሚቀደስበት፣ መሚያድርበት አምላክ ስለተቀደሰ፣ በውስጡም የሚያመልኩት በክርስቶስ ደም የተቀደሱ ቅዱሳን ምዕመናን ስልሆኑ ቤተ መቅደስ ይባላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር የሚያድርባቸው ክብሩ የሚገለጥባቸው ሁሉ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ እግዚአብሔር ይባላሉ።  በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የቤተ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚለው ሐሳብ በአራት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ።
. “ሰማይ፣ ምድር፣ ሕዋው፣ ውቅያኖስ የእግዚአብሔር ማደሪያ” ይባላሉ።
እግዚአብሔር ምልአተ መለኮቱ የማይወሰን፣ ምድርና መላዋ የማትወስነው፣ ሕዋው ውቂያኖስ የማይችለው ምሉዕ፣ ስፉሕ አምላክ ስለሆነ “ሰማይ፣ ምድር፣ ሕዋው፣ ውቅያኖስ የእግዚአብሔር ማደሪያ” ተብለው ተጠቅሰዋል። ስሙ መድኃኒት የሚል ትርጉም ያለው ኢሳያስ “ሰማይኒ መንበርየ ወምድርኒ መከየደ አየኑ ቤተ ተሐንጹ ሊተ ለስምየ”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር። ኢሳ.፷፮፡፩-፲፪ /66፡1-12/
ክቡር ዳዊትም እንዲ አለ….. “አይቴ አሐውር እመንፈስከ ወአይቴ እጎይይ እምቅመ ሀጽከ” እመኒ ዐረጉ ውስተ ሰማይ ህየኒ አንተ ወእመኒ ወረድኩ ውስተ ቀላይ ህየኒ ሀሎከ” /“
 ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር።”/ መዝ.፻፴፰/፻፴፱፡፯-፱/ 138 (139)፡7-9  
“ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። ት/ኤር.፳፫፡፳፬(23፡24)
”በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!” ፩ነገ.፰፡፳፯ (1ነገ.8፡27)
፪. “የተወሰነ ቦታ” የእግዚአብሔር ማደሪያ (ቤት) ይባላል።  
እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር የሚገናኝበት፣ ምዕመናን ቃሉ የሚሰሙበት፣እምባቸውን በጸሎት በንሰሐ የሚያፈሱበ፣ በጉባኤያቸው አምላክ በረድኤት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ቤት ይባላል።
”ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” 
 ማቴ. ፲፰፡፳ (18፡20)
ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና።ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶ ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። ማቴ.21፡121-13
የብሉይ ኪዳን መረጃ፡- ዘፍ.፳፰፡፲፪-፳፪ (28፡12-22)፣ ዘጸ.25፣ 1ነገ.8፡12-52፣ 1ነገ.9፡1፣ 2ዜና. 6፡1፣ 1ዜና. 8፡1፣ 2ዜና. 7፡4፣ ሐጌ 1፡2-13፣ ሐጌ2፡4 ዘካ.4፡8፣ መዝ.64፡4፣ መዝ.131፡7
የአዲስ ኪዳን መረጃ፡- ማቴ.21፡12፣ ማር.11፡15፣ ዮሐ.2፡13፣ ሉቃ.24፡53
ከዚህ በላይ ያየናቸው ጥቅሶች የተወሰነ ቦታ የእግዚአብሔር ቤት እንደሚባልና በዚያም ለእግዚአብሔር እንደሚሰገድ ያስገነዝባሉ።
፫. “አካለ ክርስቲያን” የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይባላል።
መረጃ፡- 1ኛቆሮ.3፡16፣ 6፡16፣ ሮሜ 8፡9፣ 2ቆሮ.6፡16
”የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” (1ኛቆሮ.3፡16)
”እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (2ቆሮ.6፡16) በእነዚህ ጥቅሶች የሰዎች ሕይወት  “የእግዚአብሔር ቤት” መሆኑን ይገልጻሉ። በሞት ቢፈርስ በትንሳኤ የሚታደስ ከእንጨት፣ ከኖራ፣ ከጭቃ፣ ከድንጋይ ያልተሰራ፣ የአምላክ ቤት፣ የአምላክ ቤተ መቅደስ ነው። ኤፌ.2፡20፣ 1ጴጥ.2፡3-6፣ ራዕ.1፡6-7
አንባቢ ሆይ! ሕይወታችንን በኃጢአት አናሳድፍ፤ ያደረብንን መንፈሰ እግዚአብሔርንም እንዳናሳዝን እንጠንቀቅ ለቤዛ ቀን ታትመንበታልና። ነቅተንም ንሰሐ እንግባእላለሁ።
 ፬. “ኢየሩሳሌም ሰማያዊት የእግዚአብሔር መቅደስ፣ የማደሪያው ድንኳን ትባላለች።”   
“ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራዕ.21፡1-4)
መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች፡- ራዕ.21፡1-4፣ 22፡4-5፣ መዝ.14፡1   
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁ  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡ እድሜ ለንሰሐ ዘመን ለፍሰሃ ሰጥቶኝ ይህችን ታህል ስለ አባታችን እንድመሰክር የረደኝ አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡


1 comment: