Thursday, September 8, 2011

የሐረሩ ስልጠና

በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • ገበየሁ ይስማው ሥልጠናው መካሄዱን አመነ የሠልጣኖች ምልመላ ሂደትን አብራርቷል
  • የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ለጉባኤ ከአዲስ አበባ ሳባኪ እንዳይጠራ ወሰነ
  • ማኅበረ ቅዱሳን በተሐድሶ ሰራዊትነት የሰለጠነ አባል የለኝም አለ
  • ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፈሉ
    ገበየሁ ይስማው
    ገበየሁ ይስማው
በቅርቡ በሐረር ከተማ በሉተራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተሐድሶ ሰራዊትነት ዙርያ የተሰጠው ሥልጠና ልዩ ልዩ ውጠየቶችን እያስከተለ እንደሆነ የምስራቅ ኢትዮጵያ የገብር ኄር መንጮች ገለጹ፡፡
ሐረር
የሐረር ከተማ እንዳንድ ምዕመናን ግብረ ተሐድሶን በተመለከተ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እነዚህ ምዕመናን ‹‹በሌሎች አህጉረ ስብከቶች የታገዱ መምህራን ለምን ሐረር ላይ እንዲያስተምሩ ይፈቀድላቸዋል? በከተማው እየተፈጸመ ባለው ግብረ ተሐድሶ ላይ ሀገረ ስብከቱ አፋጣኝ እርምጃ ለምን አይወስድም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ እና በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ያሬድ ሰባሳቢነት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ቀን በክብረ በዓላት ወቅት በሀገረ ስብከቱ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር አንድም ‹‹መምህር›› ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከአዲስ አበባ እንዳይጠራ ወስኗል፡፡ በስብሰባው  ‹‹ምእመናን መማር ያለባቸው በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ሊቃውት መሆን አለበት፡፡ እኛ ሊቃውንቱን መድረክ ስለነሳናቸው ነው ሕገ ወጦች አውደ ምህረቱን የተቆጣጠሩት ›› የሚል ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡
ብጹዕ አቡነ ያሬድም በሀገረ ስብከታቸው እየተፈጸመ ያለውን ግብረ ተሐድሶ በተጠናቀረ መረጃ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀዋሳዎችን አሰረ ፍኖት የተከተሉ የሐረር ከተማ ትጉኀን ምእመናን በከተማችው በሀገረ ስብከታቸው እንዲሁም በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለው የተሐድሶ ክንፍ ምን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ በበቂ መረጃዎች የተደራጀ ቪሲዲ ለማሰራጨት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ዘለግ ላሉ ዓመታት በተሐድሶ ሴራ የተሰቃዩ የሐረር ምእመናንም ቪሲዲው የተንኮለኞችን ሴራ በማጋለጥ እፎይታ እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡
ድሬዳዋ
ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ ውሉደ ተሐድሶ ድርጊታቸው በመጋለጡ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፍለዋል፡፡ በሦስት ሠልጣኞች ሦስት የተለያዩ ሀሳቦች ታይተዋል፡፡ የመጀመሪያው በግልጽ ወደ ሥልጠናው ሲገባ እና ሲወጣ በተቀረጸው የቪዲዮ ምስል እየታየ ለሚጠይቁት ሁሉ  ‹‹እኔ ዘመድ ልጠይቅ ወደ ሩቅ ሀገር ሄጄ ነበር የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከናካቴውም ሐረርን አላውቃትም ሔጄም አላውቅም›› በማለት ራሱን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡
ሁለተኛው ግለሰብ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በሐሰት አቀናብሮብኝ ነው እንጂ እኔ የማውቀው ጉዳይ የለም ›› በማለት እንደ ኦሪት ኃጢአተኛ በደሉን የሚሸከምለት ፍየል ለመፈለግ ሞክሯል፡፡ አክሎም ‹‹ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሬ ሰዎች በእኔ ላይ ማስረጃዎችን እንደሚያሰባስቡ አውቃለሁ ተገኘ የሚባለው ነገር ፍጹም ሐሰት ነው›› በማለት ቀርበው ለጠየቁት ግለሰቦች ሲመልስ ተሰምቷል፡፡‹‹የሥልጠናውን ሂደት የቀረጹት የሚያሳድዱኝም ሸዋዎች ናቸው›› በማለትም ለኑፋቄው የዘረኝነት መከላከያ ጭንብል ሊያጠልቅለት ሞክሯል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሁለቱ ግለሰቦች የአንድ ደብር ‹‹ሰባክያነ ወንጌል›› ሲሆኑ ቀጥለን የምንገልጸው የግብር አጋራቸው ድርጊታቸውን እንዳጋለጠባቸው ይጠረጥራሉ፡፡
ሥስተኛው ሰው ሁለቱ ወዳጆቹ የከፈቱለትን ቀጭን መውጫ ቀዳዳ በመጠቀም አንድ አካል መረጃ እንዲያጠናቅርለት ልኮት እንጂ አምኖበት ወደ ስልጠናው እንዳልሄደ ቅርብ ለሚላቸው ወዳጆቹ ተናግሯል፡፡ ጨምሮም ያሰባሰበውን መረጃ ለማኅበረ ቅዱሳን መላኩን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከሰልጣኞች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባል የሆነ አንድ ግለሰብ መኖሩን የተረዱ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማዕከልን ‹‹እንዴት ከእናንተ መካከል እንዲህ ያለ ሰው ይገኛል›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ማዕከሉም እንዲህ አይነት አባል የለንም በማለት አስተ
ባብሏል፡፡ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ከስድሳ ሺህ በላይ አባላት ካሉት ማኅበር እንዲህ ያለ መልስ አይጠበቅም፡፡ ማኅበሩ ሁሉንም አባላት የት እንደሚዉሉና እንደሚያድሩ በማያውቅበት ሁኔታ ድፍን ያለ መልስ ከመስጥት ተቆጥቦ የደረሰውን ጥቆማ በመቀበል ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ በመረጃ የተደገፈ ምሁራዊ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ገብር ኄር ግን የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ችላ የሚሉት ከሆነ ከአስተባባሪው ከገበየሁ ይስማው ጀምሮ በሁሉም ላይ ያሉትን  ዝርዝር መረጃዎች ለምእመናን የሚያሳውቅ መሆኑን ለመግጽ ይወዳል፡፡
በተያያዘ ዜና የገብር ኄር ዜና ዘገባ እንደ ሐሩር እሳት ያቃጠለው የአሰበ ተፈሪው ገበየሁ ይስማው ‹‹ሥልጠናው እንደተባለው ኢየሱስን ማለማመድ ሳይሆን ሰባክያነ ወንጌል የዓለም ሃይማኖቶችን አንድ ለማድረግ እንዴት ማስተማር ይገባቸዋል የሚል ነበር›› ብሏል፡፡ የሠልጣኞች ምልምላን
በተመለከተ ‹‹እኛ ሁሉንም ነው የጠራነው ደፍሮ የመጣውን አሠልጥነናል›› በማለት ገልጿል፡፡ ሴራው በመጋለጡ የተደናገጠው ገበየሁ ‹‹የቀረጹትንም ሆነ ፎቶ ያነሱትን እናውቃቸዋለን በመንግስት ጭምር እየተፈለጉ ነው ለሕግ እናቀርባቸዋለን›› በማለት የሐረር ምእመናን የተሐድሶን ሴራ ለማጋለጥ በሚያደርጉት ጥረት እየደረሰባት ያለውን ውርደት ለመከላከል  አልሞት ባይ ተጋዳይነቱን አሳውቋል፡፡
መረጃው የደረሳቸው የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ መረጃው ጠቃሚ እንደሆነና በሀገረ ስብከታቸው የእርምት እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ እነደሚገደዱ መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!! By ገብር ኄር

Friday, September 2, 2011

የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ

‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ


በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ አራት ሀገረ ስብከቶች ለተውጣጡ ‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ



በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • የሥልጠናው ዋና ርዕሰ ጉዳይ ኢየሱስን ማለመመድ የሚል ነበር
  • ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል
  • ፓስተር መስፍን ፤ገበየሁ ይስማውና  በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል
  • ለሥልጠናው ተሳታፊዎች ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚል ማስታዎሻ እና መጸሐፍ ተሰቷቸዋል
  • ከሠልጣኞቹ መካከል ቀደም ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በክረምት ተተኪ መምህራን ሥልጠና አሰልጠኗቸው ከነበሩት ሠልጣኞች አንድ ግለሰብ ተገኝቷል
ከድሬዳዋ ፤ ከሱማሌ ፤ ከምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ አህጉረ ስብከቶች የኦርቶዶክስ  አብያተ ክርስቲያናት ለተውጣጡ ‹‹የቤተክርስቲያን አገልጋዮች›› ግበረ ተሐድሶን በሚያስፋፉበት ስልት ዙርያ ሥልጠና መሰጠቱን  በሰነድ እና በድምጽ ወምስል የደረሰው መረጃ አመለከተ፡፡
‹‹ሃይማኖቶችን አንድ እናደርግ ሁላችንም በቀን አንዳንድ ሰው እንለውጥ›› በሚል መርህ የተጀመረው ሥልጠና በሐረር ከተማ ሉትራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከነሐሴ 23-30 ሊሰጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ትላንት ማምሻውን መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ሥልጠናው ዘወትር ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽት 2፡30 እንደተሰጠ ለመረዳት ተችሏል፡፡የሰሌዳ ቁጥሩ ዕድ 00122 የሆነ ተሸከርካሪ ለሥልጠናው አስፈላጊ የሆኑ ሎጀስቲክስ ለማሟላት ሥራ ላይ ውሏል፡፡
የሥልጠናው ዋና አሰልጣኝ የቀድሞ የሐረር ቀበሌ 10 ሊቀ መንበር የአሁኑ ፓስተር መስፍን ነው፡፡ሌሎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች የመጡ በርካታ ፓስተሮች በአሰልጣኝነት የተሳተፉ ሲሆን ዋና አስታባባሪው ደግሞ ከአሰበ ተፈሪ ለዚሁ ሥራ ወደ ሐረር ያቀናው ገበየሁ ይስማው ነው፡፡ገበየሁ ይስማው በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም የሥራ ኃላፊነት የሌለው ባለበት የሃይማኖት ችግር በተነሳ ውዝግብ በመቐሌው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የተማረውን የዲግሪ መርሀ ግብር ማስረጃ ያለተሰጠው ወልደ ተሐድሶ ነው፡፡በዚሁ ምክንያት በምዕራብ ሐረርጌ የይብሮ ወረዳ ኮተራ ቅዱስ ገብረኤል ምዕመናን አታስተምረንም በማለት እነዳባረሩት ይታወቃል፡፡ፓስተር መስፍን እና ገበየሁ ይስማው በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሥልጠናው ዋና ትኩረት የተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ኢየሱስን የማለማመድ ትምህርት›› ነው፡፡በዚህም ሠልጣኞቹ የበጋሻውን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ተደጋግሞ ሲመከሩ ተስተውሏል፡፡ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት ግለሰቦች ከሐረር ከጅጅራ ከሰበ ተፈሪ እና ከድሬ ዳዋ ከተሞች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ሲሆኑ ከነዚህ መካካል ማኅበረ ቅዱሳን በ2000 ዓ.ም ክረምት በጅማ ለግቢ ጉባዔያት ተተኪ መምህራን አዘጋጅቶት በነበረው ሥልጠና ተሳታፊ የነበረ አንድ ግለሰብ ይገኝበታል፡፡ በቅርቡ አባ ሠረቀ ብርሃን በመቐሌ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ አካሂደውት በነበረው ውይይት አንድ የኮሌጁ ደቀመዝሙር ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ካህናት ማሰልጠኛ ምንፍቅና አስተምሮኛል›› ብሎ መናገሩን ያስታወሱ ታዛቢዎች ማኅበሩ የሠልጣኞች ምልመላ ስርዓቱን መሰፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የሥልጠናውን ሙሉ ሂደት የሠልጣኞችን ዝርዝር የያዘ የሰነድ የፎግራፍ እና ቪዲዮ መረጃ ደርሶናል፡፡የተሐድሶን ሴራ በማጋለጥ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳንም መረጃው ተጠቃልሎ ደርሶታል፡፡የስልጠናው ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ከያዙት ቦታ እና ሊያደርሱት ከሚችሉት አደጋ አንጻር ማኅበሩ መረጃ አለኝ በሚል አጉል ብሒል እርምጃ ለሚወስዱ የቤተክርስቲያኒቱ አካል ፈጥኖ የማያደርስ ከሆነ ታሪክ የማይረሳው ስህተት እየፈጸመ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሚጠቀምበት ከሆነ ይህንን መረጃ ያጠናቀሩ የቤተክረስትያን ልጆች እንደ ሀዋሳ ምዕመናን የድርሻቸውን ለመወጣት ቪሲዲዎችን በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡እንደ አግባብነቱ መረጃዎችን ወደ ፊት የምንገልጥ መሆኑን እያስታወቅን ይህንን መረጃ በመሰብሰብ እና ለተገቢው አካል በማድረስ ለተጉት የቤተክርስቲያን ልጆች ያለንን አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!! ››  by http://andadirgen.blogspot.com/2011/09/blog-post_9564.html