Wednesday, August 8, 2012

የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ፆመ ፍልሰታ


ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.1318/
ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኲሕ ቅሩበ ጥቅም፡፡ አቅራቢያዬ መልካሟ ርግብየ ተነሽ፤ ነዪ፤ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው ጥላ፡፡” /መኃ.210-14/ 
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መቅደሱ፥ ታቦቱ፣ ማደሪያው፣ መንበሩ እናቱ አድርጎ መረጣት፡፡ ስለዚህ ምክንያት አብ ጠበቃት ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ከርሷ ተዋሐደ መንፈስ ቅዱስ አጸናት፡፡ እመቤታችን በዚህ ኃላፊ ዓለም 64 ዓመት ቆይታለች፡
በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት ይቻላል፡፡ እንደዚሁም በጾም አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡
ጾም» ማለት «ጾመ»  ተወ፣ ታቀበ፣ ታረመ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን የቃሉ ትርጉም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው:: ጾም ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ሁሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቆጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ነው መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው «ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ፡፡» ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለሆነ ሳይሆን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ በዋናነት ስንጾም ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከር ወዘተ መቆጠብ አለብን፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የማኅበር /የዐዋጅ/ ጾም በዓመት ውስጥ የሚጾሙት ሰባቱ አጽዋማት  አሉ:-
1.   ጾመ ነቢያት /ከኅዳር 15-ታኅሣሥ 29/
2.   ጾመ ነነዌ /ከጾመ ሁዳዴ መግቢያ 15 ቀን በፊት ያሉት ሦስት ቀናት ከሰኞ እስከ ረቡዕ/
3.   ጾመ ሁዳዴ /ከጾመ ነነዌ 15 ቀናት በኋላ፤ 55 ቀናት ይጾማል/
4.   ጾመ ገሃድ /የገና ዋዜማ እና ጥር 10 ቀን/
5.   ጾመ ድኅነት /ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ከሚመጣው ረቡዕ ጀምሮ/
6.   ጾመ ሐዋርያት ከበዓለ ሃምሳ ማግስት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 5/
7.   ጾመ ፍልሰታ /ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 ቀን/
ሰባቱ አጽዋማት ፆመ ፍልሰታ /ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 ቀን/ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ምእመናንን በፆም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት ይማጸናሉ፡፡ ሁሉም እንደሚደረግላቸው ያምናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም «በእውነት ተነሥታለች» ብለው በደስታ የፆሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡



የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ  «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል  እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን) ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማክረው መጡ፡፡
 ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ  ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡  ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው  ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት  ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ 14 (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት  በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ 12 ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን  እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
  
ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ሆነ?»  ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምስጢሩን ደብቆ «አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር  እንደምን ይሆናልአላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ  የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ  የሆነውን ሁሉ ተረከላቸው፡፡ ከዚያም ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄዱ፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

በዓመቱ ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እንዴት ይቅርብን ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ ነሐሴ 16 ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የለመኑትን ልመና ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት) ቄስ) ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ ትንሣኤዋን ዕርገቷን እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በመዝሙር ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ «እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች»፡፡
የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡  እንደዚህ ያለውን ትንሣኤ ከእርሷ በቀር ሌሎች ቅዱሳን ወይም ነቢያትና ሐዋርያት አላገኙትም በዚህም ሁኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ከማናቸውም ትንሣኤ ልዩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ የሆነ ከዳግም ሞተ ሥጋ ነጻ የሆነ ትንሣኤ ነው፡፡

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከመቃብር መነሣት ነሐሴ 16 ቀን የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚያስረዳን አባቷ ዳዊት በገናውን እየደረደረ ጸሐፊው የነበረው ዕዝራም መሰንቆውን ይዞ ቅዱሳን መላእክት ነቢያትና ጻድቃን እያመሰገኗት በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ ዐረገች ከዚያም በክብር ተቀመጠች፡፡ በዚያም ስፍራ ሁለተኛ ሞት ወይም ሐዘን ጩኸትና ስቃይ የለም የቀደመው ሥርዐት አልፎአልና (ራዕ 214-5)፡፡
የእመቤታችን ዕርገትም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ዕርገት የተለየ ነው፡፡  ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድር ሳለ እግዚአብሔርን በእምነቱና በመልካም ሥራው ስለአስደስተና በሥራውም ቅዱስ ሆኖ ስለተገኘ ሞትን እንዳያይ ዐረገ፡፡ ወደፊት ገና ሞት ይጠብቀዋል ሞቶም ትንሣኤ ዘጉባኤ ያስፈልገዋል፡፡ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም» (ዕብ 115)፡፡

ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላ ተነጥቋል «እነሆ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ»  (2 ነገ 210)፡፡ ነቢዩ በእሳት ሠረገላም ቢነጠቅም ወደፊት ሞት ይጠብቀዋል፤ ትንሣኤ ዘጉባኤም ያስፈልገዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ ስለ ዕርገትዋ ጽፏል፡፡ በቃልዋ የታመነች በሥራዋም የተወደደች ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክት እያመሰገኗትና በመንፈሳዊ ደስታ እያጀቧት ወደ ሰማይ አሳረጓት ሲል በዘመረው መዝሙር አስረድቶናል፡፡


የእመቤታችን አማላጅነት የትንሣኤያችን በኲር የሆነው የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

11 comments:

  1. betm des yemil temehert new. egeziyabeher yestelegn. ye ageagelot zemenachun yebark.

    ReplyDelete
  2. eskezariy derese alawekem neber ahun degemo maweken efelege neber egzeyabehirem fekadu hone.

    ReplyDelete
  3. sile weladite amilak mesimat endet des yilal!

    ReplyDelete
  4. እግዚአብሔር ይስጥልን መካሪ ዘካሪ አያሳጣን ቃለ ህይወት ያሰማልን::

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሰማልን መካሪ ዘካሪ አያሳጣን፡፡

    ReplyDelete
  6. ቃለ ህይወት ያሰማልን አባቶችን ከቦታው አያጥፋብን ስለ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም መስማት እንደት ያስደስታል

    ReplyDelete
  7. egzabher yistln kale hiwet yasemaln geta

    ReplyDelete
  8. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን። አሜን።

    ReplyDelete
  9. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን። አሜን።

    ReplyDelete
  10. እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን
    አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  11. እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን
    አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete