Wednesday, August 22, 2012

በምንኩስና ከዓለም መለየት እና የምነኩስና ቆብ፡፡

ምንኩስና በምንኩስና ከዓለም መለየት
ምንኩስና ማለት አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆኖ እግዚአብሔርን በማገልገልና እሱን ብቻ በማሰብ ተወስኖ መላእክትን በመምሰል ከዓለማዊው ተድላ ደስታ መለየት ማለት ነው እንጂ ሰው መሆንን ለመርሳት ወይም ለመተው አይደለም፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ሐዋርያ ጳውሎስ " ወበኅቤየስ ምውት ዓለም ወአነሂ ምውት በኅበ ዓለም በኔ ዘንድ የሞተ ነው፡ እኔም በዓለም ዘንድ የሞትኩ ነኝ ብሏል፡፡ ገላ 6፡ ፡14
ሞት ማለትም መለየት ማለት ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡ "አኮኑ ወዳዕነ ሞትነ እምኃጢአት እፎ እንከንክል ሐይወ ባቲ" ከኃጢአት ፈጽመን ተለይተናል እንግዲህ በኃጢአት መኖር እንዴት እንችላለን እንዳለ:: ሮሜ 6፡2
በምንኩስና ከዓለማዊ ግብር መለየትም ፍጹም ለመሆን ነው እንጂ በዓለማዊ ግብር ሆኖ እግዚአብሔርን ማገልገል አይቻልም ማለት አይደለም በዓለማዊ ግብር ሆነው የታዘዘውን ሕግ ፈጽመው ከጸደቁ ዓለማውያን እነ ኖኅ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ሄኖክ ኢዮብን የመሳሰሉ አሉ ማቴ 22 ፡ 32፡፡ ያዕ፡5:11:ዕብ፡11፡ 5፡6፡፡
ምንም እንኳን የድንግልናና የምናኔ ኑሮ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የምንኩስና መሥራችና አባት ቅዱስ እንጦንስ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ በምትገኝ ቆማ በምትባል ቦታ 251 . ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ሀብታሞችና ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ ዕረፍት በኋላ የነበረውን ሀብት ለድሆች መጽውቶ መንኩሶ ብዙ ዓመት በብሕትውና ኖረ፡፡በዚያን ጊዜ ብዙ ታምራትን ስለሠራ ሕዝቡ ግማሹ እሱን አይቶ ለማድነቅ የቀረው ደግሞ በእርሱ ጸሎት ለመፈወስ ወደነበረበት ቦታ ይጐርፍ ነበር፡፡ እርሱም 356 . ዐረፈ፡፡የምንኩስናን ሕይወት ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጉባዔ ኬልቄዶን /በሃይማኖት ስደት/ ምክንያት ከቁስጥንጥንያ፣ ከግብፅ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከአንጾኪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት ናቸው፡፡ ምንኩስና ከተመሠረተ ጀምሮ በየጊዜው ሕዝቡ ታላላቆችም ሳይቀሩ ወደ ገዳማቱ እየሄዱ ይመነኩሱ ነበር፡፡
 መፀኃፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮውን ስንመለከት አንድ ግብዝ ሰው ከጌታ ዘንድ መጥቶ መምህር የዘለዓለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ሲል ጠየቀው ጌታም ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ልትገባ ከወደድክ ሕጎችን ሁሉ ጠብቅ በማለት ሊጠበቁ የሚገቡ ሕጎች  ምንና ምን እንደሆኑ አስረዳው፡፡ እነዚህንስ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአቸዋለሁና የቀረኝ ምንድር ነው?  ምን ቀረኝ?  አለው፡፡ ጌታም ፍጹም ልትሆን ከወደድክስ ሄደህ ያለህን ሀብት ሽጠህ ለድሆች  ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ ሲል የምናኔ ወይም የምንኩስናን ምስጢር ገለጸለት፡፡  ነገር ግን ሰውየው ገንዘቡ ብዙ ነበርና ገንዘብህን ሁሉ ሽጠህ ተከተለኝ ባለው ጊዜ እያዘነ እየተከዘ ተመለሰ፡፡
በዚህ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው "የባለጸጋ መንግሥተ ሰማይ መግባት ጭንቅ ነው ባለጸጋ መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፡፡  ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሰምተው እንዲህ ከሆነ ማን ሊገባ ይችላል?  በማለት አደነቁ፡፡  ጴጥሮስም አሁን እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ምን እናገኛለን?  አለው፡፡ ጌታም እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ የሰው ልጅ "እኔ ዳግመኛ በክበበ ትስብእት በግርማ መንግሥት በመጣሁ ጊዜ በዐሥራ ሁለት ወንበር ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለት ነገደ እስራኤል ላይ ትፈርዳላችሁ ብሎ የፍጹምነት ደረጃውና ከብሩ እስከዚህ መሆኑን ካስረዳቸው በኋላ አያይዞ "ቤቱን ንብረቱን ወንድሞቹን እኅቶቹን እናት አባቱን ሚስቱን ልጆቹን ርስቱንና ጉልቱን በኔ ስም የተው ሁሉ በሚመጣው ዓለም ዕጥፍ ድርብ  ያገኛል ሲል ምንኩስና ወይም ምናኔ መሆኑ አስረዳቸው ማቴ፡ 19:16-27፡፡  ይህስ ለ12 ሐዋርያት ብቻ ነው ያላቸው እንዳይባል በግብር ከመተሳሰሉና ከተስተካከሉ በክብርም መመሳሰልና መስተካከል እንዳለ ሲያስረዳ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ ብሏል፡፡ ማቴ.19፡ 27-30 የድንግልና መሠረቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ መንግሥተ ሰማያት ሰውነታቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉና፤ መፈጸም የሚችል ግን ይፈጽም» ሲል የተናገረው የሕግ ቃል ነው፡፡ ማቴ. 1912
እንዲሁም ገባእተ ነግህንና ገባእተ ሠርክን ባስተካከለበት ምዕራፍ ትምህርቱ ከዓለማዊ ግብር ተለይተው በጎ ሥራን ከሠሩ ባይመነኩሱም ፍጹምነት ለዓለማዊም ለመነኩሴም ትክክል እንደሆነ የነአብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ኢዮብ ሆኖክን ፍጹምነት ማስታወስ ይበቃል ማቴ 20፡1- 17፡፡እንዲያውም በምንኩስናም እንበለ ምንኩስናም ፍጹማን የሆኑ ሁሉ "ውስተ ሕፅነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ ይረፍቁ" ስለሚላቸው የሥነምግባር ብቃት ካለፍጹምነት ዓለማዊነትና ምንኩስና እንደማይል በዚህ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በዓለማዊ ግብር ሆነው ከሚሠሩ መንፈሳዊ ሥራ ይልቅ በምነኩስና ሆነው የሚሠሩት ሥራ ሳይሻል ስለማይቀር ሐዋርያ ጳውሎስ ያላገባ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው ገንዘብ እግዚአብሔርን ያስበዋል ካለ በኋላ ያላገባ ግን ሚስቱን ለማገልገል ዓለማዊ ሥራን ያስባልና ካገባ ያላገባ ይሻላል ብሏል 1ቆሮ -7 : 32፡፡  ስለዚህ የሰብአ ዓለምና የመነኮሳት ልዩነት ይህ ብቻ ነው እንጂ ለመነኮሳት ሌላ መንግሥተ ሰማይ ለሰብአ ዓለም ሌላ መንግሥተ ሰማይ አለ ማለት አይደለም፡፡ በዘመነ ብሉይ በዚሁ ዓይነት መንኩሰው ከዓለማዊ ግበር ተለይተው ፍጹማን የሆኑ እነ መልከ ጼዴቅ ኤርምያስ ኤልያስና እነ ዮሐንስን የመሳሰሉ ነበሩ::

ምነኩስና ቆብ
የምንኩስና ቆብ ከፀሐይና ከብርድ ለመከላከል ካልሆነ በቀር ለጽድቅ  አይረባም አይጠቅምም የሚሉ ቢኖሩ፡ መነኮሳት ሌት ከቀን ቆብ አጥልቀው የሚኖሩ ከዓለማዊ ግብር ለመለየት የተነሡበት ዓላማ አስገድዶአቸው ነው እንጂ የማይከብዳቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ግዴታውም ሐዋርያው ጳውሎስ "ንሥኡ ጌራ መድኃኒት ላዕለ ርእስክሙ" በራሳችሁ ላይ የድኅነትን የመዳንንም ራስ ቁር  የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው ኤፌ 6፡17፡፡  ይህም ቢሆን ራስ ወርቁን እንጂ ቆቡን አይደለም እንዳይባል ጳውሎስን ያህል ሐዋርያ ራስ ወርቁን ቁም ነገር አይለውም  ያውስ ቢሆን ጌራ መድኃኒት ይለው ነበር? ጌራ መድኃኒት ማለቱ ድኅነተ ነፍሱን እንጂ ክብረ ሥጋውን አይደለም ሲል አይደለምን?
ምሳሌውም ጌታ በዕለተ ዓርብ ሲሰቅሉት  ተሣልቀው የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብለሃልና ይኽውም አነገሥንህ ብለው እሾሁን ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፍተውበታል "ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ" ያለውን ተከትለው ከበረከተ መሰቀሉ ለመሳተፍና እሱነ ለመምሰል ነው ራሱ ሐዋርያው "ተመሰሉ ኪያየ በከመ አነ እትሜሰሉ ለክርስቶስ" እኔ ክርስቶስን እንደ መሰልኩት እኔን ምሰሉ ብሏልና ስለዚህ ነው እንጂ የቆቡን ከባድነት የማያውቁ እንደሚሉት አይደለም::


እግዚአብሔር አባቶቻችንን ይጠብቅልን አሜን፡፡

ዋቢ መፀሐፍ፡-መርሃ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት
                   የዛሬዋ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ

 

3 comments:

  1. Replies
    1. በእኔ አስተያት ይህ ከወንጌል ትምህርት ፍጹም የተለየ የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ምክነያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋሪያት ጫካ ገብታችሁ ተደብቃችሁ ጸልዩልኝ አላለም፡፡ወጥታችሁ ስለስሜ መስክሩልኝ ማር 16፡15 ነው ያለው፡፡ገዳም የሚገቡት ይህን የአለም ስጋ ይዘው ነው ስጋ ደግሞ በክርስቶስ መስቀል እንጂ የፈለገ ጫካ ብንደበቅ አይሞትም፡፡እስኪ በደንብ እስቡበት ዛሬም ብዙ ሰው እውቀት ከማጣት መጥፋት የለበትም፡፡

      Delete
  2. በእኔ አስተያት ይህ ከወንጌል ትምህርት ፍጹም የተለየ የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ምክነያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋሪያት ጫካ ገብታችሁ ተደብቃችሁ ጸልዩልኝ አላለም፡፡ወጥታችሁ ስለስሜ መስክሩልኝ ማር 16፡15 ነው ያለው፡፡ገዳም የሚገቡት ይህን የአለም ስጋ ይዘው ነው ስጋ ደግሞ በክርስቶስ መስቀል እንጂ የፈለገ ጫካ ብንደበቅ አይሞትም፡፡እስኪ በደንብ እስቡበት ዛሬም ብዙ ሰው እውቀት ከማጣት መጥፋት የለበትም፡፡

    ReplyDelete