Friday, July 27, 2012

ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ታላቅ ሰማዕት


 1875 .. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።

Tuesday, July 24, 2012

መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት ስሕተት ነውን?


ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡  
ቅዱስ ዳዊት በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?

በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ የተናገረውን ቃል እናቶችና አባቶች በስእለታቸው ‹‹ቅዱስ ሚካኤል አድነኝ፤ ቅዱስ ግብርኤል ድረስልኝ›› እያሉ በመድገማቸው የዋሃን ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማያውቁ ነው መባል አለባቸው? ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ያዕቆብ የመላእክትን አዳኝነት በግልጽ ያወጁት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ስላልተማሩ ይሆን? ወይስ አንድ ሰባኪ የመላእክትን አዳኝነት ስላስተማረ ‹‹ገድል ጠቃሽ›› በሚል መጥላላት አለበት? ዘማርያኑስ በዚህ መልኩ መዘመራቸው ሊያስወቅሳቸው ይገባ ነበር?

Friday, July 20, 2012

የ20 ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት


ሰማዕቱ  አቡነ  ጴጥሮ
« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡  አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 .በሰማዕትነት አለፉ፡፡


1875 .. የተወለዱት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ  1921 .. በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ጊዜ ስትሾም አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ የመጀመርያ ጳጳሳት መካከል አንዱ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ "ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ" ተብለው  21 አካባቢዎችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ 

የኢጣሊያ
ፋሺስት 1928 .. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ  እና በደቡባዊ ምሥራቅ  አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደ ሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤ አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡

ለሀገራቸውና
ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡ «ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡» /መርሻ አለኸኝ /ዲያቆን/ 1986 .ም፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ ገጽ.80/

ሐዋርያው
ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው «ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡  አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው በሰማዕትነት አለፉ፡፡ / መርሻ አለኸኝ/ዲያቆን/ 1996.ም፣ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ገጽ.77/