Monday, December 10, 2012

ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው! መዝ.86፥3

በመ/ር መንግስተ አብ ፡አበጋዝ
 
የሶርያው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም የምስጋና መጽሐፉ ‹‹ነቢያት ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ›› በማለት ስለ ወላዲተ አምላክ የተሰጡ ምስክርነቶች ድንቆች መሆናቸውን መስክሯል፡፡ ከዛሬ 3000 ዓመት ገደማ ቀደም ብሎም ነቢየ እግዚብሔር ዳዊት ‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ኦ ሀገረ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ከተማ /ሀገር/ ሆይ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው፡፡›› /መዝ.86፥3/ በማለት አመስግኗታል፡፡ እነዚህ በተለያየ የዘመን ርቀት ውስጥ የኖሩ የነቢዩ ዳዊትና የቅዱስ ኤፍሬም ምስጋና ምን ይደንቅ?!
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ሕሊና ስትታሰብ ጀምሮ በዚህ ምድር 64 ዓመት በቆየችባቸው ጊዜያትና እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታ በእግዚአብሔር ቀኝ እስካለችበት እስከ አሁን ድንቅን የምታደርግ ንግሥት፣ ድንቅ የሚደረግባት ቅድስት ናት፡፡ እመቤታችን ያደረገቻቸውን ድንቆች እጹብ ድንቅ ብሎ ከማድነቅ አልፎ ልንናገረውና ልንፈጽመው አይቻለንም፡፡ ነቢዩ ‹‹በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው፡፡›› እንዳለ፡፡ በእርሷ እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ጥቂት ድንቆች እንመልከት፡-

1.    ፅንሰቷና ልደቷ ድንቅ ነው፡፡


ፅንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም በዓልን የምናዘክርበት ዕለት ነሐሴ 7 ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን እንደምን ያለ ድንቅ ነው?! በአምላክ ሕሊና ሲታሰብ፣ በአበው ልቡና ሲመላለስ፣ በነቢያት ትንቢት ሲነገርና ለሰው ልጆች ሁሉ ምክንያተ ድህነት እንድትሆን ሲጠባበቋት የኖረች እናት በማኀጸን የተቀረጸችበት ዕለት ነበርና፡፡ የእግዚአብሔር ወዳጆች ሐናና ኢያቄም ዘር በማጣት የተነሣ ሲያዝኑና ሲያለቅሱ የኖሩባቸው ዘመናት ተገትተው መካኖች በሚለው ስም ፈንታ ወላጆች የተባሉባት ፣ አርጅተዋልና አልፎባቸዋል የተባሉባቸው ጊዜአት ተቀይረው ድንቅ ፅንስን ያገኙበት ነው፡፡ በማኀጸን ሳለች ሙት የምታነሣ፣ ሕሙማንን የምትፈውስ፣ ድውያንን የምታድን፣ እውራንን የምታበራ፣ መካኖችን ወላድ ያደረገች እናት የተገኘችበት ነውና የእመቤታችን ፅንሰቷ ድንቅ ነው፡፡
ግንቦት አንድ ቀን የመታሰቢያ በዓል የምናደርግላት እመቤታችን ልደቷ ድንቅ ነው፡፡ ከአይሁድ ዛቻና ማስፈራሪያ ታመልጥ ዘንድ ቅድስት ሐና በሊባኖስ ተራራ ያደረገችው የድንግል ማርያም ልደት በመላእክት የታጀበ፣ በቤተ ዘመድ የተጎበኘና ኃጢአት ያመጣውን የዚህን ዓለም ጨለማ ያስወግድ ዘንድ ብርሃንን የምትወልድልን ፀሀይ የወጣችበት ድንቅ ዕለት ነው፡፡

የድንግል ማርያም ልደት ድንቅ የሚያሰኘው እንደ ማንኛውም ሰው በዚህ ምድር ላይ ተወልዳና አድጋ፣ አግብታና ወልዳ በሥጋ ሐሳብ ትኖር ዘንድ የመጣች አለመሆኗ ነው፡፡ ወላጆቿ አስቀድመው ሳትጸነስ  ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ትሆን ዘንድ እንደወሰኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድም ለድኀነተ ሰብእ /ምክንያተ ድኂን/ እንድትሆን የታሰበ የተለየ ነበርና ልደቷ ድንቅ ነው፡፡ /ኢሳ.1፥9/፡፡ ልደቷን ድንቅ ከሚያደርጉት ሌሎች ምክንያቶች አንዱ ደግሞ እድገቷ ነው፡፡ በቤተ መቅደስ በእደ መላእክት ቅዱሳን ሕብስት ሰማያዊ እየተመገበች ጽዋ ሰማያዊ እየጠጣች ያደገች እናት ናትና፡፡ /መዝ.45፥10/፡፡

2.    እናትነቷና ድንግልናዋ ድንቅ ነው፡፡


እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ናት፡፡ ይህ እንደምን ያለ ድንቅ ነው?! ወላጆች ሁሉ በዘመን የሚቀድሟቸውንና የሚከተሏቸውንም ሕፃናት ይወልዳሉ፡፡ የእመቤታችን እናትነት ድንቅ ነው፡፡ ከእናቱ ልደት አስቀድሞ የነበረውን አምላኳን ወልዳለችና፡፡ ‹‹ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችዉ›› እንዲል ሊቁ፡፡

በብሥራተ መልአክ የወለዱ ብዙ አንስት ቢኖሩም እመቤታችን የወለደችው በብሥራተ መልአክ ፣ ምክንያተ ፅንስ የሆነ ዘርን ያለ መቀበል /እንበለ ዘር/፣ ያለ ተፈትሖ ማኀጸን /ድንግልናን ባለማጣት/ ነውና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹ያለ ዘርዐ ብእሲ የወለደችው እናቱ ናት በሥጋ ከእርሷ መወለዱም እንደ ሴቶች መጽነስ ሥርዓት ልማድ አይደለም፡፡ ድንግል ቃልን በሥጋ ያለ ዘርዐ ብእሲ ወለደችው፡፡›› /ሃይ.አበው ዘቄርሎስ 70፥25/፡፡ ለዚህ ነው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው›› ሲል ያመሰገናት፡፡ እግዚአብሔር የድንቅ ጥበቡ ማደሪያ አድርጓታልና፡፡ 

‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ቅዱስ ገብርኤል ነኝ›› /ሉቃ.1፥19/፡፡ በማለት ድንግል ማርያምን እንደምትፀንስና እንደምትወልድ ያበሰረ መልአከ መበሥር ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?›› ለሚለው የድንግል ማርያም ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፣ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡›› በማለት የአምላክ እናቱ መሆኗን መስክሯል፡፡ /ሉቃ.1፥35/፡፡ የእመቤታችን ወላዲተ አምላክነት ምን ይደንቅ!

እናትነቷን ድንቅ የሚያደርገው ለልደቱ ዘር ያልቀደመውን፣ ሁለት ልደታት ያሉትን ጌታ መውለዷ ነው፡፡ ቅድመ ዓለም ያለ እናት የተወለደውን እመቤታችን ድኀረ ዓለም ያለአባት ወልዳልናለችና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ ሊቁ አባ መቃርስ ስለዚህ ድንቅ እናትነት እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹ከማይመረመር ልደቱ በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ ወላዲተ አምላክ እንደሆነች አመንን፤ ሕጻን ሆኖ ተወለደ በጨርቅም ተጠቀለለ በጎል ተጣለ፡፡ ይህን ጊዜ ተገኘ የማይባል ከአብ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር የነበረ ያለ ለዘለዓለም እርሱ ዘመን ተቆጠረለት ጊዜ ተነገረለት እርሱ አንድ ወልድ ሲሆን በየጥቂቱ አደገ፡፡›› /ሃይ.አበው ዘመቃርስ 98-13/፡፡

ሌሎች እናቶች አንዱን ሲይዙ ሌላውን የሚያጡ ሲሆኑ እመቤታችን ግን እናትነትን ከድንግልና ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ ‹‹ድንግል ወላዲተ አምላክ›› እየተባለች የምትመሰገን እናት ናትና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ አፈወርቅ ብላ የጠራችው ዮሐንስም ስለዚህ ነገር እንዲህ በማለት አመስግኗል፡፡ ‹‹የማኀፀንሽ መሠረት ሳይናወጥ አምላክን የወለድሽ ማርያም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል፤ ማኀተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ንጉሥ ክርስቶስን የወለድሽ ልዩ መድኃኒታችንን በመውለድሽ እናትና አገልጋይ የተባልሽ ማርያም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ሰው ቢሆን የእናትነት ባለሟልነትን አግኝተሻልና ማርያም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል፡፡›› /ሃይ.አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ 68፥ ክፍል 26፥ 37-39/፡፡

እናትነቷን ድንቅ ከሚያደርጉ ድንቆች ሁሉ የሚልቀው እመቤታችን በልተን የማንራብበትን፣ ጠጥተን የማንጠማበትን የሕይወት መብል የሕይወት መጠጥ ሰጥታናለችና ነው፡፡ ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅርኪ ወነዐብየኪ፤ ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን›› እንዲል፡፡ እኛም ከአባቶቻችን ከአባ ሕርያቆስ፣ ከቅዱስ ኤፍሬም፣ ከቅዱስ ያሬድና ከአባቷ ዳዊት ጋር ሆነን ‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ፤ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው›› እንበል፡፡

ድንግል ማርያም የመድኃኔዓለም እናቱ ስትሆን በቀራንዮ አደባባይ ደግሞ በእደ ዮሐንስ ለዓለም ሁሉ የተሰጠች እናት ናትና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ እመ ብዛኀን /የብዙኀን እናት/ የሕያዋን እናት ናትና፡፡ /ዮሐ.19፥25-27/፡፡

3.    ንጽሕናዋና ቅድስናዋ ድንቅ ነው፡፡

እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ ላዳነበት ጥበቡ ምስጢር መፈጸሚያ መቅደስ፣ የመለኮት ማደሪያ ለመሆን የበቃች ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ እመቤታችን ንጽሕተ ንጹሕን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተለዩ የተለየች፣ ከተመረጡም የተመረጠች፤ መትሕተ ፈጣሪ፣ መልእልተ ፍጡራን፣ ከፈጣሪ በታች፣ ከፍጡራን በላይ እየተባለች የምትመሰገን ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና አላት፡፡

የወላዲተ አምላክ ንጽሕናና ቅድስና ልዩ ነው፡፡ ‹‹ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና መላእክት የሚፈሩትን ትጉኀን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኀጸኗ ተሸከመችው፡፡ ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፣ ከሱራፌልም ትበልጣለች፣ ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና፡፡›› እያሉ ሊቃውንት ያመሰገኗትም ድንቅ ከሆነ ቅድስናዋና ንጽሕናዋ የተነሣ ነው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ፤ ራዕ.4፥7-9/፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በምስጋናው ‹‹ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ … ዓይኖቻቸው ስድስት ከሆኑ ከሱራፌል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፡፡ እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ .. ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው እሳት ይድኑ ዘንድ፣ አንቺ ግን ለመለኮት ማደሪያ ሆንሽ የመለኮት ባሕርይም አላቃጠለሽም፡፡ የእሳት ነበልባልን ተሸከምሽ፡፡›› በማለት ንጽሕናዋን ከመላእክት ንጽሕና ጋር እያነጻጸረ እጹብ ድንቅ እያለ ያመሰግናታል፡፡

የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና በቅዱሳን አንደበት ሲመሰገን ድንቅ ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ምልዕተ ጸጋ›› ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት›› እያሉ ያመሰገኗት ምስጋና ድንቅ ነው፡፡ ከሰው ወገን እንዲህ ያለውን ምስጋና የተቀበለ የለምና፡፡ የእግዚአብሔር እናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም የንጽሕናዋን የቅድስናዋን ድንቅነት ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ‹‹ከቅዱሳን ሁሉ ክብር ይልቅ የማርያም ክብር ይበልጣል …›› ሲል በብዙ ምሳሌ ያመሰገናት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹በምን በምን ልመስልሽ›› በማለት ምሳሌ የታጣላት ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና ያላት መሆኑን መስክሯል፡፡

የንጽሕናዋ የቅድስናዋ ምስክር ስሟ ድንቅ ነው፡፡ ማርያም ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ፍጽምት ማለት ነውና፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት ያላት ስለሆነ ውበቷ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ነውርም የለብሽም፡፡›› እንዲል /መኃ.መኃ 4፥7/፡፡ ሔዋን ንጽሐ ጠባይ ሳያድፍባት እንደነበረችው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ከጥንት ጀምሮ በጥንተ ተፈጥሮ ንጽሐ ጠባይ ሳያድፋባት ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ተጠብቃ የኖረች ድንቅ ናት፡፡ ነቢዩ ‹‹ንጉሥ ውበትሽን ወደደ›› ያለበት ምክንያቱ ከዚህ ድንቅ ንጽሕናዋ የተነሣ አይደለምን? ከአካላዊ ውበቷ ይልቅ ውስጣዊ ንጽሕናዋ ቅድስናዋ ምን ይደንቅ!

የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና አፍአዊ ብቻ አይደለም፡፡ ንጉሥ እግዚአብሔር የወደደው ውበት እመቤታችንንም ድንቅ የሚያሰኛት ሌላም አለ፡፡ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ልቡናና ንጽሐ ነፍስን አስተባብራ የያዘች ፍጽምት መሆኗ፡፡ ስለዚህ ከቅዱስ ዳዊት ጋር ሆነን በአማን ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ፣ በእውነት በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው ልንላት ይገባል፡፡

4.    ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ድንቅ ነው፡፡
‹‹ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም ይአጽብ ለኩሉ፤ ለመዋቲው ሰው ሞት (መሞት) ይገባል የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡›› እንዲል ሊቁ፡፡ የወላዲተ አምላክ ዕረፍቷ ድንቅ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤተሰቦቿ ጋር ሦስት ዓመት፣ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ከዚያ በኋላ ዘጠኝ ወር በቤተ ዮሴፍ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከልጇ ጋር እንዲሁም አሥራ አምስት ዓመት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ጠቅላላ በዚህ ዓለም ስድሳ አራት ዓመት ኖራ ጥር ሃያ አንድ ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር እንዲሉ ፡፡ ነሐሴ አሥራ አራት የፍልሰቷ መታሰቢያ፣ ነሐሴ አሥራ ስድስት ትንሣኤዋና ዕርገቷ ይታሰባል፡፡ እንደምን ያለ ድንቅ ነው?!

በቅዱሳን መጻሕፍት የተነገረ እና የተፈጸመ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ድንቅ ነው፡፡ /መዝ.131፥8 ፣ መኃ.መኃ 2፥10/፡፡

አይሁድ ግንዘተ ሥጋዋን ሊወስዱ ያሴሩበት እረፍቷ ድንቅ ነው፡፡ ለታውፋንያ ተአምር የተደረገበት እና በቅዱሳን መላእክት ተነጥቆ በገነት ዕፀ ሕይወት ሥር ያረፈበት ድንቅ በዓል ነውና፡፡ ለቅዱስ ዮሐንስ የተገለጠ ይህ ተአምር ለቅዱሳን ሐዋርያት ሁሉ በሱባኤ ነሐሴ 14 ቀን በሁለተኛው ሱባኤ ተገልጦላቸው በዝማሬ፣ በውዳሴ በታላቅም የጸሎት ሥርዓት በጌቴ ሴማኒ የሆነው እረፍቷ ድንቅ ነው፡፡

በሐዋርያው ቶማስ አማካኝነት ለሁላችን የተገለጠ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና እርገቷ ድንቅ ነው፡፡ ይህ ከሰው ልጆች ለማን ተደርጓል?! ሐዋርያው የተመለከተውን የወላዲተ አምላክን ትንሣኤ የምሥራች የሰሙና ምልክቱን ያዩ ደቀመዛሙርት እንደቀድሞው ሁሉ ትንሣኤዋን ይመለከቱ ዘንድ ሱባኤ ይዘው በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ/ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም ካቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡ ከዚህ የሚልቅ ድንቅ ነገር የተደረገለት ማን ነው?! የእመቤታችን ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ድንቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ ስለእመቤታችን የተነገረው የተደረገው እና የሚደረገው ሁሉ ድንቅ ነው፡፡ በአበው አብራክ ስታልፍ እንደ እንቁ ስታበራ የኖረች ድንቅ ዘር፣ ለእናትና አባቷ በስተርጅና የተሰጠች ድንቅ ስጦታ፣ በቤተ መቅደስ መላእክተ እግዚአብሔር የመገቧት ያጽናኗትና ያገለገሏት ድንቅ ብላቴና፣ በአይሁድ ሕግ ይጠብቃት ዘንድ ለዮሴፍ የተሰጠች ድንቅ እመቤት፣ በብሥራተ መልአክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ የተገኘች ድንቅ እናት፣ ከመፅነሷ በፊት በፀነሰች ጌዜ፣ ከፀነሰች በኋላ ፤ እንዲሁም ከመውለዷ በፊት በወለደች ጊዜ፣ ከወለደችም በኋላ ዘወትር ድንግል ናት፡፡ እንደምን ያለ ድንቅ ነው?! ፅንሰቷ፣ ልደቷ፣ እናትነቷ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ድንቅ ነው፡፡

በቅዱሳን ሥዕሎቿ፣ በጸበሏ፣ በእምነቷ፣ መታሰቢያዋ በሚደረግባቸው ነገሮች ሁሉ ላይ የምትሠራቸው ተዓምራት ድንቅ ናቸው፡፡ ስሟን ለሚጠሩ፣ መታሰቢያዋን ለሚያደረጉ፣ በዓላቶቿን ለሚያከብሩ፣ ቅዳሴዋን ውዳሴዋን ተአምሯንና መልኳን ለሚደግሙ ወዳጆቿ ሁሉ የምታደርጋቸው ድንቆች የበዙ ናቸው፡፡ እመቤታችን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘች ናትና ልመናዋ ክብሯ አማላጅነቷ የእናት ልመና ነውና ድንቅ ነው፡፡

                                ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ
                          በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው!
(ምንጭ ፡-ማኅበረ ቅዱሳን  መካነ ድር )

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

2 comments:

  1. Dn. Ge/silassie ze debregenetDecember 10, 2012 at 6:34 PM

    You are right! "nekeer negeru bentiaha". "Taimuan be andebetachin, fekruan be lebonachin tawelebn tasadereben." says MK-SHAKISSO.

    ReplyDelete
  2. KLAE HIWOT YASEMALEN

    ReplyDelete