አክዓብም ናቡቴ በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው እስከ ሞሞትም በቃ ለርስቱ የናቡቴ ልጆችም ዛሬ እርስታችንን ተዋህዶን ለእነ አድሳት ባዮች አንሰጥም እስከ ደም ጠብታ እንከፍላለን ሲሉ ነው
Thursday, August 18, 2011
አባ ሙሴ ጸሊም
አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ
በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡ ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡
አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡
የአባ ሙሴ ጸሊም በረከት ይደርብን አሜን
ዋቢ ስንክሳር ሠኔ 24
በበረሓው ጉያ ውስጥ
Wednesday, August 17, 2011
Friday, August 5, 2011
የዐሥርቱ ትዕዛዛት ዓላማ
ዐሥርቱ ትዕዛዛት የተሰጡት በሚከተሉት ዓላማዎች ነው፡፡ ይኸውም፡-
1. ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ውለታውን እንዲያስቡ
2. ወደ ፊት በአረማዊያን መካከል ሲመላለሱ ከኃጢአት እንዲቆጠቡ
3. መንፈሳዊ አካሄዳቸው ምን ምን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡
የዐሥርቱ ትዕዛዛት አከፋፈል
የክርስቲያን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞበታል ካለ በኋላ ከዐሥርቱ ትዕዛዛት የተወሰኑትን በመጥቀስ ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ይነግራል፡፡ ሮሜ 13፡8-10 ታዲያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፡፡ ማቴ 22፡34-41
1 ፍቅረ እግዚአብሔር 2 ፍቅረ ቢጽ
1. ፍቅረ እግዚአብሔር ከአንደኛ ትዕዛዝ እስከ ሦስተኛው ያሉት ሲሆኑ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
2. ፍቅረ ቢጽ ከአራተኛ ትዕዛዝ እስከ አሥረኛ ትዕዛዝ ያሉት ሲሆኑ በለእንጀራን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአዎንታዊና በአሉታ ከመነገራቸው አንጻር በሁለት ይከፈላሉ ይኸውም፡-
1. ሕግ በአሉታ የተነገሩ /አታድርግ/
2. ትዕዛዝ በአዎንታ የተነገሩ /አድርግ/
ከዚህም ሌላ ከአፈጻጸማቸው አንጻር ሲታዩ በሦስት ይከፈላሉ፡፡
1. በሐልዮ የሚፈጸሙ 1፣3፣4 እና 9 በሐሳብ
2. በነቢብ የሚፈጸሙ 2፣ 8 በመናገር
3. በገቢር የሚፈጸሙ 5፣6፣7 እና 10 በሥራ ናቸው፡፡
ብሂለ አበው
0 ለተወሰን ጊዜ ለሀይማኖት መከራከር፤ጠበቃ መሆን፤መዋጋት ብሎም መሞት አይከፋም ሁልጊዜ ለሀይማኖት መኖር ግን ከሁሉ የበለጠ መስዋእትና ክብር ያለው ህይወት ነው፡፡
o የረብዑ ምግብ ለሀሙስ የአርብ ምግብ ለቅዳሜ ይጠቅማል ነገር ግን የማክሰኞ ምግብ ለረብዑ አይጠቅምም የሀሙስ ምግብ ለአርብ አይሆንም የነፍስና የስጋ ነገርም እንዲሁ ነው፡፡
o የነፍሳችን ነገር ትተን የስጋችንን ብቻ የምናደልብ ከሆነ ነፍስን በስጋ መቃብር እየቀበርናት መሆኑን አንርሳ
o አንድ በርሜል ወተት በአንድ ጠብታ ኮምጣጤ የበጣጠሳል የብዙ ጊዜ ተጋድሎንም ጠብታ የሀጢያት ኮምጣጤ ያበላሸዋል
o ራስህን በሀሰት አትውቀስ፡፡ራስህ መክሰስ ትህትና አይደለም፡፡ ታላቅ ትህትና ሰዎች ሲወቅሱህ መታገስ ነው
o ትዕቢት ሰይጣን ያለመው ጦር ነው
o ትህትና ህፀፅን የምታስታውቅ መስታወት ናት
o ክርስትና ማለት የሰውን ሸክም መሸከምና እስከሞት ድረስ መፅናት ማለት ነው
o በባልንጀራው ላይ ክፋትን የሚያስብ ሰው ያችው የሚያስባት ክፋት ራሱን ትጎዳዋለች፡፡ በየትና ምን ጊዜ እደምትጥለው ግን አያውቅም
o ስንፍናውን ወደጥበብ፤አላዋቂነቱን ወደእውቀት ፤መጥፎ ጠባዩን ወደበጎነት የሚመልስ ሰው ብርቱ ነው
o ፀሎት ገንዘብን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ገንዘብ ግን ፀሎትን አያመጣም፡፡
o የረብዑ ምግብ ለሀሙስ የአርብ ምግብ ለቅዳሜ ይጠቅማል ነገር ግን የማክሰኞ ምግብ ለረብዑ አይጠቅምም የሀሙስ ምግብ ለአርብ አይሆንም የነፍስና የስጋ ነገርም እንዲሁ ነው፡፡
o የነፍሳችን ነገር ትተን የስጋችንን ብቻ የምናደልብ ከሆነ ነፍስን በስጋ መቃብር እየቀበርናት መሆኑን አንርሳ
o አንድ በርሜል ወተት በአንድ ጠብታ ኮምጣጤ የበጣጠሳል የብዙ ጊዜ ተጋድሎንም ጠብታ የሀጢያት ኮምጣጤ ያበላሸዋል
o ራስህን በሀሰት አትውቀስ፡፡ራስህ መክሰስ ትህትና አይደለም፡፡ ታላቅ ትህትና ሰዎች ሲወቅሱህ መታገስ ነው
o ትዕቢት ሰይጣን ያለመው ጦር ነው
o ትህትና ህፀፅን የምታስታውቅ መስታወት ናት
o ክርስትና ማለት የሰውን ሸክም መሸከምና እስከሞት ድረስ መፅናት ማለት ነው
o በባልንጀራው ላይ ክፋትን የሚያስብ ሰው ያችው የሚያስባት ክፋት ራሱን ትጎዳዋለች፡፡ በየትና ምን ጊዜ እደምትጥለው ግን አያውቅም
o ስንፍናውን ወደጥበብ፤አላዋቂነቱን ወደእውቀት ፤መጥፎ ጠባዩን ወደበጎነት የሚመልስ ሰው ብርቱ ነው
o ፀሎት ገንዘብን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ገንዘብ ግን ፀሎትን አያመጣም፡፡
ብሂለ አበዉ
• ‹‹እግዚአብሔር ሆይ አፈርና ትቢያ ሆኜ ሳለ ጻድቅ አድርገው ከሚቆጥሩኝ ሰዎች አድነኝ››
አባ እንጦንስ
• ‹‹ፍጡራንን መርምሮ ማወቅ ካልተቻልን ሁሉን የፈጠረ እርሱን መርምሮ ማወቅ እንደምን ይቻልናል››
ቅዱስ አትናቴዎስ
• ‹‹ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ የክርስቶስንም ፀጋና ክብር ሳይፈተኑ ማግኘት አይቻልም የዚህ ዓለም ፈተናና እሳት ቶሎ ያልፋል ይጠፋል ኃጢያተኞች የሚገቡበት የገሀነም እሳት ግን ለዘላለም እንደ ነደደ ይኖራል››
ቅዱስ ሚናስ
• ‹‹በማንም ላይ ክፈትን አትስሩ አትፍርዱ ይህንን ከጠበቃችሁ ርስቱን ትወርሳላችሁና››
ታላቁ አባ መቃርስ
• ‹‹ብዙ ጊዜ ብዙ እናገራለሁ በመናገሬም አዝናልሁ በዝምታዬ ግን ያዘንኩበት ጊዜ የለም››
ቅዱስ አርሳንዮስ
• ‹‹ቤተክርስትያን መጠጊያችን ነች ቤተክርስትያን የኖኅ መርክብ ነች በውስጧ እንጠለላልን ከውጭዋ ግን ማዕበልና ቀላያት ተከፍተዋል››
ቅዱስ እንድርያስ
• ‹‹ልባችንን ጠፊና በስባሽ ከኾነው ከምድራዊው ምኞት አርቀን ከበደል በንስሐ ነጹሕ ካደረግነው በጸጋ መንፈስቅዱስ የተሞላን እንሆናለን››
አባ አብርሃም መፍቀሬ ነዳያን
• ‹‹ስጋዊ ፍላጎቶችን ማሸነፍ ለአክሊለ ህይወት የሚያበቃ ሰማዕትነት ነው››
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
• ‹‹የቤተክርስቲያን ህይወት በመስቀል ላይ ስለሆነ ፈተና ይበዛበታል ስለዚህ ከግል ህይወታችሁ ይልቅ የቤተክርስቲያናችሁን አቋም አጠንክሩ››
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
• ‹‹ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ፀሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትፀልይ እደር››
ቅዱስ ይስሀቅ ሶርያዊ
• ‹‹ኃጥያታችንን እኛ እያሰብን የምንፀፀት ከሆነ እግዚአብሔር ይረሳልናል ኃጥያታችንን እኛ እረስትን የምንፅናና ከሆነ እግዚአብሔር ያስብብናል››
ቅዱስ እንጦስ
አሰግድ ሣህሉ “ተሐድሶ ማለት እኔ ነኝ” አለ
* በስም ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት አባ ሰረቀ ከሀገር ሊወጡ ነው፤
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 5/2011)፦ ወደ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ መዋቅር በመግባት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ዓላማ ለማሳካት ከሚፍጨረጨሩትና ከእነርሱም መካከል እንደ ዋነኛ ከሚታዩት የወቅቱ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅጥረኞች አንዱ ሆነው አሰግድ ሣህሉ “ተሐድሶ ማለት እኔ ነኝ” ሲል በገዛ አንደበቱ መናገሩ ተሰማ፡፡ አሰግድ ይህን ምስክርነት ስለ ራሱ የሰጠው ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ለንባብ እንደሚበቃ በተጠቆመ አንድ መጽሔት ሰሞኑን በሰጠው ቃለ ምልልስ ነው፤ ንግግሩንም በአንድ ወቅት በ‹ተሐድሶ› ጉዳይ ላይ ለጠየቀችው አንዲት ሴት የመለሰው መሆኑ ተገልጧል፡፡
ግለሰቡ ቃለ ምልልሱን ከሰጠና መጽሔቱ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ማተሚያ ቤት ከገባ በኋላ ይህ ቃሉ ከቃለ ምልልሱ እንዲወጣለት አልያም ቃለ ምልልሱ ጨርሶ እንዲቀር “ደኅንነቶች ናቸው” በሚላቸው ግለሰቦች ዋና አዘጋጁን ማስፈራራቱ ታውቋል፡፡ አሰግድ በተለያዩ አጋጣሚዎች “ደኅንነቶች ናቸው” በሚላቸው ግለሰቦች እያስፈራራ ሕገ ወጥ ፍላጎቱን እንደሚያስፈጽም ያስታወሱት የዜና ምንጮቹ ግለሰቡ ከዚህ መንገዱ እንዲታቀብ ሊገደድ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡
አሰግድ ባለበት የሃይማኖት ችግርና ባቀረበው የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከትምህርት ገበታ ቢያገደውም ታኅሣሥ 27 ቀን 2003 ዓ.ም በኮሌጁ ላይ በመሠረተው ክስ “የኮሌጁ ውሳኔ አግባብ አይደለም” በሚል ሐምሌ ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም ትምህርቱን እየተከታተለ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ለክሱ በሰጠው ምላሽ፣ “ጉዳዩ የሃይማኖት ክርክርን የያዘ ስለሆነ ፍ/ቤቱ አከራክሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የለውም” ሲል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቧል፡፡ የፍሬ ነገር ክርክሩንም በተመለከተ፣ “ከሳሽ ቤተ ክርስቲያን የማትቀበለውን ትምህርት የሚያራምዱ በመሆናቸው፣ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት በዚሁ ጉዳይ አቤቱታ ቀርቦባቸው ቤተ ክርስቲያንም ይህን ማረጋገጧ፣ ከሳሽ ያለሰበካቸው በማታለል የቀበና መድኃኔዓለም ሰበካ ጉባኤ አባል ነኝ በማለታቸው ያቀረቡት ማስረጃ በደብሩ አስተዳዳሪ የተሰረዘ በመሆኑ” የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡ ደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን (http://www.dejeselam.org/2011/02/blog-post_10.html) ማቅረቧ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በማኅበረ ቅዱሳን ላይ በየጊዜው በፈጸሙት የስም ማጥፋት ድርጊት ክስ ተመሥርቶባቸውና በማስረጃ ተመስክሮባቸው እንዲከላከሉ ትእዛዝ የተሰጣቸው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ በአቡነ ጳውሎስ ጥያቄ ፍትሕ ሚኒስቴር ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ካስደረጉ በኋላ ነገ ቅዳሜ ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን - ዲሲ ለመብረር መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡ በዋና ሓላፊው ጥብቅ ቁጥጥር ሥር በሚዘጋጀው የመምሪያው ድረ ገጽ ላይ “ክሱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በነጻ እንደተሰናበቱ” አስመስለው እንዲዘገብ ያደረጉት አባ ሰረቀ ከሕግ የበላይነት ለመሸሽ በጀመሩት መንገድ ከሀገር ለመውጣት መወሰናቸውን ነው ምንጮቹ የጠቆሙት፡፡ አባ ሰረቀ በድረ ገጹ ያወጡት የተሳሳተ ዘገባ እንዲታረም ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ባዘዘው በፍትሕ ሚኒስቴር ሰዎች ቢነገራቸውም “እምቢ፣ አይሆንም፣ አልሰርዘውም” አልኳቸው እያሉ በጀብድ መልክ ሲያወሩ መሰንብታቸው ተገልጧል፡፡ የ1200 ዜጎችን ከ56 ሚልዮን ብር በላይ አላግባብ ወስዷል የተባለው የአስካሉካን ትሬዲንጉ ግርማይ ከሕግ ተጠያቂነት መሸሽ እንደማይችል ታውቆ ሰሞኑን በኢንተርፖልና በመንግሥት ጥረት በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል፡፡ የእኛው አባ ሰረቀስ? የፍትሕ ፈላጊ ኦርቶዶክሳውያን ጥያቄ ነው፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)