· የቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ/ሕግ፣ ደንብ/ እና የኦዲት ሪፖርት ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ዕውቅና መነፈጉ በመንግሥት አካላት ፊት የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፤
· “የመንበረ ፓትርያርኩ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዘንድ ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል” (የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተሳታፊ)
· “. . . ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት ቃለ ዐዋዲው በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አለው፤ [ነገር ግን] የሕግ አገልግሎቱ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁልጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” (ብፁዕ አቡነ ናትናኤል)
· “. . . አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ/ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም እያሉ በተደጋጋሚ ይነግሩናል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፡፡. . . ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም መተኛት በዝቷል፡፡ ይህ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ አቋሙን ማሳወቅ ይኖርበታል፤ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳ ተነጋግሮ መወሰን አለበት፡፡” (ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ)
· “ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን፡፡” (ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ)
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 20/2011)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምእመናን አንድነት በሰበካ ጉባኤ ተደራጅታ በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በአገልግሎት እና በምጣኔ ሀብት በኩል በራሷ ሕግና ሥርዓት በመመራት እንድትሠራ ለማድረግ ታስቦ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ያወጣው ቃለ ዐዋዲ ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ሀብቷን እና ንብረቷን ለማስጠበቅ ያለው ኀይል፣ በፍትሕ ተቋማት ዘንድ የሚሰጠው ዕውቅና እና ተቀባይነት እያጸጸ/ እያነሰ በመምጣቱ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ፡፡ ለቃለ ዐዋዲው ሕግ እና ደንብ ዕውቅና እና ተቀባይነት ማጣት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት ክፍል ሞያዊ አቅም ማጣት ቀዳሚ ሓላፊነቱን እንደሚወስድ የተመለከተ ቢሆንም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት “የድሮው ይበቃችኋል” በሚል መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ስለ መሆናቸው የሚደነግገውን አንቀጽ እንዳሻቸው እየተረጎሙ ለቃለ ዐዋዲው ተፈጻሚነት ዕንቅፋት በመፍጠር ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያጠቁ ተነግሯል፡፡
ረቡዕ ጥቅምት ስምንት፣ 2004 ዓ.ም ሁለተኛ ቀኑን በያዘው 30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ላይ እየቀረቡ በሚገኙት የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት ከደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ተወክለው የመጡ ተሳታፊ፣ “የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ የመዘበሩ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በኦዲት ምርመራ የተረጋገጠውን ማስረጃ ለፍርድ ቤት እናቀርባለን፤ ነገር ግን አይቀበሉንም፤ እንዲያውም የሙያ ማረጋገጫ እና የሥራ ፈቃድ ባላቸው የተሠራ ኦዲት ካልሆነ በቀር የመንበረ ፓትርያርክ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው ይነግሩናል፡፡ በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮ ቢወስንበት” በማለት ጠይቀዋል፡፡
ለተወካዩ ጥያቄ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ “ኦዲት ተደርጎ ጥፋት ከተገኘ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ በሕጋችን መሠረት ኦዲተር የሚላከው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች በመንግሥት ፍ/ቤቶች ዕውቅና አላቸው” ቢሉም የሰጡት ምላሽ በጥያቄው በተጨባጭ ከተጠቀሰው ችግር አኳያ በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡
ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተወካዩ ጥያቄያቸውን እንዲያብራሩ ዳግመኛ በሰጧቸው ዕድል፣ ቤተ ክርስቲያን “ኦዲተር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው የሚመደበው” የሚል ሕግ የላትም፤ ሕጉ ቢኖርም ሁሉንም አህጉረ ስብከት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ኦዲተር ብቻ ለማዳረስ አይቻልም፤ የቤተ ክርስቲያናችን ኦዲተሮች በሕግ ዕውቅና እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል፤ እዚህ አዳራሽ ተቀምጠን ዕውቅና አለን በማለት ብቻ የሚሆን አይደለም፤ በየቦታው ስንሄድ የኦዲት ሰነዳችን ውድቅ እየሆነ ነው ያለው፤ ሊታሰብበት ይገባል” በማለት ጥያቄያቸውን አጠናክረዋል፡፡
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት የቁጥጥር /ኦዲት/ አገልግሎቱ የተመሠረተበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ /ቃለ ዐዋዲው/ በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው አስረድተዋል፤ እንደ አብነትም በአንድ ወቅት የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንደ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይመዝገብ ተብሎ በነበረበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጠየቁት ማብራሪያ መሠረት ኮሚሽኑ በተቋማዊ ሕጋችን፣ ደንባችንና መመሪያችን እንደሚመራ /እንደሚታይ መገለጹን አስታውሰዋል፡፡
የተወካዩ ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ መመለስ እንደሚገባው ያስረገጡት ብፁዕነታቸው፣ ትኩረት ያደረጉት በቤተ ክህነቱ አዘውትሮ ይነሣል ባሉት የአገልጋዮች እና ሠራተኞች አስተዳደራዊ በደል ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ “ሠራተኞች በደል ደረሰብን ብለው በፍርድ ቤት አስተዳደሩን እየከሰሱ ገንዘብ ወጥቶ ይሰጥ እየተባለ ይሰጣቸዋል፡፡ የሕግ አገልግሎት ክፍሉ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁል ጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” በማለት በአስፈጻሚው አካል በኩል የሚታየውን የሙያዊ አቅም ክፍተት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው እንዲህ ቢሉም ለጉባኤው በተሰራጨው የ”ዐዋጅ ነጋሪ” መጽሔት በቀረበው የሕግ አገልግሎቱ የሥራ አፈጻጸም ግን ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በሥራ ነገር ክርክሮችና ይግባኞች ከ34 ጉዳዮች ከግማሽ በላዩን አስፈርዶ በተፈረዱበትም ይግባኝ እንደጠየቀ ሰፍሯል፡፡
የሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በበኩላቸው ዋናው ጉዳይ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እንደተባለው ሕጋችንን አለማስከበራችን መሆኑን በራሳቸው ልምድ አስረድተዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 85/65 ተፈቅዶ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም ታትሞ የወጣውን ቃለ ዐዋዲ በመያዝ፣ “አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ /ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም” እያሉ በተደጋጋሚ እንደሚነግሯቸው ብፁዕነታቸው ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አክለውም፣ “ይሁንና በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ሦስት አንቀጽ አምስት የሰፈረውን በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፤ በጅማው ጉዳይ ስላለፈው አደጋ ርምጃ እንወስዳለን ተብሎ ትንኮሳው ግን እስከ አሁን አልቆመምም፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም እንቅልፍ በዝቷል” ሲሉ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ በጋራ መክሮ አቋም እንዲይዝበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳው አካትቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍበት አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ ጥያቄ ጋራ በተከታታይ ከቀረቡት ውስጥ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት ተሠርተዋል ተብለው የሚቀርቡ ተግባራት በእውነትም ስለ መኖራቸው ማረጋገጥ ስለሚቻልበት ሥርዓት፣ ስለ ሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በምዕራብ ጎጃም - ባሕር ዳር የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ እንደሌለ ተደርጎ በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት መነገሩ ይገኝበታል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ሀ/ስብከት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ በሀ/ስብከቱ እንደሌለ ያቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ በማኅበረ ቅዱሳን እና በአርማጌዶን ቪሲዲዎች ላይ በፕሮቴስታንቶች አዳራሽ ሲጨፍሩ የሚታዩት ‹የተቀሰጡ መሪጌቶች› ከባሕርዳር አካባቢ መሆናቸውን በማስታወስ ይልቁንም አካባቢያዊ ሁኔታው ለጠቅላላው የአማራ ክልል የተሐድሶ መናፍቃን መፈልፈያ እንዳይሆን ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተገልጧል፡፡
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም በሰጡት አጫጭር ምላሽ፣ “ቤተ ክርስቲያናችን በማኅበራት ስም እየተወረረች ነው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ያልገባቸውና ከዚህ ዓለም ትዝታ ያልተላቀቁ ናቸው፤ ማኅበራት በዘፈቀደ ሳይሆን በቋሚ ሲኖዶሱ ተጠንቶ ነው ዕውቅና የሚሰጣቸው፤ በቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ መላእክት ስም የተቋቋሙ ማኅበራት/ ሰንበቴዎች ከጥንትም ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ ተቆራኝተው የነበሩ ናቸው፡፡ በስብከተ ወንጌል ስም ላሉት ግን ተጠንተው በማእከል ደረጃ ዕውቅና ሊሰጣቸው ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
በቃለ ዐዋዲው ዙሪያ የተደረገውን ውይይት ሲያጠቃልሉም “….ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከሁለቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አስተያየት በኋላ በብርቱ የተነቃቃ ከሚመስለው ጉባኤተኛ በርካታ እጆች ወጥተው ቢታዩም ውይይቱ በተጀመረው መልኩ ነገ ጠዋት እንደሚቀጥል በመግለጽ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ከቀትር በኋላ ከተደረገው ውይይት ቀደም ሲል የ21 አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፡- መልካም አስተዳደርን/ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን/ ለማስፈን በሀገረ ስብከት እና በወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በተሰጡ ሥልጠናዎች፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ማኅበራትን በመከላከል፣ ኢ-ጥሙቃንን እና መናፍቃንን አስተምሮ እና አሳምኖ በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በማጥመቅ፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ይዞታ በማስከበር፣ አብነት ት/ቤቶችንንና መምህራንን በገቢ በመደጎም እና በማጠናከር፣ እጓለ ሙታንንና የሕግ ታራሚ የሆኑ ወላጆች ያሏቸውን ልጆች በመከባከብ ላይ ያተኮረ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡
ከሪፖርቶቹ ይዘት ውስጥ፦
v የከፋ ቦንጋ ሀ/ስብከት ውስጥ በተቀሰቀሰ ሁከት በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ላይ ጥይት እስከ መተኮስ መደረሱ፣
v በአፋር ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለራስ አገዝ ልማት በሚሠሯቸው ሥራዎች ግብር መጠየቃቸው፣
v በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ብር 800,000 የፈጀ የአብነት ት/ቤት ተከፍቶ ዲያቆናትና ካህናት ሠልጥነው እየወጡ ፍሬውን ማየት መጀመሩ፣ በሰሜን ሸዋ በብር 23 ሚሊዮን ወጭ ዘመናዊ ት/ቤት እና የአብነት ት/ቤት ያቀናጀ ተቋም መከፈቱና በተለይም ለደቡቡ የሀገራችን ክፍል መጋቢ የሆኑ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ መገለጹ፣
v በሶማሌ ሀ/ስብከት የሊቀ ጳጳሱ ቶሎ ቶሎ መቀያየር ሀገረ ስብከቱን እያዳከመው መሆኑ፣
v በአንጻሩ የአዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሠራተኞች ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዳይዛወሩባቸው መጠየቃቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን by Deje Selam