- ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቤተ ክርስቲያን ወጥ/ማእከላዊ/ የበጀት አስተዳደር በምትከተልበት አሠራር ላይ ጉባኤው ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥሪ አድርገዋል።
- . የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ይሻሻላል፤ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በዕቅድ መሥራት እንዲለመድ ይደረጋል።
- . በ2004 ዓ.ም ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይታተማል፤ በ2000 ዓ.ም በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል አቀማመጥ በሆሄያት አገባብ እና በትርጉም ስልቶች ረገድ የክለሳ ምልክት ተደርጓል፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላትን የያዘ የሆሄያት አገባብ መጽሐፍ ይዘጋጃል።
- . ጉባኤው ለውይይት እና ጥያቄ በተፈቀደው የአንድ ሰዓት ጊዜ አንዳችም ሐሳብ ሳያነሣ አህጉረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት የ35% ፈሰስ /የፐርሰንት ገቢ/ ላይ ያተኮሩ ሪፖርቶችን መስማቱን ቀጥሏል።
- . ያረፉት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ታስበዋል።
- . ‹‹ስማቸውን የጠቀስናቸው ብፁዓን አባቶቻችን አልፈው እኛ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍና ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ቀርተናል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ/
- . የመናፍቃን እና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ መምጣቱ፣ ፕሮቴስታንቶች የሚፈጥሩት ትንኮሳና የባህል ወረራ፤ በጉራጌ ዞን እስላሞች በሐሰት ‹‹ክርስቲያኖች ስምንት መስጊዶችን አቃጠሉብን›› ብለው ለተወሰነ ጊዜ ክርስቲያኖችን ማሳሰራቸው፣ የቦታ ይገባናል ጥያቄ በማንሣት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ መሞከራቸው፤ በጅማ ‹‹እምነታችሁን ለውጡ›› እያሉ ምእመናንን ማወካቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሦስት አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ሰፈር በሙርሲ ብሔረሰብ በመቃጠሉ ምእመናን አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው፤ በሰሜን ወሎ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ለማክሸፍ ወደ ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ አራት አገልጋዮች በመኪና አደጋ መሞታቸው፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባር ጽላትን በፎርጅድ የመለወጥ ተንኮልና በሶዶ ወረዳ16 አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው፤ በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ 130 ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሰው ሠራሽ አደጋ መቃጠሉ፤ የሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በዘፈቀደ መንቀሳቀስ፣ በተለይም በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሕዝቡን በየቋንቋው የሚያስተምረው ሰባኬ ወንጌል አለመገኘት፣ በአዲስ አበባ የሕገ ወጥ ሰባክያን እንቅስቃሴ፣ በሊቃውንት ያልተመረመሩ መጻሕፍትና ካሴቶች በየዐውደ ምሕረቱ ሲሸጡ መታየታቸው እና 283 ቀሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ባለመመለሳቸው ተጨማሪ ገቢ መታጣቱ በበጀት ዓመቱ ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ተካቷል
- . ለጉባኤው ከወትሮው በተለየ ከብር 600,000 በላይ ወጪ ተደርጓል
(
ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 7/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 18/2011)፦
በየዓመቱ ጥቅምት ወር የሚካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ጠዋት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ባደረሱት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ከ48 አህጉረ ስብከት/ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ/ ከእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ስድስት በመሆን ተወክለው የመጡ ከ300 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት፣
‹‹ስማቸውን በጸሎት የጠራናቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አልፈው እኛ የቀረነው ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ነው፡፡ እኛ ከእነርሱ የተሻልን ሆነን ሳይሆን ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍ በዚህ ቦታ ተሰልፈናል፡፡ ብዙዎቻችን ከሊቃውንቶቻችን ስንማር ረጅም ዘመን ቆይተናል፡፡ ብዙ ልምድ አካብተናል፡፡ መማራችን፣ ማወቃችን፣ ረጅም ጊዜ መቆየታችን ከሥራ ከተለየ ጥቅም እንደሌለው አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን እንድንሠራ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ምእመኑም ሆነ ትውልዱ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ በደል፣ ፍርሃት እንዳይደርስባቸው እንድንጠብቃቸው ለእኔና እዚህ ላለነው ብፁዓን አባቶች ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ‹በጎቼን ጠብቁ› ተብሎ ከአባታችን ቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡
እግዚአብሔር እኔ እበልጣለሁ የሚል ሥርዐተ አልበኝነትን አይወድም፡፡ ሰዎችን ከክፉ ነገር ለማዳን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ በሓላፊነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በተጠያቂነት ስሜት መፈጸም ይገባል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
በመብራት መቋረጥ ምክንያት ካጠረው የቅዱስነታቸው መልእክት በመቀጠል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የልብ ድካም ሕመም እንዳለባቸው በመግለጽ እስከ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ ያለውን የሥራ ክንውን ሪፖርት ብቻ ነው ለማሰማት የቻሉት፡፡ ቀሪው የሪፖርቱ ክፍል ከ15 ደቂቃ ጫን ያለ ‹‹የሻይ ዕረፍት›› በኋላ በጽ/ቤቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ነበር የቀረበው፡፡
ከ48ቱ አህጉረ ስብከት
በአጥቢያ ደረጃ ብር 451,996,682.53፣
በሀገረ ስብከት ደረጃ ብር 90,692,854.51፣
በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ብር 43,877,275.34፣
ገቢ ከሚያስገቡ ስምንት አምራች ድርጅቶች እና ስድስት መምሪያዎች ብር 90,766,002.09 በአጠቃላይ በ2003 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዓመት
ብር 542,762,684.62 ገቢ መገኘቱን ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ዝርዝር ላይ አመልክተዋል፡፡
‹‹ይህ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ኀይል እንደ አበው ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን በአንድነት ቢያዝና እንደ አስፈላጊነቱ በየደረጃው ለሁሉም ቢተነተን/ቢበጀት/ ችግራችን ሁሉ ተቃሎ፣ አገልግሎታችን ሠምሮ ምንኛ ባማረብን ነበር?›› ሲሉ የጠየቁት ብፁዕነታቸው እስከ አሁን ድረስ
ማዕዳችን ‹‹
ከአንድ መሶብ እየወጣ ተሠርቶ በአንድነትና በበረከት ልንቋደሰው አለመቻላችን›› እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ማጠቃለያም አጠቃላይ ጉባኤው ከተጀመረ 30 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ግባችን በቂ ነው የሚባል ባለመሆኑ ገና እጅን አጣጥፎ የሚያስቀምጥ አለመሆኑን በማስታወስ፣
‹‹…ይህ ዐቢይ እና ወሳኝ ጉባኤ በብርሃነ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ በጥልቅ መክሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር እንዲቃና፣ አገልግሎታችን እንዲሟላ፣ እኩልነት እንዲሰፍን የበጀት ማእላዊነት እንዲኖር በቅን ልቡና አስቦበት ጥናታዊ ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ አክብሮት በተሞላ ልቡና አሳስባለሁ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ስለተከናወነው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንዳተተው፣ የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ 26,187 ሐዲስ አማንያን በወንጌል ትምህርት በማመን ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ገብተዋል፤ ወደ ሌላ እምነት ሄደው የነበሩ 241 ጥንተ ኦርቶዶክሳውያን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነዋል፡፡ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰባክያን እየተዘዋወሩ እንዲሰብኩ ከመደረጉም በላይ በብፁዓን አባቶች እና ሰባክያነ ወንጌል በየወረዳውና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ሥምሪቶች ተደርገዋል፤ ታላላቅ ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡ በየማሠልጠኛው ለሰለጠኑ ካህናት፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት እና ለንስሐ አባቶች በሠለጠኑ መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በማእከል ታውቀው ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና ማኅበራት እንሰብካለን እያሉ ምእመናንን ግራ እንዳያጋቡና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያፋልሱ ጥበቃ፣ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል፡፡
‹‹እምነታችሁን ትታችሁ የእኛን እምነት ተከተሉ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ የተገኙ መናፍቃን ተከሰው በገንዘብና በእስራት ተቀጥተዋል፡፡
በአንጻሩ የተለያየ ቋንቋ የሚናገረውን ወገን በሚሰማው ቋንቋ የሚያስተምረው በቂ የመምህራን ቁጥር አለመኖሩ፣ ከሦስቱም ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት በየዓመቱ ቢመደቡም በተመደቡበት አለመገኘትና የበጀታቸው አብሮ መቅረት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎ የተጋበዙ ‹ሰባክያን› ከብር 30,000 - 40,000 ድረስ ክፍያ ካልተከፈለን እያሉ በአገልግሎት ላይ አለመገኘታቸው፣ የመናፍቃንና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየሰፋ መምጣትና
የስድስት ካህናት እና የ109 ምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መግባት፣ እንደ ሰሜን ወሎ እና መተከል ባሉት አህጉረ ስብከት መናፍቃኑ ያስከዷቸውን ካህናት በማሰለፍ የሥራ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡
ከዚህም አኳያ በተያዘው የበጀት ዓመት የአብነት መምህራንንና የካህናት ማሠልጠኛዎችን ለማጠናከር/
በዚህ ዓመት በተለይም በሰሜን ሸዋ መምህራን ከብር 400 - 2000 በሚደርስ ደመወዝ እንደተቀጠሩት፣ ለአብነት መምህራን የጡረታ ዋስትና እንደተጠበቀላቸው/፣ ሰባክያነ ወንጌልን በማብዛት የተለያየ ቋንቋ የሚሰማውን ኅብረተሰብ ለማስተማርና ለማስተባበር የየአካባቢውን ተወላጆች በየቋንቋቸው በማሠልጠን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ እና ነባሮቹም እንዲታደሱ/ከዚህም መካከል በጆርዳን በነጻ በተገኘው 3000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በኢየሩሳሌም ገዳም የሚሠራውን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ/፣ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች እንዲከበሩ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር/ካርታ/ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ቃለ ዐዋዲውን ለማሻሻልና የማጠናከሪያ ሥምሪት ለማካሄድ ዕቅድ ስለ መያዙ፣
በአጠቃላይ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ለማብዛትና ለመጠበቅ፣ በምእመናን አስተዋፅኦና በልማት ውጤት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ፣ ማእከላዊነትን የጠበቀ መልካም አስተዳደር ከላይ እስከ ታች በማስፈን የካህናትን ኑሮ ለማሻሻልና ድህነትን ለማጥፋት መታቀዱ በብፁዕነታቸው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡
ለዚሁ ጉባኤ የተዘጋጀው
‹‹ዐዋጅ ነጋሪ›› የተሰኘው የሰበካ ጉባኤ መመሪያ መጽሔት በአራተኛ ዓመት ቁጥር ሰባት እትሙ፣ 48ቱ አህጉረ ስብከት እያንዳንዳቸው ያሏቸውን
የምእመናን ብዛት፣ የገዳማት እና አድባራት ብዛት፤ በስብከተ ወንጌል፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ገዳማትን እና ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከር፣ በራስ አገዝ ልማት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ በተደረጉ አስተዋፅኦዎችና ሌሎችም ተግባራት ዙሪያ የተፈጸሙ ክንዋኔዎችን በተመለከተ የተላኩ ሪፖርቶች በአሕፅሮት ተካተውበት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰራጭቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ማሽኖች በእርጅና ምክንያት ከሚሠሩበት የሚቆሙበት ጊዜ የበለጠ እንደሆነና ለእድሳትም ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይኸው መጽሔትም በሌላ የግል ማተሚያ ቤት መታተሙ ታውቋል፡፡ ለጉባኤው ዝግጅት ቅርበት ያላቸው የቤተ ክህነቱ ምንጮች እንዳስረዱት፣
ለመጽሔቱ ኅትመት ፣ በጉባኤው ላይ ይታያል ተብሎ ለሚጠበቀው የፓትርያርኩ ከ1984 - 2003 ዓ.ም መዋዕለ ዜና የሚዘክር ዶክመንታሪ ፊልም ዝግጅት፣ ለጉባኤው አባላት አበልና መስተንግዶ በሚል የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ሁለት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አባሎች የሚገኙበት የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ብር 600,000 ወጪ አድርጓል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የጉባኤው ዝግጅት ወጭ ግን ከብር 100,000 አይበልጥም ነበር - እንደ ምንጮቹ መረጃ፡፡
የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በንባብ ቀርቦ ከተሰማ በኋላ በቀጥታ ወደ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ሽግግር ተደርጎ፣ በደቡብ ሱዳን ባለባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ሳቢያ ቅድሚያ የተሰጣቸው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀ/ስብከት የሆነው የጋምቤላ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተመጠነ ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በመጽሔቱ በተገለጸው ሪፖርት መሠረት በሀ/ስብከቱ 39 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤ 327 ካህናት በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፤ የምእመናኑ ቁጥር አልተገለጸም፤ በቅኔ፣ በአቋቋም፣ በቅዳሴ እና በመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 47 የክልሉ ተወላጆች በዲቁና እና ቅስናም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት አምነው ተጠምቀዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሀ/ስብከቱ ካስገባው ብር 1,176,115.50 ውስጥ የመንበረ ፓትርያርክ 35 በመቶ ብር 82,796.91 ገቢ ማድረጉ ተገልጧል፡፡
በዚህ መልኩ የጅማ፣ የመቐለ፣ የኢሉ አባቦራ፣ ድሬዳዋ፣ ጋሞጎፋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ባሌ፣ ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች በተከታታይ ሪፖርታቸው ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ፣ የጅማ እና የኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት ከአክራሪ እስልምና የተነሣ ያለባቸውን ተግዳሮት ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋው ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ገሪማን ‹‹ንዑድ፣ ክቡር›› እያሉ ደጋግመው በማወደሳቸው በጉባኤተኛው ተሥቆባቸዋል፡፡
በአህጉረ ስብከቱ የሪፖርት አቀራረብ ሥራ አስኪያጆቹ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በ‹ዐቃቤ ሰዓትነት› በሰጡትና በጥብቅ በሚቆጣጠሩት ከ5 - 10 ደቂቃ ባለው ጊዜ ሪፖርታቸውን በችኮላ ያቀርባሉ፡፡ ከዚሁም ላይ እንደ ወትሮው ሁሉ ለመንበረ ፓትርያርክ በሚደረገው የዘመኑ የ35 ከመቶ ፈሰስ ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የሰሰሱ መጠን የአህጉረ ስብከቱ ጥንካሬ እና ዋናው የሥራ ፍሬያቸው መለኪያ መስሎ ታይቷል፡፡
ከቀትር በኋላ ከ10፡30 - 11፡25 ባለው ጊዜ በቀረቡት ሪፖርቶች፣ (በተለይም የሰበካ ጉባኤ እና የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ) ላይ ውይይት እና ጥያቄ እንደሚኖር በተገለጸው መሠረት መድረኩ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለተሰብሳቢው ክፍት መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም አንዳችም ጥያቄ ይሁን ውይይት ሳይነሣ ቀርቷል፡፡ የፍርሃት ይሁን የፍላጎት ማጣት? ብለው ሲጨነቁ ለነበሩት በጉባኤው የ
ደጀ ሰላም ታዛቢዎች ምላሽ የሰጠው ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ፣
‹‹ጥያቄ እና አስተያየት ከሌለ ሪፖርቱ ይቀጥል›› ብለው ከመናገራቸው ቤቱ በተሰብሳቢዎቹ ለየት ያለ የጭብጨባ ዘይቤ የተናጋበት ሁኔታ ነው - አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡
በጉባኤው ላይ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የየራሳቸው ሪፖርት የሚያቀርቡበት ቀን ያላቸው ሲሆን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ዛሬ ያቀረቡትን የማእከላዊ ጽ/ቤቱን ሪፖርት ሙሉ ቃልና የ48ቱን አህጉረ ስብከት የተጨመቀ ሪፖርት
ከ‹‹ቃለ ዐዋዲ›› መጽሔት እንዳገኘነው ከዚህ በታች አቅርበንላችኋል፡፡
30ኛው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ጥቅምት 12 ቀን ለሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካስተላለፉትና በመጽሔቱ ላይ ከታተመው መልእክታቸው የሚከተለውን ይገኝበታል፡-
‹‹ይህን መሰል ጉባኤ ስናካሂድ የአሁኑ ጉባኤያችን ለሠላሳኛ ጊዜ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው፡፡ በየጉባኤያቱ የሚዘጋጁ አርእስተ ጉዳዮችና የሚወጡ ዕቅዶች፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ እየቀረቡ ከተመከረባቸው በኋላ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ስብሰባችን የጉባኤውን ሪፖርት አንብበን የምንለያይበት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዕቅድ የምናቅድበትና የምንወያይበት ስብሰባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡››
እውን ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራስ እስከ እግሯ በአንድ አዳራሽ የተገኘችበት ስብሰባ በሆነውም ባልሆነውም የሪፖርት ጋጋታ ከመጨናነቅ፣ በረባ ባልረባው የውዳሴ ዝናም ከማጭበጨብ፣ ጫን ባለ የእህል ውኃ ግብዣ ከመደንዘዝ ተርፎ፡- የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን በሚያሤሩት የውስጥ አደጋ፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በደቀኑብን የውጭ ስጋት፣ እንደተባለው ጥናትና ሥር ነቀል ርምጃ በሚሻው የፋይናንስ፣ የሰው ኀይል እና የሌሎች ሀብቶች አስተዳደሯና ልማታዊ ክንውኗ ዙሪያ ይመክር ይሆን? ከቀደመውና ከዛሬው ውሎ አኳያ የሚሆን አይመስልም፡፡ ርግጡን ግን በጉባኤው የአምስት ቀናት ቆይታ የምናየው ይሆናል፡፡
by deje selam