ይቅርታ ወይም ይቅር ባይነት የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በሚኖርበት ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስሮች ወይም ግንኙነቶች አማካኝነት ከሌሎች የማኅበረሰቡ ክፍሎች ጋር ለሚኖረው ጤናማ የኑሮ ጥምረት ትልቅ ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ። ይቅር መባባል ያለፈ በደልን አጥቦና አስወግዶ ለቀሪው ህይወት አዲስ ልቡናን በመፍጠር ግንኙነታችንን ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ ተበዳድለው፣ ተቀያይመው፣ ተኮራርፈው ከዚያም ባለፈ ደም ተቃብተው እና ለቂም በቀል ሌት ተቀን በሃሳብም በግብርም ይሯሯጡ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልቡናቸው የተቋጠረውን የመጠፋፋት ሕልምና ዕቅድ ወደ ጎን ትተው አንዱ ካንዱ በጋብቻ እስከመጣመርና አንዱ ላንዱ ዋስ ጠበቃ እስከመሆን ያደርሳቸዋል። በዚሁ መልካም አጋጣሚ ምክንያትም ሊጠፋ የነበረው ሕይወት፣ ሊፈስ የነበረው ደም እና ሊጎድል የነበረው አካል ከጥፋት፣ ከመፍሰስና ከመጉደል ይድናል።
ከዚህም ባለፈ ቂም በቀል በይቅርታ እስካልተደመደመ ድረስ ጥፋቱ መቋጫ የለውም። አንዱ ላለፈ በደሉ አዲስ በደል ሲፈፅም ሌላኛውም አፀፋውን ሲመልስ የሁለቱም ወገኖች በምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ መጠፋፋቱ ይቀጥላል። እንዲህ ዓይነቱ ለይቅርታ ቦታ አለመስጠት በተለይ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በእኛ በኢትዮጵያውያን ይብሳል። ምክንያቱ ምን ይሆን? በምጣኔ ሃብት አለማደጋችን፣ በቴክኖሎጂ አለመበልፀጋችን ወይም ገና ያልደረስንበትና ያልተማርነው ዘመናዊ ትምህርት ይኖር ይሆን? ትልቁ መንስዔ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል እንዳልሆነ የምንገነዘበው እነዚህ ምክንያትች ሞልተው የተትረፈረፉላቸው ወገኖቻችን ይባስ ብለው የችግሩ ሰለባ እነሱ መሆናቸው ነው።
ያደግንበት ማኅበረሰብም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በእትንኩኝ ባይነትና ክንዴን ሳልንተራስ እንዴት እደፈራለሁ? አስተሳሰቡ በደንብ አድርጎ አጥምቆናል። ገና ከእናታችን ማኅፀን ከመውጣታችንም ደም መላሽ ብሎ ስም ያወጣልናል። አንደበታችን እማማ አባባ ማለት ሳይጀምር በቂም በቀል ዲፕሎማ ከቤተሰባችን እና ከአካባቢያችን በከፍተኛ ማዕረግ እንመረቃለን። ከዚያ በኋላ ልክ ግብፃውያን እናቶች ልጆቻቸውን አባይ ሕይወትህ ነው እያሉ እንደሚያሳድጉት ሁሉ ለእኛም የስማችንን ትርጓሜ ከወደፊቱ ስራችን ዕቅድ ጋር እየተነገረን እናድጋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝብን እናዝናናበታለን በሚል ሽፋን የሚወጡ ዘፈኖችም የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብ ለመግለፅ እንዲሁም ለግጥሙ ቤት መድፋት እንጂ ጭብጡ በማኅረሰቡ ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ባለማስተዋል የሚዘፈኑ ዘፈኖች አሉ። “ተበድዬስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ” የሚል ዘፈን ሲያዳምጥና አብሮ ሲያንጎራጉር ያደገ ሰው ለይቅርታ ያለው ቦታ ቢያንስ ኸረ እስከ ጭራሹም ባይኖረው ምን ይደንቃል?
ሁላችንም እንደምናስታውሰው በጀግኖች አባቶቻችን ቆራጥ ተጋዳይነት ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚተርፍ የነፃነት ፋና በዓድዋ ተራሮች ተንቦግቡጎ ባልጠበቀውና ባላሰበው መልኩ ድል የተደረገው የኢጣልያ መንግስት ይህንን በዓለም አቀፍ አደባባይ የውርደት ሸማ ያለበሰውን የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ቂም ለመወጣት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን በመሪር ስቃይ አልፈዋል። እስቲ እነዚህን የነፃነታችን አምድና ለዛሬው እኛነታችን የሕይወትን መስዋዕትነት ከፍለው ስማቸውን በልባችን ፅላት ላይ በወርቅ ማኅተም ያተሙትን ወገኖቻችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን እናስባቸው።
በዚያን ጊዜ እነደዚያ ያለውን የጭካኔ ርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘውን አካል ብናገኘውና እጅና እግሩ ታስሮ ፊት ለፊታችን ቢቀርብልን ምን ዓይነት ርምጃ ይሆን የምንወስድበት? እንደው የትኛውን የቅጣት ዓይነት ብንቀጣው ነው አንጀታችን ቅቤ የሚጠጣው? ምን ዓይነት የአገዳደል ስልት ብንጠቀምና ብንገድለው ነው ያለፈውን የወገኖቻችን ሕይወት፣ የጎደለውን አካላቸውን እና የፈሰሰውን ደማቸውን ዳግም ማግኘት የምንችለው? ቁርጥርጥ አድርገን ብንፈጨውና ወደ አፈር ብንቀይረው ከዚያም ዳግም እንደ ጭቃ አብኩተን ሰውዬውን ሰርተነው እና ሃይሉ ኖሮን እስትንፋስ እንዲኖረው አድርገን እንደገና ብንቆራርጠው ይህንንም ሂደት ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን ቁጥር ብንደጋግመው ስንቶቹን ይሆን ዳግም በሕይወት የምናገኛቸው? ምንም። እርሱ በከፈተው የክፋትና የጭካኔ ጎዳና አብረነው እንድንጓዝ እና እርሱ ለሰራው ጥፋት በሚጠየቅበት ቦታ ብቸኝነት እንዳይሰማው ከማድረግና ከሚከፈለው ክፍያ ተቋዳሽ ከመሆን ያለፈ ጠቀሜታ የለውም።
ታድያ ቂም በቀሉ ፋይዳው ምንድነው? የመንፈስ እርካታ ይገኝበት ይሆን? በቂም በቀል ደስታና እፎይታን ብሎም እርካታን የሚያገኘው መንፈስ እንዴት ያለው መንፈስ ነው? በእውነት ነፍሳችን በእንደዚህ ያለ ድርጊት ደስታን ታገኝ ይሆን? በጭራሽ። ቂም በቀል ጊዜያዊ የሆነ እርካታን ለስጋችን ይሰጠው ይሆናል እርሱም ቢሆን ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ይፀፀታል። ያጣሁትን መልሼ ላላገኝ ይህንን ማድረጌ ምን ጠቀመኝ? ለምንስ የሰነፎችን መንገድ ተከተልኩኝ? እያለ ራሱን መውቀሱ አይቀሬ ነው። በደልን በበደል፣ ክፋትንም በክፋት፣ ተንኮልንም በተንኮል እንሸፍናለን በሚል የዋህ አስተሳሰብ ታስረን የነገሮችን ውል ከማጥፋት ይልቅ ጥፋትን ተራርሞ ክፍተትን በይቅረታ መሙለቱ የታላቅነትና የአስተዋይነት ብሩሕ ምልክት ነው። ይህ ይቅርታና ይቅር ባይነት መገኛው የት ይሆን?
እንደ እኔ አመለካከት ይቅርታ እና ይቅር ባይነት ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ምንም እንኳን ይቅርታ መደራረግ ለስጋዊ ኑሯችንም ታላቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም ዋናውና ከዚህ የሚበልጠው ግን መንፈሳዊው ዋጋ ነው። ይህንን መንፈሳዊ ዋጋ ያገኝ ዘንድ ዘወትር የሚተጋ ሰው ልቡናው ለይቅርታ የፈጠነ ነው። በዚህ ምድር በበዳዩ ከተበደለው በደል ይልቅ በሰማይ የሚያገኘው ክብር ሚዛን ይደፋለታል። እዚህ ላይ ግን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ነገር አለ። ይቅር ባይነት ቀላል አይደለም እንደማንኛውም ክብርን እንደሚያጎናፅፍ ተጋድሎ ሁሉ እርሱም ከፍተኛ ተጋድሎ ያሻዋል። በአፋችን ለመናገር እንደሚቀለው ያህል ለመተግበሩ ቀላል አይደለም። ይቅር ለማለት ስናስብ ብዙ ፈተናዎች ፊታችን ይጋረጣሉ። ፈተናው ከራስ ይጀምራል የቤተሰብ ፈተናም አለው እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖም አለው። እነዚህን ፈተናዎች በድል አድራጊነት መወጣት የሚችል ሰው ነው ይቅር የሚለው እና ሰማያዊውን ክብር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኘው።
ቁርሾን በሆድ ይዞ ዘወትር መበላላትን፣ መጠፋፋትን እና ልኩን/ለኳን አሳያታለሁ ባይነትን የዘወትር መገለጫው የሆነውን ሰጋችንን ሰማያዊውን ተስፋ አሻግራ ለምትመለከተው ነፍሳችን ስናስገዛ መንፈሳዊነት በሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተለኮሰ ሻማ ከሩቅ ያበራል። የዚያን ጊዜ የበደሉንን አካላት መጥተው ይቅርታ እስኪሉን ሳንጠብቅ አስቀድመን ይቅርታን እናደርግላቸዋለን። የሰማያዊው ክብር ባለቤቶች መሆናችንን እናውቃለንና ይቅርታውን ባደረግን ወቅት ከመቼውም ይበልጥ ውስጣችን በሐሴት ይሞላል። የሰላም እንቅልፍም እንተኛለን።
ቸር ያሰማን፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment