Wednesday, October 19, 2011

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርታዥ

  • ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቤተ ክርስቲያን ወጥ/ማእከላዊ/ የበጀት አስተዳደር በምትከተልበት አሠራር ላይ ጉባኤው ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥሪ አድርገዋል
  • . የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ይሻሻላል፤ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በዕቅድ መሥራት እንዲለመድ ይደረጋል
  • . በ2004 ዓ.ም ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይታተማል፤ በ2000 ዓ.ም በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል አቀማመጥ በሆሄያት አገባብ እና በትርጉም ስልቶች ረገድ የክለሳ ምልክት ተደርጓል፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላትን የያዘ የሆሄያት አገባብ መጽሐፍ ይዘጋጃል
  • . ጉባኤው ለውይይት እና ጥያቄ በተፈቀደው የአንድ ሰዓት ጊዜ አንዳችም ሐሳብ ሳያነሣ አህጉረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት የ35% ፈሰስ /የፐርሰንት ገቢ/ ላይ ያተኮሩ ሪፖርቶችን መስማቱን ቀጥሏል
  • . ያረፉት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ታስበዋል
  • . ‹‹ስማቸውን የጠቀስናቸው ብፁዓን አባቶቻችን አልፈው እኛ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍና ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ቀርተናል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ/
  • . የመናፍቃን እና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ መምጣቱ፣ ፕሮቴስታንቶች የሚፈጥሩት ትንኮሳና የባህል ወረራ፤ በጉራጌ ዞን እስላሞች በሐሰት ‹‹ክርስቲያኖች ስምንት መስጊዶችን አቃጠሉብን›› ብለው ለተወሰነ ጊዜ ክርስቲያኖችን ማሳሰራቸው፣ የቦታ ይገባናል ጥያቄ በማንሣት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ መሞከራቸው፤ በጅማ ‹‹እምነታችሁን ለውጡ›› እያሉ ምእመናንን ማወካቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሦስት አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ሰፈር በሙርሲ ብሔረሰብ በመቃጠሉ ምእመናን አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው፤ በሰሜን ወሎ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ለማክሸፍ ወደ ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ አራት አገልጋዮች በመኪና አደጋ መሞታቸው፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባር ጽላትን በፎርጅድ የመለወጥ ተንኮልና በሶዶ ወረዳ16 አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው፤ በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ 130 ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሰው ሠራሽ አደጋ መቃጠሉ፤ የሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በዘፈቀደ መንቀሳቀስ፣ በተለይም በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሕዝቡን በየቋንቋው የሚያስተምረው ሰባኬ ወንጌል አለመገኘት፣ በአዲስ አበባ የሕገ ወጥ ሰባክያን እንቅስቃሴ፣ በሊቃውንት ያልተመረመሩ መጻሕፍትና ካሴቶች በየዐውደ ምሕረቱ ሲሸጡ መታየታቸው እና 283 ቀሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ባለመመለሳቸው ተጨማሪ ገቢ መታጣቱ በበጀት ዓመቱ ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ተካቷል
  • . ለጉባኤው ከወትሮው በተለየ ከብር 600,000 በላይ ወጪ ተደርጓል
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 7/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 18/2011)፦ 
በየዓመቱ ጥቅምት ወር የሚካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ጠዋት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ባደረሱት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ከ48 አህጉረ ስብከት/ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ/ ከእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ስድስት በመሆን ተወክለው የመጡ ከ300 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት፣ ‹‹ስማቸውን በጸሎት የጠራናቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አልፈው እኛ የቀረነው ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ነው፡፡ እኛ ከእነርሱ የተሻልን ሆነን ሳይሆን ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍ በዚህ ቦታ ተሰልፈናል፡፡ ብዙዎቻችን ከሊቃውንቶቻችን ስንማር ረጅም ዘመን ቆይተናል፡፡ ብዙ ልምድ አካብተናል፡፡ መማራችን፣ ማወቃችን፣ ረጅም ጊዜ መቆየታችን ከሥራ ከተለየ ጥቅም እንደሌለው አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን እንድንሠራ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ምእመኑም ሆነ ትውልዱ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ በደል፣ ፍርሃት እንዳይደርስባቸው እንድንጠብቃቸው ለእኔና እዚህ ላለነው ብፁዓን አባቶች ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ‹በጎቼን ጠብቁ› ተብሎ ከአባታችን ቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ 

እግዚአብሔር እኔ እበልጣለሁ የሚል ሥርዐተ አልበኝነትን አይወድም፡፡ ሰዎችን ከክፉ ነገር ለማዳን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ በሓላፊነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በተጠያቂነት ስሜት መፈጸም ይገባል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡



በመብራት መቋረጥ ምክንያት ካጠረው የቅዱስነታቸው መልእክት በመቀጠል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የልብ ድካም ሕመም እንዳለባቸው በመግለጽ እስከ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ ያለውን የሥራ ክንውን ሪፖርት ብቻ ነው ለማሰማት የቻሉት፡፡ ቀሪው የሪፖርቱ ክፍል ከ15 ደቂቃ ጫን ያለ ‹‹የሻይ ዕረፍት›› በኋላ በጽ/ቤቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ነበር የቀረበው፡፡

ከ48ቱ አህጉረ ስብከት በአጥቢያ ደረጃ ብር 451,996,682.53፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ ብር 90,692,854.51፣ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ብር 43,877,275.34፣ ገቢ ከሚያስገቡ ስምንት አምራች ድርጅቶች እና ስድስት መምሪያዎች ብር 90,766,002.09 በአጠቃላይ በ2003 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዓመት ብር 542,762,684.62 ገቢ መገኘቱን ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ዝርዝር ላይ አመልክተዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ኀይል እንደ አበው ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን በአንድነት ቢያዝና እንደ አስፈላጊነቱ በየደረጃው ለሁሉም ቢተነተን/ቢበጀት/ ችግራችን ሁሉ ተቃሎ፣ አገልግሎታችን ሠምሮ ምንኛ ባማረብን ነበር?›› ሲሉ የጠየቁት ብፁዕነታቸው እስከ አሁን ድረስ ማዕዳችን ‹‹ከአንድ መሶብ እየወጣ ተሠርቶ በአንድነትና በበረከት ልንቋደሰው አለመቻላችን›› እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ማጠቃለያም አጠቃላይ ጉባኤው ከተጀመረ 30 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ግባችን በቂ ነው የሚባል ባለመሆኑ ገና እጅን አጣጥፎ የሚያስቀምጥ አለመሆኑን በማስታወስ፣ ‹‹…ይህ ዐቢይ እና ወሳኝ ጉባኤ በብርሃነ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ በጥልቅ መክሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር እንዲቃና፣ አገልግሎታችን እንዲሟላ፣ እኩልነት እንዲሰፍን የበጀት ማእላዊነት እንዲኖር በቅን ልቡና አስቦበት ጥናታዊ ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ አክብሮት በተሞላ ልቡና አሳስባለሁ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስለተከናወነው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንዳተተው፣ የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ 26,187 ሐዲስ አማንያን በወንጌል ትምህርት በማመን ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ገብተዋል፤ ወደ ሌላ እምነት ሄደው የነበሩ 241 ጥንተ ኦርቶዶክሳውያን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነዋል፡፡ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰባክያን እየተዘዋወሩ እንዲሰብኩ ከመደረጉም በላይ በብፁዓን አባቶች እና ሰባክያነ ወንጌል በየወረዳውና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ሥምሪቶች ተደርገዋል፤ ታላላቅ ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡ በየማሠልጠኛው ለሰለጠኑ ካህናት፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት እና ለንስሐ አባቶች በሠለጠኑ መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በማእከል ታውቀው ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና ማኅበራት እንሰብካለን እያሉ ምእመናንን ግራ እንዳያጋቡና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያፋልሱ ጥበቃ፣ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል፡፡ ‹‹እምነታችሁን ትታችሁ የእኛን እምነት ተከተሉ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ የተገኙ መናፍቃን ተከሰው በገንዘብና በእስራት ተቀጥተዋል፡፡

በአንጻሩ የተለያየ ቋንቋ የሚናገረውን ወገን በሚሰማው ቋንቋ የሚያስተምረው በቂ የመምህራን ቁጥር አለመኖሩ፣ ከሦስቱም ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት በየዓመቱ ቢመደቡም በተመደቡበት አለመገኘትና የበጀታቸው አብሮ መቅረት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎ የተጋበዙ ‹ሰባክያን› ከብር 30,000 - 40,000 ድረስ ክፍያ ካልተከፈለን እያሉ በአገልግሎት ላይ አለመገኘታቸው፣ የመናፍቃንና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየሰፋ መምጣትና የስድስት ካህናት እና የ109 ምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መግባት፣ እንደ ሰሜን ወሎ እና መተከል ባሉት አህጉረ ስብከት መናፍቃኑ ያስከዷቸውን ካህናት በማሰለፍ የሥራ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ከዚህም አኳያ በተያዘው የበጀት ዓመት የአብነት መምህራንንና የካህናት ማሠልጠኛዎችን ለማጠናከር/በዚህ ዓመት በተለይም በሰሜን ሸዋ መምህራን ከብር 400 - 2000 በሚደርስ ደመወዝ እንደተቀጠሩት፣ ለአብነት መምህራን የጡረታ ዋስትና እንደተጠበቀላቸው/፣ ሰባክያነ ወንጌልን በማብዛት የተለያየ ቋንቋ የሚሰማውን ኅብረተሰብ ለማስተማርና ለማስተባበር የየአካባቢውን ተወላጆች በየቋንቋቸው በማሠልጠን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ እና ነባሮቹም እንዲታደሱ/ከዚህም መካከል በጆርዳን በነጻ በተገኘው 3000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በኢየሩሳሌም ገዳም የሚሠራውን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ/፣ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች እንዲከበሩ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር/ካርታ/ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ቃለ ዐዋዲውን ለማሻሻልና የማጠናከሪያ ሥምሪት ለማካሄድ ዕቅድ ስለ መያዙ፣ በአጠቃላይ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ለማብዛትና ለመጠበቅ፣ በምእመናን አስተዋፅኦና በልማት ውጤት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ፣ ማእከላዊነትን የጠበቀ መልካም አስተዳደር ከላይ እስከ ታች በማስፈን የካህናትን ኑሮ ለማሻሻልና ድህነትን ለማጥፋት መታቀዱ በብፁዕነታቸው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡

ለዚሁ ጉባኤ የተዘጋጀው ‹‹ዐዋጅ ነጋሪ›› የተሰኘው የሰበካ ጉባኤ መመሪያ መጽሔት በአራተኛ ዓመት ቁጥር ሰባት እትሙ፣ 48ቱ አህጉረ ስብከት እያንዳንዳቸው ያሏቸውን የምእመናን ብዛት፣ የገዳማት እና አድባራት ብዛት፤ በስብከተ ወንጌል፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ገዳማትን እና ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከር፣ በራስ አገዝ ልማት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ በተደረጉ አስተዋፅኦዎችና ሌሎችም ተግባራት ዙሪያ የተፈጸሙ ክንዋኔዎችን በተመለከተ የተላኩ ሪፖርቶች በአሕፅሮት ተካተውበት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰራጭቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ማሽኖች በእርጅና ምክንያት ከሚሠሩበት የሚቆሙበት ጊዜ የበለጠ እንደሆነና ለእድሳትም ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይኸው መጽሔትም በሌላ የግል ማተሚያ ቤት መታተሙ ታውቋል፡፡ ለጉባኤው ዝግጅት ቅርበት ያላቸው የቤተ ክህነቱ ምንጮች እንዳስረዱት፣ ለመጽሔቱ ኅትመት ፣ በጉባኤው ላይ ይታያል ተብሎ ለሚጠበቀው የፓትርያርኩ ከ1984 - 2003 ዓ.ም መዋዕለ ዜና የሚዘክር ዶክመንታሪ ፊልም ዝግጅት፣ ለጉባኤው አባላት አበልና መስተንግዶ በሚል የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ሁለት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አባሎች የሚገኙበት የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ብር 600,000 ወጪ አድርጓል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የጉባኤው ዝግጅት ወጭ ግን ከብር 100,000 አይበልጥም ነበር - እንደ ምንጮቹ መረጃ፡፡

የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በንባብ ቀርቦ ከተሰማ በኋላ በቀጥታ ወደ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ሽግግር ተደርጎ፣ በደቡብ ሱዳን ባለባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ሳቢያ ቅድሚያ የተሰጣቸው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀ/ስብከት የሆነው የጋምቤላ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተመጠነ ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በመጽሔቱ በተገለጸው ሪፖርት መሠረት በሀ/ስብከቱ 39 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤ 327 ካህናት በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፤ የምእመናኑ ቁጥር አልተገለጸም፤ በቅኔ፣ በአቋቋም፣ በቅዳሴ እና በመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 47 የክልሉ ተወላጆች በዲቁና እና ቅስናም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት አምነው ተጠምቀዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሀ/ስብከቱ ካስገባው ብር 1,176,115.50 ውስጥ የመንበረ ፓትርያርክ 35 በመቶ ብር 82,796.91 ገቢ ማድረጉ ተገልጧል፡፡

በዚህ መልኩ የጅማ፣ የመቐለ፣ የኢሉ አባቦራ፣ ድሬዳዋ፣ ጋሞጎፋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ባሌ፣ ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች በተከታታይ ሪፖርታቸው ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ፣ የጅማ እና የኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት ከአክራሪ እስልምና የተነሣ ያለባቸውን ተግዳሮት ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋው ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ገሪማን ‹‹ንዑድ፣ ክቡር›› እያሉ ደጋግመው በማወደሳቸው በጉባኤተኛው ተሥቆባቸዋል፡፡


በአህጉረ ስብከቱ የሪፖርት አቀራረብ ሥራ አስኪያጆቹ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በ‹ዐቃቤ ሰዓትነት› በሰጡትና በጥብቅ በሚቆጣጠሩት ከ5 - 10 ደቂቃ ባለው ጊዜ ሪፖርታቸውን በችኮላ ያቀርባሉ፡፡ ከዚሁም ላይ እንደ ወትሮው ሁሉ ለመንበረ ፓትርያርክ በሚደረገው የዘመኑ የ35 ከመቶ ፈሰስ ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የሰሰሱ መጠን የአህጉረ ስብከቱ ጥንካሬ እና ዋናው የሥራ ፍሬያቸው መለኪያ መስሎ ታይቷል፡፡

ከቀትር በኋላ ከ10፡30 - 11፡25 ባለው ጊዜ በቀረቡት ሪፖርቶች፣ (በተለይም የሰበካ ጉባኤ እና የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ) ላይ ውይይት እና ጥያቄ እንደሚኖር በተገለጸው መሠረት መድረኩ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለተሰብሳቢው ክፍት መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም አንዳችም ጥያቄ ይሁን ውይይት ሳይነሣ ቀርቷል፡፡ የፍርሃት ይሁን የፍላጎት ማጣት? ብለው ሲጨነቁ ለነበሩት በጉባኤው የደጀ ሰላም ታዛቢዎች ምላሽ የሰጠው ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ጥያቄ እና አስተያየት ከሌለ ሪፖርቱ ይቀጥል›› ብለው ከመናገራቸው ቤቱ በተሰብሳቢዎቹ ለየት ያለ የጭብጨባ ዘይቤ የተናጋበት ሁኔታ ነው - አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡

በጉባኤው ላይ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የየራሳቸው ሪፖርት የሚያቀርቡበት ቀን ያላቸው ሲሆን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ዛሬ ያቀረቡትን የማእከላዊ ጽ/ቤቱን ሪፖርት ሙሉ ቃልና የ48ቱን አህጉረ ስብከት የተጨመቀ ሪፖርት ‹‹ቃለ ዐዋዲ›› መጽሔት እንዳገኘነው ከዚህ በታች አቅርበንላችኋል፡፡

30ኛው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ጥቅምት 12 ቀን ለሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካስተላለፉትና በመጽሔቱ ላይ ከታተመው መልእክታቸው የሚከተለውን ይገኝበታል፡- ‹‹ይህን መሰል ጉባኤ ስናካሂድ የአሁኑ ጉባኤያችን ለሠላሳኛ ጊዜ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው፡፡ በየጉባኤያቱ የሚዘጋጁ አርእስተ ጉዳዮችና የሚወጡ ዕቅዶች፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ እየቀረቡ ከተመከረባቸው በኋላ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ስብሰባችን የጉባኤውን ሪፖርት አንብበን የምንለያይበት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዕቅድ የምናቅድበትና የምንወያይበት ስብሰባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡››
እውን ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራስ እስከ እግሯ በአንድ አዳራሽ የተገኘችበት ስብሰባ በሆነውም ባልሆነውም የሪፖርት ጋጋታ ከመጨናነቅ፣ በረባ ባልረባው የውዳሴ ዝናም ከማጭበጨብ፣ ጫን ባለ የእህል ውኃ ግብዣ ከመደንዘዝ ተርፎ፡- የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን በሚያሤሩት የውስጥ አደጋ፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በደቀኑብን የውጭ ስጋት፣ እንደተባለው ጥናትና ሥር ነቀል ርምጃ በሚሻው የፋይናንስ፣ የሰው ኀይል እና የሌሎች ሀብቶች አስተዳደሯና ልማታዊ ክንውኗ ዙሪያ ይመክር ይሆን? ከቀደመውና ከዛሬው ውሎ አኳያ የሚሆን አይመስልም፡፡ ርግጡን ግን በጉባኤው የአምስት ቀናት ቆይታ የምናየው ይሆናል፡፡ 
by deje selam

Thursday, September 8, 2011

የሐረሩ ስልጠና

በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • ገበየሁ ይስማው ሥልጠናው መካሄዱን አመነ የሠልጣኖች ምልመላ ሂደትን አብራርቷል
  • የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ለጉባኤ ከአዲስ አበባ ሳባኪ እንዳይጠራ ወሰነ
  • ማኅበረ ቅዱሳን በተሐድሶ ሰራዊትነት የሰለጠነ አባል የለኝም አለ
  • ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፈሉ
    ገበየሁ ይስማው
    ገበየሁ ይስማው
በቅርቡ በሐረር ከተማ በሉተራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተሐድሶ ሰራዊትነት ዙርያ የተሰጠው ሥልጠና ልዩ ልዩ ውጠየቶችን እያስከተለ እንደሆነ የምስራቅ ኢትዮጵያ የገብር ኄር መንጮች ገለጹ፡፡
ሐረር
የሐረር ከተማ እንዳንድ ምዕመናን ግብረ ተሐድሶን በተመለከተ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እነዚህ ምዕመናን ‹‹በሌሎች አህጉረ ስብከቶች የታገዱ መምህራን ለምን ሐረር ላይ እንዲያስተምሩ ይፈቀድላቸዋል? በከተማው እየተፈጸመ ባለው ግብረ ተሐድሶ ላይ ሀገረ ስብከቱ አፋጣኝ እርምጃ ለምን አይወስድም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ እና በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ያሬድ ሰባሳቢነት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ቀን በክብረ በዓላት ወቅት በሀገረ ስብከቱ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር አንድም ‹‹መምህር›› ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከአዲስ አበባ እንዳይጠራ ወስኗል፡፡ በስብሰባው  ‹‹ምእመናን መማር ያለባቸው በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ሊቃውት መሆን አለበት፡፡ እኛ ሊቃውንቱን መድረክ ስለነሳናቸው ነው ሕገ ወጦች አውደ ምህረቱን የተቆጣጠሩት ›› የሚል ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡
ብጹዕ አቡነ ያሬድም በሀገረ ስብከታቸው እየተፈጸመ ያለውን ግብረ ተሐድሶ በተጠናቀረ መረጃ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀዋሳዎችን አሰረ ፍኖት የተከተሉ የሐረር ከተማ ትጉኀን ምእመናን በከተማችው በሀገረ ስብከታቸው እንዲሁም በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለው የተሐድሶ ክንፍ ምን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ በበቂ መረጃዎች የተደራጀ ቪሲዲ ለማሰራጨት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ዘለግ ላሉ ዓመታት በተሐድሶ ሴራ የተሰቃዩ የሐረር ምእመናንም ቪሲዲው የተንኮለኞችን ሴራ በማጋለጥ እፎይታ እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡
ድሬዳዋ
ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ ውሉደ ተሐድሶ ድርጊታቸው በመጋለጡ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፍለዋል፡፡ በሦስት ሠልጣኞች ሦስት የተለያዩ ሀሳቦች ታይተዋል፡፡ የመጀመሪያው በግልጽ ወደ ሥልጠናው ሲገባ እና ሲወጣ በተቀረጸው የቪዲዮ ምስል እየታየ ለሚጠይቁት ሁሉ  ‹‹እኔ ዘመድ ልጠይቅ ወደ ሩቅ ሀገር ሄጄ ነበር የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከናካቴውም ሐረርን አላውቃትም ሔጄም አላውቅም›› በማለት ራሱን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡
ሁለተኛው ግለሰብ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በሐሰት አቀናብሮብኝ ነው እንጂ እኔ የማውቀው ጉዳይ የለም ›› በማለት እንደ ኦሪት ኃጢአተኛ በደሉን የሚሸከምለት ፍየል ለመፈለግ ሞክሯል፡፡ አክሎም ‹‹ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሬ ሰዎች በእኔ ላይ ማስረጃዎችን እንደሚያሰባስቡ አውቃለሁ ተገኘ የሚባለው ነገር ፍጹም ሐሰት ነው›› በማለት ቀርበው ለጠየቁት ግለሰቦች ሲመልስ ተሰምቷል፡፡‹‹የሥልጠናውን ሂደት የቀረጹት የሚያሳድዱኝም ሸዋዎች ናቸው›› በማለትም ለኑፋቄው የዘረኝነት መከላከያ ጭንብል ሊያጠልቅለት ሞክሯል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሁለቱ ግለሰቦች የአንድ ደብር ‹‹ሰባክያነ ወንጌል›› ሲሆኑ ቀጥለን የምንገልጸው የግብር አጋራቸው ድርጊታቸውን እንዳጋለጠባቸው ይጠረጥራሉ፡፡
ሥስተኛው ሰው ሁለቱ ወዳጆቹ የከፈቱለትን ቀጭን መውጫ ቀዳዳ በመጠቀም አንድ አካል መረጃ እንዲያጠናቅርለት ልኮት እንጂ አምኖበት ወደ ስልጠናው እንዳልሄደ ቅርብ ለሚላቸው ወዳጆቹ ተናግሯል፡፡ ጨምሮም ያሰባሰበውን መረጃ ለማኅበረ ቅዱሳን መላኩን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከሰልጣኞች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባል የሆነ አንድ ግለሰብ መኖሩን የተረዱ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማዕከልን ‹‹እንዴት ከእናንተ መካከል እንዲህ ያለ ሰው ይገኛል›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ማዕከሉም እንዲህ አይነት አባል የለንም በማለት አስተ
ባብሏል፡፡ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ከስድሳ ሺህ በላይ አባላት ካሉት ማኅበር እንዲህ ያለ መልስ አይጠበቅም፡፡ ማኅበሩ ሁሉንም አባላት የት እንደሚዉሉና እንደሚያድሩ በማያውቅበት ሁኔታ ድፍን ያለ መልስ ከመስጥት ተቆጥቦ የደረሰውን ጥቆማ በመቀበል ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ በመረጃ የተደገፈ ምሁራዊ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ገብር ኄር ግን የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ችላ የሚሉት ከሆነ ከአስተባባሪው ከገበየሁ ይስማው ጀምሮ በሁሉም ላይ ያሉትን  ዝርዝር መረጃዎች ለምእመናን የሚያሳውቅ መሆኑን ለመግጽ ይወዳል፡፡
በተያያዘ ዜና የገብር ኄር ዜና ዘገባ እንደ ሐሩር እሳት ያቃጠለው የአሰበ ተፈሪው ገበየሁ ይስማው ‹‹ሥልጠናው እንደተባለው ኢየሱስን ማለማመድ ሳይሆን ሰባክያነ ወንጌል የዓለም ሃይማኖቶችን አንድ ለማድረግ እንዴት ማስተማር ይገባቸዋል የሚል ነበር›› ብሏል፡፡ የሠልጣኞች ምልምላን
በተመለከተ ‹‹እኛ ሁሉንም ነው የጠራነው ደፍሮ የመጣውን አሠልጥነናል›› በማለት ገልጿል፡፡ ሴራው በመጋለጡ የተደናገጠው ገበየሁ ‹‹የቀረጹትንም ሆነ ፎቶ ያነሱትን እናውቃቸዋለን በመንግስት ጭምር እየተፈለጉ ነው ለሕግ እናቀርባቸዋለን›› በማለት የሐረር ምእመናን የተሐድሶን ሴራ ለማጋለጥ በሚያደርጉት ጥረት እየደረሰባት ያለውን ውርደት ለመከላከል  አልሞት ባይ ተጋዳይነቱን አሳውቋል፡፡
መረጃው የደረሳቸው የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ መረጃው ጠቃሚ እንደሆነና በሀገረ ስብከታቸው የእርምት እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ እነደሚገደዱ መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!! By ገብር ኄር

Friday, September 2, 2011

የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ

‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ


በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ አራት ሀገረ ስብከቶች ለተውጣጡ ‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ



በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • የሥልጠናው ዋና ርዕሰ ጉዳይ ኢየሱስን ማለመመድ የሚል ነበር
  • ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል
  • ፓስተር መስፍን ፤ገበየሁ ይስማውና  በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል
  • ለሥልጠናው ተሳታፊዎች ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚል ማስታዎሻ እና መጸሐፍ ተሰቷቸዋል
  • ከሠልጣኞቹ መካከል ቀደም ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በክረምት ተተኪ መምህራን ሥልጠና አሰልጠኗቸው ከነበሩት ሠልጣኞች አንድ ግለሰብ ተገኝቷል
ከድሬዳዋ ፤ ከሱማሌ ፤ ከምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ አህጉረ ስብከቶች የኦርቶዶክስ  አብያተ ክርስቲያናት ለተውጣጡ ‹‹የቤተክርስቲያን አገልጋዮች›› ግበረ ተሐድሶን በሚያስፋፉበት ስልት ዙርያ ሥልጠና መሰጠቱን  በሰነድ እና በድምጽ ወምስል የደረሰው መረጃ አመለከተ፡፡
‹‹ሃይማኖቶችን አንድ እናደርግ ሁላችንም በቀን አንዳንድ ሰው እንለውጥ›› በሚል መርህ የተጀመረው ሥልጠና በሐረር ከተማ ሉትራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከነሐሴ 23-30 ሊሰጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ትላንት ማምሻውን መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ሥልጠናው ዘወትር ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽት 2፡30 እንደተሰጠ ለመረዳት ተችሏል፡፡የሰሌዳ ቁጥሩ ዕድ 00122 የሆነ ተሸከርካሪ ለሥልጠናው አስፈላጊ የሆኑ ሎጀስቲክስ ለማሟላት ሥራ ላይ ውሏል፡፡
የሥልጠናው ዋና አሰልጣኝ የቀድሞ የሐረር ቀበሌ 10 ሊቀ መንበር የአሁኑ ፓስተር መስፍን ነው፡፡ሌሎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች የመጡ በርካታ ፓስተሮች በአሰልጣኝነት የተሳተፉ ሲሆን ዋና አስታባባሪው ደግሞ ከአሰበ ተፈሪ ለዚሁ ሥራ ወደ ሐረር ያቀናው ገበየሁ ይስማው ነው፡፡ገበየሁ ይስማው በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም የሥራ ኃላፊነት የሌለው ባለበት የሃይማኖት ችግር በተነሳ ውዝግብ በመቐሌው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የተማረውን የዲግሪ መርሀ ግብር ማስረጃ ያለተሰጠው ወልደ ተሐድሶ ነው፡፡በዚሁ ምክንያት በምዕራብ ሐረርጌ የይብሮ ወረዳ ኮተራ ቅዱስ ገብረኤል ምዕመናን አታስተምረንም በማለት እነዳባረሩት ይታወቃል፡፡ፓስተር መስፍን እና ገበየሁ ይስማው በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሥልጠናው ዋና ትኩረት የተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ኢየሱስን የማለማመድ ትምህርት›› ነው፡፡በዚህም ሠልጣኞቹ የበጋሻውን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ተደጋግሞ ሲመከሩ ተስተውሏል፡፡ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት ግለሰቦች ከሐረር ከጅጅራ ከሰበ ተፈሪ እና ከድሬ ዳዋ ከተሞች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ሲሆኑ ከነዚህ መካካል ማኅበረ ቅዱሳን በ2000 ዓ.ም ክረምት በጅማ ለግቢ ጉባዔያት ተተኪ መምህራን አዘጋጅቶት በነበረው ሥልጠና ተሳታፊ የነበረ አንድ ግለሰብ ይገኝበታል፡፡ በቅርቡ አባ ሠረቀ ብርሃን በመቐሌ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ አካሂደውት በነበረው ውይይት አንድ የኮሌጁ ደቀመዝሙር ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ካህናት ማሰልጠኛ ምንፍቅና አስተምሮኛል›› ብሎ መናገሩን ያስታወሱ ታዛቢዎች ማኅበሩ የሠልጣኞች ምልመላ ስርዓቱን መሰፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የሥልጠናውን ሙሉ ሂደት የሠልጣኞችን ዝርዝር የያዘ የሰነድ የፎግራፍ እና ቪዲዮ መረጃ ደርሶናል፡፡የተሐድሶን ሴራ በማጋለጥ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳንም መረጃው ተጠቃልሎ ደርሶታል፡፡የስልጠናው ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ከያዙት ቦታ እና ሊያደርሱት ከሚችሉት አደጋ አንጻር ማኅበሩ መረጃ አለኝ በሚል አጉል ብሒል እርምጃ ለሚወስዱ የቤተክርስቲያኒቱ አካል ፈጥኖ የማያደርስ ከሆነ ታሪክ የማይረሳው ስህተት እየፈጸመ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሚጠቀምበት ከሆነ ይህንን መረጃ ያጠናቀሩ የቤተክረስትያን ልጆች እንደ ሀዋሳ ምዕመናን የድርሻቸውን ለመወጣት ቪሲዲዎችን በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡እንደ አግባብነቱ መረጃዎችን ወደ ፊት የምንገልጥ መሆኑን እያስታወቅን ይህንን መረጃ በመሰብሰብ እና ለተገቢው አካል በማድረስ ለተጉት የቤተክርስቲያን ልጆች ያለንን አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!! ››  by http://andadirgen.blogspot.com/2011/09/blog-post_9564.html

Wednesday, August 31, 2011

«የአሮጊቷ ሣራ» ወለደች ዐዋጅ ተሐድሶ ዘመቻ የጥፋት ፈትል እንደማጠንጠኛ

http://www.facebook.com/video/video.php?v=126800684079140&saved

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በብሉያትና በሐዲሳቱም የምትነሣው ሣራ አበ ብዙኃን ሥርወ ሃይማኖት የምንለው የአብርሃም ሚስት ነች፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የብዙዎች አባት እንዲሆን ቃል ኪዳን ሳይገባለት በፊት፣ በመካንነት ታዝን፣ ተስፋም አጥታ ትተክዝ በነበረችበት ጊዜ ሦራ ትባል ነበር፡፡

ሦራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ ልጅ እንደምትወልድ ከአብርሃም በኩል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከገባላት፣ ተስፋም ከተሰጣት በኋላ ሣራ ተብላለች፡፡ እግዚአብሔርም ስለእርሷ ለአብርሃም «የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፤ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ፤ እባርካታለሁ፤ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፤ የአሕዛብ እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ» በማለት ተናገረው /ዘፍ. 17፥15/፡፡

ሣራ ሦራ ተብላ ትጠራ በነበረበት፣ ያለተስፋ በኖረችበት የቀደመው ዘመኗ ለአብርሃም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፡፡ ሦራ ዘር ማጣት ታላቅ ሐዘን በሆነበት በዚያ ዘመን፣ መካንነት ያስንቅ በነበረበት በዚያን ጊዜ አብራም ከሌላ ይወልድ ዘንድ አዘነችለት፡፡ አብራም አጋር ወደ ተባለችው ግብጻዊት ባሪያዋ ይደርስ ዘንድ «እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ ምናልባት ከእርሷ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርሷ ግባ» አለችው፡፡ /ዘፍ.16፥2/ በትሑቷ ሦራ ምክር አጋር ከአብርሃም በፀነሰችበት ወራት ሦራን አሳዘነቻት፤ አጋርም ተመካች፤ እመቤት የነበረችውን ሦራ ስለመካንነቷ በዓይኗ አቃለለቻት፡፡ ይህ ለሦራ በእግዚአብሔር እና በባሏ በአብራም ፊት ያዘነችበት ሰቆቃዋ ነው፡፡ ሦራም ከሐዘኗ ጽናት የተነሣ አብራምን እንዲህ አለችው «መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይኗ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ» አለችው፡፡ በአብራም ፍርድም ሦራ ባሪያዋን አጋርን በመቅጣቷ አጋር ኮበለለች፡፡

እንግዲህ ከላይ አስቀድመን የጠቀስነው ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን የተሰጠው ሦራና አብራም በዚህ ሐዘን ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያዘነችው ሦራ ከቃል ኪዳኑ በኋላ የብዙኃን እናት ልትሆን ሣራ ተብላ እርሱም የብዙዎች አባት ሊሆን አብርሃም ተብሎ የተስፋው ቃል ተነገረው «በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃልኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ» /ዘፍ.17፥19/፡፡

እግዚአብሔር ለአብርሃም ሣራ እንደምትወልድ የነገርውን የተስፋ ቃል በቤቱ በእንግድነት ተገኝቶ አጸና፡፡ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች፡፡»/ዘፍ.18፥10/ አለው፡፡ ሁል ጊዜም ቃሉ የሚታመን እግዚአብሔር ይመስገንና እንደተባለው ሆነ «እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት አብርሃም ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው» /ዘፍ.21፥1/ «ሣራም እግዚአብሔር ሳቅ /ደስታ አድርጎልኛል ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች ደግሞም ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና /ዘፍ. 21፥7/፡፡

እንግዲህ መካኒቱ ሣራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ በጨዋነት ወልዳ ለአብርሃም ለዘላለም የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸምበትን ዘር ይስሐቅን አሳድጋለች፡፡ በቃል ኪዳን፣ በተስፋ የተወለደው ይስሐቅ ታላቅ ነውና «የዚህች ባሪያ /የአጋር/ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስም» አለች፡፡ እግዚአብሔርም ቃሏን ተቀብሎ ለአብርሃም «ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና...» አለው /ዘፍ.21፥1-12/፡፡

እንዲህ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የከበረችው ሣራ በብሉያት ብቻ ሳይሆን በሐዲሳትም ለተለያዩ ጉዳዮች እንደ አርአያና ምሳሌ ስትጠቀስ እናነባለን፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቶችን ሲመክር በመልካም ትሑት ሰብእናዋ አርአያ የምትሆን አድርጎ የጠቀሳት ሣራን ነው «ጠጉርን በመሸረብ፣ ወርቅን በማንጠልጠል፣ ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጪ በሆነ ሽልማት» ሳይሆን «በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ» ተጎናጽፋ ውስጧን ያስጌጠች ብፅዕት ሚስት መሆኗን መስክሯል፡፡ «ሣራ ለአብርሃም ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ፡፡» /1ጴጥ. 3፥3-6/ ብሏል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስ የማዳኑ የምስራች ከታወጀላቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ካልጠበቅን አንድንም የሚሉ ቢጽሐሳውያንን ቃል ሰምተው ያመኑ የገላትያን ሰዎች በገሰጸበት መልእክቱ ሣራን የሕገ ወንጌል ምሳሌ አድርጎ አቅርቧታል፡፡ በአንጻሩ ባሪያዋን አጋርን የሕገ ኦሪት ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል /ገላ.4፥21/፡፡

የሣራን ሕይወት በዚህ ጽሑፍ ያነሣንበትንም መሠረታዊ ምክንያትም ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌያዊ መልእክት ተንተርሰው ያለአገባቡ እየጠቀሱ የቤተ ክርስቲያናን ልጆች ምእመናንን ግራ ስለሚያጋቡ የተሐድሶ መናፍቃንና ተሐድሶአዊ ትምህርት ስለሚያስተምሩ ሰዎች ሐሳብ ለማንሣት ነው፡፡ በቅድሚያ የቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቱን ሐሳብ በአጭሩ እናብራራና፤ ተሐድሶ የዘመቻ ማወራረጃ አድርጎ ስለሚጠቀምበት ጥራዝ ነጠቅ ቃልና አስተሳሰብ ደግሞ ቀጥሎ እናመጣለን፡፡ ሐዋርያው ስለዚህ ነገር ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፡፡

«እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ? እስኪ ንገሩኝ፤ አንዱ ከባሪያዪቱ አንዱ       ከጨዋዪቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፏልና፤ ነገር ግን የባሪያዪቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዷል፤ የጨዋዪቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዷል፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳናት ናቸውና፤ ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፤ እርሷም አጋር ናት፤ ይህቺም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጆቿ ጋር በባርነት ናትና፤ ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፤ እርሷም እናታችን ናት... ስለዚህ ወንድሞች ሆይ የጨዋዪቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያዪቱ አይደለንም» /ገላ.4፥21-31/፡፡
በገላትያ መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ «የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች» ስለነበሩት ከአይሁድ ወገን የሆኑ ካልተገረዛችሁ፣ ሕገ ኦሪትንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ኦሪታዊ ሁኑ የሚሉ ሰዎችን ትምህርት እየሰሙ የወንጌልን ቃል ቸል ያሉት የገላትያን ሰዎች በግልጽ «እግዚአብሔርን ስታውቁ፣ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን ? ቀንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ...» ይላቸዋል፡፡ /ገላ.4፥9-11/
የሐዋርያው ዋነኛ ጉዳይ ሕገ ኦሪት ይጠበቅ አይጠበቅ በመሆኑም ነው «እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ?» ያላቸው /ገላ. 1፥21/፡፡ ምክንያቱም ያመኑትን ሁሉ በደሙ የዋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል ከተነገረች በኋላ ዳግመኛ ወደ ኋላ ተመልሶ ቀንና ወርን ዘመንንም እየቆጠሩ መሥዋዕተ ኦሪትን ለማቅረብ፣ ግዝረትን አበክሮ ለመጠበቅ፣ ያንንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም ወደሚል ትምህርት መመለስ ያሳፍራልና፡፡
ስለዚህ እናንተ በኦሪት እንኑር የምትሉ ሆይ! በኦሪት የተነገረውን ምሳሌ አንብቡ ብሎ የሣራን እና የአጋርን ምሳሌነት ያነሣል፡፡ በኦሪት አብርሃም አስቀድመን እንዳየነው ጨዋይቱ ከተባለችው ከእመቤቲቱ ሣራ ይስሐቅን፣ ከባሪያይቱ ከአጋር ደግሞ እስማኤልን ወልዷል፡፡ የሁለቱ ልደት ግን ለየቅል መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ ከባሪያዪቱ የተወለደው አጋር ሙቀት ልምላሜ እያላት ተወልዷልና፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በዘጠና ዓመቷ/ ከእግዚአብሔር ብቻ በተሰጠው ተስፋ ተአምራትም ተወልዷልና፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሴቶች የሕገ ኦሪትና የሕገ ወንጌል ምሳሌ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቃሉ «ይህም ነገር ምሳሌ ነው» እንዳለ /ገላ. 4፥24/፡፡ አጋር ኦሪትን ደብረ ሲናን አንድ ወገን ያደርጋል፤ ሣራን፣ ወንጌልን ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌምን ደግሞ አንድ ወገን እያደረገ እያነጻጸረ ተናግሯል፡፡
አንዲቱ /ኦሪት/ አምሳል መርገፍ ሆና በደብረ ሲና ተሠርታለችና፤ ደብረ ሲናም ከኢየሩሳሌም ስትነጻጸር በምዕራብ ያለች ተራራ ናትና፤ ስለዚህ ይህች ምድራዊት የምትሆን አምሳል መርገፍ አማናዊት ከምትሆን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር ዝቅ ያለች ናትና «ወትትቀነይ ምስለ ደቂቃ» አምሳል መርገፍ በመሆን ከልጆቿ ጋር ትገዛለች፡፡ ላዕላዊት የምትሆን ኢየሩሳሌም ግን ከመገዛት ነጻ ናት ብሎ «ወይእቲ እምነ፤ እርስዋም እናታችን ናት» ይላል፡፡ ይቺም እናታችን ሣራ ምሳሌዋ የምትሆን ወንጌል ናት፡፡
ስለዚህ ከሣራ የተወለደው ተስፋውን ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም ከወንጌል የተወለድን ክርስቶሳውያን በይስሐቅ አምሳል እንደይስሐቅ ተስፋውን መውረስ የሚገባን የነጻነት ልጆች ነን ማለቱ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ፡፡ የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤት ልጅ ጋር ተካክሎ ርስት አይወርስምና በበግና በፍየሎች ደም ምሳሌያዊ ወይም ጥላ   አገልግሎት በምትሰጥ ገረድ /ሞግዚት/ የተባለች የኦሪት ልጆች አይደለንም፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ደም ነጻ በምታወጣ አዲስ ኪዳን የወንጌል ልጆች ነንና፡፡
ሐዋርያው ይህንን ሁሉ ያለው ካልተገረዛችሁ አትድኑም የሚለውን የቢጽ ሐሳውያንን ትምህርት በመኮነን ሲሆን ይህንንም በግልጽ «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና /ገላ. 5፥6/ ይላል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ ያለው ሕይወትም ፍትወተ ሥጋን አሸንፎ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበቁ ሆኖ በመንፈስ መራመድን ነው፡፡ ይህ ሣራ በተመሰለችባት ሕገ ወንገል ውስጥ የተጠራንበት የመታዘዝ ሕይወት ነው፡፡ ሐዋርያውም ለገላትያ ሰዎች ይህንኑ ተርጉሞ ሲናገር «የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ» /ገላ. 5፥24/ አለን፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞት ጋር የሰቀሉ መንፈሳውያን፣ በፍቅር የእግዚብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽመው የጨዋይቱ /የእመቤቲቱ/ የሣራ ልጆች ናቸው፤ እንጂ ሥጋዊ ሥርዓት፣ መርገፍ፣ ጥላ በሆነው ብሉይ ኪዳን ውስጥ የመገረዝ አለመገረዝ ጣጣን የሚሰብኩ፣ የሚሰበኩ በሥጋ ልማድ የወለደችው የባሪያዪቱ የአጋር ልጆች አይደሉም፡፡
እንግዲህ በነጻነት የምትመራውን ላይኛይቱን ኢየሩሳሌምን የመረጡ ክርስቶሳውያን ለ2ሺሕ ዘመናት ያህል ክርስቶስን በመስበክ በስሙም ክርስቲያን ተብለን ስንጠራ ኖረናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ገና አስቀድሞ በ34 ዓ.ም «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ካለው ጃንደረባው ጀምረው ሠልጥና ከነበረችው ባሪያይቱ አጋር ይልቅ በተስፋው ሥርዓት የወለደችውን እመቤቲቱን ሣራ መርጠው እስከዚህ ዘመን ድረስ ኖረዋል፡፡
ከየካቲት ወር 1990 ዓ.ም ጀምሮ ግን «ተሐድሶ» በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በይፋ በጀመረው ዘመቻ ውስጥ የዘመቻው አዋጅ ማጠንጠኛ «አሮጊቷ ሣራ እኔ /እኛን/ ወለደች» የሚለው ቃል ነው፡፡ «የተሐድሶ መነኮሳት ኅብረት» የተባለው ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ እየተቋደሰ ነገር ግን በመሠሪነት ለመናፍቃን ተላላኪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በየካቲት ወር 1990 ግን በአዲስ አበባ ከተማ በኢግዚብሽን ማዕከል በፕሮቴስታንቶች ተደራጅቶ በተዘጋጀው «ጉባኤ» በይፋ ራሱን ለይቶ የ«ተሐድሶ» ጥሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲደረግ ሲያውጅ ተገኝቷል፡፡ /ይህንን ለማጋለጥ የወጣወን ቪዲዮ ፊልም ወይም ቪሲዲ ይመልከቱ/ በዚህ አዋጅ በጉልህ የሚስማው ድምፅ ከላይ የተጠቀሰው «አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች» የሚለው ንግግር ነበር፡፡ ይህንን ቃል ደጋግሞ ሲያስተጋባ የነበረው አባ ዮናስ /በለጠ/ የተባለው «መነኩሴ» «ወንጌልን ለመስበክ ተሾምኩ፤... አሮጊቷ ሣራ ወለደች፤ አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፣ ዘውዱን ወለደች፣ ፍስሐን ወለደች፣ ገብረ ክርስቶስን ወለደች... ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል...» ወዘተ እያለ አብረውት ለጥፋት የተሰለፉ ከሃዲ መነኮሳትን እየጠቀሰ ፎክሯል፡፡
በእነ አባ ዮናስ አዋጅ ውስጥ ያለው ግልጽ መልእክት ግን በሁለት መልኩ የሚታይ ወይም ሊተረጎም የሚችል ነው፡፡
1.    ቤተክርስቲያንን በእርጅና ዘመኗ ከወለደችው ከቅድስት ሣራ ጋር በማነጻጸር ራሳቸውን የዚህችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አድርገው በማቅረብ ከዚህች ቤተክርስቲያንም አካል የተገኙ መሆናቸውን በመግለጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እነርሱ የሚሉት እንደሆነ አድርገው ለማደናበር ነው፡፡
2.    ሌላው የድፍረት መልእክት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በባሪያይቱ በአጋር ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችል ኦሪታዊት፤ የጨዋይቱ የተባለች የሣራ የተስፋው ዘር ቅሪት የሌለባት፣ የወንጌል ብርሃን ያልበራባት፤ ክርስቶስን የማታውቅ፣ ጌትነቱንም የማታምን አድርገው አቅርበዋታል፡፡ ራሳቸውንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወንጌልን ለማድረስ የተሾሙ በኩራት አድርገው አቅርበዋል፡፡
የመጀመሪያውን ትርጉም ወይም መልእክት በማጉላትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም የዚህን የ«ተሐድሶ» መሠሪ አካሔድ በውል በመረዳት አውግዞ በመለየትና ውግዘት በማስተላለፍ ለ2ሺሕ ዘመናት ወንጌልን ስትሰብክ የነበረች ቤተ ክርስቲያንን ልዕልናና ክብር አጉድፎ በወንጌል ሰባኪነት ስም በማጭበርበር ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ለመዝራት ተሐድሶ እያደባ መሆኑን አጋልጧል፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነት ከሰጠው ሰፊ መግለጫ ውስጥ ይህን የተመለከተውን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡

«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» የሚል ኃይለ ቃል መናገራቸው ተዘግቧል፤ መናፍቃኑ ይህን የተናገሩት የእነሱን ከጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን አፈንግጦ መውጣት የዘጠና ዓመት እድሜ ከነበራት እና ከቅድስት ሣራ ከተወለደው ከይስሐቅ ልደት ጋር ለማነጻጸር በመፈለግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የይስሐቅ እናት ቅድስት ሣራ በመሠረቱ እናትና አባቱን የሚያከብርና የሚያስከብር እንጂ የሚያዋርድ፣ እናትና አባቱን የሚያስመሰግን እንጂ ሰድቦ የሚያሰድብ፣ በእናትና አባቱ እግር የሚተካ እንጂ እናትና አባቱን የሚክድ፣ በወላጆቹ የተመረቀ እንጂ የተረገመ ልጅ እናት አይደለችም፡፡

በቅድስት ሣራ አምሳል የተጠቀሰችው ጥንታዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ እናቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስማማ፣ እናቱን ሲሰድብና ሲነቅፍ ሐፍረት የማይሰማው ርጉም ልጅ እናት አይደለችም፤ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ልጅ አልወለደችም፣ አትወልድምም፡፡

ጠላትና አረም ሳይዘሩት ይበቅላል እንደሚባለው፣ በአንድ የስንዴ ማሳ ላይ የበቀለ አረም ቢኖር ያ አረም ሳይዘራ የበቀለ መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደማይሆን ሁሉ እነዚህ መናፍቃንም በቤተ ክርስቲያናችን የስንዴ ማሳ ላይ ሳይዘሩ የበቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በምሳሌ ዘር እንደተጠቀሰው /ማቴ.13፥24-30/ በንጹሕ ስንዴ ማሳ ላይ ጠላት የዘራው ክርዳድ ሊበቅል እንደሚችልም ታውቋል፡፡ እነዚህ መናፍቃንም የጠላት እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን አበው ተክል ባለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተወለዱ አድርገው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ የማን ልጆች እንደሆኑ ቢጠይቁ ዕውነቱን ለማወቅ በቻሉ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ «በኋላ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ገንዘብን የሚወድዱ፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ሐሜተኞች፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ የማይወዱ ከዳተኞች ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ይክዱታል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን፣ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉትን... የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና» /1ጢሞ. 3.1-7/ ሲል እንደተናገረው እነዚህ መናፍቃን ከዚህ የትንቢት ዘመን የተወለዱ እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች አለመሆናቸውን በግልጽ መንገር ግዴታ ይሆናል፡፡ /መጋቢት 26 ቀን 1990 ዓ.ም/
ጠቅላይ ቤተክህነት የተነተነበት መንገድ እንዳለ ሆኖ የ«ተሐድሶ» ቡድን «አሮጊቷ» የሚለውን ቃል የመረጠበትን መሠረታዊ ምክንያት በውል ማጤን ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የምትሰብክን ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት ሣራ ጋር አነጻጽሮ ባቀረበበት መንገድ አስበው ተናግረውት ቢሆንማ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠው የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ባዘጋጁት በዚያ የስድብ ጉባኤ ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት ትምህርትና ሥርዓት የምእመ ናንን ሕይወት ባላዋረዱ ባላናናቁ ነበር፡፡ ነገር ግን «አሮጊት /አሮጌ» የሚለውን ቃል የመረጡት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና ማደስ አለብን ለሚለው አስተሳሰብ መንደርደሪያ ነው፡፡ እነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን ተወግዘው ቢለዩም በውጪም በውስጥም ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ለመገዝገዝና አስተምህሮአቸውን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ «መምህራን» አውቀውም ሳያውቁም በየዓውደ ምህረቱ እንዲያስተጋቡ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

እነ አባ ዮናስ የ«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» ቃላቸውን ከአዋጁ ከ12 ዓመታት በኋላ አሁን በይፋ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያንን አሪታዊት፣ ጨለማ ውስጥ ናት ሲሉ አሮጊቷ ሣራ ዛሬ እኔን ወለደች፣ እገሌን ወለደች፣ እገሌን ወለደች...» የሚል ከእነ አባ ዮናስ ጋር የቃልና የስሜት ዝምድና ያለው የአዋጅ ቃል በአንዳንድ ሰባኪያን ነን ባዮች ተሰምቷል፡፡ በአባ ዮናስና በእነዚህ ሰባኪያን መካከል ያለው የአቀራረብ ልዩነት የአባ ዮናስ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ እነዚህ ደግሞ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓውደ ምህረት ላይ ማወጃቸው ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት ቃሉም ትርጓሜውም የታወቀ ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችንም ከጨዋይቱ የተወለድን ክርስቲያኖች አንድነት መሆኗ ለ2ሺሕ ዘመን የተመሰከረ ሆኖ ሳለ የአሁኖቹ «ሰባክያን» ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ነጥለው «የተስፋው ወራሾች የአሮጊቷ የሣራ ልጆች» እያሉ የሚያቀርቡበት ገለጻ ትርጓሜ ይፋ መሆን አለበት፡፡

በመሠረቱ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ የተሰበከውን ምሳሌያዊ ትምህርት ይዞ ተንትኖ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ባሉበት ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራሳቸውንና እነርሱ የመረጧቸውን የቡድን አባላት አባ ዮናስ ባቀረቡበት መንገድ «የአሮጊቷ ሣራ» ብሎ የጠሩበት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ከመውለዷ በፊት ምን ጎድሎባት፣ ምንስ አጥታ ነበር ? ቅዱስ ጳውሎስ መካኒቱ፣ ጨዋይቱ፣ እመቤቲቱ እያለ የጠራበት ቅጽል እያለ «አሮጊቷ» የሚለውን በማስጮኽ ማቅረብስ ለምን ተፈለገ ? ቀጥተኛ ምንጩስ ማነው ? ምንድነው ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ እነ አባ ዮናስ «አሮጊቷ ሣራ» ያሏትን ቤተ ክርስቲያንን ድንግል ማርያምን፣ ተክለሃይማኖትን፣ ጊዮርጊስን በልብሽ አኑረሻልና አውጪ እያሉ በአደባባይ ድፍረት ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ «ሰባክያን» የ«አሮጊቱ ሣራ» አስተምህሮ ውስጥ ያለው አንድምታስ ምንድነው ? እነ አባ ዮናስ በ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮአቸው «ቤተክርስቲያኒቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ከሰበኩበት ጊዜ በኋላ ወንጌል አልተሰበከችም የወላድ መካን ሆና የኖረች ናት» በማለት አሁን እነርሱ ያንን ለመፈጸም የተወለዱ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የእነዚህ ሰባክያን የ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮስ ከዚህ አንጻር ምን ይላል ?

ይህ ብቻ ሳይሆን አባ ዮናስ «ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል» ያለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዒላማ ያደረገ ፉከራው በእነዚህ ሰባክያን የመዝሙር መንደርደሪያዎች ውስጥ ከሚነገረውና «መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት ኢያሪኮን ያፈርሳል...» ከሚሉት አዝማች ቃል ጋር ያለውንም የትርጉም ዝምድና መጤን እንዳለበት         እንድናስብ ያስገድዳል፡፡ በተመሳሳይ ይህንኑ መንገድ ተከትሎ በየደረጃው ምእመናን እነ አባ ዮናስ በግልጽ ያወጁት የ«ተሐድሶ» ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ዓውደ ምህረቶቻችን ላይ አሁንም ወደቆሙ «መምህራን» መሻገር አለመሻገሩን ቃሎቻቸውን እያጠኑ ለመመርመር ተገደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከታቸው አካላትም የእነዚህን «ሰባኪያን» ትምህርት መርምረው ካለማወቅ በስሕተት የቀረበ ትምህርት መሆኑን ወይም በድፍረት የቀረበ ለ«ተሐድሶ» ዘመቻ የጥፋት ፈትል ማጠንጠኛ መሆን አለመሆኑን ለይተው እንደሚያቀርቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ by