ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡
በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡
ቅዱስ
ዳዊት
በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?
በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡
በዚህ
መልኩ
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ የተናገረውን ቃል እናቶችና አባቶች በስእለታቸው ‹‹ቅዱስ ሚካኤል አድነኝ፤ ቅዱስ ግብርኤል ድረስልኝ›› እያሉ በመድገማቸው የዋሃን ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማያውቁ ነው መባል አለባቸው? ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ያዕቆብ የመላእክትን አዳኝነት በግልጽ ያወጁት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ስላልተማሩ ይሆን? ወይስ አንድ ሰባኪ የመላእክትን አዳኝነት ስላስተማረ ‹‹ገድል ጠቃሽ›› በሚል መጥላላት አለበት? ዘማርያኑስ በዚህ መልኩ መዘመራቸው ሊያስወቅሳቸው ይገባ ነበር?