Tuesday, November 6, 2012

†♥†ነገረ ቅዱሳን†♥†



“በስመ ሥላሴ”
ወበዛቲ ዕለት አእረፈ አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ለአቡነ መብዓ ጽዮን፣ ንዲሁም ለአባ ጽጌ ድንግል በዓለ እረፍታቸው አደረሳችሁ አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡(እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው። በአባታቸው ስም ሀብተ ጽዮንም ብሎ ይጠራቸዋል። እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው። አባታቸው ንቡረ ዕድ ሀብተ ጽዮን እናታቸው ሂሩት ይባላሉ። ደገኛ ጻድቅ ሲሆኑ ከታወቁበት ግብራቸው በሳምንት ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጌታ ሐሞት እንዳጠጡት ያንን እያሰቡ። አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚ፣ ቡናና ትርንጎ አፈርቷል፤ ጻድቁ ሌላ አስደናቂ ታሪክ አላቸው አርብ አርብ ሲዖል እየገቡ እልፍ እልፍ ነፍሳትን ያወጡ፤ በገበያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ካስተማሩ በኋላ ይመግቡ ነበር። በየወሩ የመድኃኔ ዓለም በዓል እየዘከሩ የወጣ የወረደውን ሁሉ የገበያውንም ሰው ሁሉ ያበሉ ይመግቡ ነበር። ዛሬም ሲዖል እየገቡ ያወጣሉ። “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”ዮሐ.3፡12  እንዳለ ጌታ ዛሬም ይህንን የሚጠራጠሩ ብዙዎች አሉ። እኛ ግን በዚህ እናምናለን እንታመናለን። በጥቅምት 27 ብዙ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ቀንም ነው።  አባታችን በጥቅምት 27 ቀንም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባታችንን አንድ ገበያ የሚያህል ሰው ይከተላቸው ነበር። የአባታችን አባ መባ ጽዮን በራሳቸው ገዳም ማጢቆስ በተባለ ገዳም አፅማቸው ይገኛል። በትግራይ ሽሬ አሎጊንም የሚባል ትልቅ ገዳም አላቸው። የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድኃኔ ዓለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው። እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በዓብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች። ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ክብሩ ከጻድቁ አቡነ መበዓ ጽዮንና ከአባ ጽጌ ድንግል በረከት ረድኤትን ያድለን አሜን።

Monday, November 5, 2012

ዓመታዊ እና ወርሃዊ መታሰቢያ በዓላት


በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።ኢሳ.56:5
ቅዱሳን መታሰቢያ ለበረከት ነው። ምሳ 107 
እግዚአብሄር ለቅዱሳን በቸርነቱ ከሰጣቸው በረከት ለመሳተፍ መታሰቢያቸውን ማድረግ የግድ ነው እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።/ማቴ 1040-46/ ይላልና ይህም የተባለው በነብያት፣ በጻድቃንና  በሌሎችም ቅዱሳን ስም መታሰቢያ ማድረግ እንደሚገባ ለመግለጽ ነው።  
መታሰቢያ አንድ ሰው ለሀገሩ በስራው መልካም ስራ፡ ላበረከተው አስተዋፅኦ በጀግንነቱ ታይቶ በዚህች ኃላፊ ጠፊ ዓለም በስሙ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል ፣መንገድ ተሰርቶለት ሲዘከር ይኖራል ፡፡ እሱ ሕይወት ባይኖርም ስሙ ህያው ሆኖ ሲወሳ ይቆያል፡፡ ሰው ሁሉ እንዲያሲታውሰውም ይደረጋል፡፡ የእነዚህ አርበኝነት ምድራዊ ሃላፊ ጠፊ ነው። የቅዱሳን መታሰቢያ ስንለል ግን ፤ጻድቁን ለማስታወስ በቅዱሱ ስም የሚገነባውን ቤተክርስትያን የሚከበረውን በአል ነው። ምድራዊው መታሰቢያ  ለየት የሚያደርገው ምድራዊ መታሰቢያቸው ከሰው ሳይሆን ከሰማያዊ አምላክ ፈቃድ በመሆኑ ሥራው ነው። ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው።5 ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።መዝ.111:3

Thursday, November 1, 2012

ዜና ሕይወቱ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ልደቱ :- የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ደራሲ፣ መናኝ፣ ጻድቅ፣ ሊቅ፣ የሕዝብ መምህር እና የሥነ ምሕንድስና ባለሙያ የሆነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተወለደው በ1357 ዓመተ ምሕረት በወሎ ክፍለ ሀገር በዛሬው ቦረና በጥንቱ ወለቃ ወረዳ ሸግላ በተባለ ቦታ ነው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ስለ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ይተረካሉ፡፡ የሰኔ ድርሳነ ዑራኤል ምንባብ አባቱ በመጀመሪያ የትግራይ በማስከተል የሰግላ /ጋሥጫ/ አገር ገዢ እንደነበር ይወሳል፡፡ ገድሉ ደግሞ /ጠቢብ ወማእምረ መጻሕፍት ወአቡሁኒ መፍቀሬ እግዚአብሔር አምኁልቈ ካህናተ ደብተራ ዘውሳጤ ዓጸደ ቤተ ንጉሥ/ አባቱም የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳን /ሥዕል ቤት/ ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ ይላል፡፡ እንደ ገድሉ ገጸ ምንባብ ትርጉም ሕዝበ ጽዮን ከንጉሡ ሥዕል ቤት በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ከሚያገለግሉ ካህናት አንዱ ነው፡፡ /. . . ወእሙኒ እም ሥዩማነ ወለቃ/ እናቱም ከወለቃ ሹማምንት ወገን ነች ይላታል፡፡ ይኸውም የጥንቱ ወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና ከላላ/ ከነበሩ መኳንንት ወገን መሆኗን ያመለክታል፡፡      የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ልጅ ሳይወልዱ ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የልጅ ፍላጎታቸው እንዲሠምር ለሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳሉ፡፡ ስእለታቸውም ሥምሮ በመልአኩ ቀዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ልጃቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመማጸን ስለወለዱ ስሙን ጊዮርጊስ ብለው ጠሩት፡፡ ወላጆቹ የታላቁን ሰማዕት ስም ለልጃቸው ያወጡት ወደ ፊት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ምስክር፣ አፅራረ አምነትን አሳፋሪ፣ ካህናትንና ምእመናት በየዘመናቱ ከሚነፍሱ የኑፋቄና የክህደት ነፋሳት በወንጌል ብርሃን ነፃ የሚያወጣ ሲሉ ይህን ስም እንዳወጡለት ድርሳነ ዑራኤል እንዲህ ይተርካል፡፡ ‹‹ዘይከውን መምህረ ኵሉ ዓለም ወበጸሎቱ ዘያድኅን አሞተ ሲኦል ፍቁረ ድንግል ማርያም ወላዲቱ ለአማኑኤል፡፡ ወመገሥጾሙ ለነገሥት፡፡ ወፀሮሙ ለዐላውያን ሃይማኖት በሰይፈ ቃሎሙ ለሐዋርያት ዘያጠፍኦሙ እም ብሔረ ኢትዮጵያ፤ ወለካህናተ ጽድቅ ዘይመርሆሙ እምጽልመተ ኑፋቄ መንገለ ብርሃን ቃለ ወንጌሉ ለክርስቶስ በትምህርተ ሕጎሙ ለሐዋርያት›› ይላል፡፡
ትምህርት :-አባ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርቱን ከወላጅ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እንደተማረ ይገመታል፡፡ አባቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተምህርቱን ካስተማሩት በኋላ መዐርገ ዲቁና እንዲቀበል ማድረጋቸውን  ገድሉ ይነግረናል፡፡ ወሶበ ልህቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆነ፡፡ ባደገም ጊዜ ከጳጳስ ዘንድ ወሰደው ጳጳሱም በዲቁና አሾመው ይላል ገድሉ፡፡ ዲቁና መቀበሉን እንዲ መዓርገ ዲቁና የሰጡትን ጳጳስ ስም አይገልጽም፡፡ ዳሩ ግን መዓርገ ዲቁናን በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ መተርጉም እንደተቀበለ ይገመታል፡፡
መዓርገ ዲቁና ከተቀበለ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ለታላቅ ሐላፊነት የተመረጠውን ልጃቸውን በዘመኑ የታወቀ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ሊያስተምሩት ለሚችሉ መምህራን መስጠት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በወቅቱ ጥልቀት ያለው የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ለመማር የሚመረጠው ትምህርት ቤት ሐይቅ እስጠፋኖስ ነበር፡፡ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ በዐፄ ዳዊት /1385 - 1395/ ዘመነ መንግሥት እንደገባ ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያየ ሊቃውንት የሚገኙት፣ በብዙ መጻሕፍት የተሞላውና ዙሪያውን በሐይቅ በመከበቡ የተማሪን ሐሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነ ቦታ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ የትምህርት ቤት ሕይወቱም ከቅዱስ ያሬድ ይመሳሰላል፡፡ ቀዱስ ያሬድ ትምህርት አልገባው ብሎ ሰባት ዓመት እንደተቸገው እንደዚሁ አባ ጊዮርጊስም አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ? ብለው እስከ ሚጠይቁ ድረስ ትምህርት አልገባ ብሎት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ ‹‹ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው›› ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን ‹‹ አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ አልቀበልህም እዚያው ገዳሙን ያገልግል›› ብሎ እንደገና ላከው፡፡በዚህ ዓይነት መምህሩ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ መልሶ ወሰደውና በጥበብ እድ ሥራ ላይ ተመደበ፡፡ በጥበበ እድ ባከበተው ዕውቀትም እንደ ቅዱስ ላሊበላ ከዐለት ፈልፍሎ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ችሏል፡፡ ዛሬ ከዘመን ርዝማኔ የተነሣ ጥገና ባይደረግለትም አባ ጊዮርጊስ ፈልፍሎ ያሠራው ዋሻ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን ብዙ የትሩፋት ሥራ በሠራበት በጋሥጫ ገዳም ይገኛል፡፡ የወለቃን ወንዝ ለመሻገር ያገለግል ዘንድ ከዓለት ፈልፍሎ የሠራው ድልድይም የሥነ ምሕንድስና ሙያው የታየበት አሻራ ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁል ጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይፈጭበት የነበረው የድንጋይ ወፍጮ አሁንም በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዐ ልቡና አጠጣችው፡፡ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ጀመር፡፡