Tuesday, November 6, 2012

†♥†ነገረ ቅዱሳን†♥†



“በስመ ሥላሴ”
ወበዛቲ ዕለት አእረፈ አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅመ እግዚአብሔር” (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።) መዝ.፻፲፭፡፲፭ (115፡15)
እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ለአቡነ መብዓ ጽዮን፣ ንዲሁም ለአባ ጽጌ ድንግል በዓለ እረፍታቸው አደረሳችሁ አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!
እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡(እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር  ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“ መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው። በአባታቸው ስም ሀብተ ጽዮንም ብሎ ይጠራቸዋል። እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው። አባታቸው ንቡረ ዕድ ሀብተ ጽዮን እናታቸው ሂሩት ይባላሉ። ደገኛ ጻድቅ ሲሆኑ ከታወቁበት ግብራቸው በሳምንት ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። ጌታ ሐሞት እንዳጠጡት ያንን እያሰቡ። አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚ፣ ቡናና ትርንጎ አፈርቷል፤ ጻድቁ ሌላ አስደናቂ ታሪክ አላቸው አርብ አርብ ሲዖል እየገቡ እልፍ እልፍ ነፍሳትን ያወጡ፤ በገበያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ካስተማሩ በኋላ ይመግቡ ነበር። በየወሩ የመድኃኔ ዓለም በዓል እየዘከሩ የወጣ የወረደውን ሁሉ የገበያውንም ሰው ሁሉ ያበሉ ይመግቡ ነበር። ዛሬም ሲዖል እየገቡ ያወጣሉ። “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”ዮሐ.3፡12  እንዳለ ጌታ ዛሬም ይህንን የሚጠራጠሩ ብዙዎች አሉ። እኛ ግን በዚህ እናምናለን እንታመናለን። በጥቅምት 27 ብዙ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ቀንም ነው።  አባታችን በጥቅምት 27 ቀንም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባታችንን አንድ ገበያ የሚያህል ሰው ይከተላቸው ነበር። የአባታችን አባ መባ ጽዮን በራሳቸው ገዳም ማጢቆስ በተባለ ገዳም አፅማቸው ይገኛል። በትግራይ ሽሬ አሎጊንም የሚባል ትልቅ ገዳም አላቸው። የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድኃኔ ዓለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው። እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በዓብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች። ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ክብሩ ከጻድቁ አቡነ መበዓ ጽዮንና ከአባ ጽጌ ድንግል በረከት ረድኤትን ያድለን አሜን።
 ምንጭ፡- የኢትዮጵያውያን ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ  በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ፣ የዛሬው መጽሐፈ ስ/ሳር፣ ነገረ ቅዱሳን ፪  
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

1 comment:

  1. all u have written is very interesting and essential to all of us orthodox followers.but one thing to tell u that is "take care of spelling" b/c there are so many mis-spelt words. 10Q U FOR ALL!!!

    ReplyDelete