በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ዘወትር
ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ በምናደርሰው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› በተሰኘው የጸሎት ክፍል ውስጥ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ
በሥጋሽም ድንግል ነሽ›› የሚል የምስጋናና የምስክርነት ቃል ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በመልክዓ ማርያም
ውስጥም ‹‹ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ ወገቢረ ምሕረት መፍቅዱ›› ማለትም ‹‹ምሕረት ማድረግ ለሚወድ
መልካም መልካሙን ማሰብ ልማዱ ለሆነ ሕሊናሽ ሰላም እላለሁ!›› የሚል የምስጋና ቃል አለ፡፡
የተአምረ
ማርያም መቅድም ደግሞ የድንግል ማርያምን ሕሊና ከመላእክት ሕሊና ጋር ያስተያይና በልጦ ሲያገኘው በመደነቅ እንዲህ
እያለ ያመሰግናል፡፡ ‹‹ሥጋዊ ነገር ከማሰብ መጠበቅ ከአዳም ልጆች ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ
ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፡፡ በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር
ወርደዋልና፡፡›› ከዚህም ጋር አያይዞ ‹‹የእመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› ይህም አሳብዋ
ንጹሕና መልካም ብቻ መሆኑን ያስረዳናል፡:
እኛ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔርን እንድንመስል›› ታዘናል፡፡
(1ጢሞ4.7-8፤ 1ቆሮ11.1) ይህም በመልክ አይደለም፡፡ በሥራና በአመለካከት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን በአመለካከት
መምሰል የማይቻል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔርን ምሰሉ አንባልም ነበር፡፡ በመልክ ስለመምሰል የሚናገር ቢሆን ኖሮ ደግሞ
መልክን የሚፈጥረው ፈጣሪ ስለሆን ‹‹ምሰሉ›› አንባልም ነበር፡፡ የሚደንቅ ነው! እኛ ፈጣሪን በአሳብና
በአመለካከት እንድንመስለው ታዘዝን፡፡ ድንግል ማርያም ግን መስላ ስለተገኘች ‹‹አሳብዋ እንደ አምላክ አሳብ
ነው፡፡›› የሚል ምስክርነት ተሰጠላት፡፡
ቀደም ሲል ስለ ድንግል ማርያም ፍጹም የሕሊና ድንግልናና በጎነት ከአዋልድ መጻሕፍት ያስቀደምኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፈው ማሳየት ያስፈልጋልና እነሆ!
ብዙ
ሰዎች ስለ ድንግል ማርያም የሕሊና ንጽሕና ስንናገር በምን አውቃችው ነው? ለማለት ይዳዳቸዋል፡፡ በእርግጥ እኛ
እንኳን የድንግል ማርያምን ሕሊና የኃጥአንንም ሕሊና የምናውቅበት ችሎታ የለንም፡፡ የጻድቃን ሕሊና ከኃጥአን ይልቅ
እጅግ ይጠልቃል፡፡ የድንግል ማርያም ሕሊና ደግሞ ከሁሉ ይልቅ ጥልቅ ነው፡፡ ‹‹መንፈሳዊ ሰው በማንም አይመረመርም
እርሱ ግን ሁሉን ይመረምራል›› ከተባለ ሰው ፍጹም መንፈሳዊት ድንግል ማርያምን ሊመረምር እንዴት ይችላል?
(1ቆሮ2.15)
ታዲያ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያላችሁ ጠዋትና ማታ የምትዘምሩት የእርሷን ሐሳብ
በምን አውቃችው? ለሚሉን መልሳችን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም አሳብ ስለሚናገር ነው እንላቸዋለን፡፡ የት
ቦታ ቢሉንም ቅዱስ ሉቃስ ሲጽፍ ‹‹ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ብላ አሰበች›› ይላል፡፡ (ሉቃ1.29)
‹‹አሰበች›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ ይህን አለች ቢል ሰምቶ ነው፤ ይህን ሠራች ቢል አይቶ ነው ይባላል፡፡
‹‹አሰበች›› ሲል ምን እንላለን? የክርስቲያኖች መልስ አንድ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ምን እንዳሰበች ገልጾለት ነው
እንላለን፡፡ ሰይጣንና መናፍቃን የሚሉት አያጡምና ምናልባት ገምቶ ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ መቼም በዚህ አይሳቅም!!!
መጸለይ ነው እንጂ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም! በየርእሰ ጉዳዩ የድንግል ማርያም አሳብ ምን እንደሚመስል
መንፈስ ቅዱስ ሲገልጥ ኖሮአል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወንጌላዊው ሉቃስ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ‹‹ይህን ሁሉ
ነገር በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡›› ሲል መስክሯል፡፡ (ሉቃ2.19፤ ሉቃ2.51) መንፈስ ቅዱስ በልቧ
ያለውን ካልገለጠለት ‹‹በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር›› እያለ ሊናገር እንዴት ደፈረ? በሰው ልብ ያለውን
ከመንፈስ ቅዱስና ከሰውዬው በቀር ማንም ሊያውቅ እንደማይችል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ የለምን? (1ቆሮ2.11)
ድንግል
ማርያም በሕሊናዋ የዚህ ዓለም ምኞት አልነበራትም፡፡ እንኳን ኃጢአቱና ኃጢአት ያልሆነውም ሥጋዊ አኗኗር በልቧ
አልነበረም፡፡ ይህም ማለት ‹‹አግብቼ ወልጄ መልካም እየሠራሁ ቤተሰቦቼን እየረዳሁ እኖራለሁ›› የሚለው አሳብና
ምኞት በውስጧ አልነበረም፡፡ ይህም ፈጣራ ሳይሆን በቅዱስ ዳዊት የትንቢት ቃል ይታወቃል፡፡ ስለ እርሷ ‹‹ልጄ ሆይ
ስሚ ጆሮሽን አዘንብዪ የእናትሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ›› ብሏል፡፡ ምእመናን! አባቷ ዳዊት እረ ስሚኝ፣ ጆሮ
ስጪኝ እያለ ለምኖ ሲያመሰግናት ስሙ!!
‹‹እርሺ›› ማለት ምን ማለት ነው? አታስቢ ማለት አይደለምን?
የምትረሳውስ ምንድር ነው? የእናት የአባቷን ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት የእናት የአባትሽን ቤት አትመኚ! እንደ እነርሱ
አግብቼ፣ ወልጄ እኖራለሁ ብለሽ አታስቢ ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ! ቅዱስ ዳዊት ነቢይ ነው፡፡ እርሷ ይህን ዓለም
እንድትረሳ የመከራት እንዳይመስላችሁ፡፡ እንደምትረሳው አውቆ በፈሊጥ ትንቢት ተናገረ እንጂ፡፡ አነጋገሩ እኮ
‹‹አቤቱ ተነሥ›› እንደሚለው ዓይነት ትንቢት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ይህን ቃል ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ስለኢየሱስ ክርስቶስ
ትንሣኤ ተናግሮታል፡፡ (መዝ131.8) ኢየሱስ ክርስቶስ ዳዊት ‹‹ተነሥ›› ስላለው የተነሣ ይመስላችኋል?
እንደሚነሣ አውቆ ትንቢት መናገሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንዲሁ ‹‹እርሺ›› ቢልም እንደምትረሳው አውቆ ትንቢት
ተናገረ እንጂ ያስረሳት ዳዊት አይደለም፡፡
ታዲያ እንዲህ ኃጢአትን ሁሉ የዘነጋ ሕሊና ለማን ተሰጠው?
እንዲህ ያለ ንጽሕናንና ቅድስናን የማያመሰግን አንደበት እንደምን ያለ ነው? እንዴት ያለ በደል ነው? እንዴትስ ያለ
ድፍረት ነው? በበደል የረከስን ስንሆን ኃጢአትም ነግሣብን ሳለ ራስን ከፍ ለማድረግ ላላፈርን ለኛ ወዮታ ይገባል!
እንኳን ከኀልዮ ኃጢአት ከተግባሩም ላልሸሸን ለኛ ኀዘን ይገባል፡፡ ‹‹እርሷ እንደኛው ናት!›› የሚሉ አርሲሳን
/መናፍቃን/ ቦታቸው የት ይሆን? ሰው ባለማወቁ መጥፋቱን አያውቅም፡፡ መሬታዊው ሰው ደረጃውን አላዋቀምና ለዚህ
ስንፍናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሹ ምን ይሆን?
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ድንግል ማርያም መልአኩን
‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል›› አለችው፡፡ መልአኩ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› ባላት ጊዜ ታዲያ ምን
ብርቅ አለው? ‹‹ሴት ልጅ ጊዜዋ ሲደርስ ታገባለች፤ ትጸንሳለች›› ልትለው ትችል ነበር፡፡ እርሷ ግን ‹‹ይህ
እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ ይህም ጥያቄዋ የልቧን መታተም ያስረዳል፡፡ አንዲት ሴት ባል ባይታጭላትና ባታገባ
እንኳን ትወልጃለሽ ስትባል ‹‹ይሆን ይሆናል›› ትላለች፡፡ ወንድ ግን በተፈጥሮው የሚወልደው እርሱ ስላልሆነ
ትወልዳለህ ቢሉት ‹‹እንዴት ይሆናል?›› ይላል፡፡ የድንግል ማርያም ንግግር የሁለተኛውን ይመስላል፡፡ የወንድ
መውለድ የማይጠበቅ ነገር እንደሆነ በእርሷ ዘንድ መውለድ የማታስበው ጉዳይ ነውና ‹‹እንዴት ይሆናል›› አለች፡፡
እንደዚሁም
መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ›› ብላዋለች፡፡ ይህም ለወደፊት እንኳን ወንድ ላለማወቅ ሕሊናዋን የዘጋች መሆኗን
ያስረዳል፡፡ አለማወቋም ጾታ የመለየትና ያለመለየት ጉዳይ አይደለም በግብር ነው እንጂ፡፡ ለዮሴፍ የታጨችው ለተቃርቦ
ቢሆን ኖሮ ወንድ ስለማላውቅ ባለችው ጊዜ መልአኩም መልሶ ምነው ዮሴፍ አለ አይደል ሊላት በቻለ ነበር፡፡ ነገር
ግን መልአኩ እንደዘመናችን መናፍቃን አያስብምና የልቧን ንጽሕና አይቶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን እንደምትወልድ
ነገራት፡፡ ለማሳመንም ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› አላት እርሷም ነገሩን በጥንቃቄ መርምራ ስታበቃ
‹‹ይደረግልኝ›› ብላ በትሕትና ቃሉን ተቀበለችው፡፡ ያን ጊዜ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ
የዕለት ጽንስ ሆኖ በማኅፀኗ አደረ፡፡
የሕሊናዋ ነገር እንደዚህ ከሆነ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!›› በማለት ሰው እንዳይገድል እጁን ከደም የከለከለችውን ሴት አእምሮ ካመሰገነ እኛ ክርስቲያኖች ድንግል ማርያም በቀን ስንት ጊዜ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያልን ልናመሰግናት ይገባን ይሆን? (1ሳሙ25.33)
ይቆየን!
ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ወንድማችን ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን፡፡ ንጽህት ቅድስት ድንግል ማርያም ህይወትህን ትባርክልህ እኛንም ከክፉ ነገር ሁሉ በምልጃዋ ትጠብቀን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እሷን መማፀኛ አድርጎ ስለሰጠን ክብር ምስጋና ይገባዋል!
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDeleteGOD BLESS YOU.
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDeleteየአገልግሎት ጊዜህን ድንግል ማሪያም
ትባርክልህ
ቃለ ህይወት ያሰማልን!ድንግልን ለዘላሙ አመሰግናታለሁ!!!
ReplyDeleteወንድማችን ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን፡፡ ንጽህት ቅድስት ድንግል ማርያም ህይወትህን ትባርክልህ እኛንም ከክፉ ነገር ሁሉ በምልጃዋ ትጠብቀን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እሷን መማፀኛ አድርጎ ስለሰጠን ክብር ምስጋና ይገባዋል!
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን!ድንግልን ለዘላሙ አመሰግናታለሁ!!!
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን!! እመቤቴ ትስጥልኝ።
ReplyDelete