Monday, November 26, 2012

†አባ ገሪማ ዘመደራ†

አባ ገሪማ ዘመደራ  (“ኦ ወልድዬ ግሩም ገሪማ ገረምከኒ”)

የተሰዓቱ ቅዱሳን ሐዋርያዊ ተልእኮ መቅድም
ተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አልአሜዳ በነገሰ በአምስት ዓመት ነው። እንደመጡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በአክሱም ዐስራ ሁለት ዓመት ኖረዋል።     
ተሰዓቱ ቅዱሳን በስም አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጵሕማ፣ አባ አፍአባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ፣ አባ ጉባ ይባላሉ። እኚ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ዝም ብሎ አልተቀመጡም፤ ለሥራቸው በር ከፋች የሆነውን ቋንቋ፣ የሕዝቡን ባህል ጠንቅቀው ካወቁ በኋላ ላይ በአንድ አከባቢ ከመኖር ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በመደባቸው ቀጥታ ማስተማርን መርጠው መንፈሳዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የአክሱምን ነገስታት እርዳታና ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር። እኚው ተሰዓቱ ቅዱሳን የመጡበት ሀገራት ሮም፣ እስያ፣ አንጾኪያ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ቂሳርያ፣ ኪልቂያ ሲሆን በነበሩበት ጊዜያትም፡­-
፩. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጽንቶልናል።
፪. መጽሐፍትን ተርጉሞልናል።
፫. ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል።
፬. ብዙ ገዳማትን መስርተዋል።
፭. ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል።
ስለ እነዚህ ቅዱሳን ይህችን ታህል ካልኩኝ ዛሬ ወርሃዊ ዕለታቸው ከሚታሰበው ከእነዚሁ ቅዱሳን አንዱ ስለሆኑ አባ ገሪማ ዘመደራ ትንሽ ልበላችሁ።
አባ ገሪማ ዘመደራ፡­- ቀዳሚ ስማቸው ይስሐቅ ነው። አባታቸው ሶፎንያስ ንጉስ ሮም ነው። አባ ገሪማ ከልጅነታቸው ጀምሮ በመንፈሳዊ ትምህርት ታንጸው አድገው ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ኖረዋል። ኋላም የአባታቸውን ዙፋን ወርሰው ለ፯ ዓመት ገዝተዋል። ከዚህ በኋላ አባ ጰንጠሌዎን “ምድራዊ መንግስት ያልፋል ይጠፋል፤ የማያልፈውን ሰማያዊ መንግስት ትወርስ ዘንድ ፈጥነህ ወደኔ ና።” ብለው ላኩባቸው። ቅዱስ ገብርኤል ከእግዘዚአብሐሔር ታዞ በክንፉ ነጥቆ  በአንድ ቀን አክሱም አድርሷቸው ተገኙ። መዓርገ ምንኩስናን ተቀብለው ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቆጠር እየጾሙ ሰውነታቸውን ዝሎ መቆም እስኪያቅታቸው ድረስ አብዝተው እየሰገዱና እየፀለዩ ይጋደሉ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን መቁነን (ለገዳማውያን የሚሰጥ ምግብ) ተቀብለው ከወንድሞች ጋር ወደ መንገድ ሲሄዱ ቤተ ክርስቲያን አግኝተው እጅ ሲነሱ ካህናት እየተቻኮሉ መጥተው ቅዳሴ ሊታጎልብን ነውና ከእናንተ የሚቻለው አንድ ሰው ይርዳን አሏቸው። የቀሩት መቁነናቸውን ቀምሰውት ነበር። እሳቸው ግን ቋጥረው ይዘዋት ስለ ነበር ከቅጥሩ ውጭ አኑረው ገብተው ቀድሰዋል። እኒያም በልተው የቀደሱ መስሏቸው ለአባ ጰንጠሌዎን ሄደው ነገሯቸው። እሳቸው ሲመጡ መነኮሳቱ “ አድርውት እንደሆነ እንዳያፍር ጥቂተ እልፍ በሉ” አሏቸው። አባ ገሪማ ይህንን አውቆ እንጨቶችና ድንጋዮችም ይወገድልን እንጂ አሉ። በዙርያቸው የነበሩ ድንጋዮችና እንጨቶች ሦስት ምዕራፍ ያህል ሸሽተዋል። አባ ጰንጠሌዎን ያዩትና የሰሙት ሁሉ ደንቋቸው “ ግሩም ድንቅ ልጄ ይስሐቅ አስገረምከኝ፣ አስደሰትከኝ ሲሉ “ኦ ወልድዬ ግሩም ገሪማ ገረምከኒ” ገሪማ የተባሉት ከዚህ በኋላ ነው። መነኮሳቱም አጥፍተናል ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል። ኋላም መደራ ገብተው በዓት ሰርተው ሃያ ሦስት ዓመት በትኀርምት (በጾም) ኑረዋል። ጌታ ሀብተ ተዓምራት ሰጥተዋቸውል። በነግህ ስንዴ ዘርተው በዕለቱ ለመስዋዕት አድርሰዋል። ከመስዋዕት የተረፈውን በጠፍጣፋ ድንጋይ ቢፈጩት በርክቶ ሰባ ሰባት ቁና ዱቄት ህኖላቸዋል። ከዓለት ላይም ወይን ተክለው አብቅለዋል። ከዚህ በኋላ ብዙ ታዓምራትን ሲያደርጉ ኖረው  በሰኔ ፲፯ በሰረገላ ብርሃን ተሰውረዋል።  ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አልአሜዳ ዘመነ መንግስት በ፬፻፹ ዓ.ም ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ ሆነው ነው። የአባታችን ረድኤታቸው፣ በረከታቸው፣ ቃል­-ኪዳናቸው ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
ዋቢ መጽሐፍት
ነገረ ቅዱሳን ፪ በማኀበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል፣ 
መዝገበ ታሪክ ፪፣ 
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ በአቡነ ጎርጎርዮስ    
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡
  

1 comment:

  1. Hey! Do you know if they make any plugins to help with SEO?

    I'm trying to get my blog to rank for some targeted keywords but I'm not seeing very good gains.
    If you know of any please share. Many thanks!
    Here is my web page :: high paying jobs with mba degrees

    ReplyDelete