Friday, December 16, 2011

Wednesday, December 14, 2011

በጋሻው በመ/ር ዘመድኩን ላይ የመሠረተው ክስ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶውን ጥምረት እያጠናከረው ነው


  • “የአዲስ አበባ ጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች ኅብረት”፣ ኦርቶዶክሳውያን ፖሊሶች እና የችሎት ተከታታዮች ለመ/ር ዘመድኩን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል 
  • በድብደባ ሙከራ ወንጀል ክስ እንዲመሠረትበት የተወሰነበት መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ መ/ር ዘመድኩን ከሕገ ወጡ ቡድን ጋራ ዕርቅ እንዲያወርድ ተማፀነ
  • በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጥያቄ የተቋረጠው የክስ ዝገብ እንዲቀጥል ተደርጓል

(ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 4/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 14/2011)፦ በጋሻው ደሳለኝ በመ/ር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ላይ በስም ማጥፋት ወንጀል መሥርቶት የነበረውና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጥያቄ ተቋርጦ የነበረው የክስ መዝገብ ዳግመኛ ተከፍቶ እንዲንቀሳቀስ በፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ መመሪያ ከተሰጠ በኋላ ሁለቱ ተከሳሾች ዛሬ፣ ታኅሣሥ አራት ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡የክሱ ፋይል መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት ከሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ደግሞ “የሰባኪው ሕጸጽ” በሚል ርእስ ካሳተሙት መጽሐፍ ጋራ በተያያዘ ቀደም ሲል ተቋቁሞ የነበረው ክስ መሆኑን ለችሎቱ የተናገሩት ዳኛ ሁለቱ ተከሳሾች ያለጠበቆቻቸው የቀረቡ በመሆኑ፣ እያንዳንዳቸው እንደ ቀድሞው የብር 5000 ዋስ በማስያዝ ታኅሣሥ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ጠበቆቻቸውንና የመከላከያ ማስረጃዎቻቸው ይዘው እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ከትእዛዙ በፊት ዐቃቤ ሕግ ሙሉ ግደይ በዋስትናው ጉዳይ ላይ የተለየ አስተያየት ይኖራቸው እንደሆነ ከዳኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ የቀድሞው የዋስትና መጠን በቂ በመሆኑ ላይ ተቃውሞና ልዩነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ የመ/ር ዘመድኩን ጠበቃ የሆኑት አቶ ጌትነት የሻነው ከትእዛዙ በኋላ በችሎት ቀርበው በቀጣዩ ቀጠሮ የመከላከያ ምስክሮችን ከማቅረባቸው በፊት በክሱ ላይ ማሳሰቢያ እንዳላቸው ቢያስታውቁም ማሳሰቢያቸውን በቀጣዩ ቀጠሮ እንዲያቀርቡ በዳኛው ተነግሯቸዋል፡፡
“የሰባኪው ሕጸጽ” መጽሐፍ ያሳተሙትና የክሱ መቋረጥ ውሳኔ በተነገረበት በቀደመው የችሎቱ ውሎ ማብቂያ ላይ በአሰግድ ሣህሉ የድብደባ ሙከራ ወንጀል የተቃጣባቸው ዲያቆን ደስታ ጌታሁን በዛሬው ችሎት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ለካራማራ ፖሊስ ምስክሮቻቸውን ይዘው ቀርበው ቃላቸውን በማስመዝገብ መጥሪያ ካወጡ በኋላ ከዐቃብያነ ሕግና ከጽ/ቤቱ ሓላፊ ጋራ መነጋገራቸውን ያስረዱት ዲያቆን ደስታ ዐቃቤ ሕግ ግን ክሱን ለመመሥረት ፈቃደኛ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አቤቱታውን ያዳመጡት ዳኛው ዲያቆን ደስታ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ቀርበው እንዲነጋገሩበትና ውጤቱን ለችሎቱ እንዲያሳውቁ ትእዛዝ ሰጥተዋቸዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የዲያቆን ደስታ አቤቱታ በዚህ ውስን አጋጣሚ የፍትሕ ሥርዐቱ የሚፈተሽበት አንድ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው የችሎቱ ውሎ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንና አካባቢው የጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች ከችሎቱ ጅማሬ እስከ ፍጻሜው በቁጥር በርከት ብለው በመገኘት ድባቡን አስገርመዋል፡፡ በአርማጌዶን ካሴት እና በአርማጌዶን ቪሲዲ መ/ር ዘመድኩንን የሚያውቁ ኦርቶዶክሳውያን የችሎቱ ተከታታዮች፣ የጸጥታ አስከባሪዎችና በተለያዩ የክስ መዝገቦች የቀረቡ ጥቂት የማይባሉ ባለጉዳዮች ሳይቀሩ በአስፈላጊው መንገድ ከጎናቸው በመቆም ድጋፋቸውን እንደሚሰጧቸው ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
ትናንት መ/ር ዘመድኩን ከአርማጌዶን ቁጥር አንድ ቪሲዲ ጋር በተያያዘ በበጋሻው ተከሰው በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡበት ወቅት እንዲያሲዙት የተጠየቀውን የብር 3000 ዋስ እርሳቸው የማያውቋቸውና ችሎቱን ለመከታተል የተገኙ ምእመናን መሸፈናቸው ተመልክቷል፡፡ በዛሬው ችሎት ሁለቱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው የተጠየቁትን የብር 5000 ዋስትናም መ/ር ዘመድኩን በራሳቸው ከጨመሩት ብር 1000 ውጭ/ በተመሳሳይ መንገድ መሸፈኑ ተገልጧል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ውሎ መጠናቀቅ በኋላ በችሎቱ ሥነ ሥርዐትና በፀረ - ተሐድሶው ጎራ የታየው መተባበር ያስደነገጣቸውም ያበሳጫቸውም ከሚመስሉት አንዱ የሆነው አሰግድ ሣህሉ ከደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል “ጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች” ተወካይ ጋር መነጋገሩ ተዘግቧል፤ በንግግሩም አሰግድ ሣህሉ “ምናለ ይህ ጉዳይ በዕርቅ ቢያልቅና ይቅር ብንባባል?” የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩ የግል ጠብ ሳይሆን እርሱን ጨምሮ ሕገ ወጡ ቡድን በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በቀኖናዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ መንገድ የሚፈታበት አካሄድ አካል እንደሆነ በተወካዩ አማካይነት እንደተነገረው፤ ይቅርታ/ዕርቅ የሚያስፈለገውም ለመ/ር ዘመድኩን ሳይሆን ለሕገ ወጡ ቡድን በመሆኑ ከበደሏት ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ እንዲጠይቁም ተመክረዋል፡፡ ይሁንና አሰግድ በእርሱ በኩል በጋሻውን እንደሚያግባባ፣ ወጣቶቹም መ/ር ዘመድኩንን እንዲያሳምኑለት በመማፀን ሽምግልና በመጠየቁ መቀጠሉ ነው የተነገረው፡፡
በአጠቃላይ በትናንቱ ይሁን በዛሬው የችሎቶቹ ውሎዎች የታዩት ተጨባጭ መተባበሮች የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ንቅናቄው ሰፊ መሠረት መያዙንና ምእመኑ መንፈሳዊውን ተጋድሎ የራሱ ጉዳይ ለማድረጉ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሤራና ራስ በቀል አጉራ ዘለልነትም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚሸነፍ ይኸው የተጠናከረ አጋርነት የማያወላዳ ምስክር ሆኖ ተወስዷል፡፡
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ አሜን፡፡

Tuesday, December 13, 2011

የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት በኢትዮጵያ


ቤተ ክርስቲያን ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ነበረች። ዓለማት ከተፈጠሩ በኋላ በዓለመ መላእክት፣ በዓለመ መሬት በሕገ ልቡና እና በሕገ ኦሪት እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያትና ካህናቱ አማካኝነት ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ስታገናኝ ኖራለች። በዘመነ ሐዲስ ደግሞ በደመ ክርስቶስ ተዋጅታ ሕገ ወንጌልን ስትናኝ እና አምልኮተ እግዚአብሔርን ስታስፋፋ ኖራለች። በእነዚህ አዝማናት ሁሉ ስለ እርሷ ሳይፈሩና ሳያፍሩ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ እግራቸውን ለሰንሰለት የሰጡላት፣ በብዙ መከራዎች የተጋደሉላትን አበው፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታትን እና በእነርሱ መንገድ የተጓዙ ብዙ ሊቃውንትን አፍርታለች (ዕብ ፲፩)
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕገ አበውን፣ ሕገ ኦሪትንና ሕገ ወንጌልን አስተባብራ በመያዝ የጥበብ ምንጭ፣ የሥርዓት መፍለቂያ፣ የዕውቀት ባሕር ሆና ሁሉ የተሟላላት ስንድ እመቤት ናት። በማኅበራዊ አገልግሎቷ ደግሞ የድኩማን መጠጊያ፣ ያዘኑና የተከፉ መጽናኛ፣ የማንነትም አሻራ ነች። ለዚህም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የአብነት /ቤቶች ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት የተንኮልና የክህደት ቋጠሮ ይዘው የመጡ መስሐቲያን (አሳሳቾች) አፍረው የተመለሱት ከአብነት /ቤቶቹ በወጡ መምህራን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለሀገር መሪ ለሕዝብ አስተማሪ በመሆን ሕዝብን ያገለገሉ ደጋጎች ከእነዚህ የአብነት /ቤቶች በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ናቸው።
ሌላው ልንገነዘበው የሚገባ ቁም ነገር ቢኖር ገና ያልደረስንባቸው ብዙ እምቅ መንፈሳዊ ሃብቶች ያሉን መሆናቸዉ ነው። ለምሳሌም፦ በዜማዉ የአጫብር፣ የቆሜ፤ በቅኔው የዋድላ፣ የጎንጅ፤ በመጻሕፍት ትርጓሜ የላይ ቤት፣ የታች ቤት እየተባሉ የሚሰጡ ትምህርቶች ይትበሃሎች አሉን። እነዚህ መሠረታቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት ሆነው አካባቢያዊ መልክ ያላቸውን እምቅ እሴቶች ልንፈለፍላቸውና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ናቸው።
የቤተ ክርስቲያኒቱ አብነት /ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት አሁን በዓለም እውቅ ከሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ከሆነው ከሐርቨርድ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚያመሳስለው ነገር ያለው ሲሆን ይህም አግራሞትን የሚፈጥርና የሥረዓተ ትምህርቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። ሆኖም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥረዓተ ትምህርት በዘመን ቀዳማዊ ሆኖ መገኘቱ እጅግ የሚያኮራ ነው።
የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሳይከለስና ሳይበረዝ ተጠብቆ እስከአሁን እንዲዘልቅ ያደረጉት ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የአብነት /ቤቶች ናቸው። ስለሆነም እነዚህ የትምህርት ማዕከላት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዳይዘጉ፤ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው እንዳይሰደዱ፣ ወንበር እንዳይታጠፍ በጋር እና በተናጠል ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ሆኖም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ የእሳት ማጥፋቱ ሥራ በልማት ቢታገዝና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ቢቻል መልካም መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው።    
ገዳማት አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ ተቆጥሮና ተሰፍሮ የማያልቅ ውለታ የዋሉ፤ እንደ ዓይናችን ብሌን ልንጠብቃቸው የሚያስፈልጉ የተቀደሱ ሥፍራዎቻችን ናቸው፡፡
እነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመሩ የሊቃነ ጳጳሳቱ መገኛ፣ እና በአፍ በመጣፍ የመጣን አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚመልሱ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መፍለቂያ ናቸው፡፡ ገዳማቱ ስለሀገር፣ ስለወገን የሚጸልዩ ከእነርሱም አልፎ ለሌላው መዳን ምክንያት የሚሆኑ መናንያን፣ መነኮሳት መኖሪያ፣ የምእመናን ተስፋ፣ በረከት ማግኝያም ናቸው፡፡

ገዳማቱ፣ አድባራቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ለኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ-ሥዕል፣ የፊደል፣ የሥነ-ሕንጻ ምንጭነትና አጠቃላይ የሥልጣኔና የትምህርት ማዕከል በመሆን ያገለገሉና እያገለገሉ ያሉ የሀገር ኩራት ናቸው፡፡

በውስጣቸው የሚገኙት ንዋያተ ቅድሳት፣ ሥነ-ሕንጻዎችና ቅርሶች ለሀገርና ለወገን ኩራት ከመሆን አልፈው ዓለም አቀፍ ቅርሶች እስከ መሆንና ለሀገሪቱም በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ ያሉ ውድ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን፣ የሀገር፣ የምእመናን ተስፋና ኩራት እንዲሁም የማንነታችንና የታሪካችን መነሻ የሆኑት ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ዛሬ ተገቢው ትኩረት ባለማግኘታቸውና በበቂ ሁኔታ አስታዋሽ በማጣታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡

ገዳማቱ ሁሉ ካለባቸው ችግር ተላቀው በቋሚነት ራሳቸውን በልማት እንዲችሉ ለማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሁሉንም ምእመናን ተሳትፎ የሚጠይቅ ሰፊ ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ስለዚህ ወደፊትም ለውጥ እና የተጠናከረ እድገት እስኪመጣ ድረስ ደጋግመን ልናስብበት ይገባል፡፡

በመሆኑም በቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችንን ጽናትና ተጋድሎ ተጠብቀው የቆዩት ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ዛሬ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተኑ ነው፡፡ መነኮሳቱ በረኀብና በዕርዛት እየተሰቃዩ ገዳማት እየተፈቱ ነው፡፡ የአብነት መምህራን በተማሪዎቻቸው ብዛት የደመቀ ሰፊ ጉባኤያቸው በምግብ እጦት የተማሪው ቁጥር እየተሸረሸረ፣ መምህራን ወንበራቸው እየታጠፈ ጉባኤውም እየተበተነ ነው፡፡

ከዕድሜ ዘመናቸው የተነሣ ጥንታውያኑ ቅርሶች እና የአብያተ ክርስቲያናቱ ሕንፃዎች እየፈራረሱ ነው፡፡ መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳቱ ከአያያዝ ጉድለትም ሆነ በአግባቡ የሚጠቀምባቸው ጠፍቶ እየተጎሳቆሉ ነው፣ በተለይ በየገጠሩ በርቀት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከልብሰ ተክህኖ እስከ ዕለት መቀደሻ ጧፍ፣ እጣን፣ ዘቢብ እየጠፋ ቅዳሴ እየተስተጓጐለ ነው፡፡

እነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና አብነት ትምህርት ቤቶች በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እና በዘራፊዎች ጭምር እየተዘመተባቸውም ነው፡፡ በየገዳማቱ ተመሳስለው በመግባት፣ በችግራቸው ሽፋን መነኮሳቱን በማሳሳት፣ በኣታቸውን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ከመጣር አንሥቶ ጥንታውያኑን መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳቱን እስከመዝረፍ ድረስ ብዙ ችግሮች እየተፈጸመባቸው ነው፡፡

በእነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና አብነት /ቤቶች የሚገኙ አባቶችና አገልጋዮች ይህን ሁሉ ተደራራቢ መከራና ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በእግዚአብሔር ቸርነት ጸንተው ቢቆዩም፤ ሃይማኖታዊ እሴቶችና ቅርሶቻችን ተጠብቀው ለትወልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በየጊዜው በተለያየ አቅጣጫና መንገድ ከየገዳማትና አድባራቱ እንዲሁም አብነት /ቤቶች የሚመጡትን የድረሱልን ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የምእመናን ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡

ለነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች መልስ መስጠት የቤተ ክርስቲያንን ተተኪ በብዛት ማፍራት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን የሀገርን ታሪክና ቅርስ ማስጠበቅና መጠበቅም ነው፡፡ በተጨማሪም ከራሳቸው አልፎ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገር፣ ለወገንና ለዓለም ሰላም ቀን ከሌት የሚጸልዩትን መናኒያን ማትጋት ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን የገዳማቱን የድረሱልን ጥሪ መስማት ያስፈልጋል፡፡

የሊቃውንትና አባቶች ካህናት መፍለቂያነታቸው እንዲቀጥል መናንያንና መነኮሳቱ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን የሚጸልዩት ጸሎት እንዳይስተጓጐል፣ ጥንታውያኑ የብራና መጻሕፍት፣ ገድላትና ተአምራት ሌሎችም የእምነታችንና የማንነታችን መለያ የሆኑ ንዋያተ ቅድሳቱ በዘላቂነት ባሉበት እንዲጠበቁ ማድረግ ስፈልጋል፡፡

እሁንም የነዚህ ጥንታውያን ገዳማት፣ አድባራትንና የአብነት /ቤቶች ችግር የሰፋና በርካታ በመሆኑ የሁሉንም ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡

በችግር ያሉትን ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጥሪ የማንን ፈጣንና ተግባራዊ ምላሽ እንደሚጠብቁ ለማወቅ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

ገዳማቱን ከጠባቂነትና ከተረጂነት አላቆ ራሳቸውን በማስቻል መንገድ ቢቀናጅ ገዳማቱን፣ አድባራትና አብነት ትምህርት ቤቶቹን ከተመጽዋችነት ማላቀቅ ይቻላል፡፡

ቀጣይነት ያለው ልማት በጋራ መሥራቱና መተባበሩ ለነገ በይደር ይቆይ ሊባል የማይገባ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን በመቻል ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከልነታቸው ተጠብቆ፤ በዘላቂነት እንዲቀጥሉ በማድረግ በኩል የሁላችንም አስተዋፅኦ አለ የማባል ነው ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አካላት፣ ምእመናን ገዳማቱት አድባራቱ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶች የሀገር ሀብት በመሆናቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር በጋራ መሥራት ይገባቸዋል፡፡

እስቲ ዛሬ የታእካ ነገስት በአታ ለማርያም ገዳም የአብነት ት/ቤት ምን ያህል በችግር ላይ እንደ ሆነ በዚህ ቪሲዲ እንመልከት