Wednesday, November 30, 2011

እሳቱ ከሌለ ጢሱ አይታይም


ሰሞኑ ሀገራችን አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማዘጋጀት ሽር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ አሥራ ስድስተኛውን የአይካሳ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ፡፡ ሀገሪቱ እንዲህ ያሉ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤያትን ማዘጋጀቷ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ መልካም ገጽታዋን ለማስተዋወቅ፣ በጉባኤ ቱሪዝም የሚገኘው ገቢ፣ ከሚመጡ ባለሞያዎች ጋር የሚኖረው የዕውቀት ልውውጥ፣ የሚፈጠረው የገበያ እና የሥራ ዕድል፣ ሌሎችም፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ይህንን መሰል ጉባኤያት የሚያስከትሉት አሉታዊ ነገርም አለ፡፡ ቅርሶች ወደ ውጭ የሚወጡበትን መንገድ በመክፈት፣ ባህልን በማበላሸት፣ ዝሙት አዳሪነትን እና ቁማርን በማስፋፋት፣ ለትውልድ እና ሀገር መበላሸት ክፉ አስተዋጽዖም ያደርጋሉ፡፡
ኮንፈረንስ ቱሪዝም የተስፋባቸውን የዓለም አካባቢዎች ስንመለከት ከላይ ያነሣናቸው አሉታዊ ገጽታዎች ጎልተው ይታዩባቸዋል፡፡ አካባቢዎቹ ችግሩን ለመቋቋም የሚወስዱት ርምጃ እንደ አመለካከታቸው ይወሰናል፡፡ ኳታር እና ላስቬጋስ እኩል አመለካከት የላቸውም፡፡ በላስቬጋስ ኃጢአት ራሱ ኃጢአት አይሆንም፡፡ አደንዛዥ ዕጽ፣ ዝሙት፣ ቁማር፣ ግብረ ሰዶም እና የራቁት ዳንስ ፈቃድ እስከወጣባቸው እና ግብር እስከ ተከፈለባቸው ድረስ ሕጋውያን ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በኳታር እነዚህ ነገሮች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ ከሀገሪቱ የእምነት እና የሞራል ሕግጋት ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸውም እንደ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ተቆጥረው ርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ ወደ ቦታው የሚሄዱ ሰዎችም እነዚህን ነገሮች ዐውቀው እንዲጠነቀቁ ቅድመ መረጃ ይሰጣቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ አያሌ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶች አሏት፡፡ ዓይነተኛ የሰው ልጅ የጥበብ ውጤቶች ሆነው ለገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ ባህላዊ ምርቶች ሞልተዋታል፡፡ የአየር ንብረቷ እና የተፈጥሮ አቀማመጧ ሊጎበኝ፣ ሊታረፍበት የሚገባም ነው፡፡ እነዚህን ሀብቶቿን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከምትሆንባቸው መንገዶች አንዱ ልዩ ልዩ የቱሪዝም ዘርፎችን ማስፋፋት ነው፡፡ በተለይም የኮንፈረንስ ቱሪዝም፡፡
በኮንፈረንስ ቱሪዝም በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ ሀገር ስለሚመጡ፣ ሆቴሎችን እና የመዝናኛ ሥፍራዎችን ስለሚጠቀሙ፣ የሚውሉባቸው ቦታዎች በአንድ አካባቢ መሆኑ ለጥበቃ ስለሚመች፣ የትራንስፖርት እና የመገናኛ ዘዴዎችን በአንድ ጊዜ በማንቀሳቀስ ገበያ ስለ ሚፈጥሩ፣ እንደ መልካም ዕድል የሚታይ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ሀገሮች ታላቅ ጉባኤያትን ለማዘጋጀት ይወዳደራሉ፣ መሠረተ ልማት ያሟላሉ፣ የማረፊያ እና የመዝናኛ ሥፍራዎች ይገነባሉ፣ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋሞቻቸውን ያጠናክራሉ፤ የመገናኛ እና ትራንስፖርት መንገዶችን ይዘረጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ አሁን አሁን አያሌ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አካባቢያዊ ጉባኤያት ከሚደረጉባቸው ሀገሮች አንዷ በመሆን ላይ ናት፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥትንም ሆነ ዜጎቿን የሚያስደስት ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ጉባኤያት ሲዘጋጁ ግን አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳንሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ከሕዝቡ ባህል እና የሞራል እሴቶች፣ ከሀገሪቱ ጥቅሞች እና ቅርሶች ጋር የሚቃረኑ ተግባራት እግረ መንገዳቸውን እንዳይሠሩ ክፍተት የሚኖርባቸውን ቦታዎች ሁሉ ሊፈተሹ ይገባል፡፡
ከሰሞኑ ከሚካሄደው የአይካሳ 16 ጉባኤ ጋር በተያያዘ የሚነፍሱ ወሬዎች አሉ፡፡ በተለይም ከግብረ ሰዶም ጋር በተገናኘ፡፡ በዚህ እና በዚያ ቦታ ጉባኤ ሊያደርጉ ነው፡፡ እነርሱም ተገኝተው ሃሳባቸውን ያካፍላሉ፤ የሚሉ ነገሮች እየተሰሙ ነው፡፡
በጎረቤታችን በኬንያ በዚህ ረገድ በይፋ የሚሠሩ ተቋማት ይህንን ጉባኤ ምክንያት በማድረግ ዓይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ መጣላቸውን የሚያመለክቱ ፍንጮችም እየታዩ ነው፡፡ በድረ ገጾቻቸውም እየገለጡ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ 90 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝቧ በእምነቱ ግብረ ሰዶምን ይቃወማል ብቻ ሳይሆን ይጸየፋል፡፡ የሀገሪቱ ሕጎችም ግብረ ሰዶማዊነትን በወንጀልነት ይፈርጃሉ፡፡ ከሕዝቡ እምነት ብቻ ሳይሆን ከባህሉ ጋርም የሚጣረስ ጉዳይ ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ነገር በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ የሚሠሩ፣ ሕዝቡም ያልበላውን የሚያክኩ ተቋማት እና ግለሰቦች አጋጣሚዎቹን እንዳይጠቀሙ የሚመለከተን ሁሉ በርግጠኛነት መከላከል ይጠበቅብናል፡፡
ግብረ ሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ፣ የግበረ ሰዶማውያንን መብት ካልደገፋችሁ አንረዳም እያሉ የሚያስፈራሩ ምዕራባውያን ኃያላን አሉ፡፡ ራሳችንን አጥተን የሚመጣ ርዳታ ለቀብር ማስፈጸሚያነት ብቻ የሚውል ነው፡፡ እናም እንዲቀርብን እንንገራቸው፡፡
የጉባኤው አዘጋጆችም ቢሆኑ ወደ ጉባኤው ለሚመጡ እንግዶች የኢትዮጵያን ሕግ እና የሞራል እሴቶች አስቀድመው የመግለጽ እና የማስጠንቀቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እና ላስቬጋስ ውስጥ ሲሰበሰቡ ያለውን ልዩነት ዐውቀው መምጣት አለባቸው፡፡ በአዲስ አበባ እና በሳንፍራንሲስኮ መካ ከል ያለውን ልዩነት ሊረዱት ይገባል፡፡
የሀገራችን ሰው እሳቱ ከሌለ ጢሱ አይታይም ይላል፡፡ አሁንም ቢሆን ምናልባት በጎላ መልኩ አልወጣ ይሆናል እንጂ ያለ ምክንያት የግብረ ሰዶማዊነት ጉዳይ በዚህ ወቅት አልተነሣም፡፡ ጢሱ እንዳይታይ ከመጣር ይልቅ እሳቱ እንዲጠፋ ብንሠራ የተሻለ ውጤት እናመጣለን፡፡

No comments:

Post a Comment