የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነትና አማላጅነት
በዲ/ን ሕብረት የሽጥላ
ታሪኩን ልብ ብሎ ያነበበ ሰው ይህ ‹‹መልካምና የሚያጽናና ቃል›› ምን ይሆን? ማለቱ አይቀርም፡፡ መቼም ‹‹የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?›› ለሚለው የልመና ቃል ‹‹ምሬአቸዋለሁ ወይም እምራቸዋለሁ›› ከሚል ውጭ የሚያጽናና ቃል ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም በግምት የቀረበ ሐሳብ ሳይሆን መልአኩ ለዘካርያስ ባስተላለፈው የመጨረሻ ቃል ይታወቃል፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።›› ብለህ ስበክ ብሎ ልኮታል፡፡ (ዘካ1.16-17
መልአኩ የለመነው ምን ነበር? ምሕረት አልነበርምን? ፈጣሪ ደግሞ በምሕረት ተመልሻለሁ ሲል መለሰ፡፡ የመልአኩ አማላጅነት ተቀባይነት አግኝቷ ማለት ነው፡፡ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ይህን የመሳሰሉ ጠንካራና በርካታ መረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አግኝተን ነው እንጂ ከራሳችን ፍላጎት ተነሥተን አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ይህን ጥቅስ በተመለከተ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ አንድ ቀን ከአንድ መናፍቅ ጋር በአጋጣሚ የሃይማኖት ጉዳይ ተነሣና መነጋገር ጀመርን፡፡ ርእሱም ስለመላእክት አማላጅነት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ለማስረዳት ይህን ጥቅስ ጠቀስኩለት፡፡ ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹መላአኩ እኮ የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ እንጂ አልለመነላቸውም፤ ማራቸውም አላለም፡›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እኔም እሺ ታዲያ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አልኩት፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹መቼ ልትምራቸው አስበሃል? ብሎ ቀጠሮ ነው የጠየቀው›› ሲል ደመደመ፡፡ ምንም እንኳን የምንማረው ለመናፍቃን መልስ ለመስጠት ብለን ባይሆንም እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ድርቅና ሊያጋጥማችሁም እንደሚችል አትርሱ፡፡
እንደዚህ መናፍቅ አተረጓጎም መልአኩ የጠየቀው ‹‹እስከ መቼ›› ብሎ ቀጠሮ ከሆነ መልሱ ‹‹በዚህ ጊዜ›› የሚል እንጂ ‹‹በምሕረት ተመልሻለሁ›› የሚል አይሆንም ነበር፡፡ ጥያቄው ምን እንደነበር ከመልሱ በመነሣት ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌላው ቋንቋው አማርኛ እስከሆነ ድረስ በሌላም ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ አባት በማምሸትና በመስከር ያስቸገረውን ልጁን ‹‹ልጄ እንደዚህ የምትሆነው እስከመቼ ነው?›› ቢለው ቀነ ቀጠሮ ስጠኝ እንጂ አለው ብለን እንደማንፈታው የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሐረግ በስድሳ ስድስቱ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ከ50 ጊዜ በላይ ስለተጠቀሰ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ምሳሌውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስናደርገው ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?›› እያለ ሲጸልይ ቀን ቅጠርልኝ ማለቱ ሳይሆን አትርሳኝ እንጂ እያለ መለመኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ (መዝ12.1) ስለዚህ መልአኩም ‹‹የማትምራቸው እስከመቼ ነው?›› ሲል ‹‹ማራቸው እንጂ፤ አባክህ ማራቸው!›› እያለ እንደለመነላቸው ከምላሹም መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው፡
Kale Hiwot Yasemalen
ReplyDelete