Friday, February 10, 2012

ያኔ… /በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/!!

(በወንድማችን ገብረእግዚአብሔር)
ያኔ… /በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/!!
( በተመስጦ ሆነው ያንቡት)!
በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በደመናው ውስጥ የነበሩት ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እንዴት የተባረኩ ናቸው?
እኛም ከወደድን እና ከፈቀድን ክርስቶስን እንደ እነዚህ ደቀ መዛሙርት በተራራ ሳይሆን በሚያስደንቅ ብርሃን ውስጥ እናየዋለን፡፡ ክርስቶስ ዳግመኛ በእንዲህ ዓይነት ክብር አይመጣም፡፡ ይልቁንም በዚሁ ተራራ ባሳየው ከፊል ብርሃነ ጸዳል (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢሩ ምዕ.30፡39 ያችን ብርሃነ ጸዳል፡- አዳም ከመበደሉ በፊት የነበረች ብርሃነ ጸዳል ናት ይላታል) ሳይሆን በአባቱ ክብር እናየዋለን፡፡ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ሳይሆን ከመላእክት፣ ሊቃነ መላእክት፣ ከኪሩቤል እና ከሌሎች አእላፍ ነገደ መላእክት ጋር ሲመጣ እናየዋለን፡፡ ደመናን ይዞ ሳይሆን ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ የተጋጀችውን አዲሲቷን ኢየሩሳሌም (መንግሥተ ሰማያትን) ይዞ ሲመጣ እናየዋለን፡፡
መጥቶም በጸጋው ዙፋን ሳይሆን በፍርድ ዙፋኑ ይቀመጣል፡፡ ያኔ ሰው ሁሉ ከመጋረጃው ወጥቶ በፊቱ ይቆማል፡፡ ሁሉም ንጉሡን ያዩታል፡፡ እያንዳንዳቸውንም ይጠይቃቸዋል፡፡ መልስም ይሰጣቸዋል፡፡ ለአንዳንዶቹ፡- “እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ተርቤ አብልታችሁኛልና” ይላቸዋል /ማቴ.25፡34-35/፤ ለሌላውም፡- “መልካም አንተ ታማኝም ባርያ በጥቂት ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ” ይለዋል /ማቴ.2523/፡፡
ለአንዳንዶቹ ደግሞ፡- “እናንተ ርጉማን ለሰይጣን እና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል /ማቴ.25፡41/፤ ለሌላውም፤- “አንተ ክፉ ሐኬተኛም ባርያ” ይለውና /ማቴ.25፡26/ “እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወደ አለው ጨለማ አውጡት” ብሎ መላእክቱን ያዛቸዋል /ማቴ.22፡13/፡፡ መልካም ፍሬ ያላደረገ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እቶንም ይጣላል፡፡ በመረቡ ውስጥ የነበሩትን ክፉ ዕቃዎች ተለይተው ወደ ውጭ ይጣላሉ፡፡
“በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ” /ማቴ.13፡43/፡፡ እንደውም ጌታ ሲያስተምር እኛ ከዚህች ፀሐይ በላይ ሌላ ብርሃን ስለማናውቅ በዚያ መስሎ ነገረን እንጂ ቅዱሳንስ ከፀሐይ ብርሃን በላይ ያበራሉ፡፡…ኃጥአን ግን በኦሪት ዘጸአት ካነበብነውና ከሚዳሰሰው ጽኑ ጨለማ በላይ በሆነ ጽልመተ ደይን ተከናንበው ወደ ዘላለም እሳት ይጣላሉ /ዘጸ.10፡21/፡፡
ያኔ ምንም ዓይነት መዝገብ፣ ማረጋገጫና ምስክር አያስፈልግም፡፡ በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና የተገለጠ ስለሆነ አረጋጋጩም፣ ምስክሩም ዳኛውም እርሱ ራሱ ነው /ዕብ.4፡13/፡፡ ደሀ ባለጸጋ፣ ሰነፍ ብርቱ፣ ጥበበኛ ጥበበኛ ያልሆነ፣ ያታሰረ ያልታሰረ፣ ባርያ ጌታ የሚባል ጭምብል ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይወገዳል፡፡ ጥያቄውም የምግባርና የትሩፋት ብቻ ይሆናል፡፡ በዓለማውያን ፍርድቤቶቻችን እንደምናውቀው አንድ ወንጀል የሠራ ሰው ፕሬዝዳንትም ይሁን አምባሳደር ወይም ሌላ አለ የምትሉት ማዕረግ ቢኖሮውም ከተጠያቂነትና ከቅጣት አያመልጥም፡፡ በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት ደግሞ ከዚሁ የባሰ ነው፡፡
እንግዲያስ እኛም ይሄ ሁሉ እንዳይደርስብን ቆሻሻው ልብሳችንን አውልቀን በምግባር በትሩፋት በልጽገን የብርሃን ልብሳችንን እንልበስ፤ የእግዚአብሔርን ክብር በዙርያችን እናድርግ፡፡ በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት ከመቆም በላይ የሚያስፈራና የሚያንቀጠቅጥ ነገር የለም፡፡ እዚያ እንዳይቆሙ ከማድረግ በላይም ቀላል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው መታዘዝን እንጂ ከአቅም በላይ የሆነ ነገርን አይደለምና፡፡…
የእግዚአብሔር ሕግ ምን እንደሚል ብጠይቃችሁ ሁላችሁም አንድ በአንድ ልትነግሩኝ እንደምትችሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ታድያ ይህ ለእኔ ምን ያደርግልኛል፡፡ ይሄማ ወደ ሲዖል የሚወርዱ ኢ-አማንያንም ያውቁታል፡፡
ወንድሞቼ ያኔ በአስፈሪው ዙፋን ከመቆም ዛሬ እልፍ ጊዜ የሰማይ መብረቅ ቢዘንብብን ያሻለናል፡፡ ዛሬ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት ብንቀርብ ይሻለናል /ዕብ.4፡16/፡፡ ያኔ ያ ፍቅር የሆነው የክርስቶስ ፊት ከሚለወጥብን አሁን ሺ ጊዜ ብናፍር ይሻለናል፡፡ ያኔ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሰው ሁሉ በተሰበሰበት አደባባይ ፊት ከምናፍር ዛሬ በአንድ ንስሐ አባት ፊት ማፈር ይሻለናል፡፡ ያኔ በከንቱ ዋይ! ዋይ! ከምንል ዛሬ ለተራበው እንጀራን ብንቆርስ፣ ስደተኛውን ደሀ ወደ ቤታችን አስገብተን ብናሳድረው፣ የታረዘውንም ብናለብሰው ያሻለናል /ኢሳ.58፡7/፡፡ ያኔ ዘይት ለመግዛት ወጥተን በውጭ በር ከሚዘጋብን ዛሬ የዘይት ማሰሮአችንን ለመሙላት ብንፍጨረጨር ይሻለናል፡፡ ያኔ እንደ ባለጸጋው ከምንለምን ዛሬ ከማን ጋር መነገድ እንዳለብን ብናውቅ ይሻለናል፡፡
የፍቅር አባት እግዚአብሔር እንዲህ ይለናል፡- “በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ከመንገዱ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” /ሕዝ.18፡23/፡፡
ልብ ይስጠን!!

2 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን፡
    የቅዱሳን አባቶቻችንን ምክር ይዘን ብንፀና የመንግስቱ ወራሾች እንሆናለንና እንግዲህ ለምትበልጠው ፀጋ እንሽቀዳደም፡፡
    አዱዱ ነኝ ከሀዋሳ

    ReplyDelete
  2. Amen ! kale hiwot yasemalen !
    ያኔ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሰው ሁሉ በተሰበሰበት አደባባይ ፊት ከምናፍር ዛሬ በአንድ ንስሐ አባት ፊት ማፈር ይሻለናል፡፡ Denke mastewal naw!

    ReplyDelete