Sunday, February 12, 2012

ድርሳንና ገድል ጥያቄ

ጥያቄ ”በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ጊዜ ድርሳንና ገድል ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኔም የድርሳንና የገድል ልዩነት ብዙ ጊዜ አይገባኝም፤ እባካችሁ የድርሳንና የገድልን አንድነትና ልዩነት አስረዱኝ”

ዲ/ን ኅሩይ ባየ

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ጊዜ ድርሳንና ገድል ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኔም የድርሳንና የገድል ልዩነት ብዙ ጊዜ አይገባኝም፤ እባካችሁ የድርሳንና የገድልን አንድነትና ልዩነት አስረዱኝ”
ገብረ እግዚአብሔር
ከዲላ

ውድ ጠያቂያችን በእርግጥ እርስዎ እንዳሉት ድርሳንና ገድል በቤተ ክርስቲያን የማይነሡበት ጊዜ የለም፡፡ “የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው” ዕብ.13፥7 እንደተባለው በሃይማኖትና በምግባር ለመጠንከር ገድለ ቅዱሳንን የያዙ መጻሕፍትን እናነባለን፤ እንጸልይባቸዋለን፡፡ የቅዱሳን መላእክትንም ጠባቂነት፣ የሊቃውንትን ተግሣጽ ትርጓሜና ምክር የዕለተ ሰንበትን ክብር እና የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነት ሥራ የሚናገሩ ድርሳናትን ሁል ጊዜ እናነባለን እናደርሳለን፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለው መጽሐፋቸው “ድርሳን” የሚለውን ቃል እንዲህ ብለው ይፈቱታል “ድርሳን በቁሙ “የተደረሰ፣ የተጣፈ፣ ቃለ ነገር፣ ሰፊ ንባብ፣ ረዥም ስብከት፣ ትርጓሜ፣ አፈታት፣ ጉሥዐተ ልብ፣ መዝሙር፣ ምሥጢሩ የሚያጠግብ፣ ቃሉ የተሳካ፣ ጣዕመ ቃሉና ኃይለ ቃሉ ደስ የሚያሰኝ ልብ የሚነካ” ማለት ነው፡፡

ድርሳን ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ተራዳኢነት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ክብርና ጸጋ፣ ስለ ዕለተ ሰንበት ክብርና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚናገሩ /የሚያትቱ/ መጻሕፍት ማለታችን ነው፡፡

እስከ 2000 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ወደ 138 የሚሆኑ በድርሳን ስያሜ የሚጠሩ መጻሕፍት እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 11ዱ የመላእክት ድርሳናት ሲሆኑ የ11ዱ መላእክት ስምም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ አፍኒን፣ ቅዱስ ፋኑኤል፣ ቅዱስ ሳቁኤል፣ ቅዱስ ሱርያል፣ ቅዱስ ሱራፌልና ቅዱስ ኪሩቤል ናቸው፡፡

የመላእክትድርሳናት በአብዛኛው ተመሳሳይነት ባሕርይ አላቸው፡፡ የውስጥ ይዞታቸውም በ5 ይከፈላል፡፡ እነሱም መቅድም፣ ድርሳን፣ ተአምራት፣ አርኬና መልክእ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ድርሳን የምንለው የባለ ድርሳኑን መልአክ ግብር በፈጣሪው ዘንድ ያለውን ሞገስ የሠራቸውን ተአምራት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እያጣቀሰ የሚያብራራ ክፍል ነው፡፡ በአጠቃላይ ድርሳንን በ4 መክፈል ይቻላል፡፡

ድርሳነ መላእክት የሚባለው ድርሳነ ሚካኤል ድርሳነ ገብርኤልን የመሳሰሉትን ነው፡፡
ድርሳነ ሰንበት ስለ ዕለተ ሰንበት ክብር የሚያብራራ መጽሐፍ ድርሳነ መስቀል ደግሞ የመስቀሉን ታሪክና አመጣጥ ይተርካል፡፡
ድርሳነ ሊቃውንት ደግሞ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን የሚባለው ነው፡፡ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን ዘቅዱስ ቄርሎስንም ያጠቃልላል፡፡
ድርሳነ ማኅየዊና ድርሳነ መድኀኔ ዓለም የመሳሰሉት ድርሳናት የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያዘክሩ ድርሳናት ናቸው፡፡

ገድል፡- “በቁሙ ትግል ፈተና ውጊያ ሰልፍ ድልና አክሊል እስ ኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም የሚሠሩት ሥራ የሚቀበሉት መከራ ማለት ነው” ሲሉ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ፍቺያቸው አስቀምጠውታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ገድል ማለት ጻድቃንና ሰማዕታት በሕይወት ዘመናቸው እያሉ የሠሩትን ሥራ የሚናገር መጽሐፍ እንደሆነ አብራርተዋል /ደስታ ተክለ ወልድ 2036፣ አለቃ ኪዳለ ወልድ ክፍሌ 301/ የገድል መጻሕፍት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትእዛዘ እግዚአብሔር እንዲከበር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ከአላውያን ነገሥታት፣ ከቢጽ ሐሳውያን፣ ከጠላት ዲያብሎስና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያወሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸው በኑሮአቸው እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳዩን የሕይወታቸው መስተዋቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ገድል ስንል የቅዱሳን ታሪክ፣ ተአምራት፣ ቃል ኪዳንና መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ይህ እንዲህ ይሆናል ይቻላል ተብሎ የተነገረው ቃል በእውነት የሚኖር በቃልና በሥራም የሚገለጥ እንደሆነ የምናየው በቅዱሳን ገድል ነው፡፡ /ማቴ.10፥37፣ ሉቃ.14፥27፣ 1ቆሮ.11፥26-28/

ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው /2ቆሮ.11፥23-22 ዕብ.11፥32-40/ ራሱ የሐዋርያት ሥራ የምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያትን ግብር /ሥራ/ ገድልና ዜና የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳንም መጽሐፈ ጦቢት መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ሶስና፣ የመሳሰሉት በሰዎቹ ኑሮ የተገለጠውን የእምነታቸውን ፍሬ የሚያሳዩ የገድል መጻሕፍት ናቸው፡፡

ገድላት በ3 ይከፍላሉ እነሱም፡-

ገድለ ሰማዕታት፡- ለምሳሌ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ገድለ ፋሲለደስ፣ ገድለ ኢየሉጣ
ገድለ ሐዋርያት፡- በአንድነት የተሰበሰቡ የሐዋርያት አገልግሎት ተአምራት መከራ የያዙ መጽሐፍት
ገድለ ጻድቃን፡- ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስና የመሳሰሉትን ነው፡፡

ውድ ጠያቂያችን ምላሹን ለማጠቃለል ድርሳን ሲባል የመላእክትን ግብር በፈጣሪያቸው ዘንድ ያላቸውን ሞገስና የሠሯቸውን ገቢረ ተአምራት እየዘረዘሩ የሚናገሩ፣ ስለ ዕለተ ሰንበትና ቅዱስ መስቀል ክብር የሚያስረዱ ድርሳነ ሰንበትንና የድርሳነ መስቀል፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ምክርና ተግሣጽ እንዲሁም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የመሰከሩበት የሊቃውንት መጻሕፍት፣ በመጨረሻም የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያስታውሱ እንደእነ ድርሳነ ማኅየዊ ያሉት መጻሕፍት በድርሳን ሥር ይጠቃለላሉ፡፡

ገድል ደግሞ ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ጥበብ የቅዱሳንን መከራ ተጋድሎ፣ ተአምራትና ቃል ኪዳን የያዙ የቤተ ክርስቲያን ሕያውነት የሚገለጥባቸው መጻሕፍትናቸው፡፡ ድርሳናትም ሆኑ ገድላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይጋጩ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ የሚተረጉሙና የሚተነትኑ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሰፋ የለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ሐመረ ተዋሕዶ 1999፥61፣ ሐመር ጥር/የካቲት 2000፥27 አዋልድ መጻሕፍት ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሜጋ ማተሚያ ቤት 1995፣ የኢዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ዛሬና ነገ፣ ብራና ማተሚያ ቤት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ 1995፥16 የሚሉ መጻሕፍትና መጽሔቶችን ቢያነኳቸው መልካም ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በመላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳን ጸሎት ሁላችንንም ይጠብቀን፡፡

2 comments: