Friday, December 28, 2012

መልካም ፍሬ እናፍራ

መልካም ፍሬ እናፍራ
በአምላካችን አምሳል ተፈጥረን በአርአያው
ክብሩን እንድንወርስ አድርጎን ሕያው
አባታዊ ፍቅሩን ማጣጣም አቅቶን
ከዓለሙ ተባብረን ኃጢአታችን ከብዶን
የጥፋት ደመና አንዣቦብን ሳለን
አርነት አወጣን ፍቅሩን አለበሰን
ታምነን እንሠማራ በእምነት ጎዳና
ከቤቱ እንመገብ ሰማያዊ መና
ብርሃናችንን በሰው ፊት እናብራ
በመንገዱ እንጓዝ መልካም ፍሬ እናፍራ፡፡
                    ምንጭ፤ ሐመር 9ኛ ዓመት ቁ. 3

Thursday, December 27, 2012

“ዘይሁብ መርሐ ርቱዓ ለቤተክርስቲያን”

(ምንጭ፡- ቤተ ደጀኔ)በጸሎተ ኪዳን ዘሠርክ ላይ እንደተነገረው፥ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ ለምትሆን፥ ጸጋን ኃይልን ለምታድል፥ አምነው ለሚቀርቡት ምስጋና አንድም በሃይማኖት ለሚገኝ ክብር ማረፊያ ማሳረፊያ ላደረጋት ለቤተክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። የተገረፈላት፥ሥጋውን የቆረሰላት፥ ደሙን ያፈሰሰላት፦ ነፍሱንም አሣልፎ የሰጠላት እርሱ ነውና። የሐዋ ፳፥፳፰።                                              
          ጥንት ሙሴን እና አሮንን ልጆቹንም ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የመረጠ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፫፥፩-፳፪፣ ፳፰፥፩-፲፬ ። ይህንን ምርጫ ለመቃወም ወይም በምርጫው ጣልቃ ለመግባት የሞከሩ ዳታን፥ ቆሬንና አቤሮን ፍጻሜያቸው አላማረም። “እናንተ የሌዊ ልጆች ስሙኝ፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር ለይቶ የመረጣችሁን የእግዚአብሔርን ድንኳን አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ እንድታገለግሏቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁን ታሳንሱ ታላችሁን?” ብሎ የመከራቸውን ሙሴን አልሰሙትምና ዘኁ ፲፮፥፩-፶። ከቤተ መንግስቱም ሰዎች እነ ዖዝያን እግዚአብሔር የመረጣቸውን ገፍተው ቤተ መቅደሱን ደፍረው ነበር። “ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፥ በዕጣን መሠዊያውም ላይ ያጥን ዘንድ ወደ መቅደስ ገባ ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ፥ ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን ለተቀደሱት ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ አይገባህም፥ ከእግዚአብሔር ርቀሃልና ከመቅደሱ ውጣ፥ ይህ በአም ላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ክብር አይሆንህም፥አሉት፤” ይላል። የንጉሡም መጨረሻ አላማረም። ፪ኛ ዜና ፳፮፥፲፮-፳፫ 

ቤተ ጊዮርጊስ : የላሊበላ ምስጢራዊ ቀመር እና ሙዝየም


Tuesday, December 25, 2012

የመነኮሳት ሕይወት

የመነኮሳት ሕይወት
አባ መቃርስ መነኮስ
ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና። መዝ.፴፡፳፫
“ካህንሰ እምኢተምህረ እምኢያ ብዝኃ ስብሐተ ትኅርምተ እምኢመጽኦ ትምክህት” /”ካህን ብዙ በዘይማር ትዕቢት ኩራት ባልወጣበት በነኮስም ትኅርምት አበዛለሁ ባይል ትምሂት ባልመጣበት ነበር።”/ (አባ መቃርስ መነኮስ)
አባታችን አባ መቃርስ ከሰው ርቆ ንጽህናውን ጠብቆ በበረሃ ይኖር ነበር። ምግቡ ቆቅ ነበር። በየቀኑ አንድ አንድ ቆቅ እየተያዙለት ቀቅሎ ሲባርከው ጎመን እየሆነለት ይመገበው ነበር። አንድ መነኩሴ ከቁስጥንጥያ መጥቶ እሱ ካለበት በረሀ ሲገባ ሲያጠምድ አይቶ ለሐሜት ቸኩሎ ወደ ከተማ ተመልሶ ለሊቀጳጳሱ ነገረው። እርሱም ሰርክ ሲደርስ ሊያጠምድ ወጣ። ሦስት ቆቆችን አጠመደ፤ ሊፈትነኝ ነውን ወይስ ሆዴ አልጠግብ ብላ ይሆን አለ። ወዲያው እኒህ መነኮሳት ካጠገቡ ደርሰው “ሰላም ለከ ኦ አቡነ” አሉት ጌታ ባወቀ ያደረገው ነው ብሎ ደስ አለው። አብስለሎ ድርሻቸውን ሰጣቸው። እርሱም ድርሻውን በልቶ መለስ ቢል አስቀምጠው ሲያዩት አያቸው፤ ለምን እራታችሁን አልበላችሁም? አላቸው። እኛስ እንዲህ ዓይነቱን እንበላ ዘንድ አልተፈቀደልንም አሉት። እሱን ለመንቀፍ እንደሆነ አውቆ እፍ እፍ ቢላቸው በረው ሄደዋል። በከንቱ አምተነዋል፤ ብለው ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውታል።

Monday, December 24, 2012

የ ግብጹ የሙስሊም ብራዘር ሁድና ማህበረ ቅዱሳንን ምን አገናኛቸው ???

(በሁሉባንተ አበበ)

ጽሁፎችን በተለያየ መልኩ ስንጽፋው ለመነበብ አሰልችነቱን እንቀንሳለን ዛሬ እንዲህ  አስቤአለሁ አስኪ  . . . .  ከተመቻችሁ ተከተሉኝ  አስተያየት እቀበላለሁ ካልሆነም ደግሞ በፍጥነት ብሎጉን ዘጋ ማድረግ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም እድሜ ለነ ጎግል ዛሬ የኢሜል ያክል ብሎጎች እንደ አሸን ፈልተዋል   እያንዳንዱን በእያይነቱ ማግኘት ቀላል ነው ። ይኸው እኛም ይህንን ተከትለን ያላቅማችን ዳንኤል ክብረት እይታወች ብሎ አሳየን እይታ ዕያልን እንከተላለን አይቀርበት ይኸው እንጽፋለን እድሜ  ለኮፒይ ፔስት ቴክኖሎጅይ መጻፍ ባንችል እንገለብጣለን ።
ስሙ ሰሞኑን እንዴት እንዳለፈ እኔ ነው የማቀው  . . . ቀድመን ስንጠረጥራት የነበረች ድራማ ይኸው እውን እየሆነች እንደሆነ ተመለከትናት /እንዴት ነው ሰውለሰው እንበላት ወይስ ፓትርያርክ ለመንግስት/  ። አባት የተባሉትም ምን እንደነካቸው አላቅም ይመስለኛል ቤተክህነቱም እንደ ቤተመንግስቱ የ ቀድሞ መሪውን /የአቡነ ጳውሎስን/ ራዕይ ለማሳካት እየጣረ ይመስላል።    እንዴት ነው ይህ ነገር የራሷ  ራዕይ የሌላት ሀገር፤ የራሷ ራዕይ የሌለት ቤተ መንግስት፤ አሁን ደግሞ የራሷ ራእይ የሌላት ቤተ ክህነት ልንፈጥር ይመስላል እንዴት ነው ራዕይ የሌለው ትውልድ መረን ይሆናል እያላችሁን ? ለሁሉም መጠርጠር መልካም ነው ብየ ነው እንጂ የፓትርያርካችንን  ራእይ ለማሳካት ብላችሁ በግልጽ አልነገራችሁንም ነገሩ ሰውን እኮ ተግባሩ ነው የሚገልጠው አይደል እንዴ ? ግራ ገባን ኮ ምን እንበል ብላችሁ ነው ? ግን በእውነት ድራማዋ አፈጣጠኗም ሂደቷም ትመቻለች
 ምርጫውም ደግሞ በካርድ ነው አሉ እንዴት ነው ታዛቢስ ከውጭ አይመጣም እንዴ ? የምረጡኝ ቅስቀሳም እኮ ሳያስፈልገው አይቀርም በዚህ ዐይነት ?  ይቅርታ ይቅርታ ነገሩ ተመራጩ በታወቀበት ምርጫ ላይ ለካ ይህ አያስፈልግም ።ነገሩ መዘዙ ነው የሚብሰን ደግሞምኮ ይሁን ቢባል  ባበው ጨነቀኝ እንተወው . . .  / መቸም ይህችን ምርጫ ግብጻውያኑ የ አቡነ ሺኖዳ ልጆች  ቢሰሙ ፍርፍር ብለው ነበር የሚስቁብን/። እውነት እውነት የዚህች እቅድ አቃጅ ግን እውነተኛ ቃሉን ጠባቂ ነው የመሪውን ራዕይ የሚከተል የሚያሳካ።  ከ ቤመንግስቱ ባለራዕዮች ከሆነ ያው መቸስ የአገሪቱን  አብዛኘውን ቁጥር የያዘ እምነት መሪን በቁጥጥር ስር ማድረግ የትራንስፎርሜሽኑን እቅድ ለማካት ዋናና ዋና ተግባር መሆኑ የማይጠረጠር ነው ስለዚህ የመሪውን ራእይ ለማሳካት ይህንን ማከናወን የግድ ነው ። ከቤተክህነቱም ከሆነ ደግሞ ያው በጥቂት አመታት ውስጥ ቤተክርስትያኗን የተሃድሶወች መሮጫ ለማድረግ ለታቀደው የተሃድሷውያን የትራንስፎርሜሽን እቅድ መፈጸም ዋናውን መቆጣጠር የማይጠረጠር አስፈላጊ ነው ። ለሁሉም ከሁለቱም ቢሆን የሚደነቅ ቃል ጠባቂነት ነው ? አንዳንዴ ትክክል የሆነ ብቻን ሳይሆን ሁሉንም ማድነቅ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም …. ነገር ግን ይህ ሃይማኖት ነው ቀልድ አይደለም ይመስላል እንጂ መጨረሻው እንደ አቃጆቹ እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው ። መቸም ለመልካም ነገር ለመንፈስ ቅዱስ ስራ የምርጫ ካርድ መፍትሔ እንዳልሆነ  መነገር የሚያስፈልገው አይደለም  
ደግሞ መቸነው ከእንቅልፌ ብድግ ስል ስለ ግብጹ የሙስሊም ብራዘር ሁድና ማህበረ ቅዱሳን የተጻፈ ጽሁፍ ፌስ ቡክ አካውንቴ ላይ ተለቆ አገኘሁት ። ይህ ነገር እንዴ ነው ? ጹሁፉ ከ ሰማይ ቤት ነው ?  ብየ አሰብኩ ያለፈው የፓርላማ አስቂኝ ንግግር ትዝ ቢለኝ /ድንገት ዳግም ትዝብሏቸው በመንፈሳቸው በኩል ተናግረውት ከሆነ ብየ ነው/  ምን አልባት ደግሞ  ራእያቸውን ለማሳካት የሚታገሉት ትጉ አገልጋዮች ለክ እንደ ገደል ማሚቶ አስተጋብተውት ከሆነስ ??? እኔ እንጃ ብቻ እያሰብኩ ማፈንጠርያውን /link/ ከፈትኩት  ከፍቸ ሳየው ለካ እነእንቶኔ  ናቸው እነርሱ እንኳ ግራ የገባቸው በኦርቶዶከስ ማሊያ ለነ ማርቲን ሉተር የሚጫወቱት  እሰይ አወቃችኋቸው ? ከዚያውላችሁ እኔም ተረጋጋሁ ። “እሰይ ኤፍሬም እሸቴ አረፈ” አልኩ ደግሞ ዳግም እርሱ የጠቅላይ ሚንስትሩ መንፈስ  ባለው አልስማማም ብሎ ከመጻፍ ስንት ነገር የሚሰራበትን ሰዓቱን ከማባከን ተረፈ።  / ለነዚህ የጥቃቅን ጥቃቅኖች  እኛ ጥቃቅኖች እንበቃለን ብየ ነው / ።

Saturday, December 22, 2012

መንግስት በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ በይፋ ጣልቃ ገባ

ዋና ዋና ጉዳዮች:-
  • አስመራጭ ኮሚቴው እስከ ጥር 18 ድረስ እጩዎችን እንዲያቀርብ ሲኖዶሱ አዟል፡፡
  • የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ቅ/ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ ከመሠየም እንዲታገሥ ጠየቁ::
  • የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ አራተኛው ፓትርያሪክ ስለሚመለሱት ኹኔታ ምልአተ ጉባኤው እንዲመክር ጠይቀዋል:: 
  • የልኡካኑ አብሮ መቀደስ በአንዳንድ አባቶች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል ተብሏል
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መንግሥት የፓትርያሪክ ምርጫውን የሚከታተል ባለሥልጣን መመደቡ በግልጽ ተቃውመውታል::
  • የአስመራጭ ኮሚቴውን መቋቋም የተቃወሙ አባቶች በከባድ ጫና ሥር ወድቀዋል::
  • አቡነ ማቴዎስ ከሲኖዶሱ ራሳቸውን አግልለዋል
  • የአስመራጭ የኮሚቴው አባል አቡነ ቄርሎስ ‹‹አልሠራም፤ አላምንበትም›› በሚል ራሳቸውን አግልለዋል::
  • የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ አቡነ ሕዝቅኤል ‹‹መግለጫ አልሰጥም›› በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል:: 
 መንግሥት ‹‹ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ›› በሚል ከፍተኛ ባለሥልጣኑን የመደበው ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡ ባለሥልጣኑ አቶ ትእዛዙ ደሳለኝ የሚባሉ ሲኾኑ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ይኹንና አቶ ትእዛዙ በዛሬው የመንበረ ፓትርያሪክ ውሏቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማግባባት ያደረጉት ጥረት የሠመረላቸው አይመስልም፤ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ በምርጫው ሂደት አይሰናከልም፤ ወደፊትም ሊካሄድ የሚችል ነው፤›› ቢሉም የሰማቸው ባለመኖሩ ይህንኑ ለበላይ አካል አስታውቀዋል ተብሏል፡፡ የእርሳቸውን ሪፖርት ተከትሎ ከእርሳቸው ከፍ ያሉ ባለሥልጣን በአቋማቸው የጸኑትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዛሬውኑ ማምሻውን ወይ ባሉበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አልያም ወደ ውጭ አስጠርቶ የማወያየት፣ የማስፈራራት፣ የማስጠንቀቅ አካሄድ ሳይኖር እንደማይቀር ተገምቷል፡፡ ከዚህ በባሰ የመንግስት ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ ምናልባትም በእስልምናው የታየው ሁኔታ በኦርቶዶክሱም ይከሰታል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይሆነል፡፡
መንግስት በእኛ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያቁም!!!!!!!!  መልእክታችን ነው፡፡

Friday, December 21, 2012

የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በውሳኔያቸው ተከፋፍለዋል

የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በውሳኔያቸው ተከፋፍለዋል
  •     የዕርቀ ሰላሙ ልኡካን በሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ የወሰዱት አቋም በመንሥኤነት ተጠቅሷል
  •     ‹‹ይኾናል ብለን አንጠብቅም፤ ኾኖ ከተገኘ በጣም እንቃወማለን›› /አቡነ አትናቴዎስ/
  •     ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከሲኖዶሱ ስብሰባና ውሳኔዎች ራሳቸውን አግልለዋል
  •     ዋና ጸሐፊው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አልኾኑም

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ትላንት፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አጽድቆ ምርጫውን የሚያስፈጽም 13 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ የኮሚቴው አባላት ከቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መምሪያ ሓላፊዎች፣ ከገዳማት አበምኔቶች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራት እና ከታዋቂ ምእመናን ‹‹የተውጣጡ ናቸው›› ተብሏል፡፡
የኮሚቴውን መቋቋም ተከትሎ ለዕርቀ ሰላሙ ንግግሩ ወደ አሜሪካ የተላኩትና በቅ/ሲኖዶሱ የተሰጣቸውን ተጨማሪ የሰላም ተልእኮ ለመፈጸም በዚያው ከሚገኙት ሦስት ብፁዓን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ÷ ትላንት ሌሊቱን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ጋራ በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በደብዳቤ መላካቸውንና በዳላሱ የሰላም ጉባኤ በወጣው የጋራ መግለጫ መሠረት ዕርቀ ሰላሙን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ለመቆጠብ ተስማምተው መፈረማቸውን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው÷ ቅ/ሲኖዶሱ የልኡኩን ሪፖርት ሳያዳምጥና የሎሳንጀለሱን የሰላም ጉባኤ ውጤት ሳይጠብቅ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡

Thursday, December 20, 2012

የዕርቀ ሰላሙን በር የዘጋ ውሳኔ


ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ ሠየመ - ቤተ ክርስቲያን በከፋ የመለያየት አደጋ ውስጥ ትገኛለች !!

  • የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቁን አጽድቆ ተፈራርሟል
  • ጠቅላላ ሂደቱ በመንግሥትና የመንግሥትን አቋም በሚደገፉ ጳጳሳት ቁጥጥር ሥር ገብቷል
  • ለዕርቀ ሰላም ንግግር ወደ አሜሪካ ያመሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ‹‹መግለጫ እንሰጣለን፤ ከሲኖዶሱ ጋራ አብረን አንቀጥልም፤ ወደ ገዳም እንገባለን›› ማለታቸው እየተሰማ ነው
ከታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት ያህል በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ሲወያይ የቆየው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ የሕጉን ረቂቅ አሻሽሎ አጽድቋል፤ ለዕርቀ ሰላሙ ዕንቅፋት እንዳይኾን ትዕግሥት እንዲደረግበት ብርቱ ክርክር የተካሄደበትን አስመራጭ ኮሚቴም ሠይሟል፤ እንደ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ያሉት አባቶች ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸው እየተነገረ ነው፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ኾነው የተመረጡት ከሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ አቡነ ቄርሎስ፣ አቡነ እስጢፋኖስ እና አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መመሪያ ሓላፊዎች ውስጥ ደግሞ የዕቅድና ልማት መምሪያ ሓላፊው ሊቀ ትጉሃን ኀይለ ጊዮርጊስ ዳኜ፣ የሰበካ ጉባኤው መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ይገኙበታል፡፡ አቶ ባያብል ሙላቴ (ከማኅበረ ቅዱሳን)፣ ከታዋቂ ምእመናን መካከል ደግሞ እንደ አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ (ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት) የመሳሰሉት ሰዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡
የሲኖዶሱን ውሳኔዎች በተመለከተ በነገው ዕለት በጽሑፍ የተዘጋጀ መግለጫ እንደሚወጣ የተመለከተ ሲኾን አጠቃላይ ሂደቱ የዕርቀ ሰላሙን በር የዘጋ፣ ቤተ ክርስቲያን ወደ ከፋ የመከፋፈል አደጋ ውስጥ እንደሚከታት ተገልጧል፡፡ ለዚህም ሲኖዶሱ ዛሬ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ አስመራጭ ኮሚቴ የመሠየሙ ዜና ወደ አሜሪካ በተላኩትና በቅ/ሲኖዶሱ የተሰጧቸውን ተጨማሪ ተግባራት ለመፈጸም በዚያው በሚገኙት ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ እንደተሰማ የተወሰደው ጠንካራ አቋም በማስረጃነት ተጠቅሷል፡፡