Wednesday, October 19, 2011

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 2ኛ ቀን ሪፖርታዥ


ጉባኤው ቤተ ክህነቱ ቃለ ዐዋዲውን ማስከበር እንዳልቻለ አመለከተ
· የቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ/ሕግ፣ ደንብ/ እና የኦዲት ሪፖርት ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ዕውቅና መነፈጉ በመንግሥት አካላት ፊት የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ ዕንቅፋት ፈጥሯል፤
· “የመንበረ ፓትርያርኩ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዘንድ ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል” (የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተሳታፊ)
· “. . . ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ  በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት ቃለ ዐዋዲው በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አለው፤ [ነገር ግን] የሕግ አገልግሎቱ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁልጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” (ብፁዕ አቡነ ናትናኤል)
· “. . . አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ/ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም እያሉ በተደጋጋሚ ይነግሩናል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፡፡. . . ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም መተኛት በዝቷል፡፡ ይህ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ አቋሙን ማሳወቅ ይኖርበታል፤ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳ ተነጋግሮ መወሰን አለበት፡፡” (ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ)
· “ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን፡፡” (ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ)
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 20/2011)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምእመናን አንድነት በሰበካ ጉባኤ ተደራጅታ በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በአገልግሎት እና በምጣኔ ሀብት በኩል በራሷ ሕግና ሥርዓት በመመራት እንድትሠራ ለማድረግ ታስቦ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ያወጣው ቃለ ዐዋዲ ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ሀብቷን እና ንብረቷን ለማስጠበቅ ያለው ኀይል፣ በፍትሕ ተቋማት ዘንድ የሚሰጠው ዕውቅና እና ተቀባይነት እያጸጸ/ እያነሰ በመምጣቱ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ፡፡ ለቃለ ዐዋዲው ሕግ እና ደንብ ዕውቅና እና ተቀባይነት ማጣት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት ክፍል ሞያዊ አቅም ማጣት ቀዳሚ ሓላፊነቱን እንደሚወስድ የተመለከተ ቢሆንም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት “የድሮው ይበቃችኋል” በሚል መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ስለ መሆናቸው የሚደነግገውን አንቀጽ እንዳሻቸው እየተረጎሙ ለቃለ ዐዋዲው ተፈጻሚነት ዕንቅፋት በመፍጠር ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያጠቁ ተነግሯል፡፡


ረቡዕ ጥቅምት ስምንት፣ 2004 ዓ.ም ሁለተኛ ቀኑን በያዘው 30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ላይ እየቀረቡ በሚገኙት የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት ከደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ተወክለው የመጡ ተሳታፊ፣ “የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ የመዘበሩ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በኦዲት ምርመራ የተረጋገጠውን ማስረጃ ለፍርድ ቤት እናቀርባለን፤ ነገር ግን አይቀበሉንም፤ እንዲያውም የሙያ ማረጋገጫ እና የሥራ ፈቃድ ባላቸው የተሠራ ኦዲት ካልሆነ በቀር የመንበረ ፓትርያርክ እና የሀገረ ስብከት ኦዲተሮች በመንግሥት ዕውቅና እና ተቀባይነት እንደሌላቸው ይነግሩናል፡፡ በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮ ቢወስንበት” በማለት ጠይቀዋል፡፡


ለተወካዩ ጥያቄ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ “ኦዲት ተደርጎ ጥፋት ከተገኘ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ በሕጋችን መሠረት ኦዲተር የሚላከው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች በመንግሥት ፍ/ቤቶች ዕውቅና አላቸው” ቢሉም የሰጡት ምላሽ በጥያቄው በተጨባጭ ከተጠቀሰው ችግር አኳያ በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡


ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተወካዩ ጥያቄያቸውን እንዲያብራሩ ዳግመኛ በሰጧቸው ዕድል፣ ቤተ ክርስቲያን “ኦዲተር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቻ ነው የሚመደበው” የሚል ሕግ የላትም፤ ሕጉ ቢኖርም ሁሉንም አህጉረ ስብከት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ኦዲተር ብቻ ለማዳረስ አይቻልም፤ የቤተ ክርስቲያናችን ኦዲተሮች በሕግ ዕውቅና እንደሌላቸው በተግባር አረጋግጠናል፤ እዚህ አዳራሽ ተቀምጠን ዕውቅና አለን በማለት ብቻ የሚሆን አይደለም፤ በየቦታው ስንሄድ የኦዲት ሰነዳችን ውድቅ እየሆነ ነው ያለው፤ ሊታሰብበት ይገባል” በማለት ጥያቄያቸውን አጠናክረዋል፡፡


የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሕጋዊ መብት እና ግዴታ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ እንዲሠራበት በፍትሐ ብሔሩ ሕግ በተደነገገው መሠረት የቁጥጥር /ኦዲት/ አገልግሎቱ የተመሠረተበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ደንብ /ቃለ ዐዋዲው/ በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው አስረድተዋል፤ እንደ አብነትም በአንድ ወቅት የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንደ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይመዝገብ ተብሎ በነበረበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጠየቁት ማብራሪያ መሠረት ኮሚሽኑ በተቋማዊ ሕጋችን፣ ደንባችንና መመሪያችን እንደሚመራ /እንደሚታይ መገለጹን አስታውሰዋል፡፡


የተወካዩ ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ መመለስ እንደሚገባው ያስረገጡት ብፁዕነታቸው፣ ትኩረት ያደረጉት በቤተ ክህነቱ አዘውትሮ ይነሣል ባሉት የአገልጋዮች እና ሠራተኞች አስተዳደራዊ በደል ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ “ሠራተኞች በደል ደረሰብን ብለው በፍርድ ቤት አስተዳደሩን እየከሰሱ ገንዘብ ወጥቶ ይሰጥ እየተባለ ይሰጣቸዋል፡፡ የሕግ አገልግሎት ክፍሉ ጠበቆቻችን የዕውቀት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ሁል ጊዜ መረታት ነው ሥራቸው!!” በማለት በአስፈጻሚው አካል በኩል የሚታየውን የሙያዊ አቅም ክፍተት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡


ብፁዕነታቸው እንዲህ ቢሉም ለጉባኤው በተሰራጨው የ”ዐዋጅ ነጋሪ” መጽሔት በቀረበው የሕግ አገልግሎቱ የሥራ አፈጻጸም ግን ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በሥራ ነገር ክርክሮችና ይግባኞች ከ34 ጉዳዮች ከግማሽ በላዩን አስፈርዶ በተፈረዱበትም ይግባኝ እንደጠየቀ ሰፍሯል፡፡


የሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በበኩላቸው ዋናው ጉዳይ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እንደተባለው ሕጋችንን አለማስከበራችን መሆኑን በራሳቸው ልምድ አስረድተዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 85/65 ተፈቅዶ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም ታትሞ የወጣውን ቃለ ዐዋዲ በመያዝ፣ “አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋችሁ /ቃለ ዐዋዲው/ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ የወጣ ስለሆነ አንቀበልም” እያሉ በተደጋጋሚ እንደሚነግሯቸው ብፁዕነታቸው ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡


ብፁዕነታቸው አክለውም፣ “ይሁንና በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ሦስት አንቀጽ አምስት የሰፈረውን በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና 399 የተደነገገውን ጠቅሰን ስናስረዳቸው ቀናዎቹ ሲቀበሉን ሌሎቹ ግን ‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› በሚለው ይከራከሩናል፤ አንዳንዶቹም ‹የድሮው ይበቃችኋል› ይሉናል፤ ያሾፉብናል፤ ይሥቁብናል፤ ይሣለቁብናል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕግ የለንም፤ በጅማው ጉዳይ ስላለፈው አደጋ ርምጃ እንወስዳለን ተብሎ ትንኮሳው ግን እስከ አሁን አልቆመምም፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ከሥሯ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች በዝተዋል፤ የእኛም እንቅልፍ በዝቷል” ሲሉ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ በጋራ መክሮ አቋም እንዲይዝበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስም በአጀንዳው አካትቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍበት አሳስበዋል፡፡


በሌላ በኩል ከዚህ ጥያቄ ጋራ በተከታታይ ከቀረቡት ውስጥ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት ተሠርተዋል ተብለው የሚቀርቡ ተግባራት በእውነትም ስለ መኖራቸው ማረጋገጥ ስለሚቻልበት ሥርዓት፣ ስለ ሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በምዕራብ ጎጃም - ባሕር ዳር የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ እንደሌለ ተደርጎ በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት መነገሩ ይገኝበታል፡፡


የምዕራብ ጎጃም ሀ/ስብከት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ በሀ/ስብከቱ እንደሌለ ያቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ በማኅበረ ቅዱሳን እና በአርማጌዶን ቪሲዲዎች ላይ በፕሮቴስታንቶች አዳራሽ ሲጨፍሩ የሚታዩት ‹የተቀሰጡ መሪጌቶች› ከባሕርዳር አካባቢ መሆናቸውን በማስታወስ ይልቁንም አካባቢያዊ ሁኔታው ለጠቅላላው የአማራ ክልል የተሐድሶ መናፍቃን መፈልፈያ እንዳይሆን ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተገልጧል፡፡


ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም በሰጡት አጫጭር ምላሽ፣ “ቤተ ክርስቲያናችን በማኅበራት ስም እየተወረረች ነው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ያልገባቸውና ከዚህ ዓለም ትዝታ ያልተላቀቁ ናቸው፤ ማኅበራት በዘፈቀደ ሳይሆን በቋሚ ሲኖዶሱ ተጠንቶ ነው ዕውቅና የሚሰጣቸው፤ በቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ መላእክት ስም የተቋቋሙ ማኅበራት/ ሰንበቴዎች ከጥንትም ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ ተቆራኝተው የነበሩ ናቸው፡፡ በስብከተ ወንጌል ስም ላሉት ግን ተጠንተው በማእከል ደረጃ ዕውቅና ሊሰጣቸው ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በቃለ ዐዋዲው ዙሪያ የተደረገውን ውይይት ሲያጠቃልሉም “….ቃለ ዐዋዲው ተቀባይነት ከሌለው በቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አድርገን ተወያይተንበት እንዲሻሻልና ይኸውም በፓርላማው እንዲታወቅ እናደርጋለን፤ አለበለዚያ ጨለማ ነው የሚጠብቀን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡


ከሁለቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አስተያየት በኋላ በብርቱ የተነቃቃ ከሚመስለው ጉባኤተኛ በርካታ እጆች ወጥተው ቢታዩም ውይይቱ በተጀመረው መልኩ ነገ ጠዋት እንደሚቀጥል በመግለጽ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ከቀትር በኋላ ከተደረገው ውይይት ቀደም ሲል የ21 አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፡- መልካም አስተዳደርን/ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን/ ለማስፈን በሀገረ ስብከት እና በወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በተሰጡ ሥልጠናዎች፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ማኅበራትን በመከላከል፣ ኢ-ጥሙቃንን እና መናፍቃንን አስተምሮ እና አሳምኖ በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በማጥመቅ፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ይዞታ በማስከበር፣ አብነት ት/ቤቶችንንና  መምህራንን በገቢ በመደጎም እና በማጠናከር፣ እጓለ ሙታንንና የሕግ ታራሚ የሆኑ ወላጆች ያሏቸውን ልጆች በመከባከብ ላይ ያተኮረ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡


ከሪፖርቶቹ ይዘት ውስጥ፦
v የከፋ ቦንጋ ሀ/ስብከት ውስጥ በተቀሰቀሰ ሁከት በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ላይ ጥይት እስከ መተኮስ መደረሱ፣
v በአፋር ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለራስ አገዝ ልማት በሚሠሯቸው ሥራዎች ግብር መጠየቃቸው፣
v በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ብር 800,000 የፈጀ የአብነት ት/ቤት ተከፍቶ ዲያቆናትና ካህናት ሠልጥነው እየወጡ ፍሬውን ማየት መጀመሩ፣ በሰሜን ሸዋ በብር 23 ሚሊዮን ወጭ ዘመናዊ ት/ቤት እና የአብነት ት/ቤት ያቀናጀ ተቋም መከፈቱና በተለይም ለደቡቡ የሀገራችን ክፍል መጋቢ የሆኑ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ መገለጹ፣
v በሶማሌ ሀ/ስብከት የሊቀ ጳጳሱ ቶሎ ቶሎ መቀያየር ሀገረ ስብከቱን እያዳከመው መሆኑ፣
v በአንጻሩ የአዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሠራተኞች ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዳይዛወሩባቸው መጠየቃቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን by Deje Selam

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርታዥ

  • ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቤተ ክርስቲያን ወጥ/ማእከላዊ/ የበጀት አስተዳደር በምትከተልበት አሠራር ላይ ጉባኤው ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥሪ አድርገዋል
  • . የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ይሻሻላል፤ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በዕቅድ መሥራት እንዲለመድ ይደረጋል
  • . በ2004 ዓ.ም ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይታተማል፤ በ2000 ዓ.ም በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል አቀማመጥ በሆሄያት አገባብ እና በትርጉም ስልቶች ረገድ የክለሳ ምልክት ተደርጓል፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላትን የያዘ የሆሄያት አገባብ መጽሐፍ ይዘጋጃል
  • . ጉባኤው ለውይይት እና ጥያቄ በተፈቀደው የአንድ ሰዓት ጊዜ አንዳችም ሐሳብ ሳያነሣ አህጉረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት የ35% ፈሰስ /የፐርሰንት ገቢ/ ላይ ያተኮሩ ሪፖርቶችን መስማቱን ቀጥሏል
  • . ያረፉት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ታስበዋል
  • . ‹‹ስማቸውን የጠቀስናቸው ብፁዓን አባቶቻችን አልፈው እኛ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍና ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ቀርተናል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ/
  • . የመናፍቃን እና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ መምጣቱ፣ ፕሮቴስታንቶች የሚፈጥሩት ትንኮሳና የባህል ወረራ፤ በጉራጌ ዞን እስላሞች በሐሰት ‹‹ክርስቲያኖች ስምንት መስጊዶችን አቃጠሉብን›› ብለው ለተወሰነ ጊዜ ክርስቲያኖችን ማሳሰራቸው፣ የቦታ ይገባናል ጥያቄ በማንሣት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ መሞከራቸው፤ በጅማ ‹‹እምነታችሁን ለውጡ›› እያሉ ምእመናንን ማወካቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሦስት አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ሰፈር በሙርሲ ብሔረሰብ በመቃጠሉ ምእመናን አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው፤ በሰሜን ወሎ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ለማክሸፍ ወደ ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ አራት አገልጋዮች በመኪና አደጋ መሞታቸው፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባር ጽላትን በፎርጅድ የመለወጥ ተንኮልና በሶዶ ወረዳ16 አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው፤ በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ 130 ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሰው ሠራሽ አደጋ መቃጠሉ፤ የሕገ ወጥ ማኅበራት መብዛት እና በዘፈቀደ መንቀሳቀስ፣ በተለይም በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሕዝቡን በየቋንቋው የሚያስተምረው ሰባኬ ወንጌል አለመገኘት፣ በአዲስ አበባ የሕገ ወጥ ሰባክያን እንቅስቃሴ፣ በሊቃውንት ያልተመረመሩ መጻሕፍትና ካሴቶች በየዐውደ ምሕረቱ ሲሸጡ መታየታቸው እና 283 ቀሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ባለመመለሳቸው ተጨማሪ ገቢ መታጣቱ በበጀት ዓመቱ ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ተካቷል
  • . ለጉባኤው ከወትሮው በተለየ ከብር 600,000 በላይ ወጪ ተደርጓል
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 7/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 18/2011)፦ 
በየዓመቱ ጥቅምት ወር የሚካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ጠዋት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ባደረሱት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ከ48 አህጉረ ስብከት/ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ/ ከእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ስድስት በመሆን ተወክለው የመጡ ከ300 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት፣ ‹‹ስማቸውን በጸሎት የጠራናቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አልፈው እኛ የቀረነው ሓላፊነታችንን እንድንወጣ ነው፡፡ እኛ ከእነርሱ የተሻልን ሆነን ሳይሆን ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን መልእክት እንድናስተላልፍ በዚህ ቦታ ተሰልፈናል፡፡ ብዙዎቻችን ከሊቃውንቶቻችን ስንማር ረጅም ዘመን ቆይተናል፡፡ ብዙ ልምድ አካብተናል፡፡ መማራችን፣ ማወቃችን፣ ረጅም ጊዜ መቆየታችን ከሥራ ከተለየ ጥቅም እንደሌለው አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን እንድንሠራ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ምእመኑም ሆነ ትውልዱ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ በደል፣ ፍርሃት እንዳይደርስባቸው እንድንጠብቃቸው ለእኔና እዚህ ላለነው ብፁዓን አባቶች ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ‹በጎቼን ጠብቁ› ተብሎ ከአባታችን ቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ 

እግዚአብሔር እኔ እበልጣለሁ የሚል ሥርዐተ አልበኝነትን አይወድም፡፡ ሰዎችን ከክፉ ነገር ለማዳን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ በሓላፊነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በተጠያቂነት ስሜት መፈጸም ይገባል፡፡ የእኔና የእናንተ ሥራ ሌላ አይደለም፤ በየአካባቢው የሚነሡ ጩኸቶችንና እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር ነው፡፡ በየአካባቢያችን ት/ቤት ተሠርቷል ወይ? ወጣት ልጆቻችን ት/ቤት ገብተዋል ወይ? ብለን ማሰብ፣ መጨነቅ፣ ኮስተር ብለን ሥራችንን በሓላፊነት ስሜት እንድንሠራ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡



በመብራት መቋረጥ ምክንያት ካጠረው የቅዱስነታቸው መልእክት በመቀጠል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የልብ ድካም ሕመም እንዳለባቸው በመግለጽ እስከ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ ያለውን የሥራ ክንውን ሪፖርት ብቻ ነው ለማሰማት የቻሉት፡፡ ቀሪው የሪፖርቱ ክፍል ከ15 ደቂቃ ጫን ያለ ‹‹የሻይ ዕረፍት›› በኋላ በጽ/ቤቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ነበር የቀረበው፡፡

ከ48ቱ አህጉረ ስብከት በአጥቢያ ደረጃ ብር 451,996,682.53፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ ብር 90,692,854.51፣ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ብር 43,877,275.34፣ ገቢ ከሚያስገቡ ስምንት አምራች ድርጅቶች እና ስድስት መምሪያዎች ብር 90,766,002.09 በአጠቃላይ በ2003 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን የበጀት ዓመት ብር 542,762,684.62 ገቢ መገኘቱን ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ዝርዝር ላይ አመልክተዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ኀይል እንደ አበው ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን በአንድነት ቢያዝና እንደ አስፈላጊነቱ በየደረጃው ለሁሉም ቢተነተን/ቢበጀት/ ችግራችን ሁሉ ተቃሎ፣ አገልግሎታችን ሠምሮ ምንኛ ባማረብን ነበር?›› ሲሉ የጠየቁት ብፁዕነታቸው እስከ አሁን ድረስ ማዕዳችን ‹‹ከአንድ መሶብ እየወጣ ተሠርቶ በአንድነትና በበረከት ልንቋደሰው አለመቻላችን›› እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ማጠቃለያም አጠቃላይ ጉባኤው ከተጀመረ 30 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ግባችን በቂ ነው የሚባል ባለመሆኑ ገና እጅን አጣጥፎ የሚያስቀምጥ አለመሆኑን በማስታወስ፣ ‹‹…ይህ ዐቢይ እና ወሳኝ ጉባኤ በብርሃነ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ በጥልቅ መክሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር እንዲቃና፣ አገልግሎታችን እንዲሟላ፣ እኩልነት እንዲሰፍን የበጀት ማእላዊነት እንዲኖር በቅን ልቡና አስቦበት ጥናታዊ ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ አክብሮት በተሞላ ልቡና አሳስባለሁ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስለተከናወነው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንዳተተው፣ የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ 26,187 ሐዲስ አማንያን በወንጌል ትምህርት በማመን ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ገብተዋል፤ ወደ ሌላ እምነት ሄደው የነበሩ 241 ጥንተ ኦርቶዶክሳውያን ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነዋል፡፡ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰባክያን እየተዘዋወሩ እንዲሰብኩ ከመደረጉም በላይ በብፁዓን አባቶች እና ሰባክያነ ወንጌል በየወረዳውና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ሥምሪቶች ተደርገዋል፤ ታላላቅ ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡ በየማሠልጠኛው ለሰለጠኑ ካህናት፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት እና ለንስሐ አባቶች በሠለጠኑ መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በማእከል ታውቀው ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና ማኅበራት እንሰብካለን እያሉ ምእመናንን ግራ እንዳያጋቡና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያፋልሱ ጥበቃ፣ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል፡፡ ‹‹እምነታችሁን ትታችሁ የእኛን እምነት ተከተሉ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ የተገኙ መናፍቃን ተከሰው በገንዘብና በእስራት ተቀጥተዋል፡፡

በአንጻሩ የተለያየ ቋንቋ የሚናገረውን ወገን በሚሰማው ቋንቋ የሚያስተምረው በቂ የመምህራን ቁጥር አለመኖሩ፣ ከሦስቱም ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ደቀ መዛሙርት በየዓመቱ ቢመደቡም በተመደቡበት አለመገኘትና የበጀታቸው አብሮ መቅረት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎ የተጋበዙ ‹ሰባክያን› ከብር 30,000 - 40,000 ድረስ ክፍያ ካልተከፈለን እያሉ በአገልግሎት ላይ አለመገኘታቸው፣ የመናፍቃንና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየሰፋ መምጣትና የስድስት ካህናት እና የ109 ምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መግባት፣ እንደ ሰሜን ወሎ እና መተከል ባሉት አህጉረ ስብከት መናፍቃኑ ያስከዷቸውን ካህናት በማሰለፍ የሥራ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ከዚህም አኳያ በተያዘው የበጀት ዓመት የአብነት መምህራንንና የካህናት ማሠልጠኛዎችን ለማጠናከር/በዚህ ዓመት በተለይም በሰሜን ሸዋ መምህራን ከብር 400 - 2000 በሚደርስ ደመወዝ እንደተቀጠሩት፣ ለአብነት መምህራን የጡረታ ዋስትና እንደተጠበቀላቸው/፣ ሰባክያነ ወንጌልን በማብዛት የተለያየ ቋንቋ የሚሰማውን ኅብረተሰብ ለማስተማርና ለማስተባበር የየአካባቢውን ተወላጆች በየቋንቋቸው በማሠልጠን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ እና ነባሮቹም እንዲታደሱ/ከዚህም መካከል በጆርዳን በነጻ በተገኘው 3000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ በኢየሩሳሌም ገዳም የሚሠራውን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ/፣ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች እንዲከበሩ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር/ካርታ/ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ቃለ ዐዋዲውን ለማሻሻልና የማጠናከሪያ ሥምሪት ለማካሄድ ዕቅድ ስለ መያዙ፣ በአጠቃላይ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ለማብዛትና ለመጠበቅ፣ በምእመናን አስተዋፅኦና በልማት ውጤት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ፣ ማእከላዊነትን የጠበቀ መልካም አስተዳደር ከላይ እስከ ታች በማስፈን የካህናትን ኑሮ ለማሻሻልና ድህነትን ለማጥፋት መታቀዱ በብፁዕነታቸው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡

ለዚሁ ጉባኤ የተዘጋጀው ‹‹ዐዋጅ ነጋሪ›› የተሰኘው የሰበካ ጉባኤ መመሪያ መጽሔት በአራተኛ ዓመት ቁጥር ሰባት እትሙ፣ 48ቱ አህጉረ ስብከት እያንዳንዳቸው ያሏቸውን የምእመናን ብዛት፣ የገዳማት እና አድባራት ብዛት፤ በስብከተ ወንጌል፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ ገዳማትን እና ሰንበት ት/ቤቶችን በማጠናከር፣ በራስ አገዝ ልማት፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ በተደረጉ አስተዋፅኦዎችና ሌሎችም ተግባራት ዙሪያ የተፈጸሙ ክንዋኔዎችን በተመለከተ የተላኩ ሪፖርቶች በአሕፅሮት ተካተውበት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰራጭቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ማሽኖች በእርጅና ምክንያት ከሚሠሩበት የሚቆሙበት ጊዜ የበለጠ እንደሆነና ለእድሳትም ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይኸው መጽሔትም በሌላ የግል ማተሚያ ቤት መታተሙ ታውቋል፡፡ ለጉባኤው ዝግጅት ቅርበት ያላቸው የቤተ ክህነቱ ምንጮች እንዳስረዱት፣ ለመጽሔቱ ኅትመት ፣ በጉባኤው ላይ ይታያል ተብሎ ለሚጠበቀው የፓትርያርኩ ከ1984 - 2003 ዓ.ም መዋዕለ ዜና የሚዘክር ዶክመንታሪ ፊልም ዝግጅት፣ ለጉባኤው አባላት አበልና መስተንግዶ በሚል የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ሁለት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አባሎች የሚገኙበት የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ብር 600,000 ወጪ አድርጓል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የጉባኤው ዝግጅት ወጭ ግን ከብር 100,000 አይበልጥም ነበር - እንደ ምንጮቹ መረጃ፡፡

የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በንባብ ቀርቦ ከተሰማ በኋላ በቀጥታ ወደ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ሽግግር ተደርጎ፣ በደቡብ ሱዳን ባለባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ሳቢያ ቅድሚያ የተሰጣቸው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀ/ስብከት የሆነው የጋምቤላ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተመጠነ ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በመጽሔቱ በተገለጸው ሪፖርት መሠረት በሀ/ስብከቱ 39 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤ 327 ካህናት በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፤ የምእመናኑ ቁጥር አልተገለጸም፤ በቅኔ፣ በአቋቋም፣ በቅዳሴ እና በመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 47 የክልሉ ተወላጆች በዲቁና እና ቅስናም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት አምነው ተጠምቀዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም ሀ/ስብከቱ ካስገባው ብር 1,176,115.50 ውስጥ የመንበረ ፓትርያርክ 35 በመቶ ብር 82,796.91 ገቢ ማድረጉ ተገልጧል፡፡

በዚህ መልኩ የጅማ፣ የመቐለ፣ የኢሉ አባቦራ፣ ድሬዳዋ፣ ጋሞጎፋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ባሌ፣ ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች በተከታታይ ሪፖርታቸው ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ የሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ፣ የጅማ እና የኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት ከአክራሪ እስልምና የተነሣ ያለባቸውን ተግዳሮት ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋው ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ገሪማን ‹‹ንዑድ፣ ክቡር›› እያሉ ደጋግመው በማወደሳቸው በጉባኤተኛው ተሥቆባቸዋል፡፡


በአህጉረ ስብከቱ የሪፖርት አቀራረብ ሥራ አስኪያጆቹ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በ‹ዐቃቤ ሰዓትነት› በሰጡትና በጥብቅ በሚቆጣጠሩት ከ5 - 10 ደቂቃ ባለው ጊዜ ሪፖርታቸውን በችኮላ ያቀርባሉ፡፡ ከዚሁም ላይ እንደ ወትሮው ሁሉ ለመንበረ ፓትርያርክ በሚደረገው የዘመኑ የ35 ከመቶ ፈሰስ ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የሰሰሱ መጠን የአህጉረ ስብከቱ ጥንካሬ እና ዋናው የሥራ ፍሬያቸው መለኪያ መስሎ ታይቷል፡፡

ከቀትር በኋላ ከ10፡30 - 11፡25 ባለው ጊዜ በቀረቡት ሪፖርቶች፣ (በተለይም የሰበካ ጉባኤ እና የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ) ላይ ውይይት እና ጥያቄ እንደሚኖር በተገለጸው መሠረት መድረኩ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለተሰብሳቢው ክፍት መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም አንዳችም ጥያቄ ይሁን ውይይት ሳይነሣ ቀርቷል፡፡ የፍርሃት ይሁን የፍላጎት ማጣት? ብለው ሲጨነቁ ለነበሩት በጉባኤው የደጀ ሰላም ታዛቢዎች ምላሽ የሰጠው ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ጥያቄ እና አስተያየት ከሌለ ሪፖርቱ ይቀጥል›› ብለው ከመናገራቸው ቤቱ በተሰብሳቢዎቹ ለየት ያለ የጭብጨባ ዘይቤ የተናጋበት ሁኔታ ነው - አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡

በጉባኤው ላይ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የየራሳቸው ሪፖርት የሚያቀርቡበት ቀን ያላቸው ሲሆን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ዛሬ ያቀረቡትን የማእከላዊ ጽ/ቤቱን ሪፖርት ሙሉ ቃልና የ48ቱን አህጉረ ስብከት የተጨመቀ ሪፖርት ‹‹ቃለ ዐዋዲ›› መጽሔት እንዳገኘነው ከዚህ በታች አቅርበንላችኋል፡፡

30ኛው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ጥቅምት 12 ቀን ለሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካስተላለፉትና በመጽሔቱ ላይ ከታተመው መልእክታቸው የሚከተለውን ይገኝበታል፡- ‹‹ይህን መሰል ጉባኤ ስናካሂድ የአሁኑ ጉባኤያችን ለሠላሳኛ ጊዜ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው፡፡ በየጉባኤያቱ የሚዘጋጁ አርእስተ ጉዳዮችና የሚወጡ ዕቅዶች፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ እየቀረቡ ከተመከረባቸው በኋላ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ስብሰባችን የጉባኤውን ሪፖርት አንብበን የምንለያይበት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዕቅድ የምናቅድበትና የምንወያይበት ስብሰባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡››
እውን ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራስ እስከ እግሯ በአንድ አዳራሽ የተገኘችበት ስብሰባ በሆነውም ባልሆነውም የሪፖርት ጋጋታ ከመጨናነቅ፣ በረባ ባልረባው የውዳሴ ዝናም ከማጭበጨብ፣ ጫን ባለ የእህል ውኃ ግብዣ ከመደንዘዝ ተርፎ፡- የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን በሚያሤሩት የውስጥ አደጋ፣ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በደቀኑብን የውጭ ስጋት፣ እንደተባለው ጥናትና ሥር ነቀል ርምጃ በሚሻው የፋይናንስ፣ የሰው ኀይል እና የሌሎች ሀብቶች አስተዳደሯና ልማታዊ ክንውኗ ዙሪያ ይመክር ይሆን? ከቀደመውና ከዛሬው ውሎ አኳያ የሚሆን አይመስልም፡፡ ርግጡን ግን በጉባኤው የአምስት ቀናት ቆይታ የምናየው ይሆናል፡፡ 
by deje selam

Thursday, September 8, 2011

የሐረሩ ስልጠና

በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • ገበየሁ ይስማው ሥልጠናው መካሄዱን አመነ የሠልጣኖች ምልመላ ሂደትን አብራርቷል
  • የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ለጉባኤ ከአዲስ አበባ ሳባኪ እንዳይጠራ ወሰነ
  • ማኅበረ ቅዱሳን በተሐድሶ ሰራዊትነት የሰለጠነ አባል የለኝም አለ
  • ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፈሉ
    ገበየሁ ይስማው
    ገበየሁ ይስማው
በቅርቡ በሐረር ከተማ በሉተራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተሐድሶ ሰራዊትነት ዙርያ የተሰጠው ሥልጠና ልዩ ልዩ ውጠየቶችን እያስከተለ እንደሆነ የምስራቅ ኢትዮጵያ የገብር ኄር መንጮች ገለጹ፡፡
ሐረር
የሐረር ከተማ እንዳንድ ምዕመናን ግብረ ተሐድሶን በተመለከተ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እነዚህ ምዕመናን ‹‹በሌሎች አህጉረ ስብከቶች የታገዱ መምህራን ለምን ሐረር ላይ እንዲያስተምሩ ይፈቀድላቸዋል? በከተማው እየተፈጸመ ባለው ግብረ ተሐድሶ ላይ ሀገረ ስብከቱ አፋጣኝ እርምጃ ለምን አይወስድም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ እና በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ያሬድ ሰባሳቢነት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ቀን በክብረ በዓላት ወቅት በሀገረ ስብከቱ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር አንድም ‹‹መምህር›› ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከአዲስ አበባ እንዳይጠራ ወስኗል፡፡ በስብሰባው  ‹‹ምእመናን መማር ያለባቸው በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ሊቃውት መሆን አለበት፡፡ እኛ ሊቃውንቱን መድረክ ስለነሳናቸው ነው ሕገ ወጦች አውደ ምህረቱን የተቆጣጠሩት ›› የሚል ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡
ብጹዕ አቡነ ያሬድም በሀገረ ስብከታቸው እየተፈጸመ ያለውን ግብረ ተሐድሶ በተጠናቀረ መረጃ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀዋሳዎችን አሰረ ፍኖት የተከተሉ የሐረር ከተማ ትጉኀን ምእመናን በከተማችው በሀገረ ስብከታቸው እንዲሁም በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለው የተሐድሶ ክንፍ ምን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ በበቂ መረጃዎች የተደራጀ ቪሲዲ ለማሰራጨት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ዘለግ ላሉ ዓመታት በተሐድሶ ሴራ የተሰቃዩ የሐረር ምእመናንም ቪሲዲው የተንኮለኞችን ሴራ በማጋለጥ እፎይታ እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡
ድሬዳዋ
ከድሬዳዋ ለተሐድሶ ሰራዊትነት ሥልጠና ወደ ሐረር የተጓዙ ውሉደ ተሐድሶ ድርጊታቸው በመጋለጡ በሀሳብ ባለመግባባት ለሦስት ተከፍለዋል፡፡ በሦስት ሠልጣኞች ሦስት የተለያዩ ሀሳቦች ታይተዋል፡፡ የመጀመሪያው በግልጽ ወደ ሥልጠናው ሲገባ እና ሲወጣ በተቀረጸው የቪዲዮ ምስል እየታየ ለሚጠይቁት ሁሉ  ‹‹እኔ ዘመድ ልጠይቅ ወደ ሩቅ ሀገር ሄጄ ነበር የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከናካቴውም ሐረርን አላውቃትም ሔጄም አላውቅም›› በማለት ራሱን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡
ሁለተኛው ግለሰብ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በሐሰት አቀናብሮብኝ ነው እንጂ እኔ የማውቀው ጉዳይ የለም ›› በማለት እንደ ኦሪት ኃጢአተኛ በደሉን የሚሸከምለት ፍየል ለመፈለግ ሞክሯል፡፡ አክሎም ‹‹ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሬ ሰዎች በእኔ ላይ ማስረጃዎችን እንደሚያሰባስቡ አውቃለሁ ተገኘ የሚባለው ነገር ፍጹም ሐሰት ነው›› በማለት ቀርበው ለጠየቁት ግለሰቦች ሲመልስ ተሰምቷል፡፡‹‹የሥልጠናውን ሂደት የቀረጹት የሚያሳድዱኝም ሸዋዎች ናቸው›› በማለትም ለኑፋቄው የዘረኝነት መከላከያ ጭንብል ሊያጠልቅለት ሞክሯል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሁለቱ ግለሰቦች የአንድ ደብር ‹‹ሰባክያነ ወንጌል›› ሲሆኑ ቀጥለን የምንገልጸው የግብር አጋራቸው ድርጊታቸውን እንዳጋለጠባቸው ይጠረጥራሉ፡፡
ሥስተኛው ሰው ሁለቱ ወዳጆቹ የከፈቱለትን ቀጭን መውጫ ቀዳዳ በመጠቀም አንድ አካል መረጃ እንዲያጠናቅርለት ልኮት እንጂ አምኖበት ወደ ስልጠናው እንዳልሄደ ቅርብ ለሚላቸው ወዳጆቹ ተናግሯል፡፡ ጨምሮም ያሰባሰበውን መረጃ ለማኅበረ ቅዱሳን መላኩን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከሰልጣኞች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባል የሆነ አንድ ግለሰብ መኖሩን የተረዱ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማዕከልን ‹‹እንዴት ከእናንተ መካከል እንዲህ ያለ ሰው ይገኛል›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ማዕከሉም እንዲህ አይነት አባል የለንም በማለት አስተ
ባብሏል፡፡ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ከስድሳ ሺህ በላይ አባላት ካሉት ማኅበር እንዲህ ያለ መልስ አይጠበቅም፡፡ ማኅበሩ ሁሉንም አባላት የት እንደሚዉሉና እንደሚያድሩ በማያውቅበት ሁኔታ ድፍን ያለ መልስ ከመስጥት ተቆጥቦ የደረሰውን ጥቆማ በመቀበል ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ በመረጃ የተደገፈ ምሁራዊ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ገብር ኄር ግን የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ችላ የሚሉት ከሆነ ከአስተባባሪው ከገበየሁ ይስማው ጀምሮ በሁሉም ላይ ያሉትን  ዝርዝር መረጃዎች ለምእመናን የሚያሳውቅ መሆኑን ለመግጽ ይወዳል፡፡
በተያያዘ ዜና የገብር ኄር ዜና ዘገባ እንደ ሐሩር እሳት ያቃጠለው የአሰበ ተፈሪው ገበየሁ ይስማው ‹‹ሥልጠናው እንደተባለው ኢየሱስን ማለማመድ ሳይሆን ሰባክያነ ወንጌል የዓለም ሃይማኖቶችን አንድ ለማድረግ እንዴት ማስተማር ይገባቸዋል የሚል ነበር›› ብሏል፡፡ የሠልጣኞች ምልምላን
በተመለከተ ‹‹እኛ ሁሉንም ነው የጠራነው ደፍሮ የመጣውን አሠልጥነናል›› በማለት ገልጿል፡፡ ሴራው በመጋለጡ የተደናገጠው ገበየሁ ‹‹የቀረጹትንም ሆነ ፎቶ ያነሱትን እናውቃቸዋለን በመንግስት ጭምር እየተፈለጉ ነው ለሕግ እናቀርባቸዋለን›› በማለት የሐረር ምእመናን የተሐድሶን ሴራ ለማጋለጥ በሚያደርጉት ጥረት እየደረሰባት ያለውን ውርደት ለመከላከል  አልሞት ባይ ተጋዳይነቱን አሳውቋል፡፡
መረጃው የደረሳቸው የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ መረጃው ጠቃሚ እንደሆነና በሀገረ ስብከታቸው የእርምት እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ እነደሚገደዱ መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!! By ገብር ኄር

Friday, September 2, 2011

የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ

‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ


በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ አራት ሀገረ ስብከቶች ለተውጣጡ ‹‹ለቤተክርስትያን አገልጋዮች›› የተሐድሶ ሠራዊትነት ስልጠና ተሰጠ



በማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)
  • የሥልጠናው ዋና ርዕሰ ጉዳይ ኢየሱስን ማለመመድ የሚል ነበር
  • ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል
  • ፓስተር መስፍን ፤ገበየሁ ይስማውና  በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል
  • ለሥልጠናው ተሳታፊዎች ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚል ማስታዎሻ እና መጸሐፍ ተሰቷቸዋል
  • ከሠልጣኞቹ መካከል ቀደም ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በክረምት ተተኪ መምህራን ሥልጠና አሰልጠኗቸው ከነበሩት ሠልጣኞች አንድ ግለሰብ ተገኝቷል
ከድሬዳዋ ፤ ከሱማሌ ፤ ከምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ አህጉረ ስብከቶች የኦርቶዶክስ  አብያተ ክርስቲያናት ለተውጣጡ ‹‹የቤተክርስቲያን አገልጋዮች›› ግበረ ተሐድሶን በሚያስፋፉበት ስልት ዙርያ ሥልጠና መሰጠቱን  በሰነድ እና በድምጽ ወምስል የደረሰው መረጃ አመለከተ፡፡
‹‹ሃይማኖቶችን አንድ እናደርግ ሁላችንም በቀን አንዳንድ ሰው እንለውጥ›› በሚል መርህ የተጀመረው ሥልጠና በሐረር ከተማ ሉትራን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከነሐሴ 23-30 ሊሰጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ትላንት ማምሻውን መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ሥልጠናው ዘወትር ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽት 2፡30 እንደተሰጠ ለመረዳት ተችሏል፡፡የሰሌዳ ቁጥሩ ዕድ 00122 የሆነ ተሸከርካሪ ለሥልጠናው አስፈላጊ የሆኑ ሎጀስቲክስ ለማሟላት ሥራ ላይ ውሏል፡፡
የሥልጠናው ዋና አሰልጣኝ የቀድሞ የሐረር ቀበሌ 10 ሊቀ መንበር የአሁኑ ፓስተር መስፍን ነው፡፡ሌሎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች የመጡ በርካታ ፓስተሮች በአሰልጣኝነት የተሳተፉ ሲሆን ዋና አስታባባሪው ደግሞ ከአሰበ ተፈሪ ለዚሁ ሥራ ወደ ሐረር ያቀናው ገበየሁ ይስማው ነው፡፡ገበየሁ ይስማው በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም የሥራ ኃላፊነት የሌለው ባለበት የሃይማኖት ችግር በተነሳ ውዝግብ በመቐሌው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የተማረውን የዲግሪ መርሀ ግብር ማስረጃ ያለተሰጠው ወልደ ተሐድሶ ነው፡፡በዚሁ ምክንያት በምዕራብ ሐረርጌ የይብሮ ወረዳ ኮተራ ቅዱስ ገብረኤል ምዕመናን አታስተምረንም በማለት እነዳባረሩት ይታወቃል፡፡ፓስተር መስፍን እና ገበየሁ ይስማው በጋሻው ደሳለኝ ከነሐሴ 13-15 ሐረር በቆየበት ጊዜ በሥልጠናው ዙርያ መምከራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሥልጠናው ዋና ትኩረት የተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ኢየሱስን የማለማመድ ትምህርት›› ነው፡፡በዚህም ሠልጣኞቹ የበጋሻውን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ተደጋግሞ ሲመከሩ ተስተውሏል፡፡ስልተ በጋሻው በዝርዝር ቀርቦላቸው እንዲጠቀሙበት መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት ግለሰቦች ከሐረር ከጅጅራ ከሰበ ተፈሪ እና ከድሬ ዳዋ ከተሞች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ሲሆኑ ከነዚህ መካካል ማኅበረ ቅዱሳን በ2000 ዓ.ም ክረምት በጅማ ለግቢ ጉባዔያት ተተኪ መምህራን አዘጋጅቶት በነበረው ሥልጠና ተሳታፊ የነበረ አንድ ግለሰብ ይገኝበታል፡፡ በቅርቡ አባ ሠረቀ ብርሃን በመቐሌ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ አካሂደውት በነበረው ውይይት አንድ የኮሌጁ ደቀመዝሙር ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ካህናት ማሰልጠኛ ምንፍቅና አስተምሮኛል›› ብሎ መናገሩን ያስታወሱ ታዛቢዎች ማኅበሩ የሠልጣኞች ምልመላ ስርዓቱን መሰፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የሥልጠናውን ሙሉ ሂደት የሠልጣኞችን ዝርዝር የያዘ የሰነድ የፎግራፍ እና ቪዲዮ መረጃ ደርሶናል፡፡የተሐድሶን ሴራ በማጋለጥ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳንም መረጃው ተጠቃልሎ ደርሶታል፡፡የስልጠናው ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ከያዙት ቦታ እና ሊያደርሱት ከሚችሉት አደጋ አንጻር ማኅበሩ መረጃ አለኝ በሚል አጉል ብሒል እርምጃ ለሚወስዱ የቤተክርስቲያኒቱ አካል ፈጥኖ የማያደርስ ከሆነ ታሪክ የማይረሳው ስህተት እየፈጸመ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሚጠቀምበት ከሆነ ይህንን መረጃ ያጠናቀሩ የቤተክረስትያን ልጆች እንደ ሀዋሳ ምዕመናን የድርሻቸውን ለመወጣት ቪሲዲዎችን በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡እንደ አግባብነቱ መረጃዎችን ወደ ፊት የምንገልጥ መሆኑን እያስታወቅን ይህንን መረጃ በመሰብሰብ እና ለተገቢው አካል በማድረስ ለተጉት የቤተክርስቲያን ልጆች ያለንን አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!! ››  by http://andadirgen.blogspot.com/2011/09/blog-post_9564.html