Wednesday, September 26, 2012

“አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረን፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፋችንን ደምስስ። ከበደላችንም ፈጽሞ እጠበን፥ ከኃጢአታችንንም አንጻን፤ እኛ መተላለፋችንን አናውቃለንና፥ ኃጢአታችንም ሁልጊዜ በፊታችን ነውና። አንተን ብቻ በደልን፥ በፊትህም ክፋትን አደረግን፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።” መዝ.50/51፡1-4'


ፀሎተ ምህላ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን።
“አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረን፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፋችንን ደምስስ። ከበደላችንም ፈጽሞ እጠበን፥ ከኃጢአታችንንም አንጻን፤ እኛ መተላለፋችንን አናውቃለንና፥ ኃጢአታችንም ሁልጊዜ በፊታችን ነውና። አንተን ብቻ በደልን፥ በፊትህም ክፋትን አደረግን፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።” መዝ.50/51፡1-4

♥♥♥የይቅርታ አምልክ አቤቱ ማረን የቸርነት አምላክ አቤቱ ይቅር በለን፤ ልጅህን ልከህ ያዳንከን አቤቱ ተመልከተን ጨለማ ሕይወታችንን ወደ ብርሃን የለወጥክ  አቤቱ ታደገን።
♥♥♥በዚህ ክፉ ዘመን የገጠመንን መከራና ችግር ታርቅልን ዘንድ በአማኑኤል ስምህ በድንግል እናትህ እንለምንሃለን።
♥♥♥† በጨለማ ለነበሩት አህዛብ እንደ ነጋሪት ጮኸውመወለድህንና መምጣትህን ስላስተማሩ ነብያትህ ብለህ ከመዓት ሰውረን።
♥♥♥† የአህዛብን ምድር በመስቅልህ እርፍ አርሰው የቃልህን መዝገብ በዓለም ዳርቻ ሁሉ ስለ ዘሩ ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ብለህ ከክፉ መከራ አድነን።
♥♥♥† ድል ስለነሱ፣ አምነው ንጹህ ስለሆኑ ስለ ሰማዕታት ተኩላዎች ስለበሏቸው ስለመንጋህ ብለህ ይቅር በለን።

Tuesday, September 25, 2012

" ካልጠፋ ገላ ዓይን ጥንቆላ "

(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 15/2005) “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።”ያዕ.5:16 በዋልደባ ገዳም መንግስት በጀመረው የስኳር ፋብሪካ ብዙ በጣም ብዙ በደሎች በመነኮሳቱ ደርሷል እየደረሰም ነው፡፡ እስከአሁንም ችግሩ እልባት ሳያገኝ በመነኮሳቱ ላይ ደብደባ እንግልት እና ከገዳሙ እንዲሰደዱ እየተደረገ ነው ፡፡ 
መነኮሳቱ ግን መፍትሄው እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ እንባቸው ወደ አምላክ እየረጩ አምላክን ከመማፀን አልቦዘኑም፡፡ እንባን የሚያብስ አምላክ ግን ሁሉን ነገር በጊዜው ያደርጋል እያደረገም ነው የሚማር እና ከጥፋቱ የሚመለስ የለም እንጂ፡፡ ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያደረሱን “ፍቅር ይሄይስ ” የተሰኙ ፀሐፊ ሲሆኑ እኛም ጽሁፉ የያዘውን ቁመ ነገር ለእናነተም ልናካፍላችሁ ወደድን ፀሀፊውን አምላክ በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን፡፡ መልካም ንባብ፡፡ አምላካችን ሃገራችንን ይጠብቅልን፡፡  ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።                     
  " ካልጠፋ ገላ ዓይን ጥንቆላ "
  የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እርስ በርሱ፣ በሀሳብና በድርጊቱ መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ለዚህም የአዳምን ልጆች የአቤልንና የቃዬልን ህይወት ማንሳት የሰው ልጅ በተፈጠረ ማግስት አለመግባባትና የጥቅም እንደራሴነት አንደተጀመረ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በዘመናችን ከጉንጭ አልፋ ክርክርና ንትርክ አስከ ከፋ ግጭትና ሞት የሚያበቁ አለመግባባቶች የሚከሰቱት አንድም በስልጣን ወይም በጥቅም ይገባኛል የተነሳ ነው፡፡በነዚህ የግጭት ሰበቦች የተነሳ አለማችን ብዙ ሚለዮን ሰወችንና ብዙ ሀብትን አላግባብ አጣለች፡፡ ምናልባት የሰው ልጅ የአስተሳስብ አድማሱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ግን ልዩነቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ሂደቱ እየጨመረ መምጣቱ ለመጭዋ ዓለም አበረታች ተስፋ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሶስት ነገሮች ጋር ሊጣላ ይችላል፡፡

Monday, September 24, 2012

ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል ሶስት



ከባለፉት ሁለት ክፍሎች የቀጠለ
(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 14/2005)ቅዱስ ያሬድ ቀደምት የዜማ ምልክት ደራሲ መሆኑንም ጭምር ቤተ ክርስቲያን ለአለም የምታሳውቅበት ጊዜ ቢኖር ይህ 1500ኛ መታሰቢያ አመት ይመስለኛል ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ እያንዳንዳችን ከዛሬ ጀምረን በየአጥቢያችን ታላላቅ በአላትን ተንተርሰን የሚዘከርበትን ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ከመስቀል በዓል አከባበር ቢጀምር ባዮች ነን፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ዑደት ስፍር ቀምር የራሷን  ዜማ ያደላደለች አፍሪካዊት እመቤት ናት ብንል ጽልመት ሊጋርደው የማይችለው ገሀድ ነው፡፡ 
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶች 
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርስቶች በአምስት ይከፈላሉ እነዚህም ድርሰቶች አምስት ፅዋትወ ዜማ በመባል ይጠራሉ ፡፡ እነርሱም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ፣ መጽስዕትና ምዕራፍ ይባላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍት ላይ የቅዱስ ያሬድ ድርስቶችን በዜማ ይተበh ደረጃ ልዩነት እና አንድነት ያላቸውን በመከፋፈል አራት ይላሉ አነርሱም ድጓ ቅዳሴ ዝማሬ እና መዋስዕት ይላሉ   ይህን የሚሉት ድጓ ጾመ ድጓ እና ምዕራፍ አንድ አይነት የዜማ ይትበሀል ስላላቸውንደ አንድ ስለሚቆጥሯቸው በድጓ ውስጥ ስለሚያጠቃልሏቸው በመሆኑ አምስት ከሚሉት ጋር የሚጋጭ አይሆንም፡፡
·         ድጓ- ከጽሕፈቱና ከምልክቱ ብዛትና ክሳት የተነሳ ረቂቅ እስተግብዕ /ስብስብ/ ይባላል፡፡  ምክንያቱም የዓመቱን በዓላትና የሳምንቱ መዝሙራት ተሰብስበው ስለሚገኙ ነው፡፡ ድጓ ስብስብ ሙሾ፣ ቁዘማ መዝሙር፣ ሐዲስ፣ ፍፁም ማለት ነው ድጓ የቤተ ክርስቲያ ዜማ መድብል ሲሆን በውስጡ አራት ክፍሎች አሉ እነርሱም፡-
1.    ድጓ ዮሐንስ - ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የሚናገር ሲሆን፣ የዮሐንስን መንገድ ጠራጊነት የሐዲስ ኪዳንን መሸጋገርያነት አንስቶ የዘመረበት ነው የሚዘመርበትም ወቅት ከመስከረም 1  እሰከ ኅዳር 30  
2.    ድጓ አስተምሕሮ - ጌታችን ያሰተማረውን ትምህርት ያደረገውን ተዐምራት     የሚያነሳ ነው ማቴ.52  ማር1 39 የሚዘመርበት ወቅትም ከታህሳስ 1 እስከ መጋቢት 30፡፡
3.ድጓ ጾም - የድጓው ሦስተኛ ክፍል በዓቢይ ጾም የሚባል ነዉ፡፡
4.    ድጓ ፋሲካ - የጌታችንን ለዓለም ቤዛ ወይንም ፋሲካ ሽግግር ራሱን መስጠቱን ያነሳል የዕርገትን የጰራቅሊጦስንና የክረምትን ነገር ያነሳል የሚዘመርበት ወቀትም ከሚያዝያ/ከትንሳኤ/ እሰከ ጳጉሜን መጨረሻ፡፡

Friday, September 21, 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተግዳሮቶቿስ ምንድናቸው??? በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቤተክርስቲያን ልዕልናዋ ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ ምን ይጠበቃል ??

  • የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫና መሰል ጉዳዮች በጥቅምቱ ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ይወሰናል::
  • ቅዱስ ሲኖዶስ ከፓትርያርክ ምረጫ ጋር በተያያዘ ለቤተ ክርስቲያኗ ወሳኝ ጉዳዮችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡
(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 12/2005) ኢትዮጵያ ታላላቅ ቅዱሳንን ያፈራችበትን ወርቃማ ዘመንን ለመድገም ከአሁን የተሻለ ታላቅ አጋጣሚ ይመጣል ተብሎ መቼም የሚጠብቅ አይሆንም፡፡ ፈር ያጡት ሰርዓቶቻችን መስመር የሚይዙበት ፣ ምንም ስርዓት ያልተሰራላቸው ጉዳዮች አዲስ ስርዓት ተዘርግቶላቸው የወደፊት መጭውን እድል የምትወስንበት ፣ እንደ ግመል ያበጡትን ከፍተኛ ችግሮቻችንን የሚወገዱበት ፣ የምንፈታበት ጊዜ ከዚህ የተለየ አጋጣሚ ምቹ ሊመጣ? የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት ወርቃማዎቹ ጊዜያት ዛሬ ላለነው ትውልድ ሲናፈቁን የሚኖሩ ቢሆንም እንዲህ ያሉ ትውልድን የምንፈጥረው እጅ ለእጅ ተያይዘን ተከባብረን በአንዲት ቤተክርስቲያን ያለሰለሰ ጥረት ስናደርግ ፣  ስርዓቶቿን ስናስጠብቅና ስንጠብቅ ፣ ማንም እንዳሻው ሲፈነጭ አይቶ ዝም እየተባለ የሚታይበትን ጊዜ ሲከስም መሆነ ግልጽ ነው፡፡  
በዚህ አጋጣሚ ይህ ጊዜ ካለፈን እና መሠረታዊ ችግሮቻችንን ሳናስተካክል የነበረው ስርዓት አለብኝነት ይቀጥል ብለን ዝም ካልን ግን ምን አልባትም ለቤተክርክስቲያናችን ጥቁር አሻራ አስቀምጠን እንዳልፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በተለይ ደግሞ የዘረኝነትና የፍቅረ ነዋይ ችግሮች መጥራት ካልቻሉ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡
የውስጥ ችግሮቻችን ምንም ብዙ ቢሆኑም ትኩረት ወስድን እያንዳንዱ ስርዓት እንዲስተካከል ካደረግን በአንድ ሀሳብና በአንድ ልብ ሆነን ከውጪ ጠላቶቻችን የሚመጣብንን የሰማዕትነት ጊዜያት እየናፈቅን ብሩህ ዘመንን እያየን በቃለ እግዚአብሔር የታነጸ ታላቅ ዜጋ ፣ ትውልድ የምንፈጥርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡: በዚህ ረገድም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን አርአያነት ለእኛም ይህ ተስፋ ይሆናል፡፡

በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቤተክርስቲያን ልዕልናዋ ተጠብቆ እንዲቀጥል ከምዕመናን ምን ይጠበቃል ?? ተግዳሮቶቿስ ምንድናቸው???

(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 11/2005) የምህላው ጊዜ ተፈፅመዋል ዛሬ ላይ በአንድ ልብ ሆነን ስላ ቤተ ክርስቲያናችን የልዕልና አና ብሩህ ጊዜን እናልማለን፡፡  
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕዳሴ ዘመን:: ኢትዮጵያ ታላላቅ ቅዱሳንን ያፈራችበትን ወርቃማ ዘመንን ለመድገም ከአሁን የተሻለ ታላቅ አጋጣሚ ይመጣል ተብሎ መቼም የሚጠብቅ አይሆንም፡፡ ፈር ያጡት ሰርዓቶቻችን መስመር የሚይዙበት ፣ ምንም ስርዓት ያልተሰራላቸው ጉዳዮች አዲስ ስርዓት ተዘርግቶላቸው የወደፊት መጭውን እድል የምትወስንበት ፣ እንደ ግመል ያበጡትን ከፍተኛ ችግሮቻችንን የሚወገዱበት ፣ የምንፈታበት ጊዜ ከዚህ የተለየ አጋጣሚ ምቹ ሊመጣ? የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት ወርቃማዎቹ ጊዜያት ዛሬ ላለነው ትውልድ ሲናፈቁን የሚኖሩ ቢሆንም እንዲህ ያሉ ትውልድን የምንፈጥረው እጅ ለእጅ ተያይዘን ተከባብረን በአንዲት ቤተክርስቲያን ያለሰለሰ ጥረት ስናደርግ ፣  ስርዓቶቿን ስናስጠብቅና ስንጠብቅ ፣ ማንም እንዳሻው ሲፈነጭ አይቶ ዝም እየተባለ የሚታይበትን ጊዜ ሲከስም መሆነ ግልጽ ነው፡፡  
በዚህ አጋጣሚ ይህ ጊዜ ካለፈን እና መሠረታዊ ችግሮቻችንን ሳናስተካክል የነበረው ስርዓት አለብኝነት ይቀጥል ብለን ዝም ካልን ግን ምን አልባትም ለቤተክርክስቲያናችን ጥቁር አሻራ አስቀምጠን እንዳልፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በተለይ ደግሞ የዘረኝነትና የፍቅረ ነዋይ ችግሮች መጥራት ካልቻሉ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡
የውስጥ ችግሮቻችን ምንም ብዙ ቢሆኑም ትኩረት ወስድን እያንዳንዱ ስርዓት እንዲስተካከል ካደረግን በአንድ ሀሳብና በአንድ ልብ ሆነን ከውጪ ጠላቶቻችን የሚመጣብንን የሰማዕትነት ጊዜያት እየናፈቅን ብሩህ ዘመንን እያየን በቃለ እግዚአብሔር የታነጸ ታላቅ ዜጋ ፣ ትውልድ የምንፈጥርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡: በዚህ ረገድም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን አርአያነት ለእኛም ይህ ተስፋ ይሆናል፡፡

Thursday, September 20, 2012

ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል ሁለት



1500 ዓመት የቅዱስ ያሬድን በዓል ምክነያት በማድረግ በክፍል አንድ ስለ ቅዱስ ያሬድ "ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል አንድ" በሚል ርእስ አስነብበናችኋል፡፡ ዛሬ ደግሞ በክፍል ሁለት የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት በሚል ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ እንድትሆን ያደረጋት የልጆቿ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነትን የተመላው ባህሏ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የሥነ ዜማ ሀገር መሆኗም መጻሕፍተ ታሪክን ባነበቡ ሊቃውንት አንደበት ብቻ ሳይሆን በማዳመጥ  ትውፊት /ርክክብ/ ለኅብረተሰቡ ኀቡእ ያልሆነ ነገር መሆኑ ነው ፡፡
  ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ.74:14 ለኢትዮጵያ ከተሰጡት ታላላቅ ሀብቶች መካከል አንድ በልዩ ስጦታ ከሰማያት ከመላእክት በቀር የትም የማይገኝ እና የተም የሌለ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት ነው፡፡  የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት ግዕዝ ዕዝልና አራራይ በሚባሉ ሦስት የዜማ መደቦች ይመደባሉ፡፡ የሦስቱ መደቦች የዜማ ድምፃቸው አንድ ሲሆን አንድ መሆናቸው የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ነው ፡፡ የዜማ ስልቶች
  •        ግዕዝ- ግዕዝ ማለት ገአዘ ነፃ ወጣ ማለት ሲሆን በዜማነቱ ሲተረጎም የመጀመሪያ አንደኛ ስልት የቀና ማለት ይሆናል ዜማው ፀባይ ደረቅ ያለና ብዙ እርክርክታ የሌለው ለጉሮሮ ጠንካራ ኃይለኛ በመሆኑ ሊቃውንቱ ደረቅ ዜማ ይሉታል                  
  •    ዕዝል፡- የግዕዝ ድርብና ታዛይ ነው ምሳሌነቱ የወልድ ሲሆን ትርጓሜው ፅኑ ማለት ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ጽንዑ የሆነ መከራን ተቀብሎ እኛን የአዳም ልጆች ማዳኑን ያስረዳናል፡፡ አንድም የመለኮትና የትስብእት ተዋህዶ ረቀቅ ስለሚል  ቀስ በቀስ ሊማሩት እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡
  •       አራራይ- የሚያራራ፣ ጥዑም ልብን የሚመስጥ ማለት ነው፡፡ የዜማው ስልት ልብን የሚያራራ በመሆኑ ስያሜውን አግኝቷል፡፡ ሐዋርያትን ከበዓለ ጴንጤቆስጤ በኋላ ያረጋጋ ያጽናና እና ጥበዓተ ድፍረት ሰጥቶ  ዓለምን እንዲያጣፍጡ ስላደረገ  አራራይ ዜማ   በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል፡፡