መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው
የእግዚአብሔር ሰዎች «ወዮልኝ፤» እያሉ ራሳቸውን ገሥጸው
ይኖራሉ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ፊት ለፊት ስላየው ፥ ቃል በቃል ስላነጋገረው፡- «አቤቱ አምላኬ ሆይ፥
ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፡- «ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥
አትሞትም፤» ብሎታል። መሳ ፮፥፳፪። ነቢዩ ኤርምያስም፡- «በሆድ ሳልሠራ አውቄሃለሁ፥ ከማኀፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥
ለአሐዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» በተባለ ጊዜ፡- «ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤»
ብሏል። ኤር ፩፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤ » ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮።
እነዚህ «ወዮልኝ፤» ማለታቸው ለእኛ አብነት ነው። ታላላቆቹ እንዲህ ካሉ ከእኛ ከታናናሾቹ የብዙ ብዙ ይጠበቃል። ዕለት ዕለት
«ወዮልኝ፤» እያልን ደረታችንን ልንደቃ፥ እንባችንን ልናፈስስ ይገባል። ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በስተቀር እግዚአብሔርን ደስ
አሰኝተን አናውቅምና። ሰውን ደስ ለማሰኘት በሰውም ዘንድ ለመወደድ (ለውዳሴ ከንቱ) እግዚአብሔርን እናሳዝናለንና። እንኳን
መንፈሳዊ መሆን መምሰሉ እንኳ አቅቶናልና። ሃያ፥ሠላሳ ዓመት ቃለ እግዚአብሔር ዘር ተዘርቶብን፡- ሠላሳ፥ስድሳ፥መቶ ማፍራት
የተሳነን ዘረ ቆርጥሞች ነንና። መቁረባችን ማቁረባችን ፥ መቀደሳችን ፥ ማስቀደሳችን፥ ማሳለማችን፥መሳለማችን፥
መናዘዛችን፥ማናዘዛችን፥ መዘመራችን፥ማዘመራችን፥ መስበካችን፥መሰበካችን ሁሉ ከንቱ ሆኖብናልና። ስለሆነም «እገሌ ሳይገባው
ነው፤» የሚለውን ትተን፡- «እኔ ሳይገባኝ ነውና ወዮልኝ፤» እንበል። የእግዚአብሔር ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ
አይጠብቁምና።
«ወዮላችሁ፤»
የዓለም ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ ይጠብቃሉ፤ ተብለውም አይመለሱም፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የቃሉን ትምህርት ሰምተው፥ የእጁን ተአምራት አይተው ያልተመለሱትን ጸሐፍት ፈሪሳውያንን በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስምንት ጊዜ
«ወዮላችሁ፤» ብሏቸዋል።